Saturday, 26 November 2022 00:00

የእኛ ሰው በኳታር በኳታር የዓለም ዋንጫ በፊፋ ተቀጥሮ የሚሰራው ኢትዮጵያዊ

Written by  ግሩም ሰይፉ ከዶሃ ኳታር
Rate this item
(2 votes)

  አብዱልባሲጥ ጀማል አብዱልቃድር ይባላል። በኳታር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሲሆን በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለግዙፍ የብሮድካስት ኩባንያዎች ድጋፍ ሰጭ ባለሙያ ሆኖ እየሰራ ይገኛል። አብዱልባሲጥ በኳታር የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዓለምአቀፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህም ነው። በኳታር የሚገኘው ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ከአብዱል ባሊጥ ጋር  በዓለም ዋንጫ ስራው፤ በኳታር ስለሚኖሩና ስለሚሰሩ ኢትዮጵያውያን፤ ስለ በጎፈቃድ አገልግሎትና... ሌሎችም ጉዳዮች ቆይታ  አድርገዋል። አብዱልባሲጥ ከመላው ቤተሰቡ ጋር በኳታር ዶሐ የሚኖር ሲሆን የአራት ልጆች አባት ነው፡፡ በትምህርት እቅድና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን የያዘው አብዱልባሲጥ ለ3 ዓመታት በመምህርነት ከሰራ  በኋላ  ርዕሰ መምህር ሆኖ ማገልገል ጀምሯል። አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ፒኤችዲውን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።       22ኛው የዓለም ዋንጫ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡  በኳታር መስተንግዶ ምን ታዘብክ?
የዓለም ዋንጫው በመስተንግዶ ደረጃው ከመክፈቻው ሥነስርዓት ጀምሮ  የተዋጣለት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ በፊፋ ተቀጣሪ ሆኖ እንደሚሰራ ባለሙያ  ብቻ ሳይሆን በኳታር እንደሚኖር ሰው ከፍኛ አድናቆት ፈጥሮብኛል፡፡ ኳታር ላይ ለሁሉም ስራዎች  ሙሉ ጥናት ይደረጋል፡፡ ይህም ብዙ ስኬት እያስገኘ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ አሁን መክፈቻውን ብትመለከት ብዙ የተንዛዛ ነገር አልነበረበትም። በግማሽ ሰዓት ውስጥ  በመድረክ ላይ በቀረቡት ትርኢቶች ጥልቅ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡
የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት በተለይ በምዕራባውያን ሚዲያዎች ብዙ ማጣጣሎችና ትችቶች ነበሩ፡፡ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በመልዕክታቸው እንዳንፀባረቁት፤ “ይህን የመሰሉ አሉታዊ ተግባራትን ማቆም ያስፈልጋል።  የዓለም ህዝብ ተባብሮ ምንም ሳይለያይ የጋራ በሆነችው ዓለም በሰላም መኖር ይችላል፤ ለሁሉም ይበቃል፡፡ የሰው ዘር ይለያያል፡፡ ፈጣሪም አለያይቶ ነው የፈጠረው፤  ነገር ግን የሰው ልጅ በፈጣሪ አይን የሚመረጠው ለፈጣሪው በመገዛት ነው የሚለው መልዕክት ተላልፏል፡፡ ሰው በምንም አይበላለጥም፡፡ ጥቁር፤ ነጭ ስለሆንክ፣ አካል ጉደተኛ ስለሆንክ ስላልሆንክ፣ የተለያየ እምነት ስለምትከተል አይደለም፡፡ ጥሩና ተመራጩ ሰው ፈጣሪውን የፈራ ሰው ነው፡፡
የዓለም ዋንጫው በዓረቡ አለም ሲዘጋጅ የመጀመርያው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለመስተንግዶው በኳታር በተደረገው ዝግጅት ጎረቤት አገራትን ጨምሮ ከአየአቅጣጫው በጣም ብዙ ጫና ተደርጓል፡፡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተካሄደውን ጦርነት በመቋቋም  ይህን የመሰለ የዓለም ዋንጫ መዘጋጀቱ በአለም ላይ ኳታር ያላትን ጥንካሬ አሳይቷል፡፡ ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ ያንን ሰብረህ ዓለም ላይ ጠንክረህ መውጣት ትችላለህ፡፡
በዓለም ዋንጫው የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ባልደረባ ሆነው በመስራት ላይ ነህ፡፡ ወደዚህ ስራ እንዴት ገባህ?...  ሃላፊነትህስ ምንድነው?
