Saturday, 17 December 2022 13:17

ከባንዲራና መዝሙር ጋር ተያይዞ በመዲናዋ ት/ቤቶች የተነሳው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(9 votes)

 • የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በተማሪዎቹ ላይ በሚፈጸም የማስገደድ ድርጊት ሳቢያ ለሚደርሰው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂው ከተማ አስተዳደሩ         ነው ብሏል
     • ኢዜማ ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቀ ሲሆን በፍ/ቤት ክስ እንደሚመሰርት አስታውቋል
     • መንግስት ከተማሪዎች ሁከት ጀርባ የፖለቲካ ደባ አለ ብሏል
       
        በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ት/ቤቶች ያለተማሪዎች ፍቃድና ፍላጎት የኦሮሚያ ክልል አርማን ለመስቀልና የክልሉን መዝሙር ለማዘመር በሚደረገው ሙከራ ላይ የተማሪዎችና ወላጆች ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ት/ቤቶች የተማሪዎቹ ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የሚገኘው የወ/ሮ ቀለመወርቅ ት/ቤት ውስጥ ተማሪዎች ድርጊቱን በመቃወም ባስነሱት ረብሻ ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች ታስረዋል።  በርካቶችም በት/ቤቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ በፖሊስ መደብደባቸው ታውቋል።
ከወራት በፊት የተቀሰቀሰውና ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለው ተቃውሞ መነሻው በት/ቤቶቹ ሊደረግ የተሞከረው የኦሮሚያ ክልል አርማን መስቀልና የክልሉን መዝሙር ማስዘመር ተግባር ሲሆን ተማሪዎቹ ይህንኑ ተግባር በጽኑ ተቃውመውታል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ 500 የመንግስት ት/ቤቶች ውስጥ በ403 ት/ቤቶች የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ እንደሆነ የነገሩን አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ መምህር፤ በእነዚህ ት/ቤቶች የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርቱ የሚሰጠው በተማሪዎችና በወላጆቻቸው ፍላጎት ሳይሆን በመንግስት ማስገደድና ጫና ነው ብለዋል።
ጉዳዩ ገና ሲጀመር ስለ ሁኔታው ከተማሪዎችና ከወላጆቻቸው ጋር መወያየትና መግባባት ላይ መደረስ እንዳለበት በርካታ መምህራን ጥያቄ ብናነሳም፣ በክፉ አይን ከመታየትና ጥቁር ነጥብ ከመጣል የዘለለ ነገር አላገኘንም ያሉት መምህሩ፤ መንግስት  እያበላሁ እያጠጣሁ የማስተምራቸው ተማሪዎችን እንደፈለኩ የማድረግ መብት አለኝ የሚል በሚመስል መልኩ ተማሪዎች ያለፍላጎታቸው በማስገደድ ሊጫንባቸው የሚሞከረውን ተግባር ተቃውመው እንቢተኛነታውን እየገለጹ ነው ብለዋል። የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የመንግስት ት/ቤቶች የኦሮሚያ ክልል አርማን ለመስቀልና ክልሉን ብሄራዊ መዝሙር ተማሪዎች እንዲዘምሩ ለማድረግ የሚደረገው ግፊት የህግም ሆነ የሞራል መሰረት የለውም። የሌላ ክልል አርማ በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ ይሰቀል የሚባልበት ምክንያት የሚኖር ከሆነም የከተማ መስተዳድሩ የነዋሪዎችን ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል ብሏል መግለጫው።
በከተማዋ በሚገኙ ት/ቤቶች የኦሮሚያን ክልል አርማ ለማሰቀልና መዝሙሩን ለማዘመር በሚደረገው የማስገደድ ድርጊት ሳቢያ በተማሪዎች ላይ እና በህዝብ ንብረት ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂው የከተማ አስተዳደሩ እንደ ሌላ ውጫዊ አካል አይደለም ያለው የተቋሙ መግለጫ፣ ለችግሩ መንስኤ የሆኑት የከተማ አስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባም አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚተዳደሩ ት/ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመተግበር የሚሞከረው የኦሮሚያን ክልል አርማ የመስቀልና የክልሉን መዝሙር የማስዘመር አስገዳጅ አዋኪ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆምና ህግ እንዲከበር የሚጠይቅ ደብዳቤ ለከተማ መስተዳደሩ የጻፈ ቢሆንም መስተዳደሩ ደብዳቤውን አንቀበልም ማለቱን ተከትሎ ለዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለህግ የበላይነትና ለሀገር ሉአላዊነት፤ ለአገር ሰላምና አንድነት ሲል ጉዳዩን ለፍትህ አካል ለማቅረብ የሚገደድ መሆኑን አስታውቋል።
በከተማዋ አስተዳደር ስር በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ እየተሞከረ ያለውን በግድ የክልል አርማን የመስቀልና መዝሙር የማዘመር ተግባርን በመቃወም የተነሳው ረብሻ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ተቃውሞው በርትቶ ተማሪዎች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው ታውቋል። ከትናንት በስቲያ በወ/ሮ ቀለመወርቅ ት/ቤት በተነሳ ተቃውሞ ሳቢያ ፖሊስ በርካታ ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን በቁጥር በርከት ያሉትም በት/ቤቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ በፖሊስ መደብደባቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማደናቀፍ ጥረት የሚያደርጉ ወገኖችን የማይታገስ መሆኑን አመልክቶ፤ ሁኔታውን ሰበብ በማድረግ ተማሪዎችን ለሁከትና ብጥብጥ ሲቀሰቅሱ ነበር ያላቸውን ተማሪዎች፣ መምህራንና የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ማሰሩን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

Read 16355 times