Monday, 19 December 2022 00:00

አውራ የኑሮ ጉዳዮችን፣… ከጥቃቅን አጃቢ ወጎች ጋር አናምታታ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከበርካታ አማካሪዎችና ከሚኒስትሮች ጋር ወደ ቻይና ጉዞ ጀምረዋል። “Air Force One” የተሰኘው የፕሬዚዳንቱ ልዩ አውሮፕላን ገና ለበረራ መነሳቱ ነው። ብዙም ሳይቆይ፣ “አራቤላ የታለች?” ብለው ጠየቁ።
አውሮፕላኑ፣ ከተሟላ የቢሮ አገልግሎት ጋር፣ ለፕሬዚዳንቱ አንድ መኝታ ቤትና ሰፊ የመታጠቢያ ክፍል የተሰራለት ቢሆንም፣ መቶ ተሳፋሪዎችን አዝናንቶ ይይዛል። ቦይንግ 747 ነው አውሮፕላኑ።
በእርግጥ እንደ ማንኛውም “ቦይንግ” አይደለም። እንደ መንትያ የሚቆጠሩት ሁለት የፕሬዚዳንት አውሮፕላኖች፣ ብዙ የአገልግሎት ቁሳቁስ ተጨምሮላቸዋል። የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ አውታሮችና የጥቃት መከላከያ መሳሪያዎችም ተገጥሞላቸዋል። ለዚያውም ከአውሮፕላኖቹ ዋጋ በሚበልጥ ወጪ።
ነባሮቹን አውሮፕላኖች ለመተካት በቦይንግ እየተሰሩ የሚገኙት ሁለት አዳዲስ የፕሬዚዳንት አውሮፕላኖች፣ 4 ቢሊዮን ዶላር አይበቃቸውም ተብሏል። ዎልስትሪት ጆርናል እንደዘገበውማ፣ ወጪያቸው ከተያዘላቸው የ3.9 ቢሊዮን ዶላር በጀት አልፎ በየጊዜው እጅግ እየናረ ከመምጣቱ የተነሳ፣ ቦይንግ ኩባንያ 2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኪሳራ ይደርስበታል። ማካካሻ ለመጠየቅ እንዳሰበም ተዘግቧል።
it expected to lose $766 million more on the high-profile, years-late project to transform two 747-8 jumbo jets into flying White Houses, bringing its total losses related to the effort to nearly $ 2 billion…
መደበኛው የአውሮፕላኑ ዋጋ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር አይሞላም። የአዲሶቹ አውሮፕላኖች ስሪት እንደ ቀድሞዎቹ ቦይንግ 747 ቢሆንም፣ በቴክኖሎጂና በግዝፈት እጅግ ይበልጣሉ። “ጃምቦ ጄት” በሚል ቅፅል የተጠሩት አለምክንያት አይደለም።
ለነገሩ ከሚፈጁት ገንዘብ በተጨማሪ ስራቸውም ዘግይቷል። በሚቀጥለው ዓመት ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆኑ ነበር የታቀደው። ግን፣ በሦስት ዓመትም ላይደርሱ ይችላሉ ተብሏል። እስከዚያው፣ ነባሮቹ ሁለት አውሮፕላኖች፣ የጡረታ ጊዜያቸው ይራዘማል። ከእድሜ ጋር የጥገናና የእድሳት ወጪያቸው ቀላል አይሆንም - በየዓመቱ ለጥገና ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ።
የፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን ከዋሺንግተን ተነስቶ፣ ለረዥሙ የቻይና ጉዞ፣ መደበኛ የበረራ ከፍታው ላይ ከደረሰ በኋላ፣ ፕሬዚዳንቱ ዞር ዞር ብለው ተመለከቱ።
“አራቤላ የታለች?” አሉ።
“አልመጣችም” ብሎ መለሰ የቅርብ አማካሪያቸው - ጃረድ ኩሽነር። በኦሪጅናሉ ቋንቋ “ያሬድ” ቢሆንም፣ የእንግሊዝኛው አጠራር ነው የተለመደው - ጃረድ። የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ብቻ ሳይሆን፣ የልጃቸው የኢቫንካ ባል ነው። የአራቤላ ደግሞ አባት። አራቤላ፣ የፕሬዚዳንቱ የልጅ ልጅ ናት።
በእርግጥ፣ አሁን የተፈለገችው፣ ፕሬዚዳንቱ የታለች ብለው የጠየቁት፣ የአያትነት ሃላፊነት ሆኖባቸው አይደለም። በአሜሪካና በቻይና መንግስታት ግንኙነት ውስጥ ሕፃኗ አራቤላ የምታበረከተው አስተዋፅኦ፣ ከእድሜዋ በላይ ነው። ለቻይና ጉብኝት እንድትዘጋጅ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ተናግረዋል። የቻይናው ፕሬዚዳንትም ያውቃሉ። እንዲያውም፣ አራቤላ እንድትመጣ ጠይቀዋል። አሁን ግን፣ አውሮፕላኑ ውስጥ የለችም። አልመጣችም።
“ለምን? ምን ሆነች?”
