Saturday, 27 October 2012 09:42

በአሸባሪነት በተጠረጠሩት ተከሳሾች ላይ ውሣኔ ሊሰጥ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(13 votes)

ተከሳሾቹ የአልሸባብና አልቃይዳ አባላት እንደነበሩ ተገልጿል
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሣዳም ሁሴን ስም አካውንት ከፍተው ነበር
የዋህብይ ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም ጂሀድ ለማወጅ በዝግጅት ላይ ነበሩ ተብሏል
ዓለም አቀፍ አሸባሪ በሆኑት የአልቃይዳና የአልሸባብ ቡድኖች በአባልነት ተመልምለውና ሰልጥነው ከሶማሊያ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የጂሀድ ጦርነት ለማወጅ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ተደርሶባቸዋል በሚል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት ተከሳሾች ላይ ውሣኔ ሊሰጥ ነው፡፡ በወንጀሉ ከተከሰሱት አስራ አንድ ሰዎች ስድስቱ አልተያዙም፡፡

በእነ ሀሰን ጃርሶ መዝገብ በፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ሀሰን ጃርሶ ኬኒያዊ ሲሆን ቀሪዎቹ ተከሳሾች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡የፌደራሉ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ካቀረባቸው ክሶች መካከል የሽብር ወንጀል መፈፀም፣ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሣተፍ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና፣ በህገወጥ መንገድ የሀገር ድንበር ጥሶ መግባትና መውጣት ወንጀሎች የሚሉ ይገኙበታል፡፡ 
ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበው የወንጀል ክስ እንደሚያመለክተው፤ ተከሳሾቹ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጁት አልሸባብና አልቃይዳ ከተባሉት አሸባሪ ቡድኖች ጋር በማበርና በአባልነት በመመልመል በሶማሊያ ሞቃዲሾ በሚገኙ የማሰልጠኛ ቦታዎች ውስጥ ገብቶ በመሰልጠን በሽብር ተግባር ላይ ለመሰማራት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ተከሳሾቹ ከአልሸባብና አልቃይዳ አመራሮች የተሰጣቸውን ተልዕኮ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ በመግባት፣ የዋህብይ ሃይማኖትን እንደሽፋን በመጠቀም ጂሀድ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ የሀይማኖት ጦርነት ለማወጅ ሲዘጋጁ መያዛቸውን ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ ያመለክታል፡፡ እንደ ዐቃቤ ህግ የክስ አቀራረብ፤ አንደኛው ተከሳሽ ሀሰን ጃርሶ ወይም በቅፅል ስሙ ናዚፍ ጃተኒ፣ ጃለሉዲን አልሙሀጂሪን ወይም አቡ ሚልኪ አልቡራኒ የተባለው በ2001 ዓ.ም በጋዛ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ሰልጥኖ፣ እስከ 2003 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በሞቃዲሾ ከተማ ከሽግግር መንግስቱ፣ ከኡጋንዳና ብሩንዲ የሠላም አስከባሪ ወታደሮች ጋር ውጊያ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በ2004 ዓ.ም ሀሰተኛ የኢትዮጵያ መታወቂያ አሠርቶ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የጅሀድ እንቅስቃሴ ለአልቃይዳና አልሸባብ አመራሮች ሪፖርት በማድረግ በሀገር ውስጥ የሚካሄደውን የአልሸባብና የአልቃይዳ የሽብርና የጅሀድ እንቅስቃሴ ተወካይ ሆኖ ሲያስተባብርና አመራር ሲሰጥ መገኘቱን ዐቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ላይ ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ ባሌ ሮቤ ከተማ ውስጥ ቤት በመከራየትና ቁራን ቤት እንደሽፋን በመክፈት ከሮቤ አዲስ አበባ በመንቀሳቀስ አባላትን ለጂሀድ በመመልመል፣ በማስተማርና በማደራጀት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡በኦሮሚያ ክልል ጃጂ በሚባል ቦታ ላይ ምልምል አባላቱ ሥልጠና እንዲወሰዱ በማድረግ፣ እዚህ አዲስ አበባ በተለያዩ ሥፍራዎች ከፀጥታ ኃይሎች የተሰወረ ማረፊያ ቦታ አዘጋጅተው የአልሸባብና የአልቃይዳን ተልእኮ ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ መገኘታቸው በክሱ ላይ ተገልጿል፡፡ በዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ በ6ኛ ተከሳሽነት ስሙ የተገለፀውና በቁጥጥር ሥር ያልዋለው የሱፍ ሀሰን፤ የአሸባሪው የአልሸባብ ወታደር ሆኖ ሲንቀሣቀስ ቆይቶ፣ ከአልሸባብና አልቃይዳ አመራሮች በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የጂሀድ ጦርነት ለመቀስቀስና የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
በአጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች ዓለም አቀፍ አሸባሪ በሆኑትና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጁት የአልቃይዳና አልባብ የተሰጣቸውን የሽብር ተልዕኮ ለመፈፀም ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የጅሀድ ጦርነት ለማካሄድ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት፣ የጂሃድ ጦርነት ሥልጠና በመስጠት፣ በውጭ አገር ተወካይ ገንዘብ በማስቀመጥ፣ ገንዘብ በማሰባሰብ ከውጭ አገር ከሚገኙ የአልቃይዳና አልሸባብ አመራሮች ጋር በተለያዩ ዘዴዎች በመገናኘት፣ ሪፖርት በማስተላለፍና ተልዕኮ በመቀበል እንዲሁም የጅሀድ ጦርነት በማወጅ በህዝቦች ላይ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው መከሰሳቸውን ዐቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ላይ ገልፆታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሾቹ የሽብር ወንጀል ለመፈፀምና ለማስፈፀም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ቅርንጫፎች የሚላክላቸውን ገንዘብ እያወጡ የተጠቀሙ ሲሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዓለም ባንክ ቅርንጫፍ በሳዳም ሁሴን ስም በተከፈተ አካውንት የተላከላቸውን ገንዘብ አውጥተው ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበው አራተኛ ክስ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባትና ከኢትዮጵያ መውጣት ወንጀሎች ሲሆን በዚህም ስድስት ተከሳሾች ተጠያቂ ሆነዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት፣ በተከሳሾቹ ላይ የቀረበውን የወንጀል ክስ ተቀብሎ ከመረመረና የዐቃቤ ህግን ማስረጃዎችና የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃዎች ተቀብሎ ካየና ከመረመረ በኋላ በጉዳዩ ላይ ውሣኔ ለመስጠት ከትናንት በስቲያ ቀጥሮት የነበረ ቢሆንም በዳኞች አለመሟላት ምክንያት ቀጠሮውን በመቀየር በመጪው ጥቅምት 23/2005 ዓ.ም ውሣኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይዟል፡፡

 

Read 3351 times Last modified on Saturday, 27 October 2012 09:47