Saturday, 10 December 2022 13:36

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ሰሜን ኮሪያውያን ለልጆቻቸው “ቦምቡ፣ ሽጉጤ” እና መሰል ስሞችን እንዲያወጡላቸው ታዘዙ


       ሰሜን ኮሪያ፣ ወላጆች፣ የልጆቻቸውን ስም የሀገር ፍቅርን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲያስተካክሉ አዘዘች። የሀገር ፍቅርን ያንፀባርቃሉ የተባሉት ስሞች ግን “ቦምብ”፣ “ጠመንጃ” እና መሰል ወታደራዊ ትርጉም ያላቸው ናቸው።
ፒዮንግያንግ ከዚህ ቀደም የመጨረሻ ፊደላቸው ለስለስ ያሉ ስሞችን መጠቀም ፈቅዳ ነበር። በዚህም እንደ ኤሪ (ተወዳጅ ወይም ፍቅር የሚል ትርጉም ያለው) እና ሱ ሚ (የውብዳር ወይም ውበቱ) የሚሉና ፍቅርና ውበትን የሚገልፁ ስሞች በብዛት ጥቅም ላይ ሲውሉ ታይቷል።  አሁን ግን የሀገሪቱ መንግስት እነዚህ ስያሜዎች ጦር ጦር ሊሸቱ ይገባል ብሏል።
የሰሜን ኮሪያን ርዕዮተ አለማዊ አስተሳሰብና ወታደራዊ ዝግጁነት የማያሳዩ ናቸው የተባሉት ስሞችም በአዳዲስ አብዮታዊ ስያሜዎች ይቀየሩ ዘንድ ለወላጆች መመሪያ ተላልፏል ነው የተባለው።
የስም ለውጡ የልጆቹን ብቻ ሳይሆን የወላጆቻቸውን ወይም የአባታቸውንም ያካትታል። ወላጆች የስም ለውጡን የማያደርጉ ከሆነ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ተነግሯል።
በአማራጭነት የቀረቡት ቹንግ ኢ (ሽጉጤ እንደማለት)፣ ፖክ ኢ (ቦምቡ ወይም ቦምቢት)፣ ኡይ ሶንግ (ሳተላይት)፣ ቹንግ ሲም (ታማኝ) እና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ለሬዲዮ ፍሪ ኤስያ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የሀገሪቱ ዜጋ፥ “የሀገሪቱ መንግስት ያሳለፈውን የስም ቅያሬ በርካታ ሰዎች እየተቃወሙት ነው” ብለዋል። በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ሁሉም ወላጅ የልጆቹን ስም ፖለቲካዊ ትርጉም እንዲኖረው እንዲያደርግ የተቀመጠው ቀነ ገደብ አንድ ወር ብቻ ቀርቶታል።
በርካቶችም ይህን የሰሜን ኮሪያ መንግስት ውሳኔ መቃወማቸውን ነው ስማቸው ያልተጠቀሰ የሀገሪቱ ዜጋ የተናገሩት። በደቡብ ኮሪያ ተወዳጅ የሆኑ ስሞችን መጠቀምም በጥብቅ ተከልክሏል፤ የምዕራባዊያንን ባህል እንደሚያንፀባርቁ በማመን።  
ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደምም ከቻይና፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የተወረሱ ናቸው ያለቻቸውን ስሞችን መጠቀም መከልከሏ ይታወሳል።  አሁን ደግሞ ርዕዮተ አለማዊ እሳቤዬን እና ወታደራዊ ዝግጁነቴን በስሞችም ካላየሁት እያለች ነው።
(አል ዐይን)

