Saturday, 10 December 2022 13:40

ተበለሻሸ

Written by  ደራሲ- ምህረት አዳልጊዲ ትርጉም- ማንይንገረው ሸንቁጥ
Rate this item
(1 Vote)

 ቤቴ በድንገት ነፍስ የዘራ ይመስላል፡፡ ሳላስበው በጨለማ ውስጥ መገኘቴ ሁሉንም ነገር ባልተለመደ ሁኔታ በትኩረት እንድከታተል ሣያደርገኝ አልቀረም፡፡ ምናልባትም ቀደም ሲል የደረሰኝ የሥልክ ጥሪም ሊሆን ይችላል፡፡
ለወትሮው እቤት ውስጥ የመዋል ልምድ የለኝም፡፡ ዛሬ ግን በዶፍ ዝናብ የተነሳ በቤት መቆየቴ ግድ ነበር፡፡ የደዋዩን ማንነት ባላውቅም፣ ቀኑን ሙሉ አዕምሮዬን ሲበጠብጠኝ ውሏል። ጥሪውንም ለመቀበል ስልኩን አንስቼ “ሄሎ” ስል፣ ደዋዩ ድምፁን እንዳጠፋ ይቆያል፡፡ የሆነ ሰው እቤቴ ውስጥ እንዳለ የሚሰማኝ ስሜት ታክሎበት፣ በቀን ውስጥ ስድስት፣ ከመሸ ደግሞ ሁለት ተመሳሳይ ምላሽ አልባ ጥሪዎችን አስተናግጃለሁ፡፡ የመጨረሻው የስልክ ጥሪ የሚረብሽ ነበር፡፡
“ሄሎ” አልኩ፡፡ ምንም ምላሽ የለም፡፡ መንፈሴ እንደተናወጠ፣ “ስማ ወፈፌው! ምን እያሰብክ እንዲህ እንደምታደርግ አላውቅም፡፡ ይሄን የልጅ ሥራህን ግን ብታቆም ይሻልሃል፡፡ እብድ!” በማለት ጮኽኩበትና ስልኩን ጠረቀምኩት። ለጥቂት ጊዜ ሁሉም ነገር ሠላማዊና የተረጋጋ መሠለ፡፡ እንደውም ከጭቅጭቁ ብዬ የስልኩን ሶኬት ከግድግዳው ላይ ነቅዬው አረፍኩ፡፡
ተመልሼ ወደ መኝታ ክፍሌ ለመሄድ ደረጃውን ሥወጣ፣ መብራቱ ድርግም አለ። አከታትሎም፣ ስልኩ መጮኹን ቀጠለ። በድንጋጤ ድምፅ አውጥቼ ዘለልኩ፡፡ ወዲያው ዘወር ብዬ ወደሚንጫረረው ስልክ ተመለከትኩ፡፡ ሶኬቱን መንቀሌን በጣም እርግጠኛ ነበርኩ፣ አሁንም ግን እየጠራ ነው፡፡ ፍርሃት እንደጨመደደኝ፣ ቀስ ብዬ ወደ ስልኩ ተጠጋሁ፡፡ የመጀመሪያው ሥራዬ ነቅዬዋለሁ ብዬ ያሰብኩትን ሶኬት ማየት ነበር፡፡
“ምን አይነት ነገር ነው?” በማለት ግራ በተጋባ ሁኔታ አንሾካሾክሁ፡፡ ከድንጋጤዬ ሳልወጣ፣ ስልኩ ከተቀመጠበት ጠረጴዛ ሥር አደፈጥኩ። የስልኩን ሶኬት መንቀሌን እርግጠኛ ነበርኩ። ግን ደግሞ እንደተሰካ ነው፡፡ እየሆነ ስላለው ነገር የምጨብጠው አንዳች ሃሳብ አልነበረኝም። ስልኩ ጥሪውን ማሰማት አላቆመም፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማንሳት ወሰንኩ፡፡
“ምን አባክ ትፈልጋለህ?” በማለት አምባረቅሁበት፡፡ ጎርነን ባለ ድምፅ ከት ብሎ ከሳቀ በኋላ፣
