Sunday, 04 December 2022 00:00

ከራስ ጋር ጠብ - (ወግ)

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(3 votes)

  ከረጅም ጊዜ በኋላ...
ወንበር ስቦ ‘ራሱን ኖር አለው _የልብ የልቡን ሊያወጋው። እንግዳ ማንነቱ፣ አትሮንሱ ላይ መጽሐፍ ገልጦ “ገድለ ሕይወቱን” ሊያትትለት ሲሰናዳ፤ ነባር ማንነቱ ጆሮው እንደ ጥንቸል ጆሮ ቆመ - ሊሰማ። ከየት ልጀምርልህ? ሕይወትስ ጠርዝና ደርዝ አላትን? ከ እስከ የሚል ቅንብብ ውስጥ ምን ይነበብልህ? ይለዋል። ባለ ታሪኩን ራሱን፣ አማንን። አስቀደሞ ታሪክ ስለሚዘክራቸው፣ መስዋዕትነትን ስለከፈሉ ጀግኖች አተተለት። በጀግንነት፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀን፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድንና፣ ደጃዝማች ወንድይራድን ጠራ። በሙዚቃ፣ ክቡር ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄን፣ እማሆይ ጽጌ ብሩን  ጠቀሰ። በሥነ-ጥበብ፣ ገ/ክርስቶስ ደስታን፣ ደስታ ሐጎስን፣ ለማ ጉያን  አነሳ። በስፖርት፣ ሻምበል አበበ ቢቄላን፣ ሻምበል ማሞ ወልዴን፣ ሻምበል ምሩዕ ይፍጠርን፣ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉን፣ ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴን ጠቀሰ_ከኢሴንሸል መጽሐፉ፤ ለመሆኑ አንተ ምን ሰራህ አማን? ከየቱ የሕይወት ፈርጅ ውስጥስ ነው አሻራህ ያረፈው? ነባር ማንነቱ፣ እንግዳ ማንነቱን በትዝብት አየው። አትሮንስ ተደግፎ ታሪክ መዘብዘብ ብቻውን ምን ይሰራልሃል? ሊለው ፈለገ። እንደለመደው “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ”ይለኛል ሲል አስቦ ተወው። ታሪክ ሰሪ...ታሪክ አውሪ...ታሪክ ፈሪ...በየዓይነቱ የሆንን ሕዝቦች አለ አጨንቁሮ!
[ዝምታ:ወደ ራስ ጉዞ:
ግለ-ጥያቄ: ብስልስሎሽ
ራስ ላይ ጣት መቀሰር።]
ቀጠለ ንዝንዙን።
ምሽቱ የሚረዝምብኝ ‘ቀንህ ይጠር ‘ተብዬ ተረግሜ ነው። ደግሞም  መጻዕጉ ነኝ፤ ታሪኬ ከአልጋዬ ጋር ነው። አልጋዬ ስልህ በሌላ ጎን አትይብኝ። ምሽቱ ረጅም ቢሆንብኝም ላይነጋ አይመሽምና እየቻልኩት አለሁ። አትሮንስ ላይ ተደግፌ ታሪክ ብሰብክህ ልብህ አያመንታ። አንተን ለመገሰጽ አልሰንፍም። ወደ  ተቀመጠው ...አፉን ገጥሞ ጭንቅላቱን ወደከፈተው አማን ጣት ቀሰረበት። አምሳሉ ነው። የራሱ ነጸብራቅ። ይኼም አልበቃው።
‹‹አንተ ዱልዱም›› ሲል ዛተበት።
አንዱ ተመሪ አንዱ መሪ ሆነው ቢውሉም ቅሉ አምሳሉ ነው። ከአካሉ አካል፣ ከነፍሱ ነፍስ ነስቶ ሳለ እንደማያውቀው ሆነበት። ራስ ከእራስ ጋር ሲጋጭ ገላጋይ ማን ነው?