_________________________________________


                    ድህነቷን እናፍቀዋለሁ!
                      በድሉ ዋቅጅራ


        ኢትዮጵያ ድሀ የነበረች ጊዜ - ያኔ ያለው ለሌለው ያካፍል ነበር፤ የሌለው ጎዳና ወጥቶ፣ ደብር ተጠግቶ ለምኖ በልቶ ያድር ነበር፡፡ የድሀ ልጅ በባዶ እግሩ ትምህርት ቤት እየተመላለሰ ፊደል ይቆጥር ነበር፡፡ በኩራዝ ጭለማ ይረታ ነበር፡፡ . . . . ያኔ ነብስ ካወቅን ጀምሮ የሀገራችን ከድህነት መውጣት ያሳስበን ነበር፡፡ ወጣት ሆነን ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት እድገት በህብረት ዘመትን፣ መሰረተ ትምህርት ዘመትን፤ ሰላም እንድትሆን በብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘመትን፡፡
በወጣትነቴ ጠመንጃ ይዤ ዘብ የቆምኩላት ሀገር፣ ዛሬ በጎልማሳነቴም ሰላም አለማግኘቷ ልቤ ድረስ ይጠዘጥዘኛል፡፡ ድህነቷንም እናፍቀዋለሁ፤ ድሀ ለምኖ የሚበላበትን፣ አባወራ ጥጥ ለቀማ ቆላ የሚወርድበትን፣ ‹‹ግፋ ቢል አዶላ!›› ብሎ ወርቅ ቁፋሮ በቀን ሰራተኝነት የሚሰደድበትን፣ . . . . ድህነቷን እናፍቀዋለሁ፤ ሊያሳስበኝ ግን ልቦናዬ ጊዜ የለውም፡፡
ህይወት ረከሰ፤ ሞት ነገሰ፡፡ ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሰኝ የወፎች ዜማ ሳይሆን የሞት ዜና ነው፡፡ በድህነት ያለፉት እናትና አባቴ ሰው ተሰቅሎ ሲሞት አይተው ለሳምንታት እንቅልፍ አይተኙም ነበር፡፡ የእኔ ዘመን አገዳደል ያኔ አልነበሩም፤ የሀገሬ ልጆች ከዚያ ወዲህ ተጠበው የደረሱባቸው የጭካኔ  ፍሬዎች ናቸው፡፡ ከእንቅልፌ ስነቃ ስለምሰማው ሞት ሳስብ ውዬ ስለእሱው ሳስብ ያሸልበኛል፡፡
በየት በኩል ስለሌላ ነገር ማሰብ ይቻላል! የሀገሬ መልክ ሆኖ የሚያሳስበኝ ሞት እንጂ ድህነት አይደለም፡፡ ስለሞት ባሰብኩ ቁጥርም በልጅነቴ የኖርኩት ሰላማዊ ድህነቷ ይናፍቀኛል። ሞት በሚዘመርባት ሀገሬ ውስጥ እየኖሩ፣ ከድህነት ሊፈውሷት የሚጥሩ ዜጎቿን ልረዳቸው አቅቶኛል፡፡ እኔ ግን እላለሁ! ኢትዮጵያ ከድህነቷ የምትወጣው ማለቂያ በሌለው የዜጎች ሞት ከሆነ፣ ለዘለአለም ድሀ ሆና ትኑርልን፤ እንኑርባት፡፡

_______________________________________
 
                  “ዛሬም ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትፈርስም”


        “--የእያንዳንዳችን ችግር ሊፈታ የሚችለው የሁላችንም ችግር ሲፈታ ነው፣ በተናጠል የራሱን ችግር ብቻ መፍታት የሚችል ማንኛውም ግለሰብና ቡድን ከኢትዮጵያ ችግር በፊት ቀድሞ የሚፈታ የሰፈር ችግር እንደሌለ መገንዘብ አለበት-- በዚህ ቀን የሁላችን ባህል፣ ታሪክ ቅርስ፣ እሴት፣ የኢትዮጵያ ሃብትና የጋራ ኩራት ሆኖ የሚታይበት፣ ሁላችንም ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ መሆናችንና ውበታችን በኢትዮጵያ ጥላ ስር ጎልቶ የሚታይና የምንማርበት ዕለት ነው--፡፡
ሀገር በቤት ይመሰላል፥ ማገሩ፣ ወራጁ፣ ጣራው ተሰናስለው ቤት እንደሚሆኑ ሁሉ ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች እያንዳንዳቸው ሰበዝ ሆነው ሲደመሩ ታላቋንና ውቧን ኢትዮጵያ ያሳያሉ፡፡ -- ስለሆነም በተናጠል ጎልተን ለመታየት ሳይሆን በጋራ ለማበብ ልባችን የቀና አዕምሯችንም የሚያስተውልና የሚያሰላስል ሊሆን ይገባል--፡፡ ትናንትና ያለፈና ያመለጠ ታሪክ ነው፣ ትናንትን ለመማሪያ ብቻ መጠቀም ከቻልን ነጋችን ያማረ ይሆናል፤ ዛሬ የትናንትን ጉዳይ እያነሳን ብንወቅስና ብናወድስ ሰዎቹ የሉምና አይሰሙንም፤ ትርጉምም የለውም--፡፡ እኛ መልካም ነገን ለልጆቻን ለመገንባት ከትናንት መማር አለብን፤ መጪው ትውልድ ከልመና የተላለቀና የተማረ እንዲሆን መገፋፋቱንና መጠላላቱን መተው ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከግራ ከቀኝ ዋልታ የረገጡ እሳቤዎች አሉ፤ ከትናንት እሳቤ ያልተላቀቁ፣ ነገ የሚሰራበትን እያንዳንዱን ብሎኬት የሚያፈርሱ፤ በጋራ መኖር ሳይሆን መገፋፋትን የሚመርጡ፣ በሌሎች አጀንዳ የተገዙ፣ በንጹሃን ደም ፖለቲካ የሚሰሩ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም የሚዲያ ሰዎች አሉ፡፡ --ለእነዚህ ጊዜውን ለሳቱ ወንድሞቻችንን ያለኝ ምክር፣ ዛሬም ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትፈርስም የሚል ነው፡፡ -- የኢትዮጵያ ብልጽግናና ልዕልና የሚመነጨው ከእውነትና ፍቅር ነው፤ በአንጻሩ የተሸናፊ ሃይሎች አጀንዳ ጥላቻ፣ ግድያና መገፋፋት፤ ንጹሃንን ማጎሳቆል ነው።  ከግራም ከቀኝም ያሉ ዋልታ የረገጡ እሳቤዎች  ለኢትዮጵያ ስለማይበጁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአጀንዳዎቹ ጀሮ መስጠት የለበትም፡፡--”
(ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የብሔር ብሔረሰቦችን
ቀን  አስመልክቶ በአዋሳ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡)

