Saturday, 10 December 2022 13:29

“ስትሞት የመጀመሪያዋ ነው?” - (ወግ)

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(5 votes)

   ጓደኛዋ እየተደፈረች ነው፣ አልያም ልትደፈር ነው። ድምጿ በቀጭኑ ይሰማታል ለሊያ። በስስ ግድግዳዋ ታ’ኮ የሚመጣው የሚያቃጭር ድምፅ ይሰቀጥጣል።  በኪነ-ጥበቡ በቆመች ግድግዳ መለያየታቸው አስፈራት። ጓደኛዋ ለተደፈረች እርሷ መደፈሪያዋን ጨበጣ ያዘች።
ከፍ ያለ እሪታ ተሰማ።
በሩን ከፍታ ለመውጣት አልቻለችም። ሰው መሆን ይዟት ልቧ ተንደፋደፈ፤ ሰው መሆን ይዟት ፈራች። የጓደኛዋ ስቃይ ልቧን በላው። ሐበሻ እንደሚለው  ‘እኔን’፣ ለእኔ ያርገው እንዳትል ነገርየው መደፈር ነው፤ እኔ ልደፈርልሽ አይባልማ።
ኧ.ኧፍ..ኧ..ኧፍ...ኧ...ኧፍ ...
ይኼን ድምፅ ሌላ ቦታ ስለምታውቀው ሰውነቷን ወረራት። በእራሷ ላይ የሆነ ያህል ተሰማት።
ሁለት የጭንቅ ሰዓታት አለፉ።
ሁሉ ነገር ፀጥ እረጭ ሲል በሯን በጥንቃቄ ከፈተች። በቀኝ እጇ ዘነዘና ይዛለች። ግራ እጇ እየተንቀጠቀጠ የመዝጊያውን መሸንጎሪያ ወደ ውስጥ ይስባል። ከአካሏ የቀደመ አንገቷ ነው። ሰገግ ብላ የጓደኛዋን ዶርም አየች። ፀጥ ያለ ነው። እግሯን ከጉበኑ ማሳለፍ ግን አልቻለችም።
አንገቷን ወደ ውስጥ ሰበሰበች፤ ላያት ኤሊን መሰለች። በሯን ዳግም ገብባ ታስብ ገባች። እንዴት ተብሎ ነው የሚወጣ? የምወዳት ጓደኛዬ እየተደፈረች እንዴት ዝም እላለሁ? ግን እኮ የእኔ መኼድ ፋይዳ የለውም እሰጥአገባዋ ቀጠለ።
ከእራሷ ስትስማማ ጨከነች። የመጣው ይምጣ የሚል ወኔ አገልድማ ወጣች። በሩን በርግዳ ወደ ጓደኛዋ በር ተጠጋች። በስሱ ሮዚ ...ሮዚ ብላ ጠራቻት። በእንጨት መዝጊያዋ ስንጥቅ የሚታዩ የብርኀን ፍሞች አሉ። የመብራት ያይደለ፤የእሳት መልክ እንጅ።
ድምጿን ከፍ አድርጋ...አንቺ ሮዚ .. ሮዚ...ጓ ..ጓጓ..ጓጓጓ መልስ አልነበረም። የምታደርገው ግራ ገባት። እኩለ ሌሊት ነው። አከራዮችን ለመቀስቀስ ተሳቀቀች። ግራ እና ቀኝ ብትገላምጥ ከአስፈሪ ጨለማ በቀር የብርኀን ዘንግ አጣች። የግቢው መብራት መበላሸቱ ጎዳት። ውስጧ ይታመስ ያዘ ፣ በእጇ የያዘችው ዘነዘና እየወነጠላት ነው።
የሚያጓራ ድምፅ _ከሮዚ ቤት።
ሊያ ደነገጠች። ጉልበቷን ብርክ ያዛት። ደፍራ የሮዚን በር ለመክፈት ተሳቀቀች። ዘነዘናውን ግድግዳ አስደግፋ አስቀመጠች። በደንዳና እጆቿ የሮዚን በር ገፍተር ስታደርግ ተንደርድራ ገባች በሩ ዝግ አልነበረም ለካ።
ድንገት እንግዳ ነገር አየች።
