Print this page
Saturday, 26 November 2022 00:00

ዓለም የለየለት እብደት ውስጥ ናት!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

 • ታይዋን ሦስተኛው የዓለም ጦርነት መንስኤ እንዳትሆን ተሰግቷል
     • የፖላንድ የሚሳይል ጥቃት አርማጌዶን ሊያስከትል ይችል ነበር
     • ቁጣዋን በሚሳይል የምትገልጸው ሰሜን ኮሪያ፤ አሜሪካንን አስጠንቅቃለች!
      
      ወዳጆቼ፤ ዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ የለየለት እብደት ውስጥ ገብታለች። የዲሞክራሲ እናት፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብትና የነፃነት ግንባር ቀደም ተሟጋች እየተባለች ስትሞካሽ የኖረችው ታላቋ አሜሪካ፤ አሁን ስም ብቻ የቀራት ትመስላለች፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እየተሸረሸረ መምጣቱ ይነገራል፡: ዩኒቨርስቲዎች ከራሳቸው የተለየ አስተሳሰብ ማስተናገድ እርም እያሉ ነው፡፡  (ከዚህ በላይ እብደት አለ?!)
 በብቃታቸውና በሙያዊ  ሥነ-ምግባራቸው ስመ-ጥር የነበሩ የአሜሪካ  ሚዲያዎች አሁን የፓርቲ ልሳን እየመሰሉ ነው፤ ሚዛናዊነታቸው ቀርቶ ወገንተኝነት እያጠላባቸው መጥተዋል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ “ፌክ ኒውስ” እያሉ ከሚጠሯቸው አንዱ የሆነው CNN ለአብነት ይጠቀሳል፡፡ (የኋሊት ጉዞ ይሏል ይኼ ነው!)፡
በቅርቡ በአሜሪካ ከተካሄደው የሚድተርም ምርጫ ጋር በተያያዘ የአዲስ አድማሱ የ”እንጨዋወት” ዓምድ አዘጋጅ ኤፍሬም እንዳለ፣ ከሳምንት በፊት ትዝብቱን  አስነብቦ ነበር። እስቲ አንዲት አንቀጽ ብቻ መዘን እንይለት።
“ደግሞላችሁ…ሪፐብሊካኖቹ ሲሰብኩ፤ “ዴሞክራቶቹ በምክር ቤቶቹ አብላጫ ድምፅ ይዘው ከቀጠሉ የአሜሪካ ውድቀት ብቻ ሳይሆን የዓለም ጦርነት ሁሉ ሊነሳ ይችላል።” ይላሉ። ዲሞክራቶቹ ደግሞ “ሪፐብሊካኖች አብላጫ ወንበር ከያዙ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይሸረሸራሉ፣ ዜጎች የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች ሁሉ ያጣሉ፣ የሕግ የበላይነት ይፈርሳል፤” ዓይነት ነገር ይላሉ። እና ከእኛ ምን ለያቸው? እነሱ “ቺክን በርገር”፤ እኛ “እርጥብ” ከመብላታችን በቀር!ቂ..ቂ..ቂ..”
በሚያሳዝን ሁኔታ በዘንድሮ የሚድተርም ምርጫ  ፉክክር ላይ የተንጸባረቀችው አሜሪካ እቺው ናት ከላይ በኤፍሬም እንዳለ በስላቅ የተገለፀችው። ፅንፈኝነት የፖለቲካ ምህዳሩን ተቆጣጥሮታል። በአገሪቱ ጥላቻና ክፍፍል እየነገሰ መጥቷል፡፡ የአሜሪካ ከተሞች (በተለይ በዲሞክራቶች የሚመሩት!)  አደገኛ ወንጀሎች የሚፈጸሙባቸው ሆነዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት” እና “የኒውክሌር ጥቃት” ተዘውትረው የሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ሆነዋል። ሁሉም ጉልበት መፈታተሽ እያማረው መጥቷል። ፍላጎትን በሃይል ማስፈጸም እንደ ባህል እየተቆጠረ ነው፤ ንግግርና ድርድር ደግሞ ፋሽኑ ያለፈበት ይመስላል። (ዓለም እብደት ውስጥ ናት አላልኳችሁም!)
