Saturday, 03 December 2022 12:24

ኢራናውያን በኳታር - ኳስና የነጻነት ትግል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)

   • “እዚህ ያለነው በኢራን ለታፈኑት ድምጽ ለመሆን ነው”
       • “ህፃናት እየተገደሉ ባሉበት ሁኔታ እግር ኳስ ትርጉም የለሽ ነው”
       • ተጫዋቾች በመቃወማቸው በመንግስት ጥርስ ውስጥ ገብተዋል
      
      የኢራናውያን ተቃውሞ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ትኩረት ስቧል፡፡ የኳስ ደጋፊ ኢራናውያን ብቻ ሳይሆኑ ተጫዋቾችም ለተቃውሞው ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡ ደጋፊዎችና  ተጫዋቾች - ሁለቱም - የኳታሩን የዓለም ዋንጫ መድረክ ድምጻቸውን ለማሰማትና የአገራቸውን አገዛዝ ለመቃወም ተጠቅመውበታል። “France 24” የተሰኘው የፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ኢራናውያን የእግር ኳስ ደጋፊዎችን በኳታር አነጋግሯል።
“በኢራን ፖለቲካና እግር ኳስን ለመለየት አዳጋች ነው” ብለዋል፤ በ2022 የዓለም ዋንጫ፣ የኢራንን ጨዋታ ለመመልከት ከካናዳ ወደ ኳታር የመጡት የ53 ዓመቱ ኢንጂነር አሊ ሁማን። ኢራን በዌልስ ላይ ድል የተቀዳጀችበትን ጨዋታ ከማድረጓ አስቀድሞ ከአህመድ ቢን አሊ ስቴዲየም ውጭ ከ”ፍራንስ 24” ጋር ቆይታ ያደረጉት ሁማን፤ የእስላሚክ ሪፐብሊክ አርማው ከመሃሉ  ተቆዶ የወጣ የኢራን ሰንደቅ ዓላማን ይዘው ነበር።
ባለፈው ነሐሴ መጨረሻ ላይ የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ፣ “የፀጉር መሸፈኛ (ሂጃብ) በአግባቡ አላደረግሽም” በሚል በስነ-ምግባር ፖሊስ ተይዛ በቁጥጥር ሥር ሳለች መሞቷን ተከትሎ ነው፣ በኢራን አመራሮች ላይ ህዝባዊ ተቃውሞው እየተቀጣጠለ  የመጣው። በወጣቷ ሞት በተፈጠረ ቁጣ ሳቢያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፤ መጠነ - ሰፊ ወደ ሆነ አመጽ ተለውጧል- በአገዛዙ ላይ ያነጣጠረ።
በኳታር፣ ለተቃውሞ ንቅናቄው የራሳቸውን ድጋፍ ለማሳየት ይፈልጉ እንደነበር የገለጹት ሁማን፤ ነገር ግን በኢራን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ያንኑ ሲያደርጉ በማየታቸው መደነቃቸውን ተናግረዋል። የኢራን ተጫዋቾች ከእንግሊዝ ጋር የመክፈቻ ግጥሚቸውን ከማድረጋቸው በፊት፣ ብሔራዊ  መዝሙራቸውን ከመዘመር በመታቀብ፣ ለተቃውሞ ንቅናቄው ድጋፋቸውን አሳይተዋል።
የተጫዋቾቹ የጋራ ዝምታ ተምሳሌትነቱ በዓለም ዙሪያ የተዳረሰ ቢሆንም፣  የመዝሙሩን ግጥም በትክክል በሚያውቁት ኢራናውያን ዘንድ ግን መዝሙሩን አለመዘር  የተለየ ትርጉም አለው - የእስላሚክ ሪፐብሊኩ፤ “ፅኑ፣ ቀጣይና ዘላለማዊ” እያለ የሚያውጅ ነው፤ ግጥሙ። አዲስ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ የኢራናውያን መንግስት ለመፍጠር የሚታገሉት የኢራን ተቃዋሚዎች ግን ይህን እሳቤ አይጋሩትም። ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች የጥንቱን የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር መዘመር ጀምረዋል ተብሏል፡፡
“በተጫዋቾቹ ላይ የተቃውሞ ጩኸት ጠብቄ ነበር፤ ነገር ግን ድርጊታቸውን ሳይ ሃሳቤን አስለወጡኝ፤ በእነሱ ኩራት ተሰምቶኛል” ብለዋል ሁማን። “ለዚህ ተግባራቸው ግን በአገር ቤት መቀጣታቸው አያጠራጥርም፤ሆኖም ጠንካራ መልዕክት ነው ያስተላለፉት” ሲሉም አክለዋል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች
የኢራን ተጫዋቾች ከዌልስ ጋር ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ ግን ብሔራዊ መዝሙራቸውን ለመዘመር የመረጡ ሲሆን፤ ይህም ከደጋፊዎች ተቃውሞን አስከትሎባቸዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ራሱ የተከፋፈለ ነው። አጥቂው ሳርዳር አዝሞን፣ ተቃዋሚዎችን በመደገፍ ለበርካታ ጊዜያት ድምፁን አሰምቷል። አምበል ኢህሳን ሃጅሳፊ፣ በኢራን ሁኔታዎች “ትክክል አይደሉም” ሲል ተናግሯል። ሁለት ተጠባባቂ ተጫዋቾች፡- መህዲ ቶራቢ እና ቫሂድ አሚሪ በበኩላቸው፤ የአሁኑን የኢራን አመራር በመደገፍ የሚታወቁ ናቸው።
