Saturday, 03 December 2022 12:08

“ክፉ ደጉን ያየን ነንና ጎረቤት ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” (“ማለባበስ ይቅር”)

Written by 
Rate this item
(7 votes)

  ከዕለታት ከአንድ ቀን ዘጠኝ ጓደኛሞች ወደ አንድ ሩቅ አገር ለመሄድ መንገድ ይጀምራሉ። ብዙ ርቀት እንደሄዱ ይመሽባቸዋል።
አንደኛው፤
“ጎበዝ፤ ከዚህ ወዲያ ከቀጠልን ጨለማው ይበረታብናል። ስለዚህ እዚህ ተኝተን እንደር” አለ።
ሁለተኛው፤
“ጥሩ ሀሳብ ነው። ግን ደህንነታችን ለመጠበቁ ምን መተማመኛ ይኖረናል?”
ሦስተኛው፤
“በተራ በተራ የሚጠብቅ ሰው እንመድብና ተረኛው ሲደክመው ቀጣዩን ጠባቂ ቀስቅሶ ይተኛ” አለ።
ሁሉም በመጨረሻው ሀሳብ ተስማማና “ስለ አተኛኘት ቅደም ተከተል እጣ እናውጣ” ተባባሉ። በወጣባቸው እጣ መሰረትም ተኙ።
ሌሊት ላይ አንድ የመቆረጫጨም ድምጽ ተሰማ።
“የምንድን ነው የሚሰማው ድምጽ” ተባባሉ።
ከዳር የተኛው ሰው መለሰ፡-
“ጎበዝ ዝም ብላችሁ ተኙ፤ አያ ጅቦ እኔን እየበላ ነው!” አለ።
አያ ጅቦ ወደሚቀጥለው ተረኛ ተሸጋገረ።
በዚህ ሁኔታ ሁሉም “ዝም በሉ” እያሉ፤ ዐይናቸው እያየ ተበልተው አለቁ ይባላል!
***
በየአሮጌው መመሪያና ህግ፣ ያለ አንዳች ማሻሻያ እየተጎዳዱ መገዛት ከጀመርን ብዙ ሰነበትን። አዲስ አውጥተናል ብንልም፤”አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን” የሚባለውን አይነት  ነው (Old wine in a new bottle እንዲል ፈረንጅ)
መንግስትና መንግስት፤ በተቀያየረ ቁጥር ህዝብ ቢወድም ቢጠላም፣ ያንን ተቀብሎ መገዛት እጅግ ከመለመዱ የተነሳ እንደተፈጥሮ ህግ መወሰዱ፣ እንደ ፀሀይ  መውጣትና መጥለቅ ከሆነም ሰንብቷል።
በመካከል “ይሄኛው መንግስትና ህግ አይሻኝም” የሚል ግለሰብ ወይም ቡድን አሊያም ፓርቲ ቢወለድ፤ ወይ ይታሰራል፣ ወይ ይወገዳል አሊያም ስርዓተ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል። ከታሪክ እስከ ዛሬ ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ ከባንዳ እስከ ዘመናዊ አድር-ባይ፣  አሸርጋጅና አቀንቃኞችን የፈሰፈልነው፣ በዚህ “ጥበብ” እና “ዘዴ” ነው። ሌላው ቢቀር በጉርሻ ወይ በንክሻ “የሚባለውን ፍልስፍና ማንም ጅል አይስተውም ( Carrot and stick እንዲሉ)። በዚህ መልኩ ሲታሰብ እያንዳንዱ መንግስት ሊፈተሽ ይገባዋል ማለት ነው።
በተለይም አሁን ከመደብ ፖለቲካ ይልቅ የብሔር ብሔረሰብና ሐይማኖት እንደ ዘመን አመጣሽ ዘፈን በሚቀነቀንበት ሰዓት፣ የፖለቲካው አካሄድ እጅግ እየተወሳሰበ መምጣቱን ከነትርፍና ኪሳራው ለማስላት ከባለኪዮስክ ትንተና (Shop-keeper’s analysis) የበለጠ ስሌት አይጠይቅም። “ማንኛውም መሪ እበልጥሃለሁ” በሚል እሳቤ ሲያምታታ፣ ቀላል የዓሳ መረብ ውስጥ ሲገባ ታገኘዋለህ ይላሉ ጸሐፍት። የእኛም አገር መሪዎች ታሪክ ይሄን የሚያጸኸይ ነው። ይሄንን ለማየት የፖለቲካ ሳይንቲስት ማማከርም፣ አዋቂ-ቤት ሄዶ መስገድም አይጠይቅም!
በኢትዮጵያ አገራችን ከተማሪና አስተማሪ ትግል ጋር መተዋወቅ ትምህርት ቤት መግባትን አይጠይቅም። እንዳሁኑ ጊዜ 13,000 ተማሪ የተንሳፈፈበት ዘመን ግን ኖሮ አያቅም። ሚኒስትሩም ያሳዝናሉ። የትምህርት ስርዓት ከተጀመረ ፊደል ከተቆጠረ ጀምሮ፣ ይህ ሁኔታ አብሮን የኖረ ነው። አንዳንድ መሪዎቻችንም “እጁን እኪሱ ከትቶ፣ ባዶ ኪስ የሚያገኝ መምህር ከእንግዲህ አይኖርም” ብለውም ነበር። ሆኖም ዛሬም ከደሞዝ ጥያቄ እስከ ሥራ ማቆም አድማ ድረስ ሲገፋ እየታዘብን ነው! የሚገርመው ይህንኑ መሰል ጥያቄ ለወቅቱ ትምህርት ሚኒስትር ቀርቦ እንደነበር መታወሱ ነው። የታሪክ አዙሪት! ጥናቱን ስጠን!
እውነቱን ለመናገር የአምባ-ገነን መሪዎች ዴማጎጂም ተለይቶን አያውቅም። እነ ሂትለርስ እንደ ጎብልስ ያሉ አማካሪዎች ነበሯቸው። የእኛስ እነማን ይሆኑ? ወጣ ወረደም ያለን አማራጭ ከዕለታት አንድ ቀን ስለ ኤች አይ ቪ እንዳስጠነቀቅነው፡-
“ክፉ ደጉን ያየን፣ ነንና ጎረቤት
ያንተ ቤት ሲንኳኳ፣ ይሰማል እኔ ቤት!”
የሚለውን ስንኝ እንደግመዋለን!
ነግ በእኔ ነው ጎበዝ!! ትምርታችንን ይግለጥልን!

Read 11810 times