Print this page
Saturday, 10 December 2022 13:31

ጀምበር ያጣው ኮከብ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(6 votes)

  አጎቴ የአባቴ ወንድም በጣም የሚገርመኝ ሰው ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን ግራ ያጋባኛል፡፡ በደህና ጊዜ እኮ የተማረ ነው፡፡ በጃንሆይ ዘመን የዶክትሬት ዲግሪውን የያዘ…..፡፡ አሁን ታዲያ አንድ ቤት ውስጥ ተቆልፎ ብቻውን ይኖራል፡፡ ሚስት የለው፣ ሰራተኛ የለው፣ ጓደኛ የለው፣ ልጅ የለው….፡፡ ብቻውን ጥናት ክፍሉ ውስጥ ቁጭ ብሎ መጽሐፍ ያነባል፡፡ ስምንት ሺ መጻሕፍት አለው፡፡ እያንዳንዱ መጽሐፍ የትኛው ሼልፍ ላይ እንዳለ ያውቃል፡፡ የትኛው አረፍተ ነገር ደግሞ የትኛው ገጽ ውስጥ፡፡
አንዳንዴ ልጠይቀው እሄዳለሁ፡፡ በሩን ከሱ በስተቀር ማንም አይከፍትም፡፡ በሩ ሲንኳኳ ተቀምጦ ከሚያነብበት ይነሳል፡፡ ቀስ ብሎ፡፡ ማንበብ የያዘውን አንቀጽ ጨርሶ፡፡ መጽሐፉን በደረቱ ይደፋል … የንባብ መነፅሩን አውልቆ፣ የእይታ መነፅሩን ያደርጋል፡፡ ወደ በሩ ያመራል። የበሩ ቋሚ ላይ ሰፊ ክፍተት አለች፡፡ በሷ፣ ያንኳኳውን ሰው ይመለከታል፡፡ ሲመለከት በጥንቃቄ ነው፡፡ የሚያውቀውም ሰው ቢሆን ተጣድፎ አይከፍትም፡፡ ቆሞ ይመለከታል፡፡ ጭንቅላቱን ወደ ግራና ቀኝ እያዟዟረ፡፡ ያጠናል። ውጭ ቆሞ እንዲከፈትለት የሚጠብቀውም ሰው፣ ከውጭ በቆመበት ሆኖ ሲያጠናው ያያል፡፡
“ጋሼ ደህና ዋልክ?” ይላል፡፡
አጎቴ አይመልስም፤ ዝም ብሎ በቀዳዳ ያየዋል፡፡ አስተያየቱ ያሸማቅቃል፡፡ በአስተያየቱ፣ ውስጥን ወደ ውጭ ገልብጦ ወንድን ሴት ያደርጋል፡፡
የማይፈልገው ሰው ከሆነ፣ በደንብ በቀዳዳ ካየው በኋላ፣ በሩን ሳይከፍት፣ መልስም ሳይሰጥ ጥሎት ወደ ውስጥ ይገባል፡፡ የሚወደው ሰው ከሆነ በሩን ይከፍትና “እንዴ ልጅ እንትና!” ብሎ ያስገባዋል፡፡ ሁሉንም የእድሜ ደረጃ “ልጅ” ብሎ ነው የሚናገረው፡፡ “ልጅ” ማዕረግ ሳይሆን የዕድገት መጠን መሆኑ በአነጋገሩ ያስታውቅበታል፡፡ …… ሁሉም ሰው ለሱ “ልጅ” ነው፡፡ እሱም ራሱ ሆነ ሌላ ሰው…. አዋቂ አይደለም፡፡
አንድ ጊዜ እናቱ (የኔ ሴት አያት) ምን እንዳስቀየመችው አይታወቅም፤ በበሬ ቀዳዳ ሲያያት ከቆየ በኋላ ጥሏት ወደ ውስጥ ገብቷል። ዝናብ እየዘነበ ነበር፡፡ አሮጊቷ እየተጣራች መዝጊያውን ስትደበድብ፣ ዝናቡ አባራ፡፡ አጎቴ የሬዲዮኑን ድምፅ፣ ጨምሮ፣ የእናቱን ልመና እና ንግግር ሳይሰማው ቀረ፡፡ ልመና የማይሰማ ሰው፣ ራሱ ለምኖ ሰሚ ያጣ ነው፤ ብዬ ማሰቤ ለራሴ ብቻ ተሰምቶኝ ነበር በወቅቱ፡፡