“እቤት ውስጥ ነኝ አሽሊ” የሚል ድምፅ አሰማ። ከጀርባዬ የቆመ ያህል ድምፁ አስተጋባብኝ፡፡
በድንጋጤ ስልኩን ወርውሬ፣ እየተርበተበትኩ ተገላምጬ አየሁ፡፡ ፈጠን ብዬ ደረጃውን ወጣሁና የመኝታ ቤቴን በር ጥርቅም አድርጌ ዘጋሁ፡፡ የኮምፒዩተሬ ገፅ ከሚያመነጨው የብርሃን ዘንግ በስተቀር ቤቱን ጨለማ ወርሶታል፡፡ ለጥቂት ጊዜ ኮምፒዩተሬ የለገሰኝ የብርሃን ዘንግ ላይ እንዳፈጠጥኩ፣ በጨለማው ውስጥ አድፍጬ ቆየሁ፡፡
የመኝታ ክፍሌ የተዝረከረከ ነው፡፡ ለወትሮው ምንም አይመስለኝም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ጠላሁት፡፡ እዚህም እዚያም የተዝረከረኩት ልብሶችና ቁሶች የሚያጠሉት ጥላ፣ የሆነ ሰው ያለ እየመሰለኝ ያስበረግጉኛል፡፡ ይሄ ሰውዬ ሆን ብሎ ሊጎዳኝ የመጣ ሰው ቢሆንስ ማን ያውቃል? በዚህ ዘመን እኮ አንዳንድ ሰዎች በሌሎች ላይ የሚያደርሱትን የማይታመን እብደት ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡   
 ቤቱን ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ተጋርቼ ነው የምኖረው፡፡ በቤት ውስጥ ብቻዬን ስውል ዛሬ የመጀመሪያ ቀኔ ነው፡፡ ፍቅረኛዬ ባይኖር እንኳን፣ ሁልጊዜም የሆነ ሰው አይጠፋም፡፡ ጓደኞቼ በሙሉ ስፔን ሄደው ለማከናወን ያቀዱትን የእግር ሽርሽር ፕሮግራም ለምን እምቢ እንዳልኩ አላውቅም፡፡ ፍቅረኛዬ ብራንደን በጉዞው ላይ ለመሳተፍ መስማማቱን እንኳን ከቁብም አልቆጠርኩት፡፡ አየር ማረፊያም ሄጄ ልሸኛቸው ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡
ለምን ቀረሁ በማለት በመፀፀት ላይ ሣለሁ፣ ስልኬ ጠራ፡፡ የእጅ ስልኬ ነበር፡፡ የስልኩ ጥሪ ሞቅ ያለ ሥለነበር ድንጋጤዬን አባሰው፡፡ “ዋይ!” ብዬ ጮኽኩና ወዲያው መለስ አልኩ። በድንገት ደውዬ እርዳታ መጠየቅ እንደምችል አስተዋልኩ፡፡ ማድረግ የሚገባኝ መደወልና ተረጋግቶ መጠበቅ ነው፡፡ ወደ አልጋዬ ተጣድፌ በመሄድ ትራስጌ የተቀመጠውን ስልክ አንስቼ፣
“ሄሎ” አልኩ፡፡ የደዋዩን ማንነት አላስተዋልኩም፡፡
“የሚገርም ነው! በዚህች ጥቂት ጊዜ እንዲህ ትናፍቂያለሽ ብሎ ማን ያስባል?” አለኝ፡፡ ብራንደን ነበር፡፡
“ብራድ” አልኩ፡፡ ብዙ ኪሎ ሜትር እንደሮጠ ሰው እያለከለክሁ፣ ቁና ቁና እተነፍሳለሁ፡፡
“ደህና አይደለሽም እንዴ? እኔ እንኳን የደወልኩት በከባድ ዝናብ የተነሳ በረራችን መቋረጡን ላሳውቅሽ ነው…….”