ዶርም ውስጥ የብርኀን ዘር የለም የጀንበር ግባትን የመሰለ ነፀብራቅ እንጅ። ከሮዚ አጠገብ የተቀመጠ ፀጉሩ ሉጫ፣ ዓይነ-ጭንቁር፣ እጁ ሰላላ መላላ ወንድ። በዛ ላይ ፊቱ ጨለማ ከለር። ደነገጠች። የብዙ ታቦት ስም እየጠራች አማተበች፣ ልትወጣም ተንደፋደፈች። ነገር ግን ሁሉም የህልም እሩጫ ሆነባት መሸሽ ሸሻት።
ሮዚ፣ ቀና ብላ ምን አቅለበለበሽ? የራሴን ጉዳይ እራሴ ልጨርስበት ውጭልኝ አለቻት _ይህኔ አመዷ ቡን አለ። ሰውዬው፣ደም የጎረሰ ዓይኑን እያጉረጠረጠ በእጁ ምልክት አሳያት ፈጥና እንድትወጣ። ሃፍረት እየተሰማት ወጥታ ኼደች።
ነጋ።
ወፎች ውብ ቅላፄ ማሰማታቸውን ቀጠሉ። ከአጥቢያ ወደ ወጋገን፣ ከወጋገን ወደ ረፋድ፣ ከረፋድም ወደ ቀትር ...
ሮዚ የሊያን ቤት አንኳኳች። ከፍታላት እንደገባች “ተራው ያንቺ ነው ሂጂ ተደፈሪ” ነበር ያለቻት። የሊያ ከንፈር ተንቀጠቀጠ፣ በልቧ ደነዝ የሚል ስድብ እየነጠረ ነበር። የሆዷን መከፋት ጥርሷ መለሰው። መቼም ጥርስ የማይሸመግለው የለው።
«ለምን እንደጀመርሽ  አንቺው አትጨርሺም?»
«ወንድ ልጅ የሰይጣን አቻ ነው።ሊጠቀምብኝ መጣ ተጠቀምኩበት።»
«ሰይጣንነቱን እያወቅሽ ለምን እኔ ጋር እንዲጋደም ፈቃድሽ ሆነ?»
«ጎረቤት ቅናት አያጣውም፤ ከቀናሽ ብዬ ነው።»
ወደ አመሻሹ ሁለቱ ሴቶች በ ጭረህ እደር ከተማ አውራ ጎዳና ይጓዙ ጀመር።ሊያ ፊት ለፊት ለሚታየው ዑራኤል ቤተ-ክርስቲያን ጎንበስ ቀና ማለት ያዘች። ሮዚ መጓዟን ብቻ ቀጠለች ።
እሮጣ ደረሰችባት።
«ለምን አትሳለሚም ግን ሮዚ?»
«ከመሳለሙ በላይ መጓዝን ስለመረጥኩ»
ፊቷ ላይ አመጽ ይነበባል። ከውስጧ እንቢተኝነት ሲንቀለቀል ይስተዋላል። ሊያ ይችን ሴት ፈራቻት። ፈሪሃ-እግዚአብሔርሽን ማን ሰረቀሽ? እያለች የጓደኝነቷን ተጨነቀችላት።
አንድ ግቢ ተከራይተው መኖር ከጀመሩ ድፍን 4 ዓመት አለፋቸው። በኖሩባቸው ሦሥት ዓመታት ፈጣሪዋን አገልጋይ፣ ለጠራት አቤት _ለላካት ወዴት የምትል ፀባዬ ቀናዋ ሮዚ ነበረች። በያዙት ዓመት ግን ሃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ግርግር፣ ውዥንብር የማያስደስታት ለዓለም ፉዞ (passive) ሆናለች። ነጠላ የለበሰ፣ ኢየሱስ እያለ መንገድ ላይ የሚሰብከው፣ ጀለቢያ ያጠለቀው ሳይቀር ሞኝ እየመሰለ ይታያት ጀምሯል። አጀንዳ ይዞ ስብሰባ የሚያበዛው፣ በሱፍ እና በከረባት ከፈን ውስጥ የገባው ፖለቲከኛም ጅል ሆኗል በእሷ ቤት።
«ሮዚዬ፣ሦሥት ዓመት ስንቀመጥኮ ፀባየተኛ ነበርሽ። አሁን ምን ነው ጽልመት ወረሰሽ?»