“ጆን ኬሊ ቦታ የለንም ስላለ ቀረች” አለ አማካሪያቸው።
ፕሬዚዳንቱ ገርሟቸው ወደ ጆን ኬሊ ተመለከቱ። የባህር ኃይል ጄነራል የነበሩት ጆን ኬሊ፣ የፕሬዚዳቱ የጽ/ቤት ሃላፊ ናቸው - “ቺፍ ኦፍ ስታፍ”። በፕሬዚዳንቱ ውሎ፣ በዋይት ኃውስም ሆነ በጉዞ ላይ፣ እያንዳንዷን ደቂቃ የሚቆጣጠሩ፣ እያንዳንዷን እርምጃ የሚያስተናብሩ የፕሬዚዳንቱ ዋና ረዳት ናቸው።
የሚወጣና የሚገባ ሰው፣ ያለ ጽ/ቤት ኃላፊው ፈቃድ በአካባቢው ዝር አይልም። የመናገርና የመስማት እድል የሚያገኘው፣ በእሳቸው ፈቃድ ብቻ ነው። አራቤላ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ወደ ቻይና እንዳትሄድ መወሰናቸው ታዲያ ይገርማል? ስራቸው ነው። የዓለማችን ሁለት ኃያል መንግስታት፣ በኢኮኖሚም በፖለቲካም ዓለምን የማቃናትና የማቃወስ አቅም ያላቸው ሁለት አገራት፣ የጦርነትና የሰላም ጉዳይ ላይ አድራጊ ፈጣሪ የሆኑ አገራት ተቀናቃኝነታቸው በተጋጋለበት ዘመን፣… የመሪዎች ጉብኝት፣ የሕፃናት ጨዋታ አይደለም።
እናም፣ የፕሬዚዳንቱ አጋፋሪ፣ አራቤላ ለጉብኝቱ አታስፈልግም ብለው ካሰቡ፣ እንድትቀር ይወስናሉ። የ5 ዓመት ህፃን፣ በአሜሪካና በቻይና ፍጥጫ ላይ ምን ልታደርግ ትገባለች? ጉብኝቱ የቤተሰብ ጥየቃ፣ የእረፍት ወይም የመዝናኛ ጉዞ አይደለም። የፕሬዚዳንቱ ሃሳብ ግን ከዚህ ይለያል። መቅረቷም ገርሟቸዋል።
“ኬሊ፣… ለምንድነው አራቤላ ያልመጣችው?”
“… በቂ ቦታ ስለሌለ ነው ጌታዬ” ብለው መለሱ ኬሊ።
ፕሬዚዳከቱ፣ ግዙፉን አውሮፕላን ከፊት እና ከኋላ ዙሪያውን አዩ። ጥቂት ሰዎች ናቸው ያሉት። በደርዘን በደርዘን ሰው ቢጨመርበት የሚሞላ አይመስልም።
“ይሄ ቦይንግ 747 ነው። እዚህ ቢቀር፣… እኛን ተከትሎ እየበረረ ያለ ድጋፍ ሰጪ ቦይንግ 747 አለ። እሱም ይቅር። ለዚህ ጉዞ የሚያስፈልጉ ሰዎችንና ቁሳቁሶች ለማምጣት 20 ሌሎች አውሮፕላኖች ከኛ ቀድመው ቻይና ገብተዋል። እንዴት ቦታ ይጠፋል?”
