Saturday, 17 December 2022 13:15

የነገው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ በትኩረትና በጉጉት ይጠበቃል

Written by  ግሩም ሰይፉ ከዶሃ ኳታር
Rate this item
(2 votes)

     22 ኛው የዓለም ዋንጫ በነገው ዕለት ከ88ሺ በላይ ተመልካች በሚያስተናግደው  በግዙፉ የሉሲየል ስቴዲየም አርጀንቲና ከፈረንሳይ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል፡፡  የሁለቱ ቡድኖች የፍፃሜ ጨዋታ አለም በትኩረትና በጉጉት የሚጠብቀው ሆኗል፡፡ ፈረንሳይ በ2022 የአለም ዋንጫ አዲስ ታሪክ ልታስመዘግብ የምትችለው ሻምፒዮንነቷን በማስጠበቅ ነው፡፡ በዚህ የአለም ዋንጫ  በ2018 ራሽያ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ላይ ያገኘችውን ስኬት መድገም ከቻለች በታሪክ ለ3ኛ ግዜ የሚመዘገብ ክብረ ወሰን ይሆናል። የአለም ዋንጫን በሁለት ተከታታይ ዋንጫዎች ማሸነፍ የቻሉት ሀገራት ሁለት ናቸው -ጣልያን በ1934 እና በ1938 እንዲሁም ብራዚል በ1958 እና በ1962 አከታትለው በማሸነፍ፡፡ በ1986 ለመጨረሻ ጊዜ የአለም ዋንጫን ያሸነፈችው አርጀንቲናም ለ3ኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማሸነፍ ከፍተኛ ፉክክር ታደርጋለች።
ኳታር  ለ22ኛው የአለም ዋንጫ ያደረገችው ዝግጅት በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ሲሆን በተለይ አለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ዛሬና ነገ በሚያካሂደው ጉባኤ፤ የዓለም ዋንጫውን የምን ጊዜውም ምርጥ ብሎ እንደሚገልፀው ይጠበቃል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ራሺያ ያዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ስቴዲዮም በገባ ተመልካች ብዛት፣ በውድድሩ አስደናቂነትና ድምቀት እንዲሁም በነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት “ለደጋፊው የተመቸ ምርጥ የዓለም ዋንጫ” ተብሎ ተገልፆ ነበረ፡፡ ኳታር ይሄንን ሁሉ በዚህ የአለም ዋንጫ ላይ ማሻሻሏን ታላላቅ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ። በስፍራውም ተገኝተን የታዘብነው ይሄንኑ ነው፡፡ በአለም ዋንጫው ስታዲየም የገባው ተመልካች ቁጥር በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ፊፋ ይፋ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቱሪስቶች ብዛት ደሞ ከ700 መቶ ሺ በላይ ነው፡፡
የአርጀንቲና የመጀመርያ ድል
በ1978 እ.ኤ.አ 11ኛውን  የዓለም ዋንጫ የማስተናገድ እድል ያገኘችው አርጀንቲና፤ በ1ኛው የዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ተጫውታ ዋንጫውን በኡራጋይ ከተነጠቀች ከ48 ዓመታት በኋላ ወደ እግር ኳስ ሃያልነቷ ለመመለስ የበቃችበት አጋጣሚ ነበር፡፡  በዓለም ዋንጫው ዋዜማ አርጀንቲናን ያስተዳድር የነበረው መንግስት በመፈንቅለ መንግስት  ተገልብጦ አምባገነኑ መሪ ጄኔራል ቪዴላ ስልጣን መያዛቸው ነበር፡፡ ስለሆነም የዓለም ዋንጫው መሰናዶ በጄኔራል ቪዴላ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰትና በአምባገነናዊ ስርአቱ ከበርካታ አገራት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። የሻምፒዮናነት ክብሩን ለመጀመርያ ጊዜ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ፤ በ11ኛው የዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ጨዋታ የቀረቡት አስተናጋጇ አርጀንቲና እና ሆላንድ  ነበሩ፡፡ የፈረንሳዩ “ለኢክዊፔ” ጋዜጣና ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አስቀድመው ከተደረጉ 10 የዓለም ዋንጫዎች “ምርጡ የፍፃሜ ፍልሚያ” ብለውት ነበር፡፡ አርጀንቲና 3ለ1 በሆነ ውጤት ሆላንድን በማሸነፍ  በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን አሸንፋለች፡፡ በወቅቱ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ሴዛር ሜኖቲ፤ ከቡድናቸው የ17 ዓመቱን ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና መቀነሳቸው ቢያስተቻቸውም፣ ቡድናቸው የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ተከትሎት በነበረው ውበትን የተላበሰ አጨዋወት  አድናቆት አትርፈውበታል። ከተጫዋቾች አምበል የነበረው ዳንኤል ፓሳሬላ እና ማርዮ ኬምፐስ የተባለው አጥቂ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፉ  ነበሩ፡፡ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ማርዮ ኬምፕስ በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ከነበሩ  ተጫዋቾች መካከል  በፕሮፌሽናልነት በስፔን ላሊጋ ለሚወዳደረው ሻሌንሺያ ክለብ በመጫወት ብቸኛው ነበር፡፡