‹‹አቤት! አንተ ታሪክ ዘብዛቢ››
‹‹በአፍህ ፋንታ ልብህን ክፈት››
‹‹ከልቤ ምን አለህ?››
‹‹ጉዳይ አለኝ››
አማን ከራሱ ተለያየ። ነፍሱ መጠጊያ ታዛ፣ ያቅፋት አበርቺ ሻተች። ከራስ ምክር ለመዳን ምክር ፍለጋ ወጣች። እንደ ደርግ ...እንደዛ ዘመን ...ኮሚቴዎቹን ለመቀነስ ኮሚቴ እንዳዋቀረው...
[ምክር ረግጦ ወጣ፣ ላይመለስ ወደራሱ
ሥጋውስ ልማዷ ነበር፤ ከዳችው መሰል ነፍሱ]
11 ሰዓት ሆነ። አካሉም በ’ወይ እናት’ አውላላ ሜዳ ላይ ቆመ። አማን አለ ራሱን፤ ሁለት ሰው ነኝን? ሲል ጠየቀው። አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን ሞት ይረዳልና ከሁለትም በላይ ማንነት እንዳለው ተረዳ።
የራሱ ስሜት ነጸብራቆች፣ የአቻነት ልፊያዎቹ ሊበሉት ይደርሳሉ። በየኼደበት ይቀመጥበት ቦታ ይነሱታል። ይጠሩ ..ያብጠለጥሉታል፤ ይቆርጡ ይቀጥሉታል። ወደ ቀልቡ ሲመልሰው ‹‹ከራስ ጋር ጥል ክፋቱ›› ይላል። ትልቅ ጃኬቱን ደርቦ፣ ግራ እጁን ከሰው ደብቆ (በኪሱ ከትቶ)፣ በቀኝ እጁ መከረኛዋን ኒያላ ወደ አፉ እያደረሰ ይመልሳታል። አረጋገጡ ከፍ ዝቅ (ብቅ ጥልቅ) ነው። አውደ ውጊያ ላይ የተመታ ወታደር ይመስላል አኳኋኑ። ሰው በማይበዛበት መንገድ መጓዝ ያዘወትራል። የእሱ ዓለም በለኮሳት ሲጋራ ጭስ ቀለበት የምትታየዋ ናት። ቴሌስኮፗ። ሳብ አድርጎ ሲተነፍስ የሚፈጠረው የጭስ ቀለበት እንደ መቅርበ-ምስል ሌላ ግዙፍ ዓለም ያሳየዋል። ረሃ የሆነ...ሽር ብትን... ይባልበትን ዓለም....
‹‹አማን››
ጠሪው ሌላኛ ማንነቱ ነው። እስከ መቼ የፖላንድ ላም  ትሆናለህ? እስከ መቼ የሄደ የመጣው እያለበ ይጫወትብሃል? በላ...ንገረኛ! እስከ መቼስ ነው  ለአጉል ሱሶች እስረኛ ሆነህ መዋልህ.. ያም ያም ቸር ላይልህ፣ አንዱ በሥርዓት ሲያስቀምጥህ፣ ሌላው  ሲያነሳ ሲጥልህ ..እስከ መቼ?