____________________________________


                   በዘንድሮው የቢቢሲ ተፅእኖ ፈጣሪ መቶ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ኢትዮጵያውያን


        ቢቢሲ በዓለማችን ላይ ተደማጭነት ያላቸው፣ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆኑና  ድምፃቸውን ለሰብዓዊነት እያዋሉ ያሉ መቶ ሴቶችን በየዓመቱ ይመርጣል። የዘንድሮውን መቶ ሴቶች ዝርዝርንም ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
በዘንድሮው  ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያውያኖቹ የራይድ መሥራች ሳምራዊት ፍቅሩ እንዲሁም በትግራይ ጦርነት ለተጎዱ ሴቶች ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ የምትገኘው ወጋሕታ ገብረዮሐንስ ተካትተውበታል።
የኮምፒውተር ፕሮግራመሯ ሳምራዊት ፍቅሩ፣ምንም እንኳን እስከ 17 ዓመቷ ድረስ ኮምፒውተር ተጠቅማ ባታውቅም፣  ከራይድ የታክሲ መተግበሪያ ጀርባ ካሉት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የሃይብሪድ ዲዛይን መሥራች ነች። ከሥራ አምሽታ ታክሲ ለመያዝ ደኅንነት ስላልተሰማት እንዲሁም፣ ከሾፌሮች ጋር ይህንን ክፈይ በሚል የማያቋርጥ ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት ስላታከታት ይህንን መተግበሪያ እንደፈጠረች ትናገራለች።  ሳምራዊት ሥራውን ስትጀምረው የነበራት መነሻ ካፒታል ከሁለት ሺህ ዶላር ያነሰ ነበር። በአሁኑ ወቅት ኩባንያዋ በርካታ ሴት ሠራተኞችን ቀጥሯል።
በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉት ሴቶች ጥቂት ሲሆኑ፣ ሳምራዊት የመጪውን ጊዜ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ማነሳሳት ትፈልጋለች።
“ሴቶች በባለቤትነት የሚቆጣጠሯቸው ማዕከላት በቁጥር እያደገ ነው። በአሁኑ ወቅት ወጣት ሴቶች የፈጠራ ሀሳቦቻቸው እውን እንዲሆኑ ገንዘብ የሚያገኙበት መንገድ ሊመቻችላቸው ይገባል” ትላለች፡፡
የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኛ የሆነችው ወጋሕታ ገብረዮሐንስ፣ በትግራይ ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቅረፍ ያለመ “ህድሪና” የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሥራች ናት። ህድሪና በጦርነት የተጎዱ ሴቶችንና ህጻናትን ለመርዳት በርካታ ፕሮጀክቶችንም ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል በአገር ውስጥ ተፈናቅለው በየመጠለያዎቹ  ለሚገኙ  የምገባ ፕሮግራምና የከተማ አትክልት ማልማት  ይገኙበታል።
ድርጅቱ በጦርነቱ የተደፈሩ ሴቶችን ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር  በትግራይ በጦርነቱ ወቅት  በተጣለው እገዳ የተነሳ ሕይወታቸውን ለማቆየት ወደ ወሲብ ንግድ ከገቡ ሴቶችም ጋር በተያያዘ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አሉት።