ነገሩ አናድዷቸዋል።
“በምድረ ቻይና ከሁላችንም በላይ ዝነኛና ተወዳጅ ለሆነችው ለአራቤላ እንዴት ቦታ ይጠፋል?” አሉ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት።
የቻይው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በቀጥታ በራሳቸው አንደበት አራቤላ ቻይናን እንድትጎበኝ በክብር ግብዣ አቅርበዋል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም እጅግ ተደስተው፣ አራቤላ አብራቸው እንደምትመጣ ቃል ገብተዋል።
የዢ ጀንፒንግ ግብዣ ለይስሙላ አይደለም። ከመደበኛው የጉብኝት አቀባበል በተጨማሪ፣ ለአራቤላ ልዩ የሙዚቃና የጥበብ ትርዒት ዝግጅት በዢ ጀንፒንግ ትዕዛዝ ተሰናድቷል። ለዚያውም ለሌላ ለማንም ሰው ባልተፈቀደ እጅግ በተከበረ ታሪካዊ የቅርስ ቦታ ነው ትርዒቱ የተሰናዳው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በቻይና ጉብኝታቸው አራቤላ አብራቸው እንደምትመጣ ለቻይናው ፕሬዚዳንት ቃል ከገቡ በኋላ፣ “ቦታ የለም” በሚል ምክንያት ከጉዞው መቅረቷ በጣም ቢያናድዳቸው አይገርምም።
ጊዜው ደግሞ ጥሩ አይደለም። አሜሪካና ቻይና የሚያጣላ እንጂ የሚያዋድድ፣ የሚያወዛግብ እንጂ የሚያስማማ ነገር አጥተዋል።
በሁለቱም አገራ የተወደደች አንዲት አራቤላ ብትኖር፣ እንዴት በግዙፉ አውሮፕላን ውስጥ ቦታ ታጣለች?
ለወትሮው ውጥረት የማይርቀው የአሜሪካና የቻይና የመንግስታት ግንኙነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመቀራረቢያ መስመሮቻቸውን እየበጣጠሱ፣ ተቀናቃኝነታቸውን እያከረሩ፣ በጨዋ ደንብ፣ በዲፕሎማሲው ወግ መነጋገር እያቃታቸው ነው።
ወቀሳና አጸፋ፣ ማስጠንቀቂያና ዛቻ፣ ማዕቀብና እገዳ መወራወር አብዝተዋል። አንዱ የሌላውን ዲፕሎማቶች ማባረር፣ ከሌላው አገር በሚመጡ ምርቶች ላይ የቀረጥ ሸክም መጫን፣ ከነጭራሹ ኩባንያዎችንና ንግዳቸውን ማገድ የዘወትር የእንካ ስላንቲ ጨዋታ አድርገውታል።
ከቀድሞው የካፒታሊዝምና የኮሚኒዝም ባላንጣነት በተጨማሪ፣ በነባሩ የሆንክኮንግ ውዝግብና በአደገኛው የታይዋን ጉዳይ ላይ፣ አዳዲስ ቅራኔዎች እየተፈጠሩና እየተካረሩ፣ የመፍትሄ ፍንጮችና ተስፋዎች ጨልመዋል። ጊዜያዊ የማርገቢያ ሰበብና መላ ለመፍጠርም ተቸግረዋል።
ወዳጅነት አይደለም፤ ትብብርም ይቅር። ጭራሽ፣ የአሜሪካና የቻይና ፕሬዚዳንቶች በስልክ ለመነጋገርም ከብዷቸዋል። ተደዋውለው ሄሎ ለመባባል፣ የዲፕሎማሲ ጣጣው ብዙ ነው። የፕሬዚዳንቶቹ ተወካዮችና ባለስልጣናት ለበርካታ ቀናት ይደራደራሉ።
ማን ይደውላል? ማን ስልኩን ያነሳል? በቀጥታ ይገናኛሉ? ወይስ “አንዴ መስመር ላይ ይጠብቁኝ” የሚል አጋፋሪ ይኖራል? የስልክ ንግግራቸው ለስንት ደቂቃ ይቆያል? ማን የትኛውን ጉዳይ ይናገራል? ጨርሶ የማይጠቀስ ጉዳይስ የትኛው ነው?
