Saturday, 19 November 2022 21:14

ከእውቁ ዓለም አቀፍ ተማራማሪ ፕሮፌሰር ጋር የተደረገ ልዩ ቃለ ምልልስ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ የዩኒቨርስቲውን ፕሮጀክት ቢፈልገውም ዕቅዱ ከሽፎበታል

       ዕድሜ ዘመናቸውን በጥናትና ምርምር ውስጥ ያሳለፉት ፕሮፌሰር አበበ ዘገየ፤ የአገር ውስጥ ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ አገር ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት አገልግለዋል። የእንግሊዙ ኦክስፎርድና የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርስቲ ይጠቀሳሉ። በአዲስ አበባ ቤላ አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡ በ1953ቱ የእነግርማሜ ነዋይና መንግስቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ላይ የተሳተፉት የሻለቃ ዘገዬ የምሩ ልጅ ናቸው - ፕሮፌሰሩ። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በህይወታቸውና ሙያቸው ዙሪያ ስለምርምር ሥራዎቻቸው ስላቋቋሙት ዩኒቨርስቲ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕ/ር አበበ ዘገየ የምሩ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

          እርሶ የተወለዱበት፤ ያደጉበትና የተማሩበት ሥፍራ የተለያየ  ነው፡፡ ይህ በአባትዎ የስራ ባህርይ ሳቢያ  የመጣ ይመስለኛል፡፡ እስኪ ያጫውቱኝ?
እውነት ነው፡፡ አባቴ የክቡር ዘበኛ ወታደር ነበር፡፡ ከጣሊያን ጦርነት በኋላ የመጀመሪያው ኮርስ ተመራቂ ነበር፡፡ በወቅቱ ከታወቁት ኮ/ል ደመቀ የተባሉ የኢንተለጀንስ ሰውና ከሌሎችም ጋር ነበር አባቴ፡፡ ኮሪያም ዘምቷል፡፡ ሚሊተሪ አካዳሚን ጨርሶ እንደተመረቀ የክቡር ዘበኛ ሆኖ ብዙ  ሰርቷል፡፡ አሜሪካን ሀገር ለትምህርትም ሄዶ የሜካኒካልና የትራንስፖርቴሽን ዘርፍ ትምህርት ተምሮ ከመጣ በኋላ የሜካኒካልና የትራንስፖርቴሽን ዲቪዥን ሀላፊም ነበር፡፡ ሜሪላንድ ነው ተምሮ የመጣው፡፡
በተለያዩ ቦታዎች እየተዟዟሩ መኖር የጀመሩት አባትዎ ሻለቃ ዘገዬ የምሩ በ1953ቱ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተሳትፈው ከከሸፈ በኋላ ይመስለኛል…?
ልክ ነው! በ1953 የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ላይ ከተሳተፉት ውስጥ አንዱ ነበር። በእርግጥ ዋና ጠንሳሹ ግርማሜ ነዋይ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ አባቴም ተሳተፈ፡፡ ግን አልተሳካም። አባቴን ለምን ተሳተፍክ ብለሽ ብትጠይቂው ሙያዊ ዝርዝር ይሰጥሻል፡፡ “አገሬም ነው ፤ወታደርም ነኝ፡፡ አገሬን የሚረዳት ከሆነ አደርገዋለሁ” አለ፡፡ ግን ከሸፈ፡፡ አባቴ እጁን ሰጠ፡፡ አንድ ዓመት ከታሰረ በኋላ በግዞት ሸኖ ተላከና ለሁለት ዓመት ቆየ፡፡
እዚህ ላይ ግን መፈንቅለ መንግስቱ ለምን ከሸፈ ምን ነበር ያከሸፈው?
