Saturday, 03 December 2022 11:40

“ኢማጂን ዋን ዴይ” ለሁለት ክልል ት/ቤቶች የ10 ሚ. ብር የ ICT ስልጠና ግብአቶችን አስረከበ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    ለ 2 ዓመት የሚቆይ የ 100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት አስተዋውቋል
                    
       “ኢማጂን ዋን ዴይ” የተሰኘ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል 60 ት/ቤቶች የሚውልና 10ሚ. ብር የወጣባቸው አይሲቲ ማሰልጠኛ እቃዎች አበረከተ፡፡ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት በተለምዶ ሃያ አራት በሚባለው አካባቢ በሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤቱ ለኦሮሚያና ለደቡብ ክልል የትምህርት ቢሮ ተወካዮች ነው ዕቃዋቹን ያስረከበው፡፡
በሁለቱ ክልሎች የአይሲቲ ስልጠና የሚሰጥባቸው 60 አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተመረጡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 38ቱ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ደግሞ 22 ት/ቤቶች መመረጣቸውን የ”ማጂንዋን ዴይ” ሀላፊዎች ተናግረዋል፡፡ የሚሰጠውን የአይሲቲ ስልጠና ውጤታማ ለማድረግ ከ60 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች  ተሰባሰቡ 60 መምህራን በተመረጡ የአይሲቲ ማዕከላት ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋልም ተብሏል፡፡ መምህራኑ ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ወደ የትምህርት ቤቶቻቸው ተመልሰው ለ3ሺህ 400 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ስልጠናውን እንደሚሰጡ ታውቋል። እንደ ሀላፊዎቹ ገለፃ ከመምህራኑ በተጨማሪ 100 ልጃገረዶች 64 ከኦሮሚያ፤ 36ቱ ደግሞ ከደቡብ ክልል ከተመረጡት 60 አንደኛ ት/ቤቶች በመምረጥ በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ወይም ኮሌጆች ውስጥ ለ10 ቀናት መሰረታዊ የአይሲቲ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የአይሲቲ ስልጠና እንዲሰጥባቸው የተመረጡት ት/ቤቶች የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ አንዲሆኑ ለዚሁ አገልግሎት የሚሆን ክፍያ ለኢትዮ ቴሌኮም ይፈፀማል የተባለ ሲሆን የዚህም ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በተለይ በገጠሩና ብዙ መሰረተ ልማት ባልተሟላበት አካባቢ የሚኖሩ ህፃናትና ታዳጊዎችን የአይሲቲ ተጠቃሚ በማድረግ የዲጂታል ትምህርትን ለማስፋፋት እንደሆነ ነው የ”ኢማጂን ዋን ዴይ” ሀላፊዎች በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት፡፡  እ.ኤ.አ በ2007 የተቋቋመው “ኢማጂን ዋን ዴይ”፤ በአሁኑ ወቅት በአማራ፤ በትግራይ፤ በኦሮሚያ፤ በደቡብና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚንቀሳቀስ ሲሆን ዋና ትኩረቱም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች  ዘላቂ የልማት ሥራዎችን መስጠት እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ካከናወናቸውና እያከናወናቸው ካሉት ተግባራት መካከልም ት/ቤቶችን ማስገንባት፤ ለቤተ መፃህፍትና ለቤተ ሙከራ የሚያስፈልጉ የትምህርት መርጃ መሳያዎችን ማደራጀት፤ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን ማስቆፈር በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ላይ ለተለዩ ህፃናት ከለላ፤ ድጋፍና አስቸኳይ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ በመደበኛ ት/ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጥረት ማድረግ የሚሉት ይገኙባቸዋል።
ዓለም አቀፉ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለሁለቱ ክልሎች የአይሲቲ ስልጠና የሚሰጥባቸውን መሳሪያዎች ባስረከበበት ዕለት በነዚሁ ሁለት ክልሎች ለሁለት ዓመት የሚቆይ የ100 ሚሊዮን ብር “my home” (ቤቴ) የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ገንዘቡም ከዩኒሴፍ የተገኘ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት 24 ሺህ ለሚሆኑ ህፃናት አፋጣኝ ትምህርት፤ ለ54 ሺህ ህፃናት ጥበቃና ከለላ፤ ሥራ እንዲሁም ለ33 ሺህ 600 ህፃናት የህይወት ክህሎት ስልጠና እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ ለ3 ሺህ 400 ህፃናት ደግሞ በዕለቱ ርክክብ የተደረገበትንና 10 ሚሊዮን ብር የወጣበት የአይሲቲ ስልጠና ፕሮጀክት እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡

Read 11602 times