Saturday, 10 December 2022 13:23

የተባባሰው የምስራቅ ወለጋ ዘር-ተኮር ግድያ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

    - ጊዜው፤ የመጠየቅና የመጠየቂያ ነው
                        
          በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምሥራቅ ወለጋ ጊዳ ኪራሙ እና በአዋሳኝ ወረዳዎች በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ ዘር ተኮር ጥቃት ከተጀመረ ቢያንስ ቢያንስ ሃያ ዓመት ይሆነዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰላማዊ ትግል ብሎ ወደ አገር ውስጥ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ችግሩ እየተባባሰ ሄዷል። መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚለውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻ አውጪ ድርጅት” ብሎ የሚጠራው ቡድን፣ ያለፉትን ሶስት ዓመታት ያሳለፈው፣ በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎችን በዘራቸው እየመረጠ ቤት ንብረታቸውን ሲያቃጥል፣ ሲያፈናቅል፣ እህትና ወንድሞቻቸውን እንዲሁም አባትና እናቶቻቸውን ሲገድል፤ ሬሳ እንኳ በክብር እንዳይቀበር ሲያቃጥል ነው።
ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የቆየው ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ፣ ከጋዜጠኛ ገነት አስመላሽ ጋር በ”የኔታ ቲዩብ” ላይ በነበረው ቆይታ፣ በዚህ አካባቢ ጥቃት የሚፈጸመው ኦነግ ሸኔ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ ጭምር እንደሆኑ ጠቁሟል።
በ2013 ዓ.ም በዚያ አካባቢ የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ቦታውን ለቆ እንዲወጣ ተደርጎ፣ በተከታይ ቀናት ኦነግ ሸኔ ወረራ ከፍቶ ብዙ የአማራ ተወላጆችን መግደሉን ያስታወሰው ጋዜጠኛ አባይ፤ “ከክልሉ ፕሬዚዳንት ከአቶ ሽመልስ አብዲሳ እውቅና ውጪ ልዩ ሃይሉን ውጣ ግባ የሚለው ሰው ሊኖር አይችልም” ብሏል።
ሰሞኑን እየተባባሰ የመጣው ጥቃት የተከፈተው፣ ሕዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም በአማራ ላይ የማጥላላት ቅስቀሳ ከተካሄደ በኋላ ህዳር 13 ቀን መሆኑን ያወሳው ጋዜጠኛው፤ ህዳር 14 እና ህዳር 20 በተደጋጋሚ  ጥቃቱ መፈጸሙን ጠቁሟል። አያይዞም የክልሉ መንግስት በአካባቢው የሚኖሩ አማራዎችን አሰልጥኖና አስታጥቆ ከክልሉ ሚሊሽያ ጎን ተሰልፈው ኦነግ ሸኔን እንዲከላከሉ አድርጎ እንደነበር አስታውሶ፣ ትብብሩ በምን ምክንያት እንደፈረሰ ሳይታወቅ ከክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሽያ ጎን ተሰልፈው ኦነግ ሸኔን ሲታገሉ ከነበሩት ውስጥ አንድ ሰው መታሰሩንና መፈታቱን ተናግሯል።
ከዚህ መረጃ በመነሳትማ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ “የአማራ ታጣቂዎች” በሚል የጠቀሰው ማንን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል።
የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ግጭቱ ችግር ላይ የጣላቸውን የአማራና ኦሮሞ ተወላጆች አነጋግሯል። የኦሮሞ ተወላጆች “እያጠቃን ያለው ፋኖ ነው” ሲሉ፣ የአማራ ተወላጆች ደግሞ “የኦሮሞ ልዩ ሃይልና ኦነግ ሸኔ እየተናበቡ ነው” ብለዋል። ይህንን መናበብ የኦነግ ሸኔው ቃል አቀባይ አቶ ኦዳ ተርቢ ለቪኦኤ፤ “የኦሮሞ ልዩ ሃይል ከአራት ኪሎ ትዕዛዝ መጠበቁን ትቶ እርምጃ እየወሰደ ነው፤ እነሱም ስራ እየሰሩ ነው፤ እኛም ስራ እየሰራን ነው” በማለት ገልጾታል።
“ቀደም ሲል አማራዎችንም ሸኔዎችንም አስረዋቸው ነበር። ሸኔዎችን ፈተው ሲለቁ የወረዳው ሰዎች አማራዎችን እንዳሰሯቸው ቀሩ። እንዲያውም ወደ ነቀምት እንወስዳቸዋለን ብለው ተነሱ። ነቀምት ወስዳችሁ ወንድሞቻችንን ልታስገድሉ ነው፤ ካሰራችሁ እዚሁ አስራችሁ ለፍርድ አቅርቧቸው በሚል ህዳር 9 ቀን 2015 ዓ.ም ተቃውሞ ተቀሰቀሰ” ሲሉ ለአሜሪካ ድምጽ አንድ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአማራ ተወላጅ ተናግረዋል። ሌላው የአማራ ተወላጅ ደግሞ “ከዚህ ቀደም ኦነግ ሸኔ 800፣ 900፣ 300 ሰው በአንድ ጊዜ ሲገድልብን ነበር። መንግስት አለ ይደርስልናል ብለን ጠብቀን የደረሰልን የለም። አሁን ቁመን ለመታረድ አንፈልግም ብለን አልሞት ባይ ተጋዳይ ራሳችንን ለመከላከል እየጣርን ነው” ብለዋል።
መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ ደህንነት ማስጠበቅ ባልቻለበት ጊዜ፣ በሚችሉት መጠን እራሳቸውን ሊያጠፋቸው ታጥቆ ከመጣ ቡድን ጥቃት ለመከላከል መነሳታቸው እንዴት ከወንጀለኛ እኩል ተጠያቂ ያስደርጋቸዋል? ብሎ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በጉዳዩ ላይ የአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪል ማህበራት ወዳደረጉት መጠነኛ እንቅስቃሴ እንለፍ። መቼም በመንግስት አይን የሚፈራና የሚከበር የፖለቲካ ድርጅት አገራችን የላትም። እነዚያን ደካማዎቹን ያስተባበራቸውና የሚያስተባብራቸው አንድ አገራዊ ጉዳይ ማግኘትም ከከበደ ቆይቷል። እንዲያም ሆኖ ኢዜማ በራሱ፣ መኢአድ፣ እናት ፓርቲና ኢህአፓ ደግሞ በጋራ ሰሞኑን በምስራቅ ወለጋ በአማራው ላይ የሚካሄደውን ዘር ተኮር ጥቃት አውግዘው፣ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በመግለጫቸው ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቧል- “መንግስት ሆይ፤ የዜጎችን ደህንነት አረጋግጥ” በማለት።
ሸኔ ማለት በኦሮምኛ  አምስት ማለት ነው። ሸኔ የሚለው ስም ስያሜ ደግሞ የመጣው አሁን ይኑር አይኑር የማይታወቀው አምስቱ የኦሮሞ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት ከተስማሙ በኋላ መሆኑ የሚታወስ ነው።  ኦነግ ሸኔ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መዋቅር ውስጥ እንደሚገኝ ከዶክተር አንጋሶ እና ከአቶ ታዬ ደንዳአ በላይ ምስክር መጥራት አይቻልም። አገራችን የቸገራት ይህን ቡድን ከተሸሸገበት የመንግስት ጓዳ ገብቶ የሚያጸዳ ቆራጥ አመራር መሆኑን በድርብ ሰረዝ አስምሮ ማለፍ የግድ ነው።
የኦነግ ሸኔ ደጋፊዎችና የጀርባ አጥንቶቹ፣ ኦነግ ሸኔን “አይዞህ በርታ” ሲሉ ዓልመው የተነሱት፣ መሰረት በሌለው የታሪክ ትንተና ጠላት አድርገው በሳሉት አማራ ላይ ነው፡፡ አሁን ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት ግን በአማራው ላይ ብቻ ሳይሆን ቆመንለታል በሚሉት ኦሮሞ ላይም ነው። ይህ ብቻ ግን አይደለም። ኦሮሚያን የሽብር መሬት በማድረግ ፋብሪካዎች እንዲዳከሙ፣ ሰራተኞች በስጋትና በመሸማቀቅ እንዲኖሩ እያስገደዱ ነው። ለዚህ ደግሞ በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ በተከታታይ የተፈጸመው እገታ ጥሩ ማሳያ ነው። ከሰሞኑ በቡድኑ ታግተው የነበሩ የፋብሪካው ሰራተኞች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸው ተዘግቧል።
ሃሳቤን ሳጠቃልል፤ አበው “ሴት ሲበዛ ጎመን ይጠነዛል” ይላሉ። በአንጻሩ በተሰጠው ስልጣን በሚገባ የማይሰራ፣ ሃላፊነቱን መወጣት የሚያቅተው የመንግስት ሹም ሲበዛ አገር ትወድቃለች ማለት ይቻላል። በዚህ አጋጣሚ  የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳና ካቢኔያቸው “ምን እየሰራን ነው” ብለው እራሳቸውን እንዲጠይቁ አሳስባለሁ። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደራሴዎች ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ ያላቸውን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አስጠርተው በፓርላማ መጠየቅና የመመርመር አሰራር ቢኖር ኖሮ ተጠያቂነት ይሰፍን ነበር ብዬ አስባሁ።
በመጨረሻ በግፍ እየተገደሉ ስላለው የአማራ ተወላጆች ተቆርቁረው ድምጻቸውን በአደባባይ ላሰሙት ለአቶ ታከለ ኡማ፣ ለአቶ አለሙ ስሜ፣ ለአቶ ታዬ ደንዳአ እና ለአቶ ወንድሙ ኢብሳ እንዲሁም ለሌሎች ተቆርቋሪዎች ከፍ ያለ አክብሮት ያለኝ መሆኑን የምገልጸው በትህትና ነው።
ጊዜው፤ የመጠየቅና የመጠየቂያ ጊዜ ነው።

Read 11872 times