በዓለም መድረክ ላይ  ጦርነትን እያጋጋሉ የጦር መሳሪያ የሚቸበችቡ እንጂ አሸማጋዮች ወይም የሰላም አምባሳደሮች ፈልጎ ማግኘት ዘበት ሆኗል። (ዓለም አብዷላ!)
ላለፉት 10 ወራት ገደማ በሩሲያና ዩክሬን መካከል በቀጠለው ደም አፋሳሽ  ጦርነት፤ ዓለም ጣልቃ ገብቶ ሲያሸማግል አልታየም፤ ሲያባብስ እንጂ፡፡ ኔቶም በተጠንቀቅ ላይ የሚገኘው የኔቶ አባል አገራት በሩሲያ ጦር ከተነኩ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ነው። ጦርነት ለመግጠም ማለት ነው። ባለፈው ሳምንት  ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ላይ በምትገኝ የፖላንድ መንደር ውስጥ ሁለት ሚሳይሎች መተኮሳቸውን ተከትሎ፣ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውጥረት መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ ብዙዎች የሁለት ንፁሃን ገበሬዎችን ህይወት ለቀጠፈው የሚሳይል ተኩስ፣ ሩሲያ ላይ ጣታቸውን ቀስረው ነበር።
ሞስኮ ፖላንድ መንደር ውስጥ በተተኮሱት ሚሳይሎች፣ እጄ የለበትም ብትልም የሚሰማት አላገኘችም። “በሩሲያ ላይ የቀረበው ክስ ሆነ ተብሎ ሁኔታዎችን ለማባባስ የተደረገ ነው” ስትልም በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል ማጠናከሪያ ምላሽ ሰጥታለች- ከተጠያቂነት ባያድናትም። ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ታዲያ ከመቅጽበት “የተፈራውና የተሰጋው 3ኛው የዓለም ጦርነት አይቀሬ ሆኗል” እያሉ ሰበር ዜና - Breaking News- እያሰራጩ ሁሉ ነበር። ይሄ ምን ማለት መሰላችሁ? በሩሲያና በዩክሬን መካከል ለ276 ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በአንድ ጀንበር በሩሲያና በኔቶ ወይም በሩሲያና በመላው አውሮፓ (አሜሪካን ጨምሮ) መካከል የሚካሄድ ይሆናል ማለት ነው። ያኔ ደግሞ ሩሲያ ዓለምን ስታስፈራራበት የቆየችውን ኒውክሌር ትመዝ ይሆናል። አብረን እንጠፋታለን በሚል እልህ። (ያኔ ባይደን እንዳሉት፤ አርማጌዶን ሆነ ማለት ነው!)
 ደግነቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከአማካሪዎቻቸው ጋር ተወያይተው በሰጡት ምላሽ፤ “የተተኮሱት ሚሳይሎች ከሩሲያ የመሆናቸው ዕድል ዝቅተኛ ነው” ብለው ውጥረቱን አረገቡት። (የጦርነት ነጋዴዎችን ቢያበሽቅም!) በኋላ ላይ የፖላንዱ  ፕሬዚዳንት አንድሬ ዱዳም በተመሳሳይ፣ የጆ ባይደንን ግምት የሚያጠናክር መረጃ ሰጡ - “ሚሳይሎቹ የተተኮሱት ከዩክሬን አየር መከላከያ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።” በማለት። (ለጊዜውም ቢሆን ዓለም እፎይ አለች!) እንዲያም ሆኖ ግን ሩሲያ ከተጠያቂነት አልዳነችም። የኔቶ አዛዥ ለዩክሬኑ አየር መከላከያም ቢሆን ተጠያቂዋ ራሷ ናት ብለዋል-ሩሲያ!!
በነገራችን ላይ  ብዙዎች ለሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መባባስ የአሜሪካና የአውሮፓ እጅ እንዳለበት  ያምናሉ - በተለይ ደግሞ የአሜሪካ። በእርግጥም ታላቋ አሜሪካ ከዩክሬን ጋር ጦርነቱን የምትገጥም ያህል ነበር፣ ሁኔታውን ስታጋግልና ስታባብስ የነበረችው። ጦርነቱ በገሃድ ሲጀመር ግን ሁሉም እጁን ሰበሰበ። አጋርነቱን በጦር መሳሪያና በሰብአዊ ድጋፍ ብቻ ወሰነ። አሁን ታዲያ የዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች በጦርነቱ ወድመዋል። በየቀኑም ውድመቱ ቀጥሏል። የትኛውም አገር ወይ ዓለማቀፍ ተቋም ጣልቃ ገብቶ ለማደራደርና ጦርነቱን ለማስቆም ሙከራ ሲያደርግ አይታይም። የጦር መሳሪያ ድጋፉ ግን ቀጥሏል። አውዳሚው ጦርነት  መቼ ያበቃል? ማንም አያውቅም። (ለነገሩ የውክልና ጦርነትም እኮ ነው።) በዩክሬን አማካኝነት እነ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የገጠሙት  ጦርነት ነው። በእርግጥ አሜሪካና አውሮፓ በጥምረት በሩሲያ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥለውባታል- የታሰበውን ያህል ባያሽመደምዳትም።
ሰሞኑን አንድ የአሜሪካ ጦር አዛዥ በሰጡት መግለጫ፤ “አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ አገሪቱ ነጻነቷን እስከምታረጋግጥና ሩሲያ የዩክሬን ስጋት መሆኗ እስኪያበቃ ድረስ እንቀጥላለን” ብለዋል። (ንግግሩ ጦርነቱ በቅርቡ እንደማያበቃ ጠቋሚ ነው!) በሌላ በኩል፤ የአውሮፓ አገራት የጦር ጀነራሎች ሰሞኑ በብራሰልስ ተሰብስበው ሲመክሩ ነበር ተብሏል።  ዩክሬን ራሷን ከሩሲያ ጥቃት ትመክት ዘንድ አገራቱ የጦር መሳሪያ በመርዳት ላይ ሲሆኑ የጦር መሳሪያቸው ክምችት እየቀነሰ መሆኑ አሳስቧቸው ነው ለምክክር የተቀመጡት፡፡  የማታ ማታም፣ የአውሮፓ ህብረት የ70 ቢሊዮን ዩሮ የጦር መሳሪያ ግዢ እቅዱን ይፋ አድርጓል። (ለመተላለቅ 70 ቢ. ዶላር!!)
 ዓለም የለየለት እብደት ውስጥ መሆኗን የሚያረጋግጥ ሌላ አብነት ልጥቀስ። ቁጣዋን እንኳን ሚሳይል በማስወንጨፍ የምትገልፀው የኒውክሌር-ታጣቂዋ ሰሜን ኮሪያ፤ በቅርቡ በአንድ ቀን ውስጥ በርካታ ሚሳይሎችን በማስወንጨፍ በራሷ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ መስበሯ ተነግሯል። (ሚሳይል እንደ ሪችት ነው የምትተኩሰው!)
ከሰሞኑም  ሰሜን ኮሪያ፣ አጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏን ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች፡፡ ሚሳኤሉ ወንሳን ከተሰኘችው የሀገሪቱ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ፣ ወደ ባህር እንደተወነጨፈ  ነው የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።  ፒዮንግያንግ የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ  ቾይ ሰን ሁይ፣ አሜሪካን ያስጠነቀቁበትን መግለጫ ካወጡ ከጥቂት ሰአት በኋላ ነው ተብሏል።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ባለፈው ሳምንት በካምቦዲያ ካደረጉት የሶስትዮሽ ስብሰባ በኋላ የመጀመሪያ አቋሟን ያንፀባረቀችው ሰሜን ኮሪያ፤ የዋሽንግተን በቀጠናው እጇ መርዘምን ተቃውማለች። በካምቦዲያው የሶስትዮሽ ስብሰባ አሜሪካ ሁለቱን አጋሮቿን ከሰሜን ኮሪያ ለመጠበቅ ኒውክሌር እስከ ማስታጠቅ ድረስ  ቃል ገብታለች።
ሀገራቱ የሚያደርጉት የጦር ልምምድም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መናገራቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል። የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾይ ሰን ሁይም፣ የሦስትዮሽ ምክክርም ሆነ የጦር ልምምድ፣ የወረራ ዝግጅት ነው ብለውታል።
ይህ የወረራ ዝግጅታቸው ግን ይዞባቸው የሚመጣውን ከባድ ስጋት አይቋቋሙትም ሲሉም ዝተዋል። የኮሪያ ልሳነ ምድርን እያወከች ነው ባለቻት አሜሪካ ላይም፣ ሀገራቸው ከባድ እርምጃ እንደምትወስድ ነው ያስጠነቀቁት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ፤ ከጎረቤቷ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመመከት ወታደራዊ ሀይሏ በተጠንቀቅ እንደሚገኝ አስታውቃለች። (ሁሉም ተፋጠዋል እኮ!)
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አከታትላ የሞከረቻቸው የአጭርና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች በአምስት አመት ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዋን መጠቀሟ አይቀሬ መሆኑን ያሳያል የሚሉት አሜሪካና አጋሮቿ፤ በጋራ ወታደራዊ ልምምድ ላይ ተጠምደዋል። (ሰሜን ኮሪያ ደግሞ ለምን አብራችሁ አየኋችሁ እያለች ነው!)
ሁለቱ የዓለማችን ሃያላን አገራትም- አሜሪካና ቻይና፣ ከተፋጠጡ ከራርመዋል- በተለይ በታይዋን ጉዳይ። ለጦርነት እያሟሟቁ ነው ቢባል ነው የሚሻለው፡፡ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ፣ በቅርቡ የቻይና ወታደሮች፤ “ለጦርነት እንዲዘጋጁ” ትዕዛዝ መስጠታቸው የተሰማ ሲሆን የቻይና ብሔራዊ ደህንት ስጋት መጨመሩንና ጥርጣሬም ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል ተብሏል።
ቻይና፤ የግዛቴ አካል የምትላት ታይዋን፣ ከምዕራባውያን ጋር የመሰረተችው ወዳጅነት ነው ይሄን ሁሉ አቧራ ያስነሳው፡፡ እናም ብዙዎች ታይዋን ለሦስተኛው የዓለም ጦርነት መንስኤ እንዳትሆን ስጋት አላቸው፡፡ (እንዴት አይሰጉ!) ፕሬዚዳንቱ እኮ በታይዋን የመጣብንን አንምርም ብለው ተፈጥመዋል።
ዓለም የለየለት እብደት ውስጥ መሆኗን ማሳያ እኒህ ብቻ አይደሉም። ተዘርዝረው አያልቁም። (እኛም ዘንድ መቶ ሺዎችን በጦርነት አስጨርሰው፣ አሁንም ሌላ ጦርነት ለመጀመር የሚዳዳቸው አልጠፉም!) ተዋግተን ብቻ ስለማንወጣው ፈጣሪ ይያዝልን ማለቱ ሳይበጅ አይቀርም፡፡ እኔ የምላችሁ ግን ዓለምን ከገባችበት ከዚህ እብደት ማነው የሚያወጣልን? ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡
ፈጣሪ ለዓለማችን ሰላምን ያውርድልን!!
መረጃ በቁጥር
ዩክሬንና ሩሲያ በጦርነቱ የተገደሉባቸው ወይም የቆሰሉባቸው ወታደሮች (ከእያንዳንዳቸው) ከ100 ሺ በላይ
በዩክሬን በጦርነቱ የተገደሉ ሲቪሎች 40ሺ
ዩክሬን ከአሜሪካ ያገኘችው የደህንነት ድጋፍ (ከፌብሯሪ 24 ጀምሮ) ከ18.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ
የሩሲያ ወረራ ዩክሬን ላይ ያደረሰው ኪሳራ (ጉዳት) 1 ትሪሊዮን ዶላር
ዩክሬንን ዳግም ለመገንባት የሚጠይቀው ወጪ  349 ቢሊዮን ዶላር
ሰሜን ኮሪያ በአንድ ቀን ውስጥ የተኮሰቻቸው ሚሳይሎች 23



Read 757 times