_____________________________________________


                     ለኢትዮጵያ ሀገሬ፦
                       ሙሼ ሰሙ


          የገደለው ባልሽ፤ የሞተው ወንድምሽ
ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፤ ከቤትሽም አልወጣ
ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን በግድ ለመጫን ሲባል አቅመ ደካሞችን፣ ሴቶችንና ሕጻናትን ጨፍጨፎ ቅዠቱኝ ማሳካት የቻለ ሕዝባዊ ትግል የለም። የጠራ ሕዝባዊ አጀንዳ ያለው፣ በበሰለ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ ዙርያ የተሰባሰበና የተደራጀ የነጻነትና የመብት ታጋይ በሌሎች ጭቁን ሕዝቦች ላይ በግፍ እጁን አያነሳም።
በዛው ልክ፣ የትም አካባቢ የሚገኝ ጭቁን ሕዝብ በሌላው ጭቁን ሕዝብ ላይ ግፍ በመስራት ነጻነቴንና መብቴን አረጋግጣለሁ፣ ትግሌንም ከግብ አደርሳለሁ ብሎ አያምንም።
የጠላቴ ጠላት በሚል የጅምላ ፍረጃና ዘርን በማጥራት ሰበብ የሚካሄድ ግፈኝነት፣ ዛሬ የጋራ ጠላቴ የሚለውን ሲጨርስ ነገ ደግሞ በጅምላ የኔ ናቸው ወደ ‘ሚላቸውና የሞራል ከለላና ሽፋን ወደ ሰጡት በመዞር የእናትና የአባት የዘር ግንዳቸውን እያሰሰ፣ የሐይማኖት መሰረታቸውን እየመረመረ፣ የትዳር ጓደኛቸውን ዘር እየመነዘረ፣ እነሱም እንደሚበላቸው ከታሪክ መማር ይገባል።
ለየትኛዎቹም ዓይነት ግፈኞች የነፍስ አድን ትርክት የመቀመር አባዜ የመጨረሻ ውጤቱ፣ እጅን በእጅ የመብላት ያህል የዜሮ ድምር ስሌት ነው።

_________________________________________


                  የእኛ የኢትዮጵያውን ቀን መቼ ነው???


       አገራችን ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትሻሻላለች ብለን ብንጠብቅም ነገሮቿ እየባሱ የልጆቿ ችግሮች እየጠኑ፣ ኑሯችን እየከበደና የዜጎች የመኖር መብት እየተጣሰ፣ ከተማና መንገድ ማስዋብን ግንባታን አጠንክረን እየሰራን በግማሽ እየኖርን አለን!!!
ይሄ በየዓመቱ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሁሌም ይደንቀኛል። ከዚህ በላይ እንደ አገር የምናገኘው እድል መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ ህዝባችንን አንድ ለማድረግ ሁሉም የሚታቀፍበት “የኢትዮጵያ ቀን” ብለን ሰይመን፣ በብሔር ብሔረሰባችን አልባሳት ተውበን፣ (ባህላችንን እያስተዋወቅን) በመንገድ ላይ ስንሄድ፣ ወዴት ልትሄድ ነው ስንባል “የኢትዮጵያን_ቀን” ላከብር ብለን አገራችንን መጥራት፣ አንድነታችንን ማሰብ ስንችል፣ በጎጥ የሚያኖረንን፤ እያጋደለን ያለውን ብሔር ብሔረሰቦች ብለን የመቧደን ቀንን እናከብራለን።
የእኛ ቀን የታለ? እኛ በሰዎች (በዜጎች) እኩልነት የምናምን፣ በአንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከባብረን ተነጋግረን ተስማምተን መኖር የምንፈልገው ኢትዮጵያውያን ቀናችን መቼ ነው? በእኛ አይምሮ በአገር ብሔር ይጠራል እንጂ፤ በብሔር አገር አይጠራም!!!
ኢትዮጵያዬ ቀንሽ መቼ ነው???
(ሰናይ ኢትዮጵያ)

Read 816 times