«ሊነጋ ሲል ይጨልማል።»
«ከብዙ ወንድ ጋር መጋደሙም አይረባሽም። ቤተ-ክርስቲያን መሳለሙም አይጎዳሽም።»
«ሥራ ለሠሪው፤ እሾህ ለአጣሪው ነው። በሕይወቴ ዘው አትበይ እንደ ዕርጎ ዝንብ።»
ረጅም ፀጥታ በመሐላቸው ነገሰ።
ነጠላ ጫማ፣ ነጭ ካልሲ ፣ጫፉ የሚታይ ጥቁር ታይት፣ በአንድ ጎን የተሰበሰበ ሽቲ፣ ቀለል ያለች ጃኬት፣ ገጣሚዎች የሚያዘወትሯትን ዓይነት እስካርፕ፣ ቁጥርጥር የተሰራ ፀጉር ሮዚ ነች።
ፍላት ጫማ፣ ጅንስ ሱሪ፣ እጀ ቆራጣ ቲ-ሸርት፣ የተለያዩ ጥገናዎች የተካሄዱበት ፊት (በሜካፕ)፣ የፈረስ ጭራ የመሰለ ፀጉር _ሊያ ነች።
መንገዱ እረዘመባቸው። ወዴት? እንደሚሄዱ አያውቁም። እግራቸው ወደ መራቸው ይራመዳሉ፣ አፋቸው ያመጣውን ያወራሉ።
የመጀመሪያው ቅያስ
ሁለት ወንዶች ገጥመው ይደባደባሉ። የጠቡ መነሾ አይታወቅም። የአንደኛው ወንድ ፊት የሳኮ ያህል ይደበደባል። ሌላኛውም በስሱ ይቀመሳል። ጠባቸውን ሁለቱ ሴቶች አዩ። ሊያ ጮኻ ለመገላገል አሰበች። ሮዚ ግን እርምጃዋን ቀጠለች። ብቻዋን ስትፈራ ጊዜ ወደ ጓደኛዋ እሮጠች።
«ሮዚ፣ለምን አንገላግላቸውም? ለምን በዝም አለፍሻቸው?»
«የተጣሉት ወንዶች ናቸው ሸይጣኖች»
ሁለተኛውን ቅያስ ተያያዙት።
ጉልት ቢጤ አገኙ። ቀሚስ የለበሱ እናቶችሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ብርቱካን፣ ሎሚ  እና መሰል ነገሮችን ይዘው ተቀምጠዋል። ከመጋረጃ ጀርባ የሚማር ልጅ ያላቸው፣ የብዙ ቤተሰብ ኃላፊዎችም ናቸው። በእህል አልያም በሳንቲም የሚቀይሩት አትክልት እና ፍራፍሬ ነው ዋስ መከታቸው።
በገበያው መሐል አቋርጠው ሲያልፉ ከአንዷ ምስኪን እናት መቀነት ብር የሚሰርቅ ሌባ አዩ።ሊያ ልትናገር ስትቃትት ሮዚ አልፋ ሄደች። እንደለመደችው እሮጣ ደረሰችባት።
«ሌላው ይቅር ቢያንስ የዚች እናት መሰረቅ አያሳስብሽም?»
«የሚያሳስበኝስ የመጣሁትን መንገድ ተመልሶ መሄዱ።»
መሸ። ወደ ቤታቸው በገቡ ጊዜ በግቢው ግርግር ተፈጠረ። የመንደሩ ሴቶች ዱላቸውን እየነቀነቁ “ሮዚ የሚሏት ወንድ አውል የታለች?” አሳዩን ይችን ወይጦ እያሉ ይፎገሉ ጀመር። ባሎቻቸውን በተራ እንደቀመሰችባቸው ነው የሚጋሩት አመክንዮ። ድንጋይ ያገኘ ድንጋይ፣ ስለት የያዘ ስለት ..ጡንቻማውም ባዶ እጁን ሊወግራት ተሰልፏል።
የግቢው ባለቤት ወደ ቤቱ አንድም ድንጋይ እንዲወረወር አልፈለገም። ቤቴን በድንጋይ ከሚያደባዩት ይቺን ነቀዝ አውጥቼ ብወረውርላቸው ይሻላል ሲል ወሰነ። እንዳለውም “ነይ ውጭ ይፈልጉሻል፤ ቤቴ ጋር አንድ ድንጋይ ቢያርፍ አንላቀቅም “አላት። እሺ ብላ ተነሳች። በሩን እግሯ ሳይሻገር የሰፈርተኛው ጫጫታ አወካት።
«ግን ምን ሆነው ነው?» (ባለቤቱን ነበር የጠየቀችው)
«ባሎቻችንን አማገጠች ነው የሚሉሽ»
«እና ባል ብርቅ ነው እንዴ?»