ባለፈው አመት በተካሄደው የአረብ ካፕ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ስራ ተሳትፌ ነበር፡፡ በአልቱማማ ስታዲየም በተካሄደው ውድድር ከመክፈቻው እስከ መዝጊያው በጎ ፈቃደኛ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ከዛ በነበረኝ ልምድ በመነሳት ነው፣ ከፊፋ ጋር በኮንትራት ተስማምቼ ወደ ዚህ ስራ የገባሁት፡፡ እግር ኳስ በሜዳ ላይ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር ብዙ ስራዎችን የሚያንቀሳቅስ ነው፡፡ ለበጎ ፍቃደኝነት ብቻ 15 ተከታታይ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡ በስፖርቱ ይህን ሃላፊነት በመወጣት ከማገኘው ልምድ ባሻገር ለህይወቴም የጠቀመኝ ነው፡፡
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የምሰራበት ማዕከል ዓለም አቀፍ የብሮድካስት ማዕከል ይባላል፡፡ የዓለም አቀፍ ብሮድካስት ሚዲያዎች ዋና መናኸርያ፤ ማዘዣ ጣቢያው ነው፡፡ ከዓለም ዋንጫው ጋር ተያይዞ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችና ልዩ ልዩ ስርጭቶች፤ በየስታዲየሞች፤ በደጋፊ አደባባዮች ፋን ዞኖች፤ በተለያዩ ከተማዎች በአጠቃላይ  ዓለም ዋንጫን በተመለከተ የሚካሄዱ ሁሉም ቀረፃዎች  በማዕከሉ የሚያልፉ ናቸው፡፡ በዚህ ማዕከል የእኔ ስራ ድርሻ በፕሮዳክሽን ዲፓርትመንት ሲሆን ትልቁ ሃላፊነቴ የሎጀስቲክ ስራዎችን በቅልጥፍና ማካሄድ ነው። በየስታዲየሞቹ የተለያዩ ቀረፃዎችን የሚያደርጉ ጋዜጠኞች ሲሄዱ የሚፈልጓቸው የብሮድካስት መሳርያዎች  በቀላሉ እንዲደርስላቸው በማድረግ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ በፕሮዳሽን ዲፓርትመንቱ ውስጥ 12 ሾፌሮች አሉ፡፡ እነሱን ማስተባበርና ማሰማራት ነው ዋናው ተግባር፡፡ ከብሮድካስት ባለሙያዎቹ ማናቸውም ጥያቄዎች በኢሜል አድራሻ ይቀርባል፡፡ በተለይ በየስታዲየሙ የተመደቡ የቬኑ ስራ አስኪያጆች venue managers አማካኝነት ለእኛ ዲፓርትመንት በኢሜል መልዕክት ይላካል። በሚሞላው ፎርም በዚህ ቦታ ላይ ይሄ “ይሄ እቃ ይፈለጋል” የሚለው ነገር ተዘጋጅቶ ይላካል። በፕሮዳክሽን ዲፓርትመንት ያሉት ሃላፊዎች የቀረቡትን መጠይቆችና ትእዛዞች ተቀብለው ወደ እኛ ያስተላልፋሉ፡፡ ያንን የሚያስተላልፉትን በመንተራስ ከማዕከሉ የብሮድካስት መጋዘን በማውጣት በሚፈልጉበት ቦታና ሰዓት በቀላሉ ማድረስ ነው። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ተግባር በቅልጥፍና ለማከናወን የዘረጋው አሰራር አለው፡፡ ከበርካታ ዓለም አቀፍ የብሮድካስት ኩባንያዎች ጋር  ነው  የምንሰራው እኔ በተለይ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ባለሙያዎች ጋር በተደጋጋሚ እየሰራሁ ነው፡፡ ሁሉም የዓለም ሚዲያዎች አሉ። ከቲቪ ከሬዲዮና ዩቲዩብ ባለሙያዎች ጋር በመስራት ከፍተኛ ልምድ አለው። ፊፋ በዓለም ዋንጫው ይህን አገልግሎት ለመስጠት የሚሰራው “ሆም ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ” (HBC) ከሚባል ኩባንያ ጋር ነው፡፡ በዚሁ ብሮድካስት ኩባንያ ላይ እንግዲህ ዋናው ሃላፊነቴ ስራዎችን መቆጣጠርና ማፋጠን ነው፡፡
በኳታር  የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ነህ ፡፡ ስለ ትምህርት ቤቱ ብታወጋን?  