ጥሩ! መፈንቅለ መንግስቱን የጠነሰሱትና ያቀዱት ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ብዙዎች አልተሳተፉበትም፡፡ በደንብም አላቀዱትም ነበር፡፡ የመንፈቅለ መንግስት ሙከራው መክሸፍ ዋናው ምክንያት ይሄ ነው፡፡ ጥቂት ሰዎች ናቸው የሚያውቁት። ግርማሜ ንዋይ፤ መንግስቱ ንዋይ፤ ኮ/ል ደመቀና ጥቂት ሌሎች ሰዎች። በዚህ ምክንያት ነው የከሸፈው፡፡
በእርግጥ መፈንቅለ መንግስቱን ሲጠነስሱ ለሀገር በመቆርቆር እንጂ ስልጣን ፍለጋ ወይም ለራስ ጥቅም በማሰብ አልነበረም፡፡ በዛን ወቅት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ እየወጡ፤ በኢኮኖሚ እያደጉና ብዙ ሥራ እየሰሩ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀርታለች፤ መለወጥ አለባት ብለው ነው መፈንቅለ መንግስቱን የሞከሩት፡፡ ቢሳካላቸው ኖሮ ሀሳባቸው ኮንስቲቲዩሽናል ሞናርኪ ለመፍጠር እንጂ ሚሊታሪ ዲክታተርሽፕ አልነበረም፡፡
በወቅቱ እኛ ልጆች ነን፤ ሁለት ታላላቆቼ እንጂ እኛ ትምህርትም አልጀመርንም። አምስት ነበርን፡፡ ያኔ የግዞት ቦታ ምረጥ ተባለ። ያን ጊዜ አይገባኝም፤ ግዞት ምረጥ መባሉ፡፡ አየሽ ዘገየ ያኔ አንድ ሰው አልነበረም፡፡ ቤተሰብ አለው አያቶቼ ዘመድ አዝማድ አለ። የኢትዮጵያ ቤተሰብ ሰፊ ነው፡፡ ግዞት ስትላኪ ቤተሰቤን እንዴት ነው የማስተዳድረው ብለሽ ታሰላስያለሽ፡፡ ስለዚህ አባቴ በግዞት እያለ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ግብርና ጀመረ። በዚያ ነው ቤተሰቡን ያስተዳደረው፡፡
የግዞት ኑሮ ከሌላው ማህበረሰብ ኑሮ በምን ነበር የሚለየው?
በግዞት አንድ ቦታ ተልከሽ ስትኖሪ፣ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ከሰኞ እስከ እሁድ ፖሊስ ጣቢያ እየሄድሽ ትፈርሚያለሽ፡፡ አባቴም ለሁለት ዓመት ይህንን ያደርግ ነበር፡፡
እዚያ ቦታ ላይ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ነው ሁሌ እየሄዱ የሚፈርሙት?
አዎ! ከዚያ ቦታ ዞር ብለሽ እንዳትሄጂ፤ መኖርሽን ከሰኞ እስከ እሁድ ፖሊስ ጣቢያ እየሄድሽ ማረጋገጥ አለብሽ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያ ምህረት ተባለና ከሁለት ዓመት የግዞት ኑሮ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለስን። ምህረት ሲደረግ ምህረት የምትባል እህቴ ተወለደች፡፡ እንደምታውቂው የኢትዮጵያ ሥም አብዛኛው በምክንያት የሚሰየም ነው፡፡ ለምሳሌ ዘውድነሽ ብሎ እህቴን ሲሰይም፤ ተሹሞ ሻለቃ ሆኖ አሜሪካ ተምሮ ጥሩ ደረጃ በደረሰበት ጊዜ ነው፡፡ ከእስርና ከግዞት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ደህና ሥራ ያገኘው በወሎ ጠቅላይ ግዛት የሆስፒታሎች ሀላፊ ሆኖ ወሎ በተላከ ጊዜ ነው። በነገራችን ላይ እኔ ተስፉና ዘውድነሽ አባታችን ግዞት ሲላክ አብረን ሄድን፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ የእኔ ታላላቆች በእምነትና ዮናስ ትምህርት ጀምረው ስለነበር ትምህርታቸው እንዳይቋረጥ አጎናፍር የምሩ የተባሉ ቀበና ይኖሩ የነበሩ አጎታችን ጋር ቀሩ፡፡ ምክንያቱም ያኔ ሸኖ ት/ቤት የለም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደሴ ሄደን እኔ አንደኛ ክፍል ገባሁ። ታላቅ ወንድሜ ወ/ሮ ስህን ት/ቤት ገባ፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ የመጀመሪያው ረሃብ ገባ፡፡ ከፍተኛ ረሀብ ነበር የተከሰተው፡፡
“ክፉ ቀን” እየተባለ የሚጠራው ነው?
