Saturday, 10 December 2022 12:55

ከሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች በግጭት ሲናጡ ሰነበቱ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

   - ፖሊስ በግጭቱ ሳቢያ የጠፋ የሰው ህይወት የለም ብሏል። 97 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ገልጿል
      - የአዲስ አበባን ህዝብ መብትና ፍላጎት በጉልበት ለመጨፍለቅ የሚደረገው= እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም ኢዜማ አሳስቧል።
      - አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የዚህ በህገ-ወጥ ተግባር ተባባሪ በመሆኑ በህግ ሊጠየቅ ይገባል ተብሏል
               
          ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እንዲውለበለብ ለማድረግና የክልሉን መዝሙር በግድ ለማዘመር የተደረገው እንቅስቃሴ  ከፍተኛ ግጭትና ሁከት ቀስቅሷል። ድርጊቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ረብሻ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ወላጆች መቁሰላቸውን ተነግሯል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ሁከትና ረብሻውን አነሳስተዋል ያላቸውን 97 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ህግ የማስከበር ተግባሩንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ከወራት በፊት በተጀመረውና ሰሞኑን ተጠናክሮ በቀጠለው ይህንኑ የኦሮሚያ ክልልን ባንዲራ የማሰቀልና የክልሉን “መዝሙር በግዴታ የማዘመር ድርጊትን የተቃወሙ በርካታ ተማሪዎች መዝሙሩን አንዘምርም ሰንደቅ አላማውንም አንሰቅልም” በማለት ት/ቤታቸውን እየለቀቁ ወጥተዋል።
ባለፈው ሐሙስ ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አምባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትና አርብ ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ በዚሁ ክፍለ ከተማ ድል በትግልና አዲስ ተስፋ መጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች በተቀሰቀሰ ረብሻ በርካታ ተማሪዎች  በድንጋይ መወራወር መቁሰላቸው ተገልጿል። “እኛ የምንዘምረው የአገራችንን ብሔራዊ መዝሙር ነው የምንሰቅለውን ብሔራዊ ሰንደቅ አላማችንን ነው ከዚህ ውጪ የሆነ ነገር አናደርግም” ባሉ ተማሪዎችና መዝሙሩን መዘመር አለባችሁ በሚሉ ወገኖች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭትና ሁከት እየተስፋፋ ሄዶ ማክሰኞ ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሙሉ ብርሃን (አዲስ ብርሃን) እና በዚሁ ክፍለ ከተማ ቀጨኔ ደብረሰላም ት/ቤቶች ከፍተኛ ረብሻ እንዲፈጠር ሆኗል። በዚሁ ዕለት በየካ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ 12 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው ረብሻና ግጭት በርካታ መምህራንና ተማሪዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል። ረቡዕ ህዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ፤ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት “የኦሮሚያ ክልል ባንዲራን አንሰቅልም፤ መዝሙሩንም አንዘምርም በማለት የተቃወሙ ተማሪዎችና መምህራን ድብደባ እንደደረሰባቸውና ለእስር መዳረጋቸው የታወቀ ሲሆን  ይህን  ድርጊቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ግጭትም በርካታ ተማሪዎችና መምህራን ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።
አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ት/ቤቶች የተቀሰቀሱትን ረብሻዎች ተከትሎ ወሰድኩት ባለው እርምጃ 97 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ጠቁሞ፤ በግጭቱ ሳቢያ የጠፋ የሰው ህይወት አለመኖሩንና ህግ የማስከበሩን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ይህን ተግባር አስመልክቶ ኢዜማ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደገለጸው፤ የአዲስ አበባ ህዝብን መብትና ፍላጎት በጉልበት ለመጨፍለቅ ሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆምና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉት መምህራንና ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ፓርቲው ባወጣው በዚሁ መግለጫው፤ “ባለፈው ዓመት ታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ የተጀመረውና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እየተሰፋፋ የሄደው በሃይልና በግዳጅ የክልል መለያ አርማን የማሰቀልና  የክልል መዝሙርን የማዘመር  ህገ ወጥ ተግባር አላስፈላጊ ውጥረትና ግጭት እንዲቀሰቀስና የትምህርት ሂደቱ እንዲስተጓጎል አድርጓል ብሏል። ሁኔታዎች እየተባባሱ ሊሄዱ እንደሚችሉም የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውንም ጠቁሟል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ት/ቤቶች የሚደረገው ህገ-ወጥ የሆነና የአንድን ክልል መዝሙርና መለያ አርማ ከአገር ሰንደቅ ዓላማና  ብሔራዊ መዝሙር እኩል ወይም በላይ በማድረግ ተማሪዎች ላይ ለመጫን የሚደረገው ሙከራ ግጭትና ሁከትን ወደ ከተማዋ ለማስረግ መታሰቡን አመላካች ነው” ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።
