Saturday, 17 December 2022 13:46

‹