እሱ በአፄ ምኒሊክ ጊዜ የነበረው ነው፡፡ ይሄኛው አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት በአፄ ሀይለ ስላሴ ጊዜ የተከሰተው ነው፡፡ በዚህ በረሃብ ምክንያት አባቴ በየአካባቢው ይዞር ነበር፡፡ ያኔ ወሎ በጣም ትልቅ ነበር፤ እስከ አሰብ ደረስ ነበር ድንበሩ፡፡ ወሎ በስፋት ከሀረር ቀጥሎ ሁለተኛ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ከአባቴ ጋር አልፎ አልፎ እዞር ነበር፡፡ በወቅቱ አባቴ ዋናው ሰራው “አስፋው ወሰን  ሆስፒታል    ነበር፡፡ ታላቅ ወንድሜ ዶክተር እንዲሆን ተፅዕኖ ያደረበትም አባቴ ሆስፒታል ይመራ በነበረበት ወቅት 8ኛ ክፍል ሆኖ ሆስፒታል እየሄደ ያስተረጉም ስለነበር ነው። በዚያን ጊዜ በሆስፒታሉ ነጮች አስተማሪዎች ነበሩ፡፡ አሜሪካኖች የቡልጋሪያ ዜጎችና ሌሎችም ነበሩ። ለእነሱ የትርጉም ስራ እየሰራ ሁሉን እያየ አደገና በኋላ  ዶክተር ሆነ። ታላቄ ነው ዮናስ ዘገዬ ይባላል፡፡ የህክምና ዶክተር ነው። ደሴም ብዙ ሰርቷል። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልም እንዲሁ። የአእምሮ ህክምና ላይ ነው ያተኮረው። ከውጭ በየጊዜው እየመጣ የነፃ ህክምና ይሰጣል፡፡
የሆነ ሆኖ ያንጊዜ ለእኔ ጥሩ ወቅት ነበር። አባቴ ከእስርና ግዞት ወጥቶ ጥሩ ስራ አግኝቶ የቤተሰቡን ህወት የቀየረበት ነው፡፡ ከደሴ ተመልሰን እኔ ኮከበ ፅባህ ገባሁና ተማርኩኝ። ከዚያ የሀይስኩል ትምህርቴን ተፈሪ መኮንን ተማርኩኝ፡፡ ያኔ የተማሪ እንቅስቃሴ ነበር። ተማሪው በተለይ የኛ ታላላቆች የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሆይ ሆይ ይሉ ነበር። እኛ ዩኒቨርስቲ  ባንገባም ተፈሪ መኮንን ስለምንማር ሁሉንም እናይ ነበር፡፡ ከ11ኛ ወደ 12ኛ ክፍል ሳልፍ (እ.ኤ.አ 1973 ማለት ነው) ነፃ የትምህርት እድል አግኝቼ አሜሪካ ሄድኩ፤ ሀይለኩል እዚያ ጨረስኩኝ፡፡
አብዮቱ ሳይፈነዳ ነዋ ከሀገር የወጡት?  
አዎ አብዮቱ ሳይፈነዳ ነው የወጣሁት። በዚህ እድለኛ ነኝ እላለሁ፡፡ ምክንያቱም የኔ ጓደኞች አብዛኛዎቹ አልቀዋል፡፡ በዚያን ጊዜ አባቴ አንድ የገባው ነገር ነበር፡፡ ያ ነገር ምን መሰለሽ … ያቺ የ1953ቷ መፈንቅለ መንግስት መጀመሯ ነው እንጂ ማለቋ እንዳልነበር ነው የተገነዘበው፡፡ ሁላችንንም አሸሸንና እንድንማር አደረገ፡፡
እርስዎ ምን አጠኑ?
ያጠናሁት ሶስዮሎጂ ኢኮኖሚክስና ፊሎዞፊ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እንደገና እንግሊዝ ሀገር ሄድኩና ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቼ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲ ለ4 ዐመት ተማርኩኝ። እዚያም የተማርኩት ሶስዮሎጂ ነው። እዚያ የአካዳሚክ ስራ ጀመርኩኝ ሌላ ስራ ሰርቼ አላውቅም፡፡ እ.ኤ.አ ከ1986 ጀምሮ የአካዳሚክ ስራ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡
ከኦክስፎርድ ጀምሮ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ እንዳስተማሩ ሰምቻለሁ። እስኪ ያብራሩልኝ?
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለትንሽ ጊዜ ሰርቻለሁ። ከዚያ በኋላ ወሪክ የሚባል አስተማርኩ። ቀጥሎ ካሊፎርኒያ ፕሮፌሰር ሆኜ ሄጄ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አስተምሬያለሁ፡፡ ሶስት ልጆች አሉኝ አብረውኝ ሲዞሩ ነው የኖሩት። አሁን ትልልቅ ሆነዋል፡፡ እኔ ሁልጊዜ ኢትዮጵያና አፍሪካ ላይ ነው ስሜት ያለኝ፡፡ በፈረንጆቹ 80ዎቹ ተነስቼ ልመጣ ነበር፡፡ በፈረንጆቹ 80ዎቹ ማለት የደርግ ጊዜ ስለነበር አባቴ “አይሆንም ከዚህ ከሄድክ ሁለት ሳምንት አትኖርም” ብሎ እምቢ አለኝና ቀረሁኝ፡፡ እንግሊዝ እያለሁ ፀረ አፓርታይድና ናሚቢያን ኢንዲፔንደንስ ላይ ብዙ እሰራ ነበር። እ.ኤ.አ በ1996 ማንዴላ ሲፈታ የማውቃቸው ሰዎች ጠሩኝና ደቡብ አፍሪካ ለኢንተርቪው ሄድኩኝ፡፡ ብቻ ለ15 ዓመታት ያህል በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ እና ኤች ኤስ አርሲ የሚባል ተቋም ሰርቻለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ዋናው አላማችን የአፓርታይድ ቅኝ ግዛት ያጠቃውን ሀገር እንዴት ነው የምንለውጠው የሚል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰርተናል፡፡
ቃሊቲ አካባቢ የሚገኘውን ዩኒቨርሲቲ አፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA)ን እንዴት ነው ያቋቋሙት?