እኔ ልጠይቀው ስሄድ፣ በበሩ ስንጥቅ ከላይ እስከ  ታች አጣርቶ ጊዜውን  ወስዶ ካየኝ በኋላ፣ በሩን ከፍቶ “ልጅ ነፃነት ተማሪ ቤት ዛሬ የለምንዴ?!” ይለኛል፤ ተከትዬው ወደ ሳሎን ቤት እሄዳለሁ፡፡ ሶፋው ላይ ተቀምጦ ማንበቡን ይቀጥላል፡፡ እኔ አብሬው ትንሽ ከተቀመጥኩ በኋላ፣ ዝም ሲለኝ ተነስቼ፣ ቤቱ ውስጥ መዘዋወር እጀምራለሁ፡፡ መኝታ ቤቱ እገባለሁ፡፡ አልጋው፣ አልጋ ልብሱ፣ አልጋው ስር ያለው ነጠላ ጫማ…. እኔ ተወልጄ ነገራትን መለየት እስከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ አልተለወጡም፡፡
ጥናት ቤት ውስጥ ገብቼ መጻሕፍቶቹን እመለከታለሁ፡፡ “የለውም” የሚባል መጽሐፍ ሊኖር አይችልም፡፡ ከጥናት ጠረጴዛው ጎን ያለው ሼልፍ፣ የሚወዳቸው መጻሕፍት የሚቀመጡበት ነው፡፡ የ”ኔቭል ሹት” ስብስብ ሙሉውን፣ የ”ኤ ጂ ክሮኒን”፣ የግጥም መጻህፍት፣ የሳይንስ ልቦለዶች …. አይዛክ አሲሞቭ፣ የኮምዩኒስት መጻሕፍት… መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ከሞላው መጻህፍት መሀል የለበትም፡፡ ጎድሏል፡፡
ጠረጴዛው ላይ ያሉ ወረቀቶችን እመለከታለሁ፤ ከባድ የሂሳብ ስሌቶችና የተከፈተ የሳይንስ መጽሐፍ አይጠፋም፡፡ ማታ ማታ የሂሳብ ጥያቄዎችን መስራት ይወዳል፡፡ ቀን ቀን መጽሐፍ ነው የሚያነበው፡፡ …. የራሱን ጥያቄ በስሌቶች ውስጥ የሚፈታ ይመስለኛል፡፡
የማስታወሻ ደብተሮቹን እከፍታለሁ፡፡ ሁሌ፣ሦስት የማስታወሻ ደብተሮች አሉት፡፡ አንዱ በቢቢሲ ላይ የሰማውን ዜና አሳጥሮ፣ ቀን ጠቅሶ የሚጽፍበት ነው፡፡ ሁለተኛው፣ ሀሳቦቹን ወይም ከንባብ ያገኘውን አንኳር ሀሳብ በአጭሩ የሚያሰፍርበት ነው፡፡ ሦስተኛው፣ በቀን ውስጥ የተመገበውን ምግብ አይነት፣ ሰዓቱንና ምግቡ የሚወስድበት ሰአት፣ ጣዕሙ እንዴት እንደነበር ገልጾ የሚያስቀምጥበት ነው፡፡
ዓይኔ የትናንቱ ምግብ ላይ አረፈ፡፡ ትናንት ከምሽቱ ሁለት ሰአት ላይ አንድ ስኒ ሻይና አንድ ዳቦ በልቷል፡፡ በአንድ ዳቦ እና ሻይ ነው እየራበው ቁጭ ብሎ የሚያነበው፡፡ የሚበላው አጥቶ ወይንም መብላት አቅቶት እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ በቂ፣ እንዲያውም ትርፍ ገንዘብ ያለው ሰው ነው፡፡ ግን በሆነ ምክንያት፣ ራሱ ላይ ወስኗል፡፡ ልክ እናቱ ላይ አላትም ብሎ እንደወሰነው፡፡ አጎቴ ወሰነ ማለት ወሰነ ነው። ከነገ ወዲያ ነው እመመገበው ካለ፣ ከነገ ወዲያ እስኪመጣ ከመጠበቅ ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ የለም፡፡ …. የማንም ጭንቀት ወደሱ አይደርስም፡፡ እሱ ራሱ ደግሞ መጨነቅ ማቆሙ ጭንቀት አይፈጥርበትም ወይ? የሚለው ጥያቄ ራሱ እኔን ያጨናንቀኛል፡፡
ባለፈው እናቴ በሳህን ምግብ ልካለት በእቃ ቀንሼ አመጣሁለት፡፡
“ዛሬ እንኳን … (እንደ ጃንሆይ ዘመን ሰዎች ነው የሚናገረው) የሻይ እና የዳቦ ቀን ነው” ብሎኝ… ብቻዬን በልቼ የተቀረውን ይዤ ተመለስኩ፡፡
ሌላ ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ስራ ተገኝቶለት ‘አልፈልግም’ ማለቱን ስሰማ “ለምን ስራውን ተውከው?” አልኩት፡፡ በመጽሐፍ ፊቱን ከከለለበት አውርዶ ያየኝ ጀመር፡፡ ልክ በር ላይ በስንጥቁ ቀዳዳ አጣርቶ እንደሚያየው….፡፡
“ሰርቼ በኋላስ?” አለኝ፡፡
ግራ እየገባኝ፤ “ብር ታገኛለህ”
“አግኝቼስ?”
“የምትፈልገውን ነገር ታሟላለህ፤ ትገዛለህ ትሻሻላለህ…”
አሁንም ዝም ብሎ ሲያኝ ቆየ፡፡ የምለውን ነገር እያመዛዘነ መስሎኝ በጉጉት ጠበቅኩት። “ተሻሽዬስ?” አለኝ፡፡ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ ደስተኛ ትሆናለህ ቀጥዬ ብለው፣ “ተደስቼስ?”   “በህይወት ትኖራለህ” ብለው “ኖሬስ?” ማለቱ አይቀርም፡፡
አንዳንዴ በጣም እናደድበታለሁ፡፡ እየተናደድኩበትም ቤቱ ልጠይቀው እሄዳለሁ። በስንጥቋ ቀዳዳ ሲያየኝ ልቤ ይፈራል፡፡ እናቱን ጀርባውን ሰጥቷት እንደሄደው እኔንም ጀርባውን ሰጥቶኝ እንዳይሄድ፡፡ ውድ እናቱ-አያቴ ከሞተች ብዙ ጊዜ ሆናት፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ አብረን በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን መሸ፡፡ እሱም ዝም ብሎ ዐይኑን ጨፍኖ ጣቱን ግንባሩና አገጩ ላይ አስደግፎ እያሰበ ነው፡፡ ወቅቱ ክረምት ውስጥ ነው፡፡ በሩቅ መብረቅ ብልጭ ብሎ ይጠፋል፤ የመብረቁ ድምጽ ዘግይቶ ይሰማል፡፡ ነጎድጓዱ፡፡
ድንገት ዐይኑን ገልጦ፤ “አንተ ፊዚክስ ተምረሀል አይደል?” አለኝ፡፡
“አዎ” አልኩት፡፡
“መብራት ከድምጽ ሲጓዝ እንደሚፈጥን ታውቃለህ?”