በሌላ በኩል፤ የቡድኑ ማናጀር ካርሎስ ኪውይሮዝ፣ ተጫዋቾቹ በእግር ኳሱ ላይ ብቻ ያተኩሩ ዘንድ የማይመለከታቸውን ጉዳይ እንዳይጠየቁ አበክሮ ተሟግቷል። በዓለም ዋንጫ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ለሰነዘሩ ጋዜጠኞች ማናጀሩ በሰጡት ምላሽ፤ “ልጆቹ እግር ኳስ ብቻ እንዲጫወቱ ተዋቸው። ወደዚህ የዓለም ዋንጫ አምጥቶ የማይመለከታቸውን ጉዳይ መጠየቅ ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
የኢራን ተጫዋቾች ተናገሩም አልተናገሩም፤ የዓለም ዋንጫ  ከተጀመረ አንስቶ በጥብቅ ክትትል ውስጥ ናቸው ተብሏል። የግብ ድላቸውን ደስታ የሚገልጹበት ሁኔታ ሳይቀር ለፖለቲካ ትርጉም እንዲያመች ይሰነጠቃል፣ ይተረጎማል፣ ይተቻል።
“የቡድኑ ተጫዋቾች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ናቸው” ያሉት ሁማን፤ “ምንም ነገር ቢያደርጉ ከመነቀፍና ከመተቸት አያመልጡም” ብለዋል።
አሊ ሞታሃሪ የተባሉ አንድ ወግ አጥባቂ የፓርላማ አባል በተጫዋቾቹ ላይ በሰነዘሩት ትችት፤ “ያ እንዲሆን ፈጽሞ መፈቀድ አልነበረበትም።
ተጫዋቾቹ የእስላሚክ ሪፐብሊክ ስርዓቱ ተወካዮች ናቸው፤ የግላቸውን አመለካከት የማንጸባረቅ መብት ፈጽሞ የላቸውም” ብለዋል። እነዚህ ተጫዋቾች አገርን በመወከል ወደ ኳታር እንዲጓዙ ያደረጉትን የኢራን የስፖርትና ባህል ሚኒስቴር ሃላፊዎችንም ክፉኛ ወቅሰዋል፤የፓርላማ አባሉ፡፡
የኢራን አመራሮችን በአደባባይ መተቸትም ትልቅ አደጋን ያስከትላል። ከኢራን- ዌልስ ግጥሚያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በ28 ዓለማቀፍ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው የኢራኑ ተጫዋች- (ቮርያ ጋፉሪ) በፖሊስ የመያዝ  ተሰምቶ ነበር፡፡ ከአራት ወራት በፊት ጋፉሪ አምበል የነበረበትን የኢሽቴግህላል ክለብ ለቆ እንዲወጣ ተገደደ- በኢራን መሪዎች ላይ በሚሰነዝረው ተደጋጋሚ ትችቶች ሳቢያ።
ከአህመድ ቢን አሊ ስቴዲየም የደህንነት በሮች አቅራቢያ፣ አራን ጋድባሪ፣ “ሴቶች፣ ህይወት፣ ነፃነት፣ "ማህሳአሚኒን”  የሚለውን የኢራናውያን የተቃውሞ መፈክር የያዘ ሰንደቅ (ባነር) በኩራት ይዞ ነበር የቆመው።
“በኢራን የተነፈግነው ይህን መፈክር ነበር። ለዚያ ነው አብዮት ማቀጣጠል የፈለግነው” ብሏል፤ የ31 ዓመቱ የዳታ ተንታኝ። አክሎም ሲናገር፤ “የእግር ኳስ ቁምነገሩ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ነው፤ ነገር ግን በኢራን አዋቂዎችና ህፃናት እየተገደሉ ባሉበት ሁኔታ ይሄ ትርጉም - የለሽ ነው” ብሏል።
ከማህሳ አሚኒን ሞት ወዲህ በተቃዋሚዎች ተደጋግሞ የሚስተጋባው መፈክር፤ “ሴቶች፣ ህይወት፣ ነፃነት” የሚል ነው። “ለኢራን ነጻነት” የሚለውም የተለመደ የነጻነት  መፈክር ነው። የኢራን ሰብአዊ መብቶች ተቋም ባወጣው መረጃ መሠረት፤ የተቃውሞ ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ 51 ህጻናትን ጨምሮ 416 ሰዎች ተገድለዋል።
“ብሄራዊ  መዝሙርን አለመዘመር ብቻውን በቂ አይደለም፤ ተጫዋቾች የበለጠ ማድረግ አለባቸው” ብሏል ጋድባሪ። “እዚህ ያለነው ለእነሱ ብለን አይደለም፤ ቢያሸንፉ ወይም ቢሸነፉ ደንታችን አይደለም። እኛ እዚህ ያለነው ንቅናቄውን  ለመደገፍ ነው” ሲል በቁርጠኝነት ተናግሯል።
ጋድባሪ ወደ ኳታር የመጣው ከኢራን ሳይሆን ከአሜሪካ ነው፤ ስለዚህም በአደባባይ አገዛዙን በመተቸቱ የሚጋፈጠው ብዙም አደጋ የለም፡፡ ከኢራን ተጉዘው ለመጡት  ጓደኞቹ ግን ሁኔታው የተለየ ነው። ከኢራን የመጡ የእግር ኳስ ደጋፊዎች በተቃውሞ ንቅናቄው ቢሳተፉም ቅሉ፣ አንዳቸውም ለ”ፍራንስ 24” ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም፤ ወደ አገራችን መመለስ የማንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት።
አንድ የኳታሩን ተቃውሞ የሚቃወም የእግር ኳስ ደጋፊ  ብቻ ነው፣ ለቃለ -መጠይቅ ፈቃደኛ ሆኖ የተገኘው፡፡
“ይህ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ጉዳይ ነው፤ ማንም ለኢራን ውስጣዊ ችግር ባህርማዶ መጥቶ ተቃውሞ ማድረግ የለበትም” ያለው ኢራናዊው፤ “እኛ እዚህ ያለነው ቡድናችንን ለመደገፍ ነው። ለዓለም ዋንጫ አልፈዋል፤ በዚህም እንኮራባቸዋለን፤ እንዲያሸንፉም እንፈልጋለን” ብሏል።