ደቡብ አፍሪካ እየሰራን ስለኢትዮጵያም በደንብ እናስብ ነበር፡፡ ከዚያ ዳኒ ፒቲያና የሚባል ጎበዝ ቻንስለር ነበረ፡፡ አለቃዬም ነበር። እናም አዲስ አበባ ካምፓስ እንከፍታለን ብለን ሃሳብ አቀረብን። እኔ ነበርኩ ፕሮጀክቱን ይዤ የመጣሁት። ከዚያ ድርድር ጀመርን፡፡ ስንጀምር በርካታ ችግር ነበረብን፡፡ አንደኛው በራሳችን በኩል ያለ ችግር ነበር፡፡
ምን አይነት ችግር?
የራሳችን የዩኒሳ ችግር ነበር፡፡ ምን መሰለሽ? ዚምባቡዌ ውስጥ ብዙ ተማሪዎች ነበሩን፡፡ ዚዝምባብዌ በዶላር ነበር የሚከፍሉን፡፡ ሀገሪቱ ተበጠበጠችና ዜሮ ገባ፡፡ እዚህስ መጥተን ገንዘቡን ምንድነው የምናደርገው የሚለው ነበር አንዱ ችግራችን፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ፕሮጀክት በተለየ ሁኔታ የመለስ ዜናዊ ፕሮጀክት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
እንዴት ማለት ነው?
መለስ ይህን ፕሮጀክት በጣም ፈልጎታል። ለምን ካልሽኝ… የራሱን ሰዎች አስገብቶ ለማሰልጠን፡፡ እሺ ብለን መጣን። እንዳልኩሽ ሪፖርት የፃፍኩት እኔ ነበርኩ፡፡ እናም በዚህ ፕሮጀክት አራት ዋና ዋና ችግሮች ነበሩብን። የመጀመሪያው የዶላር ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በብር ምንም አናደርገውም። ሂልተን በዚሁ ጉዳይ ትልቅ ኮንፍረንስ አዘጋጅተን ነበር- ለማስተማር፡፡ ከዚያ መለስ ጠራን። የዶላሩን ጉዳይ በተመለከተ ተማሪዎቹ ወይም ዩኒቨርሲቲው በአዋሽ ባንክ ይክፈሉና ከዚያ በዶላር ታወጣላችሁ ተባልን። ይሄኛው ጉዳይ መፍትሄ አገኘ፡፡ በአንድ ስብሰባ አለቀ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካዘዙ ችግር በአንዴ ይፈታል፡፡ ምክንያቱም ራሱ ይሄ ፐሮጀክት እንዲሳካ የፈለገበት ምክንያት ነበረውና እሱን እንመጣበታለን፡፡
ሁለተኛው የማስተማሪያ ቦታ አልነበረንም። አሁን ዩኒቨርሲቲው ያለበት ቃሊቲ ያለው ኮምፓውንድ በደርግ ጊዜ ባንክ የሰራው ነው። እና እነመለስ ቀምተው ይዘውት ነበር፡፡ ከዚህ ቦታ የተወሰነውን ክፍል ሰጡን፣ ይሄም ችግር ተቀረፈ፡፡ ሶስተኛው የኢንተርኔት ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጨረሻ ነው፡፡ ኢንተርኔት በጣም ያስፈልገና። እንዴት እናድርግ አልን፡፡ እሱ ምንም ችግር የለውም፤ እንደ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የራሳችሁ ሳተላይት እንዲኖራችሁ እንፈቅዳለን፤ አዘጋጁ ተባልን። ልክ እንደነ ኢሲኤና የመሳሰሉት ማለት ነው ያኔ ኢንተርኔት የለም ነበር ሳተላይት ተፈቀደልን። ይሄም ተፈታ፡፡ አራተኛው ችግራችን የጉምሩክ ጉዳይ ነበር። በዚህ ዘርፍ ያለውን አንድ ሀላፊ ጠራና መፅሀፍት ኮምፒዩተሮችና ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉ ነገሮችን ያለችግር እንድናስገባ ነገረልን፡፡ ይሄም ችግር