“አዎ”
“ድምጽ በሰከንድ ሦስት መቶ ሜትር ይጓዛል… ተመልከት እዛ” ብሎ ወደ ሰማይ ጠቆመኝ፡፡ “አሁን እዛ ወዲያ ማዶ ብልጭታ ሲታይ መቁጠር ጀምር” አለኝ፡፡
የመብረቁ ብልጭታ ሲታይ “አንድ ሁለት” እያልኩ መቁጠር ጀመርኩ፤ ሶስት ላይ ስደርስ የመብረቁ ነጎድጓድ ተሰማ፡፡ “ስለዚህ ይሄ መብረቅ የወደቀው ቅርብ ነው፤ ዘጠኝ መቶ ሜትር ርቀት በስተምዕራብ” አለኝና መልሶ ዓይኑን ጨፈነ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ስለ ህይወትና በአጠቃላይ ስለ ነገራት ያለውን እምነት ለማወቅ እፈልግና ሳልችል በመቅረቴ ግን እበሳጫለሁ፡፡
የጥንት ሬዲዮውን እየጎረጎረ በተሰባበረ ድምጽ የሚተላለፈውን ስርጭት እያዳመጠ በተመሰጠበት ቀስ ብዬ ሾልኬ እሱ ሳያየኝ ጥናት ቤቱ እገባለሁ፡፡
የድሮ ጋዜጦች ላይ የሚያስፈልጋቸውን ዜናዎች በመቀስ ቆራርጦ በክላሰር ውስጥ ካስቀመጠበት ቦታ አንስቼ እያገላበጥኩ እመለከታለሁ፡፡ ….ሌላም አወርዳለሁ…. እመልሳለሁ፡፡ አተራምሳለሁ፡፡ … አንድ ጆሮዬን ወደ ሳሎን ቤቱ እና እሱ እተቀመጠበት ጋር በተጠንቀቅ አስቀምጬ፡፡
አንድ ጊዜ፣ የሆነ ፎቶግራፍ አገኘሁ፤ ውጭ ሆኖ ማስተርሱን እየተማረ በነበረበት ዘመን የተነሳው ነው፡፡ በዛ ዘመን ቄንጠኛ የነበረውን የማልከም ኤክስ አይነት መነፅር አድርጓል፡፡ ፒፓ በአፉ ነክሷል፡፡ የተስፋ እድገቱ ያላቆመበት ዘመኑ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡
ከፎቶግራፉ ጀርባ በጥሩ እጅ ጽሁፍ የተላከ መልዕክት ሰፍሮበታል፡፡ እንደ ፖስት ካርድ፡፡ የተላከው ወደ አገር ቤት እንደሆነና የተላከላት ሴትም ‘ወርቅነሽ’ የተባለች እንደሆነች ጽሁፉ ይገልጻል፡፡ ግን ፎቶውና መልዕክቱ ለተላከላት ሴት አልደረሳትም፡፡ ወይንም የተላከው ፎቶግራፍ ለላኪው አጎቴ ተመላሽ ተደርጓል። አድራሻ ቢስ ሆኖ ወይንም አድራሻው ስለተሳሳተ፡፡ ፎቶው ጀርባ ላይ የሰፈረው ባለ ሁለት መስመር ጥቅስ ብቻ ነው፡፡
“ጀንበር በማጣትህ ስታዝን ክዋክብት ይረግፉብሀል”… የሚል መልዕክት፡፡ መልዕክቱ ፎቶግራፉ ላይ ለሚታየው ሰው የተነጣጠረ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፡፡
ምናልባት ወርቅነሽ የተባለችዋ ሴት ያች እናቴ ያወራችልኝ፣ ለትምህርት ሲሄድ ቀለበት አስሮላት የነበረችው እጮኛው ትሆናለች ብዬ ለራሴ ገመትኩ፡፡ ለትምህርት ሄዶ ሲቆይባት ጓደኛውን አግብታ የጠበቀችዋ ሴት፡፡ …
ትምህርቱን ጨርሶ ወዲያው መመለስ ሲኖርበት፣ አንድ አመት ስራ ሲሰራ ቆየ፡፡ ከአንድ አመቱ ቆይታ በኋላ የተመለሰው ወጣት፣ ከአራት አመት በፊት የሄደው አልነበረም፡፡ የአሁኑ እሱነቱ ያኔ ሲመለስ መፈጠር የጀመረ መሰለኝ፡፡ የድሮውን እሱነቱን እዛው የቆየበት አድማስ ማዶ ጥሎት መጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይሄ የኔ እምነት ነው፡፡
ሁሉንም ሰው “ልጅ” ብሎ መጥራት ጀመረ። ማንበብ እና ራሱን ማግለል መለያው ሆነ፡፡ ያጣትንም ጀንበር መልሶ አላገኛትም፡፡ የረገፉትንም ክዋክብት ከልብሱ  እና ትከሻው ላይ አራግፎ በተቀየሰው መንገድ ላይ ሳይሆን፣ ባልተጀመረው፣ ባልተፈጠረው ብቻውን መጓዝ ቀጠለ፡፡
ብቻውን፡፡


Read 968 times