Saturday, 26 November 2022 00:00

በጥንቃቄና በጥርጣሬ የሚጠበቀው የህወሓት ትጥቅ መፍታት እያወዛገበ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 • “በሰላም ስምምነቱ መሰረት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ እየሰራን ነው”- ጄነራል ታደሰ ወረደ
  • “የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ካልወጣ ህወሓት ትጥቅ የሚፈታበት ምክንያት የለም” - አቶ ጌታቸው ረዳ
                
      በመንግስትና በህውሓት አመራሮች መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ የማድረጉ ሂደት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ አለመሆኑን ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን የህውሓት ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ በአመራሮቹ ዘንድ እያወዛገበ ነው፡፡
የህውሃት ጦር አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በህውሃት ሃይሎች በኩል የሚፈፀመውን ትጥቅ የመፍታት ሂደት ለመጀመር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙና ከሰራዊቱ አዛዦችና ከሰራዊቱ አባላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን እንዲሁም ለሰራዊቱ አዛዦችና እስከታች ድረስ ላሉ የሰራዊቱ አባላት ተሰጥቷል። ከዚህም በመቀጠል የሰራዊቱን የውጊያ ግንባሮች የማፍረስና ሰራዊቱን ወደ ተቀመጠለት ቦታ የማጓጓዙ ጉዳይ የሚቀጥል ይሆናል፤ ይህም የማጓጓዝ አቅማችንና የሎጀስቲክ ሃይላችን እስከፈቀደ ድረስ የሚከናወን ይሆናል ብለዋል፡፡ “ሰራዊቱ በአንድ አስተሳሰብ አንድ ዕዝ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ነው፡፡ ትልቁ ስራም ይህ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ደግሞ ጀምረናል ብቻ ሳይሆን እየጨረስን ነው ያለነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀሩን ጥቂት ስራዎች ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል ጀነራሉ፡፡
“ጀነራል ታደሰ ሰሞኑን ለትግራይ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በእኛ በኩል ማንኛውም በትግራይ ውስጥ ያለው የትግራይ ኃይል በአንድ ኮማንድ ስርአት ውስጥ ሆኖ የሚንቀሳቀስ፤ ግዳጅ የሚፈፅም ነው፡፡
ከዚህ ውጪ የሆነ ኃይል የለንም፤ ስለዚህም ከቁጥጥር ውጪ የሚሆን ነገር የሚኖር አይመስለኝም” ብለዋል፡፡
“ኃይል ማንቀሳቀሱ ቀላል ነው የሚሆነው አቅም ነው የሚወስነው፤ ይህ የሎጀስቲክ ጉዳይ ነው፤ ትግበራው ተጀምሯል” ብለዋል- በመግለጫቸው፡፡
የህውሃቱ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ከቢቢሲው ሃርድቶክ አዘጋጅ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ካልወጣ በስተቀር ህውሓት ትጥቅ  የሚፈታበት ምንም ምክንያት አይኖርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በፌደራል መንግስትና በህውሃት ሃይሎች መካከል ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በስምምነቱ አተገባበር ላይ ምንም የተቀየረ ነገር  እንደሌለ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ስምምነቱ የትግራይ ህዝብ ደህንነት በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።
ስምምነቱ የተፈረመው በትግራይ ክልላዊ መንግስትና በፌደራል መንግስቱ መካከል እንደሆነም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፤ ባለፉት ሳምንታት ስተፈረመው የሰላም ስምምነት ለህወሓት ታጣቂዎች በመግለጽ፣ ታጣቂዎቹ ትጥቅ መፍታትና ከያዟቸው አካባቢዎችም በመልቀቅ ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ እንዲሄዱ የማድረግና የማግባባቱ ስራ ከፍተኛ ፈተና እደገጠመው አንዳንድ የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ለመፍታት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። በተለይ በሽሬ፣ በአድዋና በአክሱም አካባቢ የሚገኙ የህወሓት ታጣቂዎች የሰላም ስምምነቱን አክብረው ትጥቅ ለመፍታ ብዙም ፈቃደኝነት አለማሳየታቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።



Read 8866 times