Saturday, 03 December 2022 12:56

ብሬክስሩ ትሬዲንግ በዓመቱ 65 ሚ. ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     በ20 ዓመታት ውስጥ ባለ ብዙ ፋሲሊቲ ሜትሮፖሊስ (ከተማ) ለማቋቋም አቅዷል

        ብሬክስሩ ትሬዲንግ አ.ማ. ዓመታዊ የሽያጭ ዕቅዱን በ65 በመቶ በማሳካት 65 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ በተካሄደው ሦስተኛው መደበኛ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ነፃነት ዘነበ እንደተናገሩት፤ የ2014 በጀት ዓመት የሽያጭ መጠን 65 ሚሊዮን ብር ደርሷል።
ጠቅላላ ጉባኤው በ2014 የበጀት ዓመት 100 ሚሊዮን ብር ገቢ  ዕቅድ ቢያስቀምጥም፣ ድርጅቱ የዕቅዱን 65 በመቶ በማሳካት፣  65 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የቦርድ ሰብሳቢው አስታውቀዋል።
“የባለአክሲዮኖች ድርሻ በሽያጭ ካገኘነው ገቢ 50 በመቶው ነው” ሲሉም ገልፀዋል፡፡ በ2014 የበጀት ዓመት የኩባንያውን ንግድ ለማስፋፋት የተነደፈውን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ በስኬት መድረሱንም አቶ ነፃነት ተናግረዋል።
“ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ለመክፈት ባቀድነው መሰረት በአዲስ አበባና አዳማ ከተማ ሁለት ቅርንጫፎችን መክፈት ችለናል” ብለዋል፤አቶ አቶ ነፃነት። “በደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያና ካሜሩን ቢሮ ለመክፈት የምናደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ የሚያስችል በጀት መድበናል። በተጨማሪም፣ መንገዶችን ለማመቻቸት የሚረዱ ሃሳቦችን ከተወሰኑ ግለሰቦች ጋር በመለዋወጥ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ብሬክስሩ ከዚህም ባሻገር “ጆብ ክርኤሽን” ከተባለ የኬንያ ኩባንያና ከደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል” ሲሉም ገልጸዋል፤ሰብሳቢው፡፡
ጠቅላላ የባለአክሲዮኖቹ ጉባኤ ተወያይቶ የኦዲትና አጠቃላይ ሪፖርቶችን እንደሚያጸድቅ የተገለጸ ሲሆን፤ የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ድልድልና የኩባንያው የስራ ዕቅድም ለውይይት ቀርቦ እንደሚጸድቅ በበዓሉ ላይ ከተሰራጨው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።
ብሬክስሩ ትሬዲንግ፤ አርቆ አስተዋይ፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድ የመገንባት ራዕይ ያለውና “ቅን” በተሰኘ ቡድን በ2019 ዓ.ም የተመሰረተ የንግድ ኩባንያ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተሻሉ አዳዲስ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ፣ የየራሳቸውን ንግድ በዲሲፕሊን እንዲያከናውኑና ከሌሎች ጋር ውጤታማ ትብብር እንዲፈጥሩ የማማከርና የስልጠና አገልግሎቶችን መስጠቱ ተጠቁሟል፡፡
ብሬክስሩ ትሬዲንግ፤ በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ኩባንያዎችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የሥልጠና ማዕከሎችን፣ የስብሰባ ማዕከላትን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ሪል እስቴትን፣ ቢሮዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ጂምናዚየሞችን፣ ሙዚየሞችንና ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የሚያቅፍ ባለብዙ ፋሲሊቲ ሜትሮፖሊስ (ከተማ) ለማቋቋም ማቀዱ ታውቋል።
           

Read 1595 times