Saturday, 03 December 2022 12:19

ሁዋዌ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና እየሰጠ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  • ሥልጠናው 5G፤ ክላውድ ኮምፒውቲንግ፤ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን--ያካትታል
       • ሴት መምህራንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሥልጠናው ተሳትፈዋል



           የትምህርት ሚኒስቴር ከሁዋዌ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር፤ “ሴቶችን በዲጂታል ክህሎት ማብቃትና የሴቶች አመራርን በቴክኖሎጂ መደገፍ” በሚል መሪ ቃል፣ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና ለሴት መምህራን መሰጠቱ ተገለጸ።
የመጀመሪው ዙር ስልጠና ከህዳር 12 እስከ ህዳር 14 ቀን 2015 የተካሄደ ሲሆን ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ሴት መምህራን በስልጠናው መሳተፋቸው ታውቋል። ሁለተኛው ዙር ስልጠና ህዳር 15 የተጀመረ ሲሆን ስልጠናው በዲጂታል ክህሎት (5G፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ክላውድ) እንዲሁም በሴቶች አመራር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሊሚንግ ዬ፣ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሁዋዌ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የሴቶችን የኑሮ ደህንነት በማሻሻል ረገድ  ዲጂታል ቴክኖሎጂ ያለውን ፋይዳ እየመረመረ  ነው ብለዋል።
“ሴቶች በቴክኖሎጂ እንዲሳተፉ ለመርዳት እንዲሁም ዕምቅ አቅማቸውን እንዲያወጡና ህብረተሰባችንን ወደላቀ ብልፅግናና ፍትሃዊ መጪ ዘመን ይመሩ ዘንድ የበለጡ ዕድሎችንና መድረኮችን ለመክፈት ቁርጠኞች ነን” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲ እና ዲጂታል ትምህርት ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ ዘላለም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ትምህርት ሚኒስቴር በICT ዘርፍ በሰው ሃብት ልማት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የትምህርት ዘርፉን የሚያግዝ ተግባራዊ ሥልጠና ለማግኘትም ሁዋዌን ከመሳሰሉ የግል ኩባንያዎች ጋር እንደሚሰሩ በአጽንኦት ተናግረዋል። ሁዋዌ ለሴቶች መምህራን ሥልጠና በመስጠት ላደረገው ትብብርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አንዳንድ ሰልጣኞች እንደተናገሩት፤ የክፍል ውስጥ የማስተማር ሂደቱ ይበልጡኑ ንድፈ-ሃሳባዊ በመሆኑ፣ ክፍተቱን ለመሙላት ተግባራዊ ስልጠና ወሳኝ ነው፡፡
እ.ኤ.አ ከ2008 አንስቶ ሁዋዌ በርካታ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ መርሃ ግብሮችንና ውድድሮችን በዓለማቀፍ፣ በክልላዊና አገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የጀመረ ሲሆን ከእነሱም መካከል፡ “የስኮላርሺፕ መርሃግብሮች፤ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር፤ ሁዋዌ አይሲቲ አካዳሚ፤ ሁዋዌ ዴቨሎፐርስ ትሬይኒንግ፤ ሁዋዌ ክላውድ ዴቨሎፐር ኢንስቲቲዩት፤ ውመን ቴክ እና ቴክኖሎጂ ፎር ኢጁኬሽን” ይጠቀሳሉ፡፡
በተመሳሳይ ዜና፤ የ2022 “Seeds for the Future” መርሃ ግብር በኢትዮጵያ፣ ከህዳር 12 እስከ ህዳር 19 ቀን 2015 የተካሄደ ሲሆን፤ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከ60 በላይ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል ተብሏል።
መርሃ ግብሩ የ8 ቀናት የኦንላይን ስልጠና ሲሆን ከተማሪዎቹ የ15 ሰዓታት ሙሉ ትጋትን የሚጠይቅ እንደሆነ ተጠቁሟል። ሥልጠናው በቁልፍ ቴክኖሎጂዎች (5G፣ ክላውድ ኮምፒውቲንግ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ላይ መሰረታዊና ከፍተኛ ደረጃ ኮርሶችን የሚያካትት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

Read 1269 times