Saturday, 03 December 2022 12:07

6ኛው አገር አቀፍ “አግሪ ፊስት” ሊካሄድ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የአረንጓዴ ልማትንና የተፈጥሮ ጥበቃን ባህል እንዲያደርግ ታስቦ የዛሬ ስድስት ዓመት የተጀመረው 6ኛው ዙር አገር አቀፍ አግሪ ፊስት ( አረንጓዴ ፌሽታ) ዘንድሮ በሰባት ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች ሊካሄድ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት አርቲስት ቤቴልሄም ጌታሁን (ቤቲጂን) አምባሳደር አድርጎ ሲሰራ እንደነበር የገለፁት አዘጋጆቹ ዘንድሮም በሰባት ከተሞች ተግባራዊ እንደሚሆን ባለፈው ሃሙስ ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በ ቫይብ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የግሪን ፊስት መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወጣት ታደሰ ልብሴ እንዳብራራው ዘንድሮም ከታህሳስ ወር ጀምሮ በሰባት ከተሞች የሚከበር ሲሆን የመጀመሪያው በውሃና ኢነርጂ ጥበቃ ላይ ትኩረቱን ያደረገ “ዋተር ኤንድ ኤነርጂ ኤክስፓ” በአዲስ አበባ፤ ሁለተኛውና በአዳማ ከተማ የሚካሄደው ደግሞ ከተሞችን ከብክለት የፀዱ ማድረግ ላይ የሚያተኩረው “የአረንጓዴ ቤተሰብ ሩጫ” ሲሆን 3ኛው በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚካሄደው “ እንጓዝ እናፅዳ” የተባለውና ሰዎች አእምሯቸውን ከቆሻሻ ሀሳብ ከተማቸውን ከቆሻሻ የሚያፀዱበት የእግር ጉዞ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ አራተኛውና በጅግጂጋ ከተማ የሚካሄደው “ዮዝ ኤንድ ግሪን ዴቬሌፕመንት ዲያሎግ” የተሰኘ ሲሆን ከወጣቶች ጋር በአረንጓዴ ልማት ባህል ላይ ውይይት የሚካሄድበት ነው ተብሏል፡፡
5ኛው በሀዋሳ ከተማ የሚከናወነው የአረንጓዴ ዲፕሎማት ሀይኪንግ ሲሆን 6ኛው በባህር ዳር ከተማ የሚከናወነው ደግሞ ጣና ሀይቅ በእንቦጭ ብቻ ሳይሆን በፕላስቲክም ብክለት እየደረሰበት በመሆኑ ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል አካባቢን እንዳይበከል ማድረግ የሚቻልበትን የሚያሳይ “ግሪን ፋሽን ሾው” ይካሄዳል፡፡ ሰባተኛውና ማጠቃለያው “ግሪን ኮሚዩኒቲ አዋር” በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድና በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ አስተዋፅኦ ያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና የሚያስገኙበት ነው ተብሏል፡፡ ይህ ፕሮግራም እውን እንዲሆን በአጋርነት ለመስራትና ሀሳቡን ለመደገፍ ዋልታ ቴሌቪዥንና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከግሪን ፌስት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡  

Read 21071 times