በአገሪቱ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ የአዲስ አበባ አስተዳደርና የፌደራል መንግስት ሃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸው አረዳድ ትክክለኛ አይደለም ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ ባለስልጣናቱ ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር በስልጣን ላይ መቆየት የማይችሉ እንደሚመስል የተደረሰበት ሁኔታ ነው ብሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ት/ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ ወይም በፌደራል መንግስቱ ስር ያሉ መሆናቸውን ያስታወሰው የፓርቲው መግለጫ፤ በከተማ በአስተዳደሩ ወይም በፌደራል መንግስቱ ስር የሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን የኦሮሚያ ክልል መዝሙር ዘምሩ የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ አውለብልቡ ማለት ፍጹም አግባብነት የሌለው ተግባር ነው ብሏል። መጪው ትውልድ አገሩን የበለጠ እንዲወድ ማድረግ በሚገባቸው ት/ቤቶች ከፋፋይ ትርክቶችን ማስተጋባት በሀገር እጣ ፈንታ ላይ መቀለድ ነው ሲልም አክሏል።
ፓርቲው ሰሞኑን በየት/ቤቶቹ በተነሱ ግጭቶች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆች ጥልቅ ሀዘኑን ገልጾ፤ ለእስር የተዳረጉት መምህራንና ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱና የከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት የህዝብ ተመራጮች ለመረጣቸው ህዝብ ድምጽ እንዲሆኑ ጠይቋል። ጉዳዩ ወደ ብጥብጥና አለመረጋጋት ከተሸጋገረ ዋንኛ ተጠያቂዎች መሆናቸውንም  እንዲገነዘቡ አሳስቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በአገሪቱ እየነፈሰ ያለው የሰላም አየር ያላስደሰታቸውና መንግስት ሙስናንና የተደራጀ ሌብነትን ለመከላከል የጀመረው ጠንካራ እንቅስቃሴ ያስደነገጣቸው ኃይሎች፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥን ለመቀስቃስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቁመው፤ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ከሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው ግጭት የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡት የህግ ባለሙያው አቶ ታረቀኝ መስፍን እንደሚናገሩት፤ ሰንደቅ አላማ የአንድ አገር ህዝቦች ተስማምተው ይወክለናል፣ ይገልጸናል ብለው ያስቀመጡት የሀገር ምልክትና መገለጫ ነው። ሰንደቅ አላማ ለዜጎች ክብራቸውን ማመልከቻና ደማቸው ነው። ይህንን ታላቅ ትርጓሜ ያለውን ሰንደቅዓላማ በማሳነስ፤ በክልል መለያ አርማ ለመተካትና ብሄራዊ ባንዲራን አሳንሶ ያንን ለማስበለጥ እየተደረገ ያለው ጥረት የከፋ ህገ-ወጥነት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አዲስ አበባ ከተማ የሁሉም ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ሳለ፤ የአንድ ክልልን መዝሙር ብቻ መዘመርና አርማውን ማውለብለብ ምን አይነት መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ማሰብ ያስፈልጋልያሉት የህግ ባለሙያው ሌሎች ክልሎችም መዝሙሮቻቸው እንዲዘመሩና መለያ አርማቸው እንዲውለበለብ ጥያቄ ቢያቀርቡ፤ በምን አግባብ ምላሽ ሊሰጣቸው ነው ሲሉ ይጠይጥቃሉ፤ “በከተማዋ የአንድ ብሔር መዝሙር ማዘመርና አርማውን ማውለብለብ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልል አካል ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የታለመ ነው” ሲሉም ያክላሉ፡፡
አዲስ አበባ የፌደራል መንግሰቱ መቀመጫና እጅግ የተሰባጠረ ህዝብ ያላት ከተማ በመሆኗ እነዚህ ወገኖች ያሰቡትን ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ አይደለችም ያሉት አቶ ታረቀኝ ፤መስቀልም ሆነ መውለብለብ ያለበት የአገሪቱ ህጋዊና ብሄራዊ ሰንደቅ አላማ ብቻ ሲሆን መዘመር ያለበትንም የሀገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ብቻ ነው አስፈላጊ ከሆነ ይህን ብሔራዊ መዝሙር በአገሪቱ ሁሉም ቋንቋዎች በማስተርጎም እንዲዘመር ማድረግ ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን አሁን እየተኬደበት ባለው መንገድ መቀጠል መዘዙ ከባድ ነው።
የበሽር አልአሳድ ሶሪያ እንዲህ ፍርስርሷ የወጣው ከትምህርት ቤት በተነሳ ግጭት መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ነው ብለዋል- ህግ ባለሙያው።


Read 12372 times