“ጥሩ ነው፡፡ ይሄውልህ ብራድ ስማኝ” በማለት እየተንሰቀሰቅሁ ወሬውን አቋረጥኩትና
“የሆነ ሰው እቤት ውስጥ አለ፡፡ በጣም ፈርቻለሁ” አልኩት፡፡ በከባድ ሁኔታ እያለከለክሁ ማንሾካሾኬ፣ ምን ያህል እንደተሸበርኩ ያሳብቃል፡፡
“ውይ! ውይ!” ሲል፣ የሱንም ድንጋጤ ከድምፁ መረዳት ቻልኩ፡፡
“ለፖሊስ እደውላለሁ፡፡ እኔም እንደምንም ብዬ እቤት እመጣለሁ፡፡ መዋኘት ቢኖርብኝ እንኳን ግድ አይሰጠኝም፡፡ አሁን አንቺ የት ነሽ?” አለኝ፡፡
“መኝታ ቤቴ ተደብቄ ነው ያለሁት” አልኩና ተንሰቀሰቅሁ፡፡ ወዲያው የመኝታ ቤቴ በር በኃይል ተንኳኳ፡፡ ማንኳኳት ሳይሆን በሩን ለመስበር የተደረገ ሙከራ ይመስላል፡፡
“ብራድ!” ብዬ በኃይል ጮኽኩና ስልኩን ወርውሬ ወደ በሩ አፈጠጥኩ፡፡ ፈጠን ብዬ በመጠጋት የልብስ ማስቀመጫ ሳጥኑን ገፍቼ በሩ ላይ ገደገድኩት፡፡ በሩን በቀላሉ ገንጥሎ እንዳይገባ ያደረግሁት ሙከራ ነበር፡፡ ከበሩ ወደ ኋላ እያፈገፈግሁ ስመለስ፣ ስቅስቅ ብዬ አለቀስሁ፡፡ ምንም አይነት እርዳታ ሳይደርስልኝ ልሞት እንደምችል ማሰቡ ሆድ አስባሰኝ፡፡
“ከዚህ ብትሄድ ይሻልሃል” ጮክ ብዬ ተናገርኩ፡፡
“በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሰዎች ይደርሱልኛል” አልኩ፣ ይፈራ እንደሆን በሚል ተስፋ፡፡
“አሽሊ” አለኝ በድጋሚ፡፡ ድምፁን ለመቀየር የተጠቀመበት አንዳች ዘዴ እንዳለ ያስታውቃል። “ምን ነካሽ አሽሊ?” በማለት አስደንጋጭ የሹፈት ድምፅ አወጣ፡፡ ምን ላደርግ እንዳሰብኩ ማወቁን ገመትኩ፡፡
“ምንድን ነው የምትፈልገው?” ጠየቅሁት። የሆነች ጥቂት ጊዜ ለመግዛት እንጂ፣ ይሄ ነው የሚባል ምላሽ አገኛለሁ ብዬስ አልነበረም፡፡
“ካንቺ በቀር ሌላ ምን ልፈልግ እችላለሁ?” አለኝ ከጥቂት ዝምታ በኋላ፡፡ አልተዋጠልኝም፡፡
“አንተ ማን ነህ? ስሜንስ እንዴት ልታውቅ ቻልክ?” ጠየቅሁት፡፡ ምላሽ ነፈገኝ፡፡
“እባክህ አትጉዳኝ” በማለት እንዲራራልኝ ተማጠንኩት፡፡
“ልጎዳሽ ብፈልግማ እስካሁን ምን ያግደኛል” እውነቱን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቀኑን ሙሉ ከኔው ጋር በአንድ ጣርያ ሥር ቆይቶም ሊሆን ይችላል የሚለው ሃሳብ ራሱ ሰውነቴን ውርር አደረገው። ማን ያውቃል? በዚሁ ክፍልም ውስጥ አብሮኝ ሊሆን ይችላል የሚል ስሜት ተሰማኝ፡፡ ተገላምጬ ወደ ኋላ ለማየት ብሞክርም አይን ቢያወጡ የማይታይበት ሁኔታ ውስጥ መሆኔን ተረዳሁ፡፡ ከኮምፒዩተሬ ገፅ የሚመነጨው የብርሃን ዘንግ ልገሳውን ስላቆመ፣ ቤቱን ሙሉ ለሙሉ ድቅድቅ ጨለማ ወርሶታል፡፡