በቀላሉ ተፈታ፡፡ እንደምታውቂው ጉምሩክ አካባቢ ብዙ ጣጣ አለው፡፡ እነዚህን አራት ዋና ዋና ችግሮች እዚያ ቁጭ ባልንበት በአንድ ሰዓት ስብሰባ ውስጥ ፈታልን፡፡ እኔ በስብሰባው ላይ እንዲያውም አልተገኘሁም። ሳውዝ አፍሪካዎቹም ለአገርህ ነው የምታደላው ሲሉ፤ በዚህ በኩል ያሉት እንዲሁ አንዳንድ ነገር ይሉ ስለነበር ስብሰባውን መከታተል አልፈለግሁም። ችግሩ በቀላሉ እንደሚፈታ አውቅ ነበርና፡፡ በኔ ጥናት መሰረት በሁለት ዓመት ውስጥ ነበር ስራ እንጀምራለን ብዬ ሪፖርት ያቀረብኩት በ6ወር ጀምሩ ተባልን፡፡
ከዚያ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እኔና 7 አስተማሪዎቸ 8 ሆነን መጣን ከደቡብ አፍሪካ፡፡ በመጀመሪያ የተላክነው ሜክሲኮ አደባባይ ፊት ለፊት ወደ ሚገኘው ፌደራል ፖሊስ መስሪያ ቤት ነው፡፡ ለምን መለስ ፖሊሲዎቹ እንዲማሩለትና ዕውቅና ማረጋገጫ እንዲያገኙለት ይፈልግ ነበር፡፡ እነሱ ያልገባቸው ምን መሰለሽ? የምንሰጣቸውን ኮርሶች በሙሉ የምንሰጠው በመግቢያ ፈተና ነው፡፡ ይህን አልፈሽ ከተማርሽ ደግሞ በመጨረሻ ብቁ መሆንሽንና ያለመሆንሽን የምንፈትነውና የምናሳውቀው እኛ ሳንሆን የውጭ ፈታኝ (ኤክስተርናል ኤግዛማይነር) ነው። እኛ ይሄኛው ይሄኛው ብቁ ነው ብለን ስናቀርብ፤ የውጪው ፈታኝ ይመለከትና ይወስናል፡፡
ከዚያ ሊሰለጥኑ የመግቢያ ፈተና የፈተንናቸው ፖሊሶች በሙሉ ወደቁ፡፡ እኔ ይህንን አወቅሁና ወጣሁ፡፡ ምክንያቱም ገና ከጫካ ነዋ የመጡት፡፡ ኡኡ… አሉ፡፡ እኔንም ሲፈልጉኝ አጡኝ፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመለስኩ፡፡ እንግዲህ ያኔ ይሄ ተፈጠረ፡፡  እነሱ ሀሳባቸው፤ መለስም ችግሩን ቶሎ ቶሎ የፈታው፤ የራሱን ካድሬዎች ለማሰልጠን ነበር፤ አልሆነም በሙሉ ወደቁባቸው፡፡
ከዚያስ ምን ሆነ?
ከዚያማ የያኔው የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበረው የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ነበርና፤ ነገሮች ቀስ በቀስ እየተስተካከሉ መጥተው፤ ለሌሎች የሀገር ልጆች የመማር እድል ከፈተ፡፡ እኛም እውቀት ሳይኖራቸው ካድሬ ስለሆኑ ዝም ብለን ዲግሪ አንሰጥም ማለታችን አሁንም ያስደሰተናል፡፡ ሌሎች የመግቢያ ፈተናውን በብቃት ያለፉ ኢትዮጵያዊያን ተምረው ፒኤችዲ የጨረሱ ሁሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ደመቀ የተባለ ሰው በእንግሊዝኛ ፒኤችዲውን አግኝቶ በደብረማርቆስ ዩንቨርሲቲ ያስተምራል፡፡ ብቻ ለካድሬዎቹ የታሰበው ዩኒቨርሲቲ በርካታ ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን እንዲማሩበትና እንዲወጡበት ሆነ፡፡ ይሄ በጣም ነው የሚያስደስተኝ፡፡
በሌላ በኩል ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲማሩም ምክንያት እንደነበሩ  ይነገራል…?