“ እዚህ ያለነው ለታፈኑት ድምጽ
ለመሆን ነው”
ትውልደ ኢራናዊ-አሜሪካዊቷ ኒካ፤ ከስር የለበሰችውን የማህሳ አሚኒን ቲ-ሸርት ለማሳየት የብራዚል ሸሚዟን መግለጥ ነበረባት። በኢራን- እንግሊዝ ግጥሚያ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ ድምጿን ማሰማቷን ተከትሎ፣ የማስፈራሪያ መልዕክት ከደረሳት በኋላ ነው፣ ከስታዲየም ውጭ ትኩረት ላለመሳብ የወሰነችው።
ከካሊፎርኒያ የመጣችው ኢንጂነርም፣ በፀጥታ ሀይሎች እንዳይወረስባት በመፍራት ቲ-ሸርቷን በግላጭ ከመልበስ ታቅባለች። የጸጥታ ሃይሎች፣ ማናቸውም ቁጣ ቀስቃሽና አግላይ የፖለቲካ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ቃላት ወይም ምስሎች የያዙ ነገሮችን እንዲወርሱ የፊፋ ህግ ይፈቅድላቸዋል፡፡
የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የፎቶግራፍ ባለሙያ በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው፣ በአህመድ ቢን አሊ ስቴዲየም የፀጥታ ሃይሎች፣ የኢራናውያን ተቃዋሚዎችን ባንዲራ ወርሰዋቸዋል።
ኒካ በኳታር የዓለም ዋንጫ ለመታደም የፈለገችው የኢራንን አገዛዝ የሚደግፉ የእግር ኳስ ቲፎዞዎች መድረኩን በበላይነት እንዳይቆጣጠሩት ለማድረግ መሆኑን ተናግራለች።
“ብዙ ሰዎች የተቃውሞ ንቅናቄውን ለመደገፍ ወደዚህ አልመጡም፤ እናም አገዛዙ የራሱን ደጋፊዎች በመላክ አጋጣሚውን ይጠቀምበታል” ያለችው ኒካ፤ “እኛ የመጣነው ይበልጥ ጠንካራ እንደምንሆን  ተስፋ በማድረግና ከእነርሱ የላቀ ጩኸት ለማሰማት ነው” ብላለች።
ኒካ፤ የእግር ኳስ  ጨዋታ በቀጥታ ከስታዲየም ስትመለከት የመጀመሪያዋ  ነው። “የዓለም ዋንጫ በዓለም ላይ ትልቁ የስፖርት ኹነት ነው። ትልቅ የፖለቲካ መድረክ ሊሆን ይችላል። እኛ እዚህ ያለነው በኢራን ለታፈኑት  ድምጽ ለመሆን ነው” ስትል ኒካ ለ”ፍራንስ 24” ቲቪ ተናግራለች።

Read 699 times