“ጥቂት የደስታ ጊዜ እንድናሳልፍ ብቻ ነው የምፈልገው” በማለት አከለ፡፡ በዚህ ጊዜ የገዛሁትን ሻማ ለማግኘት ወደ መሳቢያው አመራሁ፡፡
“በሩን ክፈቺው፣ በኔ ይሁንብሽ፣ ብዙ ጊዜ አይፈጅብንም” አለ፡፡
“ሰማኸኝ! ፍቅረኛዬ በአቅራቢያ ነው ያለው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ይደርሳል”
“አውቃለሁ” አለና በሩን በኃይል መምታቱን ቀጠለ፡፡ የልብስ ማስቀመጫ ሳጥኑን በኃይል ወደ በሩ እያስጠጋሁ ጩኸቴን አቀለጥኩት፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁሉም ነገር እረጭ አለ፡፡ በዳበሳ ቦርሳዬን ከፍቼ ሲጋራና መለኮሻውን አወጣሁ፡፡ ላጨስ አልነበረም፣ መለኮሻውን ፈልጌ እንጂ፡፡
ትራስጌ ኮሜዲኖ ላይ ሻማውን አስቀምጬ አበራሁትና የአልጋዬ ጠርዝ ላይ ቁጢጥ እንዳልኩ በፍርሃት ድባብ ውስጥ ሆኜ ወደ በሩ ማፍጠጤን ቀጠልኩ፡፡ እውነት ቀኑን ሙሉ ከኔ ጋር እዚሁ ቤት ውስጥ ነበር? ወይስ እንደዛ ያለው ሲያላግጥብኝ ነው? ለነገሩ የሆነ ሰው እቤት ውስጥ እንዳለ የተሰማኝ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ግን ማንም በቤት ውስጥ እንዳልነበረ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይሄ የተረገመ መብራት! ለነገሩ መብራቱ ምን ያድርግ፤ ይሄ የተረገመ አሮጌ ቤት እንጂ! ዝናብ ትንሽ ጠብ ካለ፣ መብራቱ ድርግም ይላል፡፡ ትንሽ ጠብ ካለ እኮ ነው!
ለአንድ ሰዓት ያህል ንቅንቅ ሳልል በፍፁም ፀጥታ ውስጥ ቆየሁ፡፡ እረጭ እንዳለ ቀስ ብዬ እየተራመድኩ ወደ በሩ ሳመራ፣ የስልኬ ጥሪ በድንጋጤ አዘለለኝ፡፡ ስልኩ መኖሩንም ረስቼ ቆይቻለሁ፡፡ መለስ ብዬ አነሳሁትና፣
“ብራድ” ብዬ አንሾካሾክሁ፡፡
“ፍቅር፣ ቁልፉን ላገኘው አልቻልኩም” ሲለኝ፣ በስተመጨረሻ እቤት እንደደረሰ ገባኝ፡፡
“ቆይ፣ እምም… ምናልባት በዝናብ ተወስዶ ይሆናል” አልኩና የራሴኑ ግምት መልሼ ጠላሁት፡፡ ግን ደግሞ ሊሆን የሚችል ነገር ነው።
“አደራ ተጠንቀቅ! ሰውየው አሁንም እቤት ውስጥ ነው ያለው” ማስጠንቀቂያዬን እያስተላለፍኩ፣ ላየው ጓጉቼ ወደ መስኮቱ አመራሁ፡፡
“ምንም አልሆንም አትስጊ፡፡ አንቺ ብቻ ተረጋግተሽ ባለሽበት ቆይ” ሲለኝ፣