የአሜሪካና የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናት ከበርካታ ቀናት ድርድር በኋላ ይስማሙ ይሆናል። ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ፣ የግዛት ወሰንና የድንበር ውዝግብ ላይ ለመስማማት ወይም የመቶ ቢሊዮን ዶላሮች ውል ለመፈራረም አይደለም። በስልክ ለጥቂት ደቂቃ ለመነጋገር ነው።
የጉብኝት ጉዞማ፣ ለዚያውም በአንድ ቀን አዳር በማግስቱ ለሚሰነባበቱበት ጉብኝት፣ የወራት ድርድርና ሽኩቻ ይኖራል።
በእርግጥ፣ ችግሮችንና ውዝግቦችን ለመፍታት፣ ካልተቻለም ውጥረቶችን ለማርገብ የታሰበ ንግግርና ጉብኝት፣… ቀድመው በቅጡ ቢያስቡበት አይገርምም። የሰላምና የብልጽግና ጉዳዮች ብዙ ቢዘጋጁበት አይበዛበትም። የሕይወትና የኑሮ ጉዳዮች ናቸውና።
ደግሞም፣ የሚያጣሉ ነገሮችን ለመፍታት ወይም ውጥረቶችን ለማስታገስ የተወጠነ ጉብኝት ወይም ንግግር፣ ለአዳዲስ ቅሬታዎች ሰበብ እንዳያመጣ፣… ቅራኔዎችን በእልህ የሚያባብስ የብልጣብልጥነት መድረክ እንዳይሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው። ቢያንስ ቢያንስ፣ በጨዋ ደንብ ተገናኝቶ መነጋገር አይሻልም?
እንዲህ ሲባል ግን፣ ዋና ዋና ቁምነገሮችን መዘንጋትና ወግ ወጉን ብቻ መተወን ማለት አይደለም።
በጎሪጥና በጥላቻ ስሜት እየተያዩ፣ ለይምሰል ብቻ ፈገግታ ማሳየት፣ የይስሙላ ሰላምታ መለዋወጥ፣ በአንቱታ መናገር፣… ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ውጥረቶችን ለማስወገድ ባይሆን ለጊዜው ለማርገብ የሚያገለግል፣ የመፍትሔ ዘዴዎችን ለመሞከር እድል የሚፈጥር መሆን አለበት-ንግግርና ጉብኝት።
ጥፋትና ጉዳት የሚያስከትሉ፣ እየተጋጋሉ እየተራገቡ የሚመጡ አደገኛ ችግሮች ግን፣ እልህን እየወለዱ፣ የመፍትሔ እድልን እየዘጉ የጥላቻ ሰበቦችን ያባዛሉ።
አንዱ ሌላውን ፊት እንዲነሳ ገጽታው እንደበረዶ ተጋግሮ፣ አንደበቱም ሌላውን የሚጋረፍ ውርጭ የሚተነፍስ፣ ቆፈን የሚያስይዝ ከሆነ፣… ለመነጋገር አለመሞከር ይሻላል።
ከተገናኙና ከተነጋገሩ አይቀር፣… ቢያንስ ቢያንስ፣… ግግሩን በረዶ መስበር፣ ቆፈኑን መግፈፍ ያስፈልጋል። መላ ከተገኘ፣ የሚችል ሰው ከተገኘ ነው ታዲያ።
መላ ሲጠፋ፣ ባለሙያዎቹ ሁሉ ሲጨነቁ ሲጠበቡ ይታያችሁ።