ትምህርት ቤቱ ስራውን ከጀመረ ሁለት አመት ሆኖታል፡፡ በ15ሺ ካሬ ሜትር ላይ የሰፈረ ሲሆን ትምህርት ቤቱን በስጦታ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ የለገሱት የኳታር አሚር ናቸው፡፡ ለዚህ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለስራና ለጉብኝት ኳታር በመጡበት ወቅት ለማህበረሰቡ ትምህርት ቤት እንዲሰጥ ለአሚሩ በይፋ መጠየቃቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የኳታር አሚር  ከ6 ሚሊዮን ሪያል በላይ ወጭ በማድረግ ከማሳደሳቸውም በላይ ሁሉንም በማሟላት ለማህበረሰቡ አበርክተውታል፡፡ በትምህርት ቤቱ ከ120 በላይ ተማሪዎች ይገኛሉ፤ ከኢትዮጵያና ከሌሎች 14 አገራት የተውጣጡ ናቸው፡፡ የኳታር፤ የሱዳን፤ የኤርትራ፤ የሶርያ፤ የፍልስጤም፤ የኢራን፤ የየመን ዜግነት ያላቸው ይገኙበታል፡፡
ትምህርት ቤቱን ለየት የሚያደርገው ለኢትዮጵያውያኑ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል በምንሰጠው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት አስደናቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡  ከኬጂ ጀምሮ በእንግሊዝኛ እናስተምራለን፡፡ አማርኛ ቋንቋን እንደ አንድ ትምህርት አይነት ነው የምንሰጠው፡፡ ተማሪዎቻችን በየእለቱ ብሄራዊ መዝሙር ይዘምራሉ፤ ባህላቸውን ታሪካቸውን ይማራሉ፤ ማንታቸውን ያጎለብታሉ፡፡ ይህ ትምህርት ቤት በመከፈቱ ማህበረሰቡ ወደ አገር ቤት ልጆቹን እየላከ የሚያስተምረው ነገር እየቀረ መጥቷል፡፡ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው እየኖሩ እንዲማሩ አድርጓል፡፡ በትምህርት ቤቱ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ የማስተማር ፍቃድ ቢኖረንም፣ በየዓመቱ አንድ ክፍል እየጨመርን ነው የምንሄደው።  አሁን እስከ አራተኛ ክፍል ነው የምናስተምረው፡፡ በየዓመቱ አንድ ክፍል እየጨመርን እንቀጥላለን፡፡
ከመምህራኖቻችን መካከል ኢትዮጵያውያን አሉ። ከፊሊፒንስ፤ ከናይጄርያ፤ ከግብፅም መምህራንን ቀጥረናል፡፡ በነገራችን ላይ ከኢትዮጵያ ስርዓተ ትምህርት ባሻገር በኳታር ውስጥ ያለ ማንኛውም ትምህርት ቤት ግዴታ ማስተማር ያለበት ሶስት  ትምህርቶች አሉ፡፡ የአረብኛ ቋንቋ፤ የኳታር ታሪክና የእስልምና ትምህርት ናቸው። የእስልምናው ትምህርት ለሙስሊም ተማሪዎች ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ ሶስቱን የትምህርት አይነቶች በዋናነት የምናስተምረው ተማሪዎቻችን በኳታር ከመኖራቸው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እዚህ አገር የተወለዱ ልጆች ወደፊት በኳታር ውስጥ ለመኖርና ስራ ለማግኘት የኳታርን ታሪክና አረብኛን በደንብ ማወቅ አለባቸው፡፡ የአገሩን ባህልና እሴቶች ለሌሎች የሚያስተዋውቁበት እውቀት ነው፡፡
ከኳታር በፊት በሳውዲ አረቢያዋ ከተማ ሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት ለ10 ዓመታት በርዕሰ መምህርነት አገልግያለሁ። ከሳውዲ በፊትም ኢትዮጵያ ላይ በአዳማ ከተማ በሚገኝ  ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ነበርኩ፡፡
በኳታር ስለሚገኘው የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ምን አጫውተን?