“እያየሁህ አይደለም፡፡ በመስኮቱ አሻግሬ እየተመለከትኩ ነው” አልኩት ጉጉቴን በሚገልፅ ድምፀት፡፡
“ቆይኝ” አለና ጥቂት ደቂቃዎች ቢወስድበትም፣ ከቤቱ ትይዩ ወዳለው ጎዳና ጥግ በመሄድ እንዲታየኝ ሆነ፡፡
“አየሁህ ፍቅር!” አልኩት፡፡ መላው አካሉ በዝናብ ርሷል፡፡
“ቤቱ እረጭ ካለ አንድ ሰዓት አልፎታል፣ ሆኖም ሰውየው እስካሁን እዚሁ እንዳለ ነው የማስበው” አልኩት፡፡
ወደ ቤቱ አሻግሮ እየተመለከተ “ቆይ፣ ቆይ” አለኝና ወደ ቤቱ እየተጠጋ ”የሆነ ሰው ያየሁ መሰለኝ“ በማለት አከለበት፡፡
“ፍቅር፣ በፍፁም አትጠጋ! እንደምትመጣ ያውቃል፡፡ እየጠበቀህ ነው! እባክህ ወደ ቤቱ አትጠጋ! ወደ ኋላ ተመለስ፡፡ ደግሞ ከእይታዬ ተሰውረሃል” ላንቃዬ እስኪሰነጠቅ ድረስ ጮኽኩ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ከእግሩ ኮቴና ከዝናቡ ድምፅ በስተቀር ምንም አልተሰማኝም፡፡ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ የጩኸትና የትግል ግብግብ አይነት ድምፅ ይሰማኝ ጀመር፡፡ የሱው ድምፅ ነው። “ብራድ! ብራድ!” እያልኩ ብጮህም ምላሽ አጣሁ፡፡
በሩ ላይ የተገደገደውን ዕቃ አንስቼ ለመክፈት ሮጬ ተጠጋሁ፡፡ በአዕምሮዬ እየተመላለሰ የሚያስጨንቀኝ፣ የኔ ፍቅር ብራድ ተጠቅቶ መጎዳቱ ብቻ ነው፡፡ ይሄም የሆነው ደግሞ በኔው የተነሳ መሆኑን ልቋቋመው ከበደኝ፡፡ “ብራድ!” በማለት አንዴ አምባርቄ ሳዳምጥ፣ መላው ቤት ፍፁም ፀጥታ እንዳረበበበት አስተዋልኩ። ትንፋሼን ሰበሰብኩና ራሴን አረጋግቼ፣ ደረጃዎቹን ተከትዬ ወደ ታች ወረድኩ፡፡ ወደ ግራ በመታጠፍም ኩሽና ውስጥ ገብቼ መደርደሪያው ላይ ያገኘሁትን ቢላዋ በመያዝ ወደ ዋናው በር አመራሁ፡፡
በሩን ከፍቼ “ብራድ!” በማለት ጮክ ብዬ ተጣራሁ፡፡ ምንም አይነት ሰው በቦታው አይታየኝም፡፡ አንዳችም እንኳን ህያው አካል አይንቀሳቀስም፡፡ ሦስት እርምጃ ወደፊት በመራመድ፣ በውሃ የተጥለቀለቀው በረንዳ ላይ ደረስኩ፡፡ የዝናቡ ውሃ ባዶ እግሬን ውጦት እስከ ቁርጭምጭሚቴ ድረስ አሰመጠኝ፡፡ የቤቱን ተለዋጭ ቁልፍ ሊያገኝ ያልቻለበት ምክንያት ገባኝ፡፡ በፍርሃት እንደተሸበብኩ ወደፊት ሥራመድ፣ ቦርሳው በጎዳናው ውሃ ተወስዶ ሲንሳፈፍ አየሁና ወደዚያው ሮጥኩ፡፡ “ብራድ!” አገኘዋለሁ በሚል ተስፋ ጮኽኩ፡፡
