Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 October 2012 09:44

ያሰብከው ብቻ ሳይሆን፤ ያላሰብከውም አጋዥህ ነው!!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንዳንድ የህይወት ታሪክ፤ እንደሁልጊዜው፤ ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡
አንድ ወንደላጤ ሌሊት ሌሊት አይጥ ታስቸግረዋለች፡፡ ምን እንደሚያደርጋት ግራ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ዘዴ ሲያወጣ ሲያወርድ ይቆያል፡፡ በመጨረሻ አንድ መላ ያገኛል፡፡ ዱሮ ወፍ ሲያጠምድ እንደሚያረገው፤ አንድ እንጨት ላይ ገመድ ያስርና እንጨቱን መሬት ላይ አቁሞ የብረት ድስት ክዳን አስደግፎ ያመቻቸዋል፡፡ የብረት ድስት ክዳኑ መካከሉ ላይ ክብ ቀዳዳ አለው፡፡ ከሥር መሬቱ ላይ የሚበላ ነገር አስቀምጧል፡፡ አይጢቱ ምግቡን አይታ ብረት ድስቱ ክዳን ስር ስትገባ ገመዱን በመጐተት ክዳኑ ላይዋ ላይ እንዲከደንባት ማድረግ ነው! ዘዴው ይሄ ነው!

