Saturday, 10 December 2022 13:25

በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ምን ይላሉ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 - ኳታር በኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ፕሮጀክቶችን እየደገፈች ነው
     - በኳታሩ አሚር ስም የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል ይገነባል

    በኳታር የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑትን አቶ ፈይሰል አሊዬን በኳታር የሚገኘው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ አነጋግሯቸዋል።
          


           “በዲፕሎማሲው ዓለም ከ18 ዓመት በላይ ሰርቻለሁ”
ኳታር ከመምጣቴ በፊት  በዲፕሎማሲው ዓለም ከ18 ዓመታት በላይ ልምድ አለኝ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የገባሁት በ1997 ዓ.ም ነው፡፡  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቆይታዬ፤ በተለያዩ የውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያኖችና ትውልደ ኢትዮጵያኖችን  ከአገራቸው ጋር ለማስተሳሰር፤ በሚኖሩበት አገር መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲከበር ለማድረግ የሚያስችል  አንድ የስራ ክፍል አለ፡፡ የዲያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዲያሬክቶሬት ጀነራል ይባላል። በዚያ ዲፓርትመንት ውስጥ በዲያሬክተርነትና በዲያሬክተር ጀኔራልነት አገልግያለሁ፡፡ ከዚያ በፊት በሚኒስትር ቆንስላነት ደረጃ በዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለአምስት አመታት ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ ከተመለስኩ በኋላ ለአራት አመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ጉዳዮች ዲያሬክተር ሆኜ ነው ያገለገልኩት፡፡ በአጠቃላይ አሁን የምናየው የዲያስፖራ ፖሊሲ ቀረፃ፤ የዲያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂና የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በስፋት ተሳትፈናል፡፡ በውጭ አገር ያሉ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው እጅግ በርካታ ነው፡፡ በትክክል ተቆጥሮ የታወቀ ባይሆንም በግምት ከ3 ሚሊዮን በላይ ይሆናል፡፡ ይህ ቁጥር ከብዙ አገራት የህዝብ ብዛት የላቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ኳታር 400 ሺ ዜጎች ነው ያሏት፡፡ ከበርካታ አገራት ህዝቦች  በቁጥር የሚበልጡ ብቻ ሳይሆን የተለያየ ክህሎት፤ እውቀትና ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በምዕራባውያን አገራትና በመካከለኛው ምስራቅ በተለያየ የስራ ሃላፊነት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። በአፍሪካ አገራትና በጎረቤት አገሮችም የሚኖሩ አሉ። በመላው ዓለም ተበትነው ሲኖሩ በአብዛኛው ህይወት የሰጠቻቸውን እድል የሚጠቀሙም ቢሆን፤ በእውቀታቸው በጉልበታቸውና በሙያ ልምዳቸው የሚሰሩ ቁጥራቸው በርካታ ነው። ይሄን እውቀት፤ ልምድና ሰርተው ያገኙትን ሃብት ለአገራቸው ቢያመጡት፣ ለዜጎቻቸው የተሻለ የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን ያገኙትን ልምድና እውቀት አገራቸውን ለመለወጥ ሊጠቀሙበት ይገባል ወይንም በዚያ ተግባር ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ድርጊታቸውም እነሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እኛ የማልማት አቅማችን ትልቅ ነው፡፡ ይሄንን ወደ ልማት ወደ ሃብት የሚቀይር የፋይናንስ አቅም ከመጣ አገራችንን በፈጠነ ሁኔታ ማሳደግ እንችላለን፡፡ የዲያስፖራው ፖሊሲ አንዱ ትኩረት፤ የዲያስፖራውን አቅም፤ እውቀቱን ጉልበቱንና ልምዱን እንዲሁም በተለያዩ አገራት ያገኘውን ሃብቱን ለአገሪቱ ልማት በማዋል፣ ራሱም ተጠቃሚ በመሆን እንዲሰራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ በተለያዩ የውጭ አገራት ሲኖሩ ጥቅማቸው የሚጎዳበት መብታቸው የሚጣስበት ሁኔታ አለ፡፡ የሚኖሩበትን አገር ህግና ስርዓት ጠብቀው እስከሰሩ ድረስ የእነሱ መብትና ጥቅም መከበር አለበት፡፡ መብትና ጥቅማቸው ተጥሶ ሲገኝ በየአገሩ ያለው ኤምባሲ አንዱ ትልቁ ስራው ይህን ማስከበር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በውጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ጉዳዮች ላይ ስንሰራ፤ ዲያስፖራው እንደ አንድ የልማት አቅም እንዲታይ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የእኔ የስራ ልምድ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ለኢትዮጵያውያን የስራ እድል ያለውን ያህል የሚበደሉበትም ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ዜጎች ያሉትን እድሎች እንዲጠቀሙ፤ ሲበደሉ ደግሞ መብታቸው እንዲከበር የማድረግ  ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በሳውዲ አረቢያ ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያም እስከ 2020 ዓ.ም በኳታር ከሰራሁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፕሮቶኮል ጉዳዮች ዲያሬክተር ጀነራልነት እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ  ሰርቻለሁ፡፡ ከ6 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አዳዲስ አምባሳደራትን ሲሾሙ ነው ወደ ኳታር ተመድቤ የመጣሁት፡፡
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሪፎርም
ተሃድሶው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የውጭ ግንኙነት  ስራችን ዋና አላማ እንደ ሃገር ብሄራዊ ጥቅማችንን ማስከበር ነው፡፡ ብሄራዊ ጥቅም በብዙ መልኩ ይገለፃል። የመጀመርያው ከአገራት ጋር ያለን ግንኙነት በፖለቲካው፤ በማህበራዊ ትስስሩ፤ በህዝብ ለህዝብ፤ በኢኮኖሚው፣ በዲፕሎማሲው… በሁሉም መስክ  ጥቅም መምጣት አለበት፡፡ ግንኙነት  ከፈጠርንበት አገር ጋር ሊኖር የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው የዜጎች መብትና ጥቅም የሚከበርበት ሁኔታ ነው። በሌላ በኩል የአገር ገፅታ ግንባታም አለ፡፡ ሁሉም አገር በዲፕሎማሲው በሰራው ልክ ገፅታው ይገነባል፡፡
ኢትዮጵያ ሃብታም አገር ስላልሆነች ከሚገኘው ጥቅም ጋር ዲፕሎማሲውን ማስተሳሰር ያስፈልጋል። የውጭ ግንኙነታችን ትልቁ ትኩረት ከጎረቤት አገራት ይጀምራል፡፡ ኢትዮጰያ የባህር በር የሌላት አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ይህን የባህር በር አገልግሎት የምናገኘው ከጎረቤቶቻችን  ነው። ስለዚህም ከአገራቱ ጋር የጠበቀ የዲፕሎማሲ ትስስር ያስፈልገናል፡፡ ጎረቤት ላይ የተፈጠረ ችግር አንተም ዘንድ ይደርሳል፡፡ አንተ ጋ የተፈጠረ ችግርም ጎረቤት ዘንድ ይደርሳል፡፡ ስለዚህም ጎረቤት ሆነን እስከተፈጠርን ድረስ በሁሉም መስክ ተባብረን መስራት አለብን፡፡ ጎረቤቶቻችን በሰላም ማደራቸው ሰላም መሆናቸው፤ የእኛ ሰላም መሆን ነው፡፡ በዚያ ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ ግን ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም የምናደርጋቸው ዲፕሎማሲዎች  ከአገራችን ጥቅም አንፃር የተቃኙ መሆን አለባቸው፡፡ እያንዳንዱን አገር የምንቀርበበትን መንገድ በደንብ ማየት መተንተን፤ ለዚያም የሚያስፈልግ የሰው ሃይል አደረጃጀትና በጀት የመመደብ ሁኔታ ወሳኝ ነው፡፡
ዋናውና ትልቁ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አጠቃላይ ሪፎርም በዚህ አቅጣጫ ነው። ተሃድሶውን ስንሰራው ከሆነ አገር ጋር ያለን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በምን ደረጃ  ላይ እንደሚገኝ ያስቀምጣል። ስለዚህም ለጎረቤቶቻችን ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ከየክፍለ አህጉሩ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን አገራትም ዲፕሎማሲያችን ይመለከታል። ከመካከለኛው ምስራቅ አኳያ በተለይ የዜጎቻችንን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የምንሰራው፡፡ ህዝባችን ወደዚህኛው የዓለም ክፍል በህጋዊና  ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እንደሚፈስስ ይታወቃል፡፡ በተደራጀ  ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለበርካታ የአዕምሮ፤ የስነልቦናና የፋይናንስ  ጉዳት የሚዳረጉ ወገኖቻችን ጥቂት አይደሉም። ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከሚሰደዱት ዜጎች መካከል ለአዕምሮ፤ ለስነልቦናና  ለአካል ጉዳት የሚዳረጉ አሉ፡፡ ጥቂቶቹ በስነልቦና ተጎድተውም ቢሆን የፈለጉት ቦታ ይደርሳሉ፡፡  ብዙ መከራ ደርሶባቸው ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎችም አሉ፡፡ ይህን ለማስቆም በመካከለኛው ምስራቅ የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር መስራት ያስፈልጋል፡፡