ያው እንግዲህ እድሉ ሲገኝ ለሀገርሽ ምንም ብታደርጊ አትረኪም፡፡ እኔ እንግዲህ በውጪ ዩኒቨርሲቲዎች ከሰራሁ በኋላ ብቅ እልም እያልኩም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ለ15 ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ ለምሳሌ ወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ቫይስ ፕሬዚዳንት ሆኜ ሰርቻለሁ፤ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲም አገልግያለሁ ሌላም ሌላም ቦታ። የእኔ እሳቤ ምንድን ነው… በተለይ በእኛ እድሜ ያሉ ሁሉም የኢትዮጵያ አስተማሪዎች እኩል ናቸው እላለሁ፡፡ እንዴት ካልሽኝ… ቀድሞ በነበሩት ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩ ናቸው። አዲስ አበባ፤ ጅማ፤ ባህር ዳር፤ መቀሌ፤ ጎንደር፤ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩ ስለሆኑ ሁሉም እኩል ናቸው እላለሁ፡፡ እና እኔ ሳውዝ አፍሪካ ብዙዎችን አስተምሬያለሁ። እና እኔ ያስተማርኳት ልጅ ትምህርቷን ጨርሳ “ሄድ ኦፍ ፋውንዴሽን” ሆናለች፤ እናም ፃፈችልኝ። ደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ውስጥ 75 ነፃ የትምህርት ዕድሎች ሰላሉ ኖሚኔት አድርግ አለችኝ፡፡ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ከመምህር አካለወልድ ት/ቤት አንድ በድምሩ ሰባት ሰዎችን ኖሚኔት አደረግኩ፡፡ አራቱ አለፉ። 72ቱ የትምህርት እድል ለመላው አፍሪካ የተሰጠ ነው፡፡ ከሁሉም ከፍተኛ ቁጥር ኖምኔት ያደረኩት እኔ ነኝ፡፡ ሌሎቹ አንድ ቢበዛ ሁለት ነው የሚያገኙት፡፡ ሄዱ ተማሩ፡፡ መምህር አካለወልድ የነበረና አሁን ስለ ንጉስ ሚካኤል የፃፈ ምስጋናው የሚባል ነበር ትምህርቱን ጨርሶ ተመልሶ አሁን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ያስተምራል። ሙዝ ግደይ የተባለ አሁን ከህውሃት ጋር ሆኖ የሚበጠብጣችሁ፤ ከደብረፅዮን ቀጥሎ የህውሃት ቃል አቀባይ፤ እሱም ፖለቲካል ሳይንስ ጨርሶ ነው የተመለሰው፡፡
ብራይት ማን የምንለውም ከደቡብ አካባቢ ዲን ኦፍ ሎው ነበር ፒችዲውን ጨርሶ አሁን ባህር ዳር ያስተምራል፡፡ የሚገርምሽ አራቱም ስኬታማ ሆነው ነው የተመለሱት፡፡ ለዚህ ነው የቀድሞ አስተማሪዎች እኩል ናቸው የምለው። ከዚያ በኋላ እኔ ከወሎ ዩኒቨርስቲ ወጥቼ ወልዲያ ስሄድ፤ እኔና ፕሮፌሰር ያለው አንድ ዕቅድ አቀድን፡፡ እነዚህ አራቱ ሄደው ውጤታማ ከሆኑ፤ ሌሎች ለምን አንልክም ብለን ከወልዲያ ዩኒቨርስቲ ወደ 20 ሰው ላክን፡፡ 10 ዓመት 15 ዓመት ሰራሁ አይደለም ቁም ነገሩ። አንድም አመት ሰርተህ ጥሩ ከሰራህና አቅም ካለህ ታልፋለህ ብለን ነገርናቸው፡፡ ላክናቸው፡፡ አንድ ሰይድ የሚባል የማቲማቲክስ ሰው ነበር፤ እንግሊዝኛ ፍፁም አይችልም ይላሉ፡፡
ግን ጎበዝ ማቲማቲሺያን እንደሆነ ሰምቻለሁ። ሄዶ በሶስት ዓመት ጨረሰ፡፡ በጣም ብሪሊያንት -ብሩህ ነው፡፡ አሁን ተመልሶ እያስተማረ ነው፡፡ ሌላው የግብርና ዲን የነበረው ደምሰው ይባላል -መርሳ ነበር፡፡ እሱም እንደዚሁ ነው፡፡
ያኔ እኔና ፕ/ር ያለው ወልዲያ ዩኒቨርስቲ በነበርንበት ጊዜ የቦርድ ሰብሳቢው ንጉሱ ጥላሁን ነበር፡፡ እሱንና ፕ/ር ያለውን ደቡብ አፍሪካ ይዣቸው ሄድኩ፡፡ ከዚያ ከኬፕታውን ዩኒቨርስቲ፤ ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲና ከዌስተርኬፕ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመልን፡፡ ወደ 22 ይሆናሉ ሄደው የተማሩት፡፡ ብቻ እድሉን ካገኙ ኢትዮጵያኖች በሚገባ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ ወደ ኋላ የሚያስቀረን እድል አለማግኘት ብቻ ነው፡፡
የሀገራችንን የትምህርት ሥርዓት  እንዴት ይገመግሙታል?