በማራዶና ጀብድ የአርጀንቲና ሁለተኛ ድል
13ኛው የዓለም ዋንጫ በ1986 እ.ኤ.አ በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ዞን የምትገኘው ሜክሲኮ ያስተናገደችው ነበር፡፡  ይህ ዓለም ዋንጫ በመስተንግዶ ማራኪነት፤ በስታዲየሞች በታየው “ሜክሲኳውያን ማዕበል” የተባለው የድጋፍ አሰጣጥና አርጀንቲናዊው ኮከብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ባሳየው የላቀ ችሎታ የማይረሳ  ነው፡፡  በዚህ ዓለም ዋንጫ ላይ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት አርጀንቲናና ምእራብ ጀርመን ነበሩ። ከ115ሺ በላይ ተመልካች ባስተናገደው ታላቁ አዝቴካ ስታዲየም የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ 2ለ2 በሆነ ውጤት እስከ 83ኛው ደቂቃ ቆየ። ማራዶና ለቡድን አጋሩ ጆርጌ ቡርቻጋ አመቻችቶ ባቀበለው ምርጥ ኳስ አማካኝነት  የማሸነፊያ ጎል ተመዘገበችና በአርጀንቲና 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ከ30 ሚሊዮን በላይ አርጀንቲናውያንም በድሉ ፌሽታ መላው አገራቸውን በደስታ አጥለቅልቀው ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ አርጀንቲናን በአምበልነት እየመራ ለታላቁ የዓለም ዋንጫ ድል የበቃው ማራዶና ፤ በአንድ ተጫዋች ጀብደኛነት ውድድርን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየበት ነበር፡፡ አርጀንቲና እስከ ዋንጫው ባደረገችው ግስጋሴ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና አምስት ጎሎችን ከማግባቱም በላይ ለሌሎች  አምስት ግቦች መመዝገብም ምክንያትም ሆኗል፡፡ ማራዶና በምርጥ ችሎታው ዓለምን ማንበርከክ ቢችልም፤ በተለይ በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ላይ በእጁ ያስቆጠራት ግብ ግን የብዙዎችን አድናቆት ወደ ቁጣ ቀይራዋለች፡፡ በወቅቱ ለንባብ የበቃው የፈረንሳዩ ጋዜጣ “ሌኢክዌፔ” ማራዶናን ‹‹ግማሽ መልዓክ ግማሽ ሰይጣን››  ብሎታል፡፡
የዓለም ዋንጫ ድል ሃትሪክ በጀርመን  
14ኛው የዓለም ዋንጫ በ1990 (እኤአ) በጣሊያን አዘጋጅነት የተደረገ ነው፡፡ በውድድሩ ታሪክ  ዝቅተኛ የግብ ብዛት የተመዘገበበት ወቅት ነበር፡፡ አዘጋጇ ጣሊያን በግማሽ ፍፃሜው ከጨዋታ ውጪ የሆነችው በአርጀንቲና ተሸንፋ ነበር፡፡ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ቢሆንም ግን በክለብ ደረጃ የሚጫወትበት ናፖሊ ክለብ ደጋፊዎች ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ ጣልያን ትተው እሱን እንደግፍ በሚል ተወዛግበዋል፡፡
በዚህ ዓለም ዋንጫ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት  በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ አርጀንቲና እና ምዕራብ ጀርመን ነበሩ፡፡ በሮም ኦሎምፒክ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የምእራብ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን  አርጀንቲናን 1ለ0 ረታ። ከአራት ዓመት በፊት በፍፃሜ ጨዋታ በታላቁ አዝቴካ ስታዲየም በማራዶና በተመራው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን የደረሰበትን ሽንፈት በመበቀል ለ3ኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቃ፡፡ በወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበረው ፍራንዝ ቤከን ባወር ደግሞ የዓለም ዋንጫን በተጨዋችነት በ1974 (እኤአ) ላይ ካሸነፈ ከ16 ዓመታት በኋላ በአሰልጣኝነት በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ አስደናቂ ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡

Read 12098 times