 በሌላ በኩል፤ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አገራት የኢንቨስትመንት አመንጪዎች ናቸው። ሁሉም ባይሆኑም የየራሳቸው የኢንቨስትመንት አቀራረብና ሃብት አላቸው፡፡ ያንን ሃብት አገራችን ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉት እንሰራለን፡፡ ሶስተኛው ትኩረት የቱሪዝም አመንጪ አገራት መሆናቸውን ከመገንዘብ የሚመጣ ነው፡፡ ቱሪስቶች ከመካከለኛው ምስራቅ ተነስተው ወደ አውሮፓና ሩቅ ኤሽያ እየሄዱ ናቸው፡ ለእነሱ ምቹ የሆነ አመቺ የቱሪዝም መሰረተ ልማት በመገንባትና መስተንግዶዎችን ጨምሮ ሁኔታዎችን ካመቻቸን ካላቸው የቱሪዝም አቅም የተወሰነውን መውሰድ እንችላለን፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትራችን የተገነቡና የተጀመሩ ትልልቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች መኖራቸውን እናውቃለን፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ክልሎችም ለቱሪዝም ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ናቸው፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመካከለኛው ምስራቅ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መዳረሻ እንዲያደርጓት መስራት ያስፈልጋል፡፡
ከኳታር አኳያ በተጨማሪነት የምንሰራበት ጉዳይ አለ፡፡ ኳታር የታዋቂው ዓለም አቀፍ ሚዲያ አልጀዚራ መቀመጫ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ከአልጀዚራ ጋር በሚዲያው ዘርፍ በመተባበርና ሚዲያው በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ተፅእኖ በመጠቀም፤ የአገራችንን መልካም ገፅታ ለመገንባት መስራት ይቻላል፡፡ ለአገራችን የሚዲያ ተቋማት የልምድ ልውውጥና የሙያ ስልጠናዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡ ከላይ የዘረዘርናቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች ለመፈፀም የሚያስችል ሪፎርም ነው፤ በዲፕሎማሲው መስክ የተደረገው፡፡ በተለይ አሁን ያለው አለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ውጭ ግንኙነት ስራችን  ይያያዛል፡፡ያንን የሚመጥን የውስጥ ተቋማዊ ፍተሻነው የተደረገው፡፡
የኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት
የኳታርና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት አሁን ባለው ሁኔታ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። በዓለም አቀፍ መድረኮች እንተባበራለን፡፡ አሁን ያሉት የኳታር አሚር የኢትዮጵያን ሁኔታ ይከታተላሉ፡፡ አባትየው ሼክ አህመድ ቢን ካሊፋም እንደዚያው ናቸው፡፡ የኳታር መንግስት፤ አሚሩ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ በተመሳሳይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ቀጥሎ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በ2019 ላይ ኳታርን ጎብኝተዋል፡፡  በከፍተኛ የአገር መሪዎች ደረጃ የሚደረጉ ጉብኝቶች የሁለቱን አገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ደረጃን ያሳያሉ።  ጉብኝቱ ብቻ ሳይሆን ከጉብኝቱ ቀጥሎ የተሰሩ በርካታ ስራዎችም አሉ፡፡ በሁሉም መስክ ከ10 በላይ ስምምነቶችና ወደ 12 የሚደርሱ የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርመናል- በሚዲያ፤ በትምህርት  በኢኮኖሚ፤ በንግድና፤ በግብርና ዘርፎች፡፡ ይህ ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያቸውን የበለጠ ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት ማሳያ ነው፡፡ በኳታር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለይ ለልጆቻቸው በራሳቸው ካሪኩለም እንዲማሩ እድል