እኔ በዚህ አገር ያለውን የትምህርት ሁኔታ ለማስተካከል ብዙ ነገር መሠራት አለበት ባይ ነኝ። ምክንያቱም በየሥርዓቱ ሁሉ ነገር ይቀያየራል። አንዱ ሲመጣ የነበረውን በሙሉ አፍርሶ ከዜሮ ይጀምራል፡፡ የኃይለ ስላሴን ዘመን ደርግ የፊውዳል ሥርዓት ነው ብሎ አፍርሶ እንደገና ይጀምራል፡፡ ሌላውም እንደዛው፡፡ አሁን ፕ/ር ብርሃኑ ተረክቦታል። እንግዲህ የሚስተካከል ነገር ይኖር እንደሆነ አብረን እንመለከተለን፡፡ የአሁኑን ለማስተካከል የበፊቱን መነሻ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ሲሞከር ቋሚና ቀለም ያላቸው ነገሮች የሉም፡፡ ተመልከቺ፤ አሁን እኔ ስማር ሁለት ዩኒቨርስቲ ነበር፡፡ የህዝቡ ቁጥር 30 ሚሊዮን አይሞላም ነበር፡፡ አሁን ፖፑሌሽኑ አድጓል። ዩኒቨርስቲዎቹም 50 ደርሰዋል፡፡ ግን ደግሞ የትምህርት ጥራት ጉዳይ በስፋት እንደችግር ይነሳል፡፡ ህዝቡ ስላደገ የዩኒቨርስቲ መብዛት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ጥራቱን ማስጠበቅም በዚያው ልክ ሊሰራበት ይገባል ባይ ነኝ። በጥራት ማስጠበቁ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሳተፍ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ደቡብ አፍሪካም እንግሊዝም ነበሩ። አሁን ኢትዮጵያ ነው ያሉት። ዋና መቀመጫዎ የት ነው?
ከኮቪዱ በፊት እዚህ ነበርኩ፡፡ ብዙ ሥራ አቅጄ ነበር የመጣሁት። ኮቪድ 19 ሲከሰት ልጆቼ መቀመጫ አሳጡኝ፤ አስደነገጡኝ። ተመልሼ እንግሊዝ ሄድኩኝ፡፡ ዋና መቀመጫዬ እንግሊዝ ኦክስፎርድ ነው፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ መምጣቴ ነው፡፡
አሁን እዚህ ሥራ ይዘው እንደመጡና የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ጥናት እየሰበሩ መሆኑን ነው የሰማሁት። ምን ዓይነት ጥናትና ምርምር ላይ ነው ያተኮሩት?
አሁን እዚህ የመጣሁት ለበርካታ ሥራ ነው። በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትነት የተመዘገበ ተቋም መስርቼያለሁ፡፡ “ክሬደል ሴንተር ፎር ሪሰርች” ይሰኛል፡፡ እንደ ቢዝነስ ተቋምም ነው። ትኩረቱ ጥናትና ምርምር ላይ ሲሆን በሱ ነው የምሰራው፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እየጀመርን ነው። ከመጣሁም ገና ሁለት ወር አልሞላኝም፡፡
አሁን የመንግስት ሥራ ሙሉ በሙሉ ተው ማለት ነው?
አዎ! የመጨረሻው የመንግስት ሥራዬ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ነበር፤ አሁን በትምህርት ሚኒስቴር ስር ተጠቃልሏል። እዛ እያለሁ በጣም እዞር ስለነበር አገሩን በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ አሁን ምን ላይ ነው ጥናትህ ያተኮረው ካልሽኝ፤ የሴቶች ችግሮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አሁን ሰሞኑን ወደ አርጎባ ማህበረሰብ ሄጄ ነበር፡፡ ያለ እድሜ ጋብቻን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ ገና በ13 ዓመታቸው ወይ ያገባሉ ካልሆነ ሳዑዲ አረቢያ ይላካሉ። ይህንን እንዴት እንፍታ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ አንኮበር ሄጄ ነበር መንገዱ ሊያልቅ ነው፡፡ ይህ ቦታ ሰው አይሄድበትም። ይህ ትልቅ ቦታ እንዴት አይታወቅም? እንዴት አይጎበኝም? እንዴት ወደ ሀብትነት አይቀየርም? የሚል