[ትዝ አሉት፤ የአገሪቷ መሰሪዎች፤ ቀን የሰጣቸው ሰዎች፤
ትዝ አሉት፤ ግፍ አይፈሬዎች፤ በሌላ እንባ የሚስቁት
ትዝ አሉት፤ ጥጋበኞች፤ የአቅም መፈተኛ አድራጊዎች]
መንታ መንገድ ላይ ቆመ። ሁሉም ሠው ተሰትሯል። ብዙ ውሾችን ያስከተለ ሰው ከፊቱ መጣ። ለአማን ጠላቱ ነበር። በአጠገቡ ሲያልፍ “ዘመድ ከዘመዱ አህያ ከአመዱ” ሲል ተረተበት። ቅኔ አያስፈልገውም “ውሻ ውሻን ቢያረባ ምኑ ነው ነውሩ አማን?” ብሎ አፉን አስያዘው። ተላለፉ ትዝብት አትርፈው።
መንገዱ መንታነቱ ሕይወቱ መሆኑን ተረዳ። ደንቆሮ የሰማ’ለት ያብዳል እንዲሉ ራሱን በምሣሌ ሲገልጠው አንዳች ስሜት ወረሰው። መኼዱን እንጅ የሚኼድበትን አያውቅም ።እግር ስለተሰጠ ብቻ አይኬድ። መንገድ ስላለ ብቻ አይኬድ። ጨነቀው _አማንን። ልቡ አመነታ። የቅርብ ትውስታዎቹ ትዝታ ለመባል በቁ። እንዲሁ በ”ነበር” ሊጠሩ መሆኑ ነው። “የፖላንድ ላም ነህ ይበለኝ ደፍሮ?” አለ እየጨነቀው። መላ ቅጡ እየተምታታበት።
በእጁ የያዛት ሲጋራ አላለቀችም። ፊቱ ቦዟል። ሆዱ ሰፋ፣ ቂጡ ከበድ ያለ ሰው ሊተላለፍ ቀረበው። አጭር ሰላምታ፣ ረጅም ጭስ ተለዋወጡ። ሰውዬው አቻውን ስላገኘ ፍስኀ ሆነለት። ባኮ ወደ ማገባደዱ ሲጠጉ ቦርጫሙ የአማንን ሲጋራ ለመነው ...አለማመኑ ያለ ቃል ነው።
‹‹ከአለሁበት ድረስ መጥተህ እሳት ለመንከኝ?››
‹‹ምን ታደርገዋለህ አማን...››
‹‹ለመሆኑ ሰው ከራሱ ጋር ሲጣላ ማን ነው ሚገላግለው?››
‹‹ሦሥተኛ ራሱ ነዋ ...እንጅ በቤተሰብ ጠብ ማን ይገባል ብለህ ነው››
ተላለፉ።
አንድም ሦሥትም ብሎ የሚያመልከው ፈጣሪውን ብቻ ነበር። አሁን ግን ነገሮች የራሱንም ምሥጢር ገለጡለት አንድም ሦሥትም ...ሌላም ሌላም እንደሆነ። ሰው ቅዱስም ንጉሥም ሲል ምሉዕ - ጌታ ተስፋዬ፤ ሰው ቅዱስም እርኩስም ብሎ ወደ ራሱ መለሰው። ስለ ጠቡ፣ ከራሱ ጋር ስላለው ግብግብ አለ...
[...እላፊ ነገር አውርቼ፣ ከሠው ጋር ብጣላ ስቼ
ገላጋይ ይገባበታል፣ ጠቡን በእርቅ ይፈቱታል።
ግን ጥሉ ቢሆን ከእራሴ፥ የራሴን ድንበር ገፍቼ
ሰዎቹ እንዴት ያዩታል፣ ጠቤንስ ምን ያደርጉታል?]
አማንን ያሸነፈ ወጠምሻ አልነበረም። በራሱ ግን ተሸንፏል። ወኔውን የሰለበ ሌላ ማንነት አለ ከውስጡ። “የወረቀት ገጾች ሲሰበሰቡ በቀጭን ጠርዛቸው ላይ ቢጽፉባቸው ይነበባሉ። ሲነጣጠሉ ግን ቀለሙ ይኑር አይኑር አይታወቅም፤ አንድን እንጨት ልትሰብረው ጉልበት አታጣም የተደራረበውን እንጨት ግን አትችልም ድር ሲያብር አንበሳ ያስር ይሉትን ሥነ-ቃልስ አታውቅምን አማን? የሚለው ሌላ አዋቂ ማንነት አለ ከውስጡ። እንዲተባበሩ የሚለምነው፣ ታሪክ እንዲሰራም የሚገፋፋው። ለአሸናፊነት መገዛትን ልመድ፤ አሸናፊውም ፍቅር ነው ወዳጄ! ... የሚለው። ቀደም ብሎ...ከፖላንድ ላምነት ሊያድነው የሚታገል አቅም ሲፋፋ፣ ሰቅዞ የሚይዝ ወኔ በልቡ ሲያድግ ይሰማው ነበር። በመጨረሻም ወንድም በወንድሙ ላይ ቀርቶ ራሱ በራሱ ላይ ተነስቶ አየ።
ጉብታ ላይ ተቀመጠ። ተግሳጹን ሊቋቋም ባለመቻሉ እጁን ለምዕዳን ዘረጋ።
በራሱ ጅራፍ አነሳ፣ ገላው ለቁስል ዋለ፤ ይኼ የሚያሳየው የእሱን የገረፋ ጥንካሬ ወይስ ለስቃይ ስስነቱን?
ከበሮ ትዝ አለው። የጌታውም የጀርባው ሰምበር። የጅራፉ መጠን። እንዲሁ እንባ ያረገዙ ዓይኖቹን ገለጠ። ዕፅ አየ። ዕፀ-በለስ ወይስ ዕፀ - ሕይወት?...
ፊት ለፊቱን መስታወት ፊት ቆሞ የሚጮህ ውሻ ይታየዋል። የራሱን ነፀብራቅ በመስታወቱ እያየ የሚነጫነጭ ውሻ። እኔም ውሻውን እያለ ቀይ ጃኬቱን አውልቆ ደንዳና ክንዱ ላይ አስቀመጠ።
ድጋሚ ወንበር ስቦ እራሱን ኖር አለው።
ረቂቅ የመለኮት ጥሪ፣ በቀበሌ የታጀበ ነጎድጓዳማ ድምጽ ተሰማው። ውሸት የጠቀማት (ያገጣጠማት) አካሉ ፈራች። ትደርስበት ስፍራ የላትም። የሚያዝዘው ንጉሥ በዛ ጋድም እንዲሁ። ያልተዳሰ ኑሮ ይዞ መቃብር መዳስ ይሆናልን? ሲል እራሱን አለዘበ ሊወያይ (ሊደራደር)። ፍሬ  ነገሩን ወደ ልቡ ጽላት ሊመራ። የእንግዳ ማንነቱን ተግሳጽ ወ ምዕዳን ሊቀበል።
«አማን፤ ተመልሰህ መጣህ?»
አነጋገሩ የፍቅር ነው።
«አዎን! እጅህ ላይ ነኝና እባክህ ዳግም ፍጠረኝ..»
«የሰው ልጅ ለመኖር አየር ይፈልጋል። አየርን ግን በዓይኑ  ያየ አለ? የለም! ውኃ ለዓሣ መኖር ያስፈልጋል። ውኃን ግን ዓሣ ያየዋል ብለህ ታስባለህ? አላስብም! ፈጣሪህ ለአንተ መኖር ያስፈልጋል። ዳሩ ማየት ትችላለህ? አልችልም። አየህ የማይታዩት ኃያላት ናቸው። ያልታዩ ፀባይዎችህን ፈትሽ።»
  [ፀጥታ ፡ መፈራራት ፡ሐሳብ]
ፀጥታው በአማን ተሻረ።
«ታዲያ ምን በጀኝ?» (በተማጽዕኖ)
«ሰዎች ዕፀዋትን ቢንከባከቡ ሊበሉ፤ወይ ሊያጌጡባቸው ነው። ዕጽዋትም ሰውን ቢንከባከቡ ሰው ሞቶ አፈር ሲሆን ለመመገብ ነው። ሁሉም ተደጋጋፊ ነው። ሥጋህ ካለ ነፍስህ በረት ናት፤ ነፍስህም ካለ ሥጋህ ቦታ አትይዝም። ትኖር እንደሆን ተደጋገፍ፣ ትጓዝ እንደሆን ተደናቀፍ...ማዶ ለአንተ ምቹ ሥፍራ አለ። “ሰይጣን ሲጣል የወደቀበትን ዋሻ” ማለትም ሆድህን ጥላው።»
በክትፎ አይጨክንምና ከተኛበት ብንን አለ።እስከ አሁን የረዘመችው፣ ህልሙ ውስጥ የተከወነችው፣ ይህች “ከራስ ጋር ጥል” አጭር ታሪክ ጣመችው። ድጋሚ ሊያልም ተኛ። ሲነሳ “ከራስ ጋር ፍቅርን” ይዞ እንዲነሳ ይሁንለት።


Read 11082 times