ተፈጥሯል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ለኳታሩ አሚር  ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ትልቅ ትምህርት ቤት ተሰጥቶናል፡፡ ይህ ትምህርት ቤት ሙሉ እድሳት ተደርጎለት፤ የውስጥ መሰረተ-ልማት ተሟልቶለት ነው የተሰጠን፡፡ ኳታር ላይ እንደዚህ አይነት እድል ያገኙ አገራት ጥቂት ናቸው። ምናልባትም ከአፍሪካ ሱዳንና እኛ እንደሆንን እገምታለሁ፡፡ ይህ የሚያሳየው  የሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ውጤታማ መሆኑን ነው፡፡ በኳታር እስከ 30ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ናቸው፡፡ ከኳታር መንግስት ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት አድርገናል፡፡ በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያውያን  የስራ እድል እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ይህም የግንኙነታችን ሌላው ውጤት ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ረገድ የፕሮሞሽንና የጥበቃ ስምምነት በኳታር በኩል አልቆ በኛ በኩል ሊረጋገጥ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህም በሁለቱ አገራት ዜጎቻቸው ኢንቨስት የሚያደርጉበትና ለኢንቨስትመንታቸው ጥበቃ የሚያገኙበት ዋስትና እንዲፈጠር፤ ከታክስ ነፃ የሚሆኑበት አሰራር እንዲዘረጋ ነው፡፡ የሁለቱም አገራት ዜጎች ኢንቨስት ካደረጉ ኢትዮጵያ ግብር ከከፈለ በኳታር እንዳይከፍል፤ ኳታር ግብር ከከፈለ በኢትዮጵያ እንዳይከፍል የሚያደርግ ነው። በአንድ ኢንቨስትመንት ሁለት ግብር እንዳይከፍሉ ማለት ነው።  የኢትዮጵያ ብሮድካስት ጋዜጠኞች በአልጀዚራ የሚዲያ ተቋም ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ የፋና እና ሌሎች የክልል ሚዲያ ተቋማትም በተመሳሳይ እድል እንዲጠቀሙ ሆኗል።  በጤናው ዘርፍ ኳታር  በኢትዮጵያ  የአይን ህክምና  ፕሮጀክቶችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየደገፈች ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ የመጀመርያውን ምዕራፍ ጨርሰን ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ነው የምንገኘው፡፡ በሂደት ላይ ያለው ደግሞ ልዩ የኩላሊት ህክምና ሆስፒታልን በኳታሩ አሚር ስም ኢትዮጵያ ላይ መገንባት ነው፡፡ ክእነዚህ በሻገር የምንተባበርበት ብዙ መድረክ አለ፡፡ የሁለትዮሽ ግንኙነት ብቻ አይደለም፡፡ ኳታር በብዙ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ንቁ ተሳታፊ ናት፡፡ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ። የጋራ ጥቅማችንን ለማስከበር እንተባበራለን። በተባበሩት መንግስታት ኒውዮርክ፤ በጄኔቫ፤ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ላይ በእጩዎቻችን በውሳኔዎቻችን እንደጋገፋለን እንተባበራለን፡፡ በብዙ ዓለም አቀፍ መድረኮች የምንተባበርበት በመተማመን ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት አለን፡፡ ኢትዮጵያ በምንም አይነት በቲፎዞ አንድን አገር የምትደግፍበት ወይም የምትጠላበት ታሪክ የላትም፤ ሁሉንም አገራት በእኩል ዓይን ትመለከታለች፡፡ በመከባበር በመተባበር መንፈስ አብሮ መስራት ነው ፖሊሲያችን፡፡ ባለፈው የገልፍ ቀውስ ጊዜ  የተወሰኑ አገራት በኳታር ላይ ማዕቀብ ጥለው ነበር፡፡  የአንድ ወገን ቲፎዞ ሆነው የወጡ ብዙ አገራት ነበሩ። ኢትዮጵያ ያንን አቋም አልያዘችም፤ ገለልተኛ አይደለም የሆነችው፤ ችግራቸው እንዲፈታ ነው። ጥረት ያደረገችው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ እዚህ በመጡ ጊዜ ከኳታሩ አሚር ሼክ ተሚም ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ‹‹እናንተ አንድ ህዝብ ናችሁ፤ አንድ ባህል ያላችሁ አንድ እምነትና ስነልቦና ያላችሁ ናችሁ፤ ህዝባቻችሁ በጋብቻ የተሳሰረ ነው፤ ይህን ህዝብ አትለያዩ ሰላም ፍጠሩ፤ ለሰላም መስዕዋትነት መክፈል ካስፈለገ ክፈሉ፤ ይሄ ህዝብ እንደ ድሮ አብሮ እንዲኖር አድርጉ፡፡ ይህን በማድረግ ታሪክ እንዲያስታውሳችሁ ሥሩ›› ነው ያሏቸው፡፡ የውጭ ግንኙነታችን ዋነኛው መርህ፤ የጋራ መከባበር (mutual respect) ነው። ወገንተኛ ያለመሆን፤ ሁሉን አገር እንደ አገር ማክበር፤ ለሰላምና መረጋጋት አስተዋፅኦ ማድረግ ነው- መርሃችን እንደ አገር በዓለም ላይ በዚህ ደረጃ ነው መታየት  የምንፈልገው፡፡

Read 11197 times