ምን ይሻላል? የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትንሽ ፍንጭ ታያቸው። ይህ የሆነው የአሜሪካ ፕሬዚዳት ወደ ቻይና ለጉብኝት ከመነሳታው በፊት ነው። ገና በመጀመሪያዎቹ የስልጣናቸው ወራት፣… ያኔ የቻይናው ፕሬዚዳንት ለጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚመጡበት ዋዜማ ላይ ነው።
“እንኳን ደህና መጡ” በሚል መንፈስ የተዘጋጀው አቀባበል፣ በወዳጅነት ስሜት የደመቀና የሞቀ መንፈስ እንደማይኖረው ሁሉም እርግጠኛ ሆነዋል። በእርግጥ፣ ወግ ነውና ፕሬዚዳቶቹ ይጨባበጣሉ።ጋዜጠኞች ቪዲዮ ከነድምጹ ይቀርጻሉ። ፎቶ ያነሳሉ። ጥያቄዎችን ያዥጎደጉዳሉ። ከብዙ አቅጣጫ ብዙ አማራጭ ፎቶ ለማንሳት የሚሯሯጡ ባለሙያዎች፣ ፕሬዚዳንቶቹ እንደገና እንዲጨባበጡ ይፈልጋሉ።
እንደገና ተጨባብጠው ፈገግ ይላሉ። ሌላ እጃቸውን አንስተው በሰላምታ መዳፋቸውን ያወዛውዛሉ- በሩቁ ለህዝብ ሰላምታ የሚያሳዩ ይመስል- ህዝብ ባይኖርም። ከዚያም ወደ እንግዳ መቀበያው አዳራሽ ይገባሉ።
ምቹ ሶፋቸው ላይ ሁለቱ ፕሬዚዳቶች ሚስቶቻቸውን ከጎን አድርገው፣ ለሻይ ግብዣ ይቀመጣሉ። ይሄ ሁሉ አቀባበል፣…የሻይ ግብዣውም ጭምር በ15 ደቂቃ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ነው የታሰበው።
እንደ በረዶ የተጋገረ ገጽታና አንደበት ይዘው፣ ለረዥም ጊዜ አብሮ መቀመጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል። የኩርፊያና የቅሬታ ሰሜትን ይበልጥ የሚያጋንን ይሆናል። ቶሎ ሻያቸውን ፉት ብለው፣ ፎቶ ተነስተው፣ የአቀባበል ስርዓቱን በፍጥነት ማጠናቀቅ ቢችሉ ይሻላል። ለዚህ ተብሎ ነው በ15 ደቂቃ እንዲያልቅ የጊዜ ሰሌዳ የተያዘለት። በረዶው መፍትሄ የለውም። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ግን አንድ ሌላ መላ ታያቸው።
የአምስት አመቷ አራቤላ፣… በኩርፊያና በቅሬታ ቆፈን የጨለመውንና የተኮማተረውን የጉብኝት መንፈስ ማፍካት ትችላለች ብለው አሰቡ።
አራቤላ የልጅ ልጃቸው ናት።
የቻይና ቋንቋ ከሞግዚቷ ተምራለች፤ ለምዳለች። ገና ሕጻን ናት። በማታወቃቸው ሰዎች መሃል ገብታ መጫወትና መናገር አልለመደችም። ቢሆንም ግን፣ በቻይና ቋንቋ ለቻይናው ፕሬዚዳንት “እንኳን ደህና መጡ” ብላ የመናገር ድፍረት አታጣም። ከምታውቃቸው ሰዎች ጋር ስትሆንማ፣ እንደልቧ ትናገራለች- በቻይንኛ- ማለትም ማንደሪን በሚሉት የቢሊዮኖች ቋንቋ፡፡
የ5 ዓመቷ ሕጻን፣ የሁለቱ ኃያል መንግስታት መሪዎች በጨዋ ደንብ እንዲነጋሩ የጉብኝቱን መንፈስ መቀየር ትችላለች?