ትልቅ ቁጭት አለኝ፡፡ አየሽ እዚህ ሀገር ብዙ ችግር አለ። ሁሉንም ችግር መንግስት ይፍታው ብሎ እጅ አጣጥፎ መቀመጥ አይቻልም፡፡ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚቋቋሙበት ዓላማም በመንግስት የማይሸፈኑ ችግሮችን ለመፍታት ነው፡፡ አንኮበር ታሪካዊ ነው፤ ከአዲስ አበባ ደርሶ መልስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይሄ ትልቅ ቦታ መታየት፤ መጎብኘት፤ መደነቅና ለሀገር ሀብት መሆን አለበት፡፡ በዚህ ላይ እንሰራለን፡፡
ሌላው በጣም የተደሰትኩበት ነገር፣ ኮቪድ መጥቶ ከሀገር ከመውጣቴ በፊት ባህርዳር ላይ በአፍሪካ ሊትሬቸር ላይ ያተኮረ ትልቅ ጉባኤ አዘጋጅቼ ነበር፡፡ የአፍሪካ ሊትሬቸር አባልም ነኝ፡፡ ካምፓላ ዛንዚባር ይካሄዳል። እኔም ኢትዮጵያም መካሄድ አለበት ብዬ እዚህ አምጥቼው ነበር፡፡ እና አንዱ ሱዳናዊ ዋናው የአማርኛ ስነ-ጽሁፍ የት ነው ያለው ብሎ ጠየቀኝ። ደብረ ማርቆስ ነው አልኩት። እንዴት? አለኝ፡፡ ደብረማርቆስ ደወልኩና መምጣት እንፈልጋለን ብዬ ሄድን፡፡ ይህ ሱዳናዊ በጣም ተገረመ፡፡ እሱ የዳርፉር ሰው ነው፡፡ ባራካ ይባላል። የታወቀ የስ-ጽሁፍ ሰው ነው፡፡ በጣም ተደነቀ ከዚያ አንድ ነገር ማድረግ አለብን አልንና 15 አጭር ልብወለዶች መረጥን፡፡ ከዚያ ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉመው ታትመዋል። በቅርቡ ይመረቃሉ። የሚመረቁትም ደብረማርቆስ ነው፡፡ ይሄም በቂ አይደለም ደብረማርቆስ “ሂስቶሪካል ሩት” ከሚባሉት አምስተኛ ሆኖ መጨመር አለበት። ምክንያቱም አባይ አለ፤ ብዙ ቤተክርስቲያናት አሉ፤ ብዙ ስዕል አለ፤ ሥነ ፅሁፍ በጉልህ የሚፈልቅበት ነው፡፡ አውሮፕላን ጣቢያውም በቅርቡ ስራ ይጀምራል፡፡ ደበረ ማርቆስ፤ባህር ዳር፤ ጎንደር፤ ላሊበላ አክሱም… መሆን አለበት ብዬ ግፊት እያደረግን ነው፡፡ እንዴት ካልሺኝ ሁለት ግሩፕ አለ፡፡ አንድ እኔ አባል የሆንኩበት እንግሊዝ አገር ያለ ኢቨንት ይመጣል፡፡
“አንግሎ ኢትዮጵያን ሶሳይቲ” ይባላል። ሲልቪያ ፓንክረስት ያቋቋመችው ነው። 75 ዓመት አስቆጥሯል። 75 ዓመታችንን እናከብራለን ሲሉ እንደዛ ከሆነ፣ ሲልቪያ ፓንክረስት የተነሳችው አፄ ሀይለ ስላሴ በግዞት በነበሩበት ጊዜ ፀረ ፋሽስት ሆና እሱን ለመቃወም ነው፡፡ ቀጥሎ ኢትዮጵያ መጥታ የመጀመሪያው “ኦቭዘርቨር” የተሰኘ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ኤዲተር ነበረች፡፡ የአሉላ ፓንክረስት አያቱ ነች፡፡
ስለዚህ ይህ 75ኛ ዓመት ለምን እንግሊዝ አገር ብቻ ይከበራል ቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር የተገናኘ ነው ብዬ እሱን ሁነት እዚህ ልናመጣው ነው። ፖዚሽን ፔፐር ተዘጋጅቷል- ታይዋለሽ። ሁነቱ ሁለት ቦታ ነው የሚከበረው አንዱ ደብረ ማርቆስ ነው፡፡ ይህም ከጀነራል ዊንጌትና ሳንፎርድ ት/ቤቶች ጋር የተገናኘ ታሪክ አለው። እሱን እየሰራን ነው፡፡ እሱን ካሳካን አንድም ታሪክን ፕሮሞት እናደርጋለን፡፡ ሁለተኛ ለቱሪስት መዳረሻነትም ይሆናል፡፡ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ በቀረኝ እድሜ ለሀገሬ ብዙ ነገር ለመስራት እቅድ ይዤ ነው ድርጅቱን ያቋቋምኩት። ለወደፊት የሚሆነውን አብረን እናያለን፡፡ እንግዳ ስላደረግሽኝ በእጅጉ አመሰግናለሁ። ከዚህ በላይ ብዙ የምናወራቸው በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ እየተገበርን እያሳካን ስንሄድ ደግሞ በቀጣይ እንነጋገርበታለን፡፡  


Read 1522 times