እንደጠበቀው ማታ ላይ አይጢቱ ወጥመዱ ውስጥ ገባች! ወጣቱ እንዴት እንደሚገድላት ማሰብ ጀመረ፤ 
“ዝም ብዬ ቀጨም አድርጌ ልፈጥፍጣት!” አለ በመጀመሪያ ሀሳቡ፡፡
ቀጥሎ፤
“የለም፤ ውሃ ላፍላና በላይኛው የክዳኑ ቀዳዳ የፈላ ውሃ ብለቅባት፤ እዛው ንፍር ትላለች!”
አለ፡፡ በዚሁ መሠረት የፈላ ውሃ ለቀቀባትና እሱ መደመዝናኛው ሄደ፡፡
አመሻሽቶ ሲመለስ፤ በነፈረ-ውሃ መላ አከላቷ የነፈረና ገላዋ የላቆሰ አይጥ ፈልጐ፤ ክዳኑን ሲከፍተው፤ አይጢት
ሆዬ ክዳኑ ክፈፍ ላይ ጥጓን ይዛ ውሃ እስኪበርድላትና ክዳኑ እስኪከፈት ትጠብቅ ኖሮ፤ ፈትለክ ብላ ወጥታ
አመለጠች፡፡
ወጣቱ ተናደደ፡፡
“እንዲህ አደረግሽ! ቆይ ጠብቂ!” ብሎ ዝቶ ይተኛል፡፡
በሌላ ቀን፤ ወጣቱ አዘናግቶ ሌላ ዘዴ አስቦ ጠበቃት! ወጥመዱን አጠመደና ሲያበቃ፤
“ከገባች የማደርገውን አውቃለሁ ቆይ!” አለ፡፡
እሜት አይጥ ሰዓቷን ጠብቃ ጡብ ጡብ እያለች ወጥመዱ ውስጥ ገባች፡፡
“አሁን አለቀላት፡፡ ፍም በቀዳዳው ከትቼ አነዳታለሁ!” አለ፡፡
እንዳለው አደረገ፡፡
ከመዝናናት ሲመለስ ያረረች አይጥ ማየት ራሱ ቀፈፈው፡፡ ነገ ጠዋት አንደኛዬን ጠራርጌ እጥላታለሁ ብሎ ወሰነና
ተኛ፡፡
ጠዋት ተነስቶ ክዳኑን ሲከፍት ምንም ነገር የለም፡፡ ለካ ክዳኑ የተቀመጠበት ወለል በአንድ በኩል ተዳፋት ኖሮት፤
ቀዳዳ አግኝታ አይጥ ፈትለክ ብላለች፡፡
ወጣቱ ተናደደ፡፡ ፀጉሩን ነጨ፡፡ በቃ፤ ዘዴ የለም ብሎ ተኛ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ድንገት ጠዋት ሲነሳ አንድ የማይካ ሳህን፣ ውሃ የሚያስቀምጥበት ውስጥ፤ አልፎ አልፎ ሥጋ
ይጥልበት የነበረ አለ፡፡
አይጢት ሥጋ አገኘሁ ብላ እዚያ ውሃ ውስጥ ገብታ ስትንፈራፈር አገኛት፡፡ ተፍረምርማ፣ አጣጥራ አጣጥራ
ሞተች፡፡
ከነቆሻሻው ውሃ ደፋት! በዘዴ እሠራለሁ ያለውን ጥበብ፤ ሁኔታው ራሱ አሳካለት!!
***
የምናስበው ወጥመድ ሁሉ ላይሠራ ይችላል፡፡ ከሠራስ? ብሎ ማሰብ ግዴታ ነው፡፡ ያጠመድነው ሁሉ ተሸነፈ ብለን መቀመጥ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ በኋላስ? ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ አማራጭ ዘዴን ማሰብ ከሌለ ሁልጊዜ የነገሮች ሁሉ ጥግ ቅርብና ከአፍንጫ አጠገብ መስሎ ይታየናል፡፡ ለአማራጭ አስተሳሰብ ዛሬም ክፍት መሆን አለብን! በግትርነትና በርን በመዝጋት፣ የእስከዛሬው መንገዳችን ብቸኛውና አንድዬ ነው ማለት ለዲሞክራሲ ቀናው ሁዳድ አይደለም፡፡ ምንም ቢሆን ምን ሌሎች የሚያስቡትን ማወቅ፤ ለተሳትፎ እንዲጋበዙና ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ አካባቢ (Democratic Space) ይፈጥራል፡፡
ድህነትን ለማጥመድ ብሎም ቀርፎ ለመጣል ማሰብ አንድ ነገር ነው፡፡ ከዚያ በላይ ማሰብ ግን አልተከለከለም፡፡ ለምሳሌ ራዕያችን ዐባይን መገደብ ነው ካልን፤ ዐባይን አጠመድነው ማለት ነው፤ እንበል! ከዛስ? ከዐባይ መገደብ በኋላ ራዕያችን ምንድን ነው? ራዕይ ውቂያኖስ ነው፡፡ ራዕይ ዩኒቨርስ ነው! እስከጽንፉ ማሰብን ይጠይቃል! ለዚህ ደግሞ የሃሳብ እርዳ ተረዳን፣ የአገር ግንባታ እሳቤ መተጋገዝን ይጠይቃል፡፡ አገር የጋራ ናት ማለትን የግድ ይለናል!!
የሚያዳሉለት ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት ሲኖር ዲሞክራሲን ማራመድ ከባድ ይሆናል! ወይም ከናካቴው አይቻልም! “ባሏ የሚወዳትን ሚስት ጀበና ይከብዳታል፡፡ ለጋ ዱባ ያንቃታል!” ይባላልና፤ ከልጆች ሁሉ የተመረጥኩ ነኝ በሚል ስሜት፤ ወይም የበለጠ “የባለቤቱ ልጅ ነኝ” በሚል ተዓብዮ፤ ጥፋት ማጥፋትና መረን መሆን ይከተላል፡፡ ይሄ ደግ አደለም፡፡
ለኢትዮጵያ ህዝብ የምንናገረው ለኢትዮጵያ ህዝብ ይሁን! ለራሳችን ወገን የምንናገረውና ከዚያ ውጪ የምንናገረው ቋንቋ ቅኝቱ ለየቅል ነው፡፡
ለድርጅት አባላችን የምናስተላልፈው መልዕክትና ለሀገራችን ዜጋ የምናስተላለፍው ሃሳብ በቅጡ መለየት ይኖርበታል፡፡ “ሁለት ወፍ በአንድ ድንጋይ” እዚህ ላይ የሚያዋጣ አይሆንም!
በዝቅተኛ መደብ፣ በመካከለኛ መደብም ሆነ በከፍተኛ መደብ ያሉ የህብረሰብ ክፍሎች የሚጋሩት ፖለቲካ፤ የሚመረሩበት ኢኮኖሚ፣ የሚሰቀቁበት ማህበራዊ ምስቅልቅል፣ አለን የሚሉት ባህላዊ እሴት እንዳላቸው ማየት፣ ሚዛናዊ በሆነ ዐይን ማንነታቸውን ማክበር፤ እኛ ካለንበት ቦታ ያላቸውን ርቀት ማጤን፣ ለአንድ መሪ፣ አለቃ፣ ማህበር ወይም ድርጅት አሊያም ፓርቲ ቀዳሚ ኃላፊነት ነው፡፡ ምንም ቢሆን ምንም፤ “ሰው በአገሩ፣ አንበሳ በዱሩ፣ አሳ በባህሩ” እንዳለና እንደሚኖር ማሰብ ስለኃላፊነትና ስለተጠያቂነት የምናስበውን ሁሉ ምሉዕ ያደርግልናል፡፡
አገር አገር ናትና አገሬው ጉዳይ አለው፡፡ ብናምነውም ባናምነውም፣ ብንገምትም ባንገምትም፤ አገሬው ያገባኛል ማለቱን አንርሣ! አገሬ ብሎ ለአገሩ እሚያስብ አለ! “ያሰብከው ብቻ ሳይሆን፣ ያላሰብከውም አጋዥህ ነው!” የሚባለው ለዚህ ነው!!

Read 4730 times