የአሜሪካው ፕሬዚዳት ከባለቤታቸው ጋር፣ የቻይናው ፕሬዚዳንትም ከባለቤታቸው ጎን፣ ለሻይ ግብዣው ተቀምጠዋል። ህፃንዋ አራቤላ በወላጆቿ አደፋፋሪነት መጣች። ድምጿ ጮኽ ብሎ ባይሰማም በለመደችው በቻይንኛ ቋንቋ፣ እንኳን ደህና መጡ ብላ ተናግራለች።
ይህም ብቻ አይደለም። በቻይና አገር በሰፊው የሚታወቁ የብሒል የግጥም ስንኞችን አሳምራ አቀረበች።
የቻይናው ፕሬዚዳንት በጣም ገረማቸው። ከተቀመጡበት ተነሱ- የሕጻኗን ግጥም ለመስማት። የጉብኝታቸው መንፈስ ተቀየረ። በረዶው ተሰበረ። ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች፣ ከአንድ ሰዓት በላይ በጨዋ መንፈስ ተነጋገሩ።
የዓለማችን ችግሮች መፍትሔ አገኙ ማለት ግን አይደለም።
የቻይናና የአሜሪካ ቅራኔን የሚያፍታታ፣ ሁለቱን ፕሬዚዳንቶች የሚያስማማ ሃሳብ ተገኝቷል ማለትም አይደለም።
ዋናው ጉዳይ ደግሞ ይሄ ነው። አራቤላ፣ ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በጨዋ ደንብ እንዲነጋሩ የጨለማውን ድባብ ለመግፈፍ ረድታለች። መፍትሔ ግን አትሆንላቸውም።
ለነገሩ፣ ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች እንደፈለጉት አልሆነም። አራቤላ ለጉብኝት ወደ ቻይና አልመጣችም።
የአሜሪካ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ተበሳጭተዋል።
የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ቅር ብሏቸዋል።
ደግነቱ፣ አራቤላ ተወዳጅ የቻይና ዜማ እየዘፈነች በቪዲዮ ተቀርጻ አዘጋጅታለች። ሁለቱ ፕሬዚዳቶች በዚህ ተጽናንተዋል። ዢ ጂንፒንግ፣ ለታላቅ የእራት ግብዣ ለታደሙት የሃያል አገራት መሪዎችና ባለስልጣናት፣ የአራቤላን ዘፈን በሰፊ ስክሪን እንዲታይ አድርገዋል።
በጣም ተወዳጅ ዘፈን ነው።
እንዲያውም ዝነናዋ የቻይና ዘፋኝ፣… ማለትም የፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ባለቤት፣ ዜማውን በመዝፈን ትታወቃለች።
ታዲያ፣ ዝነኛና ተወዳጅ ዘፋኝ ብቻ  አይደለችም። ባለስልጣንም ናት። የአገሪቱ ትልቅ የኪነ-ጥበብ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መሪም ናት። እና ደግሞ ሜጄር  ጄነራል።
እንግዲህ ዝነኛዋ ድምጻዊና ቀዳማዊቷ እመቤት የዘፈነችውን ነባር ዜማ ነው አራቤላ የዘፈነችው።
ጥያቄ የለውም። የሁለቱን መንግስታት  ጨፍጋጋ የተቀናቃኝነት መንፈስ ፈካ ለማድረግ ችላለች - ህጻኗ አራቤላ። ጥሩ ነው። በጣም እንጂ።
አደገና የኢኮኖሚኛ የፖለቲካ ቅራኔዎችን ለመፍታት በጨዋ ደንብ የመነጋገር እድል ለማመቻቸት እንጂ፣ አደገኛዎቹን ቅራኔዎች ለመጋረድና ለማድበስበስ እስካልሆነ ድረስ መልካም ነው።
ዘና የሚያደርጉና ቀለል ያሉ ተቀጽላ ነገሮች፣ ለኮስታራዎቹ ከባባድ ቁልፍ ጉዳዮች እስካገለገሉ ድረስ፣ በጎ ናቸው።
በዋና ዋናዎቹ ስራዎች ምትክ፣ ቅጥያ ቅርንጫፎችን ሲያወዛውዙ ለመዋል ከሆነ ግን፣ ከንቱ ድካም የሆናል።
ግንዱንና ቅጥያዎችን አናምታታ-በተለይ በኛ አገር የተለመደ ስህተት ስለሆነ።


Read 9262 times