«እሱን ለእነርሱ መልሺ»
እየሳቀች ወጣች። በተደጋጋሚ ደሟ የፈላው ሰፈርተኛ፣ የመጀመሪያውን ድንጋይ ወደ ሮዚ ወረወረች። የሮዚ ከመሬቱ ጋር መሰፋት ድንጋዩ ከባለግቢው ሚስት ግንባር ላይ እንዲያርፍ አደረገ። ሁሉም ሰፈርተኞች ድንጋጤ ዋጣቸው። ለሮዚ የተባለው፣ለሮዚ የተባለው...እያሉ አጉተመተሙ። የተመታችዋ ውኃ እንኳ ሳትል ሞተች። ሁሉም በእጁ የያዘውን ጥሎ እንደ እንጨት ቆመ።
[የሰው፡ትርምስ። የጫጫታ፡መዓት።
የእንባ ፡ጎርፍ። የዋዌው ፡መብዛት ፡ ኹከት።
ደረት፡የሚደቃው ፣ፊት፡የሚነጨው፡
የአልቃሹ ፡ ብዛት። የጥቁሩ፡ መኪና ና፣
የጥቁር፡ለባሾች፡ ፍጥነት ሁሉም ለሮዚ ግርምትን ጫረባት።]
ፖሊሶችን መሬት ወለደቻቸው። ከየት መጡ ሳይባሉ ተከሰቱ። የተደገነ ጥይት፣ የተኮሳተረ ፊት፣ ተከታታይ ጥያቄ፣ ገዳይዋ ማን ናት? እንዴት መታቻት? ፖሊስ ጣቢያ ኼዳ ትጣራ፣ ወንጀለኞችን ሰብስቧቸው ...ብዙ ንትርክ፣ ገዳይዋን ያዟት...ፖሊስ ጣቢያ!
ሮዚ ከገዳይዋ ጋር መታሰሯ አልደነቃትም። ይልቅ “ማን ነበር ዛሬ ተረኛ መዝናኛዬ?” እያለች ነበር በልቧ።
ፖሊሱ ቀረባት።
«ለመሞቷ ሰበብ እንደሆንሽ ታውቆሻል?» (ፍም የመሰለ ፊት ይዟል)
«አካበዳችሁት! ስትሞት የመጀመሪያዋ ነው እንዴ?»
«አትፈታተኝኝ! እንዳልደፋሽ ...»
«አታካብዳ! ስትገድል የመጀመሪያህ ነው እንዴ?»
በንዴት እየገፈተረ ወደ ምድር-ቤት አስገባት። ገዳይዋም ከእርሷ ጋር ነበረች። የጎሪጥ ተያዩ። ሮዚ ለገዳይዋ ጠላት ነች_ባሏን ስለምታማግጥባት።
«አንቺ ጋለሞታ! በሕይወቴ ስትጫወቺ ኖርሽ። ዛሬ ደግሞ ለአንቺ የወረወርኩት ለሌላ ሆኖ ታሰርኩ...»
«እንዲህ ነበርኮ መወርወር ያለብሽ ብላ ግንባሯን በትንሽ ድንጋይ ጠበሰቻት።»
ገዳይዋ ውኃ ሳትል ሞተች። ሮዚም “ስትሞች የመጀመሪያሽ ነው እንዴ?”እያለች አስከሬኗን ትጠይቅ ያዘች እስር ቤት ውስጥ። ሕይወት ለእሷ ትርጉም አልባ ናት ዓለምም እንዲሁ።

Read 4964 times