“ሰርፕራ….” የሚል ድምፅ ከበስተኋላዬ በጆሮዬ ሲገባ፣ ለማሰብ አፍታም ጊዜ አልወሰድኩም፡፡ በቅፅበት በእጄ የያዝኩትን ቢላዋ አወናጭፌ ጉሮሮው ላይ ሰካሁት፡፡ ደሙ ተፈናጥሮ ፊቴን ሲያለብሰው፣ እያንቋረረ ነበር። ኬቪን ነው፣ የጄን ፍቅረኛ፡፡ በውስጤ ያለው ስሜት ክውታ ይሁን ፍርሃት አልታወቀኝም። አጥብቄ የያዝኩትን ቢላዋ እንኳን ለማላላት አልቻልኩም፡፡ አሁንም ቁና ቁና እየተነፈስኩ ነው፡፡
“ወይኔ አምላኬ!” የሚል ሌላ ድምፅ ደግሞ ከጀርባዬ ሰማሁ፡፡ እንደገና እጄን አወናጨፍኩና ቢላዋውን ብራድ ጉሮሮ ላይ ሰካሁት፡፡
“ብራድ” በማለት ስሙን በለሆሳስ ተነፈስኩ። ምናልባት ክውታ ይሆናል፣ ልቤ በአየር የተሞላ መስሎ ይሰማኛል- የቀዝቃዛ አየር እስትንፋስ፡፡ ጉሮሮው ላይ የተሰካውን ቢላዋ ያዝ እንዳደረገ፣ ደም እየተፋ፣ ሸርተት ብሎ ከፊት ለፊቴ ሲዘረጋ፣ ደርቄ ቀረሁ፡፡
ጆሮ የሚሰነጥቅ ጩኸት ወደ ህሊናዬ መለሰኝና ዘወር ብዬ ተመለከትኩ፡፡ ጄን እና ኪሻ ክው ብለው እንደደረቁ ቆመዋል፡፡ ጄን ባደረኩት አሰቃቂ ተግባር የተነሳ ራሷን መቆጣጠር ተስኗታል፡፡ በእጃቸው “መልካም ልደት!” የሚል የጨርቅ ሰሌዳ (ባነር) ይዘዋል፡፡ መላ አካላቸው በዝናብ በመራሱ፣ ኪሻ እያለቀሰች ይሁን፣ አይሁን መለየት ተስኖኛል፡፡ ሆኖም ሁለቱም በከፍተኛ ድንጋጤና ክውታ ውስጥ እንደነበሩ ግን አስተውያለሁ፡፡ ከዝናብ ጋር የተቀላቀለው የራሱ ደም ውስጥ እየዋኘ ያለውን የኬቪንን በድን እየተመለከተች፣ ጄን አምርራ በመጮህ እንባዋን አዘራች፡፡ እየተንሰቀሰቀች ወደ በድኑ አካል ስትሄድ፣ ኬቪን ከኋላ እየሮጠች በመድረስ፣ እቅፍ አድርጋ ልታረጋጋት ሞከረች፡፡
“ምንድነው ያደረኩት?” ትንፋሽ ያጠረው ሹክሹክታ አሰማሁ፡፡
“ብራድ” አልኩና ተንበርክኬ ጭንቅላቱን ቀና በማድረግ አቀፍኩት፡፡ “እባክህ ንቃ! እባክህ አይንህን ክፈት!” በማለት ከዝናቡ ድምፅ ጋር በሚወዳደር መልኩ፣ ባለ በሌለ ኃይሌ እየጮኽኩ ተንሰቀሰቅሁ፡፡
“አዝና…… እወድ…..”  ቃላቱን መጨረስ አልቻለም፡፡ ድርቅ ብሎ ቀረ፡፡ አይኑ ፍጥጥ፣ አፉ ከፈት እንዳለ እስከ ወዲያኛው አሸለበ፡፡ የቱንም ያህል ብጮህና ብንሰቀሰቅ እሱንም ሆነ ኬቪንን ወደ ሕይወት ልመልሳቸው አልችልም፡፡ ሆነም ቀረ፣ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ተግባር እንድፈፅም የዳረገኝ ፍርሃትና ድንጋጤ ውስጥ ነበርኩ፡፡ ቢያድለኝ፣ ጓደኞቼ ያዘጋጁልኝ የመልካም ልደት ሰርፕራይዝ ነበር፡፡ የልደቴን ቀን አስመልክተው ድንገት ሊያስደንቁኝና ሊያስደስቱኝ ነበር፡፡  

Read 5315 times