Saturday, 03 December 2022 12:13

ከኦነግ ሸኔ ተማሩ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 “ሌላ የትግራይ ሸኔ ለመሸከም ሀገር አቅምና ፍላጎት የላትም”
             
        የእነ አቦይ ስብሐት ቡድን - ትሕነግ፤ አዲስ አበባ እንደገባ የተከሰተ ነገር በማስታወስ ልጀምር።
አንድ የጭነት ማመላለሻ ማኅበር፣ ከአሰብ የእርዳታ ስንዴ ጭኖ ለማምጣት ከእርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት ጋር ውል ይገባል። ማኅበሩ መኪናዎቹን ወደ አሰብ ሲልክ፤ ስንዴውን የትግራይ እርዳታ ድርጅት በአመዳም የማርቸዲስ መኪናዎች  አዲስ አበባ ጭኖ አመጣው።  የማኅበሩ ሰብሳቢ የነገሩን እውነትነት አረጋግጠው ፤መግለጫ ለመስጠት ግን እንደማይፈልጉ በመናገር አላቆሙም፤ ያሉኝ “እነዚህን ሰዎች የምንጥላቸው እኛ ነን” ነው።
የእነ አቦይ ስብሀትን ቡድን ለማንበርከክ በልዩ ልዩ መንገድ አስተዋጽኦ ለላደረጉ ሁሉ ከፍ ያለ አክብሮቴን አስቀድሜ መግለጽ እፈልጋለሁ።
የእኔ አቦይ ስብሐት ቡድን “ጸረ ኢትዮጵያ፣ ጸረ የትግራይ ህዝብ” መሆኑን አስቀድመው ተረድተው፤ በትግራይ መሬት ላይ የተፋለሙትን  የዘንዶ ሕዝባዊ ሰራዊት አባላትን በዚህ ሰዓት አለማስታወስ ውለታቢስነት ነው። አቶ አብርሃም ያየህና አቶ ገብረ መድህን አርአያ፤ የእነ አቶ ስብሐትን ቡድን የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሳወቅ ያደረጉት አስተዋጽኦ  በክብር መታወስ አለበት።
በመንግሥትና በእነ አቶ ስበሐት ቡድን (ትሕነግ) መካከል ደቡብ አፍሪካ ላይ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በክልሉ የሰላም አየር እየነፈሰ መሆኑ እየተዘገበ ነው። የዘንድሮዋ ሕዳር ማርያም
በአክሱም የጽዮን በሰላም መከበሩን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል። ይህ ተመስገን የሚያሰኝ ነው።
ዓመታዊ የአክሱም ጽዮን በዓል በሰላም መከበሩ የሚሰጠው ደስታ ቢኖርም፣ በስምምነቱ የተነሳ የእነ አቶ ስብሐት ቡድን ሶስት ቦታ ላይ ተከፍሎ እየተወዛገበ የመገኘቱ ዜና ግን የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። የስምምነቱ ደጋፊዎች እነ ዶ/ር ደብረጽዮን፤ በደቡብ አፍሪካና በኬንያ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሰራዊታቸው ትጥቅ እንዲፈታ ወደተዘጋጀለት ካምፕ እንዲሰባሰብ እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል። ኬንያ ላይ ተደራዳሪ ከነበሩት አንዱ በኬንያ የኢትዮጵያ አምብሳደር ባጫ ደበሌ (ጄነራል)፤ ሐሙስ ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም በገለጹት መሰረት፤ የእነ አቶ ስብሀት ቡድን እስከ ቅዳሜ ባለው ጊዜ ውስጥ የነፍስ ወከፍና የከባድ መሳሪያ ትጥቁን ይፈታል፡፡ ይህ ለትግራይ በአጠቃላይም ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ የምስራች ነው።
ከዚህ የምስራች ጎን ትልቅ መርዶም አለ። ይኸውም በሰላም ስምምነቱ ያኮረፈው የቡድኑ አንዱ ክፍል፤ የደፈጣ ውጊያ ለመጀመር እየተዘጋጀ መሆኑን የመሰማቱ ጉዳይ ነው። በዚህ ሰሞን ወደ መቀሌ በሚገባው የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ላይ የተሰማሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ፈንጂ ማጥመዱና የተጠመደው ፈንጂ እንዲከሽፍ መደረጉ የማህበራዊ ሚዲያዎች አጀንዳ እንደነበር  አይዘነጋም፡፡ መረጃውን ሰጥቶ ፈንጂው ሰው ከመጉዳቱ በፊት እንዲከሽፍ ያደረገው የአካባቢው ሰው መሆኑ ታውቋል።
ጉዳዩ ከፈንጂው መምከን ላይ አይደለም፤ ከእሳቤው ላይ ነው። የእነ አቦይ ስብሐት ቡድን በሴራ ሽረባው የታወቀ ቡድን መሆኑ አይዘነጋም። የደረሰበትን መሸነፍ ተቀብሎ በከተማ እንደ ሰላማዊ ነዋሪ እያሰበ በጫካ እየተታኮሰ ለመቀጠል አያቅድም ተብሎ አይገመትም። የሰይጣን ጆሮ አይስማና የቡድኑ እጅ የለበትም ከተባለ የጅምሩን አደገኛነት መንግስት ከልብ ሊያስብበት ይገባል።
ከእነ አቶ ስብሐት ቡድን ሰራዊት ምን ያህሉ ትጥቁን አውርዷል? ስንቱስ በያለበት አድፍጦ ተቀምጧል? ደግሞ ስንቱ የደፈጣ ውጊያ ለማድረግ ሀገርን ሰላም ለመንሳት ተዘጋጅቷል? መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው። ይህ በትክክል አቅሙን መገመት የማይችል ክፍል በቸልታ ሊታይ አይገባም። ከሁሉም ከሁሉም በላይ የትግራይ ህዝብ ጦርነት እንደመረረው ማሳየትና አፍ አውጥቶ አፈንጋጩን ክፍል “ተወኝ ሰላም ላግኝበት” ማለት አለበት።
መንግስት ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ከኦነግ ሸኔ ጋር የአይጥና የድመት ጨዋታ እየተጫወተ ያለው፤ ኦነግ ሸኔን በእንጭጩ መቅጨት ባለመቻሉ ነው። ሌላ የትግራይ ሸኔ ለመሸከም ሀገር አቅምና ፍላጎት አላት ብዬ አላምንም።
ለ50 ዓመታት የጦር ሜዳ ሆነው የትግራይ መሬትና ህዝብ ዳግም ወደ ጦርነት ለመመለስ  ይስማማል ብዬ አላምንም፡፡ ህዝብ ነጻ ሆኖ ይኖር ዘንድ መንግስት ሃላፊነቱን መወጣት አለበት። ይህን ጉዳይ ቸል ማለት በአንገት ላይ እባብ መጠምጠም መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
በአጭሩ ኦነግ ሸኔ መማሪያ ይሁናችሁ ማለቱ ይቀለኛል።

Read 2077 times