ኳታር ውስጥ ኢትዮጵያውያን  በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡ በሙያዊና በጉልበት ስራዎች  ላይ ይገኛሉ። በምህንድስናው፤ በኢንፎርርሜሽን ቴክኖሎጂው፤ በህክምናው፤ በትምህርቱ ይሰራሉ፤ ብዙ ኢንጂነሮች ብዙ ዶክተሮች፤ በፖሊስነት፤ በመንግስት መስርያ ቤት፤ በግለሰብ ድርጅቶችም ተቀጥረው ይሰራሉ፡፡ በሱፐር ማርኬቶችና በየንግድ ሱቆች ውስጥ በሽያጭ ሰራተኝነት የሚያገለግሉም ይገኙበታል፡፡ በኳታር ውስጥ ሁሉም እንደየችሎታው እንደየሙያው በሁሉም የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ ነው የሚኖረው፡፡ ምንም አይነት የስራ እድል ቢወጣ ቅጥር የሚከናወነው ችሎታን አማክሎ፡፡ ተወዳድሮ ችሎታውን ያሳየ ሁሉ የትም ቦታ መግባት ይችላል፡፡
የተሳካላቸውና አንቱ የተባሉትን  እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሁለት ቅርንጫፍ የግል ሆስፒታል እስከመክፈት የደረሱም አሉ፡፡ በአጥንትና ተያያዠ ጉዳቶች ህክምና ላይ ስፔሻላይዝ ያደረጉ በመሆናቸው በሆስፒታላቸው በዓለም ዋንጫው የተጎዱ ተጫዋቾችን እስከ ማከም ደርሰዋል። ለዓለም ዋንጫ በተሰሩ ስታድየሞች የስነ ህንፃ ዲዛይን ላይ የተሳተፈ ኢትዮጵያዊ አለ፡፡ በንግድ ላይ ተሰማርተው የተወጣላቸው ነጋዴዎችም አሉ። በሆቴልና ሬስቶራንት የሚሰሩ፤ በባልትና እና በባህል አልባሳቶች ሽያጭ  በመስራት የተሳካላቸው ይገኙበታል፡፡ ማህበረሰቡ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚያደርገው እንቅስቃሴ በምሳሌነት ይጠቀሳል። የመሰረትነው ማህበር ለህዳሴው ግድብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ይታወቃል፡፡ የቦንድ ግዢው ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጧል፡፡ በኳታር በየስራ ቦታው የሚከበር፤ አገሩን የሚወድ ማህበረሰብ ነው፡፡
ወደፊት ኢትዮጵያ ተመልሰህ በአገርህ የመስራት ፍላጎት አለህ?
በአሁኑ ወቅት በኳታር ከስራዬ ጎን ለጎን ፒኤችዲዬን እያጠናሁ ነው፡፡ በቱርክ አገር በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ለሶስተኛ ዲግሪዬ በኦንላይን ነው ትምህርቱን የምወስደው፡፡ ከጨረስኩ በኋላ አገሬ በምትፈልገኝ ሃላፊነት ለመስራት ዝግጁ እሆናለሁ። በባህርማዶ እየኖርኩና እየሰራሁ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከሙያዬ ጋር በተያያዘ ሌሎች አገራት ላይ የቀስምኳቸው ጥሩ ጥሩ ስራዎች አሉ፡፡ እነዚህን ተመክሮዎች ወደ አገር ቤት አምጥቼ የመስራት ፍላጎት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት ትልልቅ የስፖርት መድረኮችን እንድታዘጋጅ እሻለሁ።  ከዓለም ዋንጫው የቀመስኩትን ልምድ፤ በትምህርት መስኩ ያገኘሁትን  እውቀት ወደ አገር ቤት በመመለስ አስተዋፅኦ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡

Read 7274 times