Monday, 28 November 2022 16:19

የፒያሣ እብዶች (ወግ)

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(1 Vote)

  «ደብዝዘሽ አጋለጥሻቸው» የምትለዋን የእዮብ መኮንን ዘፈን ወንዶች ሁሉ ለሚስቶቻቸው ይጋብዛሉ (ሚስቲቱ ቆንጆም ትሁን መልከ-ጥፉ)። አጀኒ ይኼን ዘፈን በተለየ መልኩ ይጋብዛታል ለፒያሣ፤ ለአራዶቹ ሰፈር። «ደብዝዘሽ አጋለጥሻቸው ለእሱ እና ለጓደኞቹ mantra ነች። (በቡድሂዝም/በሂንዱይዝም ተመስጥኦን ለማምጣት የሚደጋግሟት ቃል ወይም ድምፅ ማንትራ ናት_ፒያሣም ለአጀኒ እና ጓደኞቹ እንዲሁ ነች፤om mani padme hum ዓይነት።»
 «ከሩቅ ሳትስቢ
አየሁ ከልቤ ስትገቢ» ይላታል ሲነጋ ሲመሽ ፒያሣን። አገርም እንደ እናት ይወደዳል ወይ? ቢሉት አገር ተብየው እንደ ፒያሣ ከሆነ፣ ለምን አይወደድ ነው የአጀኒ መልስ።
የአጀኒ እጆች  ለጋዜጣ ቅርብ ናቸው። አዲስ አድማስን እና አዲስ ዘመን ጋዜጣን ከልቡ ይወዳቸዋል። ፒያሣ ውስጥ ከታዋቂው ባቅላባ ቤት እስከ ታዋቂው ለውዝ ሻጭ ድረስ የእርሱ ግዛት ነው። በግዛቱ መሐል ተዘርግተው በ፵፭ብር ከሚቸበቸቡት መጽሐፍት መካከል ፒያሣን ያያል። አገላበጦ አገላብጦ ያስቀምጣታል። አድማጭ፣ አንባቢ አድርጎ ፈጥሮኝ እንጅ ፒያሣ ለአንቺ ብጽፍ ሰማይ ምድሩ አይበቃኝም፤እሙች ይላል ደጋግሞ።
እሁድ’ለት ፀሐይ አድፍጣ ነበር።
አጀኒ ጋዜጦቹን በብብቱ ይዞ ማዕዘኑ ላይ፣ህንጻ ሥር ተቀምጦ ለውዝ ከሚሸጠው ራስታ ፊት ጎንበስ አለ። ሁለት የወረቀት ጥቅልል ከፈገግታ ጋር ተቀበለ። ለውዙን በግራ እጁ ጋዜጣውን በቀኝ እጁ ይዞ ከአጼ ሚኒልክ ሀውልት ጋር ተፋጠጠ። እምዬ አለ በልቡ። የአረቄ ስካር እንደያዘው ተንደርድሮ  ሀውልቱ ሥር ኼዶ ተቀመጠ።
አዲስ ዘመንን ገለጠ።
ኃይለማርያም ወንድሙ 2014 ዓ.ም አካባቢ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያወጣትን የፒያሣ ቅኝት ማንበቡን ያዘ። ፒያሣ አራዳ ትባል እንደነበር፣ የአዲስ አበባ ሥምና ዝና የፀናው በፒያሣ እንደሆነ፣ አመሠራረቷ ለጣሊያኖች መኖሪያና መዝናኛ ታስባ እንደሆነ፣ mayor (ከአንተ ዘንድ ይግባ ካንተ ይብዓ - ከንቲባ... ከቢትወደድ ወልደ ጻድቅ ጎሹ እስከ አዳነች አበቤ) እንደሆኑ፣ የመጀመሪያው ሆቴል የሆነው ጣይቱ መገኛ መሆኗ፣ ዛሬ ፖሊስ የምንለው ሥራውን የጀመረው ፒያሣ አካባቢ የአራዳ ዘበኛ በመባል እንደነበር... አወቀ። ይወዳት የለ ደስታው ወደር አጣ። የሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት፣ የአምፒር ሲኒማ ቤት፣ ፈር ቀዳጅ የሙዚቃና የሥነ-ጥበብ መነሾ መሆኗን ሲያወሳለት አጀብ አጀብ እያለ ተነሳ። ደስታ ጋለበው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጥር ግቢ ውስጥ ስብከት ይሰማል። ከዕውቀት እና ከብልሃት የሚናገር፣ የሚያምር ለስላሳ ድምጽ፣ የአጋገር ለዛ ያለው _ እዮብ ይመኑን የሆነ። አላፊ አግዳሚው፣ የሰላም ስብከት፣ የሕይወት ስብከት የጠማው ሁሉ ጆሮውን ወደ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ሲያዘነብል ይታያል። አጀኒም አማኝ ነውና ቀረበ።
ባሕሩ፣ ተራራው፣ ዛፎች፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋከብቶቹ፣ እንስሳት፣ ዕፀዋት፣ አዕዋፋት፣ ዐሣዎች፣ አዝዕርቶች፣ ዓለማትም ሰዎችም እንዲኖሩ ታሪኩ የሚረዝመው ወይቤ እግዚአብሔር ለይኩን ብርሃን ወኮነ ብርሃን| ዘፍ 1:3| በሚለው... በ”ይሁን”ታ ነውና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጥር አጠገብ ቆሞ ስብከቱን ይሁን ይል ጀመር።
የሰባኪው ድምጽ ከፍ አለ።
«አዲስ ቀን ሲጨመርልን፣አዲስ ፀሐይ ስትወጣ አምላክ የታረቀን ነው የሚመስለን አይደል? ይልቅስ እሳት የለበለበው ዛፍ መስለን፣ የመርገምት ካባ ደርበን ሲያየን ለንስሃ ጊዜ መስጠቱ ነው። አምላክ፣ የአንተን ኃያልነት የእኔን ደካማነት ግለጥልኝ የሚል ጩኸት ከእኛ ይጠብቃል። ሲራክ፣ የሕይወትህን ፍጻሜ አስብ ኃጢያት አትሰራም  ያለውን ማስታወስ ያሻል። ሺ ዓመት ንገሥ ግን ትሞታለህ የሚል ደፋር ተናጋሪ ይሻል አምላክ! እውነት ነው፣ የበተነውን ያህል መሰብሰብ፣ የዘራነውን ያህል ማጨድ ተስኖናል። አፌ ኮቸችላ እስኪመስል ፆሜ፣ ጉልበቴ እስኪንቀጠቀጥ ሰግጄ፣ እስኪደክመኝ አንኳኩቼ በሩ  የማይከፈተው ለምን ነው? ትል ይሆናል ምናልባት ምናልባት ራስህን ጠርጥረው።»
[አጀኒ ፈዘዘ። እራስን መጠርጠር እንዴት ያለ ነው? እኔ የፒያሣ የአራዳይቱ ልጅ ተንኮል አለብኝ እንዴ?_ከራሱ ጋር እሰጣገባ ያዘ። የሲጋራ አምሮቱ ሲያፋፍመው ጎንበስ ብሎ ለኮሰ። ሁለት ሦሥት ጊዜ ደጋግሞ ቁራጯን በእግሩ እረገጣት። ከቤተክርስቲያኗ በስተጀርባ መቆሙን ረስቷል።]
ወደ ጀሮው ተግሳጽና ምዕዳን ደረሰ።
«ሰው የመከራው ቀን ሲረዝምበት፣ሰው ለጥያቄው መልስ ባጣ ጊዜ፣ አምላክ እረስቶኛል/ትቶኛል፣ ባይወደኝ   ነው እንጅ፣ ኧረ የለም ከማለት ይደርሳል። እግዚአብሔር  አላይ አለኝ ይላል። ምናልባት ምናልባት እርሱ አላይ ብሎ ሳይሆን እኛ ላለመታየት በቅተን እንዳይሆን ራሳችንን እንጠርጥረው። እንጂማ...ዓይኖቹ፤ አይደክሙ ኃያላን፣ አያንቀላፉ ትጉኃን፣ አይጨልምባቸው ብሩኀን፣ አይሞቱ ሕያውያን፣ አያዳሉ ጻድቃን ናቸው። ምናልባት ምናልባት ተደብቀን እንዳይሆን። እጠራሃለሁ አታደምጠኝም ብንለው መቼ ጠራኸኝ ነው እሚለን። የእሱ መጥሪያ አንደበት ንጽሕና እና ምግባር ቢሆንኮ ነው። ትጣራለህ እሰማህማለሁ ይላል እኮ። ታዲያ አጠራራችን ነው ችግሩ።»
የአጀኒ ፊት እንደ እስስት ሲለዋወጥ ይታያል። ውስጡ የተነካ ይመስላል። በደንብ ጆሮውን ሰጠ። ስብከቱ ቀጠለ...
«አምላክን ማግኘት ፈቃዱን ማግኘት ማለት ነው። ፈቃዱን ማግኘት ደግሞ ከማይፈቅደው መራቅ ነው። በሚገኝበት ጊዜ እንፈልገው፤ የዛኔ ፈለግንህ ግን አላገኘንህም ለማለት አያስደፍርም። ወይንን በመርዝ ዕቃ፣ መርዝን በማር መለወስ የሚፈቅደውን በማይፈቅደው እያቀረብን እንዳይሆን እንጠንቀቅ። ምጽዋቱ ከንፍገትና ከስስት ጋር፣ ሽብሸባው ከጭፈራ ጋር ሌላውም ከሌላው ጋር እያቀረብን እናስቀድሳለን ግን አንቀደስም። ይህ ነው የሚወደውን በማይወደው ማቅረብ። ከእኛ ሩቅ ነህ እንዳንለው ሰው እስከመሆን ቀርቦናል። እንዴት ነው የምትወደን እንዳንለው እስከሞት ወዶ አሳይቶናል። ይሄን ያደረገ ለጥቂት ጥያቄዎቻችን መልስ አጥቶ ይመስላችኋል? ምናልባት ምናልባት ራሳችንን እንጠርጥረው...»
አጀኒ ስብከት አይወድም። ዛሬ ግን ቁስሉን የሚያክለት ሰው አግኝቷል። ሙጀሌ ለሆኑበት ጥያቄዎቹ መንቀሻ መርፌ በመምህር እዮብ በኩል የተሰጠው መሰለው። ታዲያ የእኔ ትልቁ ችግር ምንድን ነው? ብሎ ጠይቆ ማድመጡን ያዘ።
ሰባኪው ቀርቦ የሰማ ያህል መለሰ።
«የሚታየው ለጊዜው ነው፤ የማይታየው የዘላለም ነው። ... ዓይኖችህን ከሚታየው አንስተህ ወደ ማይታየው ወርውረው። በእዮብ እና በሚስቱ መካከል የነበረው ልዩነት ዕይታ ነበር። እሷ የልጆቿን ማጣት፣ የባሏን ቁስል ታያለች፤ እሱ ግን የአምላኩን ሰጪ ነሺ ስልጣን ያከብራል። ዮናስ በዓሣነባሪ ሆድ ውስጥ ሆኖ መንጋጋ አልያም ጨጓራ አይደለም ያየው። ይልቅ ወደ መቅደስህ እመለከታለሁ አለ እንጅ። እናንተም የማይታየውን እዩ። የእጁን ሥራ የማዳኑን ተግባር እያያችሁ ጠብቁት። ለምን ቀጣኝ አትበሉ? ይኼንንማ የሥጋ አባቶቻችንም መልካም መስሎ እስከታያቸው ድረስ ያደርጉታል። እሱም አባት ነውና እስክንታረም ያደርገዋል። መከራ በዛብኝ አትበሉ። ከመከራ በላይ አስተማሪ፣ ከመከራ በላይ መካሪ፣ ከመከሪ በላይ ዘካሪ የለም። አስታውሱ COVID-19 ን። ስንቱ ነው መስጠትን ያስተማረው? ስንቱ ነው እዝነትን ያስለመደው...»
አጀኒ አልቻለም። ተቁነጠነጠ። እራሱን መውቀስ ጀመረ። በኪሱ ያሉት የሲጋራ ፓኮዎች አጭሰን እያሉ ወረፋ ይዘዋል። በፌስታል የተጠቀለለው ጫት በጥርስ መፈጨት ናፍቆታል። ጋዜጦችም አንብበን አንብበን እያሉት ነው። የፒያሣው አማኙ እብድ _አጀኒ ግራ ገባው። እግሩ እንዳደረሰው መጓዙን ቀጠለ።
ሽበት የተዋረረው ሰው ከፊቱ ነበር። አካሉን ምርኩዝ ላይ ጥሎ ያዘግማል። ወደ እርጅና እንግድነት የገባ ይመስላል። አጀኒ ይኼን የውብ ሪዝ ባለጸጋ ቀረበው። ከያዘው ፌስታል የተወሰኑ የጫት ዘንጎች አውጥቶ ለሽማግሌው ለገሰ። ተቀበለ። እኩል ምንዠክ ጀመሩ...
ትንሽ ተጉዘው ከአንዲት ጥላ ሥር እርፍ አሉ። በዓይን የተግባቡ ይመስላሉ። አጀኒ ስለ ፈጣሪው የሚያወራውን፣ የሚያጽናናውን ይወዳል።
ተረት ጀመረለት።
«ሰውየው ሁለት ሸክሎች ነበሩት። አንዱ ሰባራ ነው። ውኃ ቀድቶ ወደ ቤት ሲወስደው እያፈሰሰ ነበር። ይኼ ባለ ሥንጥቅ ሸክላ ተሰማውና “ጌታዬ እባክህ ጣለኝ ፤አልረባህም። ሰንጣቃ ስለሆንኩ ውኃ ላደርስልህ አልቻልኩም” ይለዋል። ባለቤቱ ግን “አይ አልጥልህም። ለእኔ ውኃ ባታደርስም ያፈሰስከው የሜዳ ሳሮችን አጠጥቶ አሳድጓል” አለው ይባላል። ይኸውልህ እግዚአብሔርም ከነ ሥንጥቃችን፣ ከነክፍተታችን ነው የሚወደን ይኼንንም ከእዮብ ነው የሰማሁት»
አጀኒ አእምሮ ነቃ አለ። እውነት ነው! አዳምንምኮ የፈለገው በድምፅ ነበር። ዳሩ አዳም እራሱን አውቆ ስለነበር “እርቃኔን ነኝ" አለ እንጂ..
ሽማግሌው ቀጠለ።
«የሚታገሰን፣ የሚፈትነን እራሳችንን እንድናውቅኮ ነው። እርሱ እንደ ዓለም ምርጫ አያበዛም ሞትን ወይም ሕይወትን ሰጥቶናል። ጥያቄዎቹን ሁሉ ከእነ መልሱ ሰጥቶን ሳለ እኛ ተፈታኞች ከበደን። ዓለምን የሚወድ ሁሉ ከእርሱ ጋር ጥል እንደሆነ ተጽፏል። ከኃጢያት ጋር ያልተቆራረጠ መንግስቱን እንደማይወርስ ተጽፏል። ወድቆ መነሳት ያልቻለ ጠላቱ እንጅ ልጆቹ ወድቀን መነሳት እንደምንችል ተጽፏል። ንስኀን መሰላል አድርጎም ሰጥቶናል። አሁን ግን ከእኛ እኩል እየተራበ ነው። ልጆቹን ተኩላ ነጥቆ ጨርሶበት፤ የሚፈቅደውን በማይፈቅደው ለውሰውበት።»
ብዙ እየተባባሉ ቀናቸውን በስብከት ገፉት። አብረው አያድሩና ተለያዩ_ስለ እራስን ማወቅ ተረድተው። አጀኒ ደራርቦ የለበሰውን መስቀል መዳበስ አበዛ። ጀማሪ አማኝ ከጳጳስ ይበልጣል ይሉትን ሆነ። ለመጀመሪያ ጊዜ ልቡን የነካው ሰባኪ፣ ወደ ሌላ ሃይማኖት ጣቱን የማይቀስር ሰባኪ፣ ጩኸትን ሳይሆን ዕውቀትና ብልሃትን የተላበሰ ሰባኪ መስማቱ ቅዠት እየመሰለው ነው። ብቻውን ያወራል። ድንጋይ በእግሩ ይጠልዛል፣ በሲጋራው የጭስ ቀለበት ፒያሣን ያያል መሸለት።
አጀኒ የታወቀ አማኝ እብድ ነው። ሲመልሰው ስብከት ሲያደምጥ የዋለው እራሱን ይመስላል። እብደቱ ሲነሳ በየሽንቁርቁሪያው እየገባ አንጋረ ፈላስፋን መጽሐፍ ውለዱ ይላል፤ ሲጋራ ገዝቶ ሳይከፍል ይሮጣል፤ ጫት ቤት ገብቶ ውይቱን ገረባውን ይለቃቅማል። ጓደኞቹ እብዶች በተቃራኒው ፓለቲካን ይተነትኗታል።
«ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ፓርቲ ኃላፊን አምጥቶ ሌላ ሥልጣን የሚሰጠው ለምን ነው?» ሲል ያነሳል አንዱ።
«ላዩ ስብጥርን ለማሳየት፤ ውስጡ በአንድ ሙያ ላይ expert የሆነ ሰው ሐሳቡ ስለማይቻል ሌላ ሙያ ሰጥቶ ለመገላገል» ሲል ይመልሳል ሌላው።
ይሳሳቃሉ። መላምቶቻቸው ሁሉ ጠርዝ እና ደርዝ አላቸው። የትም ተወለድ ፒያሣ ዕደግ፤ አብደህም ሆነ በጤናህ ይላሉ። የፒያሣ እብድ ከቦሌ ጤነኛ መብለጡን ያምናሉ። ለምን ቢባሉ? አማኝ፣ አንባቢ፣ አዋቂ፣ ሐሳብ ያላቸው መሆናቸውን ይገልጣሉ። አማኙ፣ ተጠራጣሪው፣ ኢ-አማኒው ኹሉም ይግባባሉ_በሐሳብ። ተማር ልጄ የምትለዋን “ነግድ ልጄ”  እያሉ ሲሳሳቁ ይውላሉ።
በየቅያሱ ሲጋራ፣ ጫት እና መጽሐፍ የያዘ አይታጣም። ቀርቦ ለጠየቃቸው የዕውቀት ሌማታቸው ያቀርባሉ፤ ያስቆርሳሉም። የእገሌን ሥራ ማን ተረከው? እንትን የሚባለው ቴአትር መቼ ታዬ? እንትን የሚባለውን መጽሐፍ ማን ተረጎመው? የአገሪቱ አካሄድ እንዴት ነው?...የሚላቸው ቢገኝ ኢትዮጵያማ ጠመድ... ጠመድ ነው አረማማዷ ብለው ጀምረው በማንትራቸው ፒያሣ ይቋጩታል።
የፒያሣ እብድ ቀልድ ያውቃል። ማመን ያውቃል። ሐሳብ ያውቃል። የጥበብ መጀመሪያዋ ነችና አራዳ። ቅናትን የሚጠሉት ብዙ ናቸው።” ንፅፅር ደስታ እንደሚሰርቅ” የገባቸው ናቸው።
ምሽቱን ተሰባሰቡ። ከዋክብት ጨረቃን እንደሚከቡ አማኙ እብድ አጀኒን ሌሎቹ እብዶች ከበው ተቀመጡ። አንድ አላፊ መንገደኛ ዞር ብሎ አጀኒን አለው...
«ምን ትመኛለህ? ወዳጄ»
«ልኬን አውቃለኹ የሚሆነኝን
ተመኝ ካሉኝ...
ልበልጥ የምሻ ፥የነበረኝን።»
እንዲህ ናቸው። ፉክክራቸው ከራሳቸው ጋር። ተወዳድረው መቅደም የሚፈልጉት ራሳቸውን ነው። ሎሬቱ አይ ፒያሣ! የሚል ግጥም ሳይጽፍ መቅረቱ ያስተዛዝባል።
ሽማግሌው ስቆ ቀረበ። ባልዕነቱ፣ ፈታሔነቱ፣ ኃያልነቱ፣ መንጽሒነቱ ያልተምታታብህ አጀኒ።
«ለዚች ዓለም ምንድን ነህ?»
«ግማሽ ፈረስ፡ ግማሽ ፈረሰኛ ነኝ።»
ምሽቱ ለዓይን ያዘ። ክብ እንደሰሩ የት እንደሚያድሩ  ያዜሙ ያዙ።
«ዶሮ በቆጥ ያድራል፥ ከብትም በበረቱ
የሰው ልጅ ፍቅር ነው፥ ዞሮ መግቢያ ቤቱ» ይሉ ጀመር የፍቅር ሰፈር ልጆች እብድ መሳይ ሊቆች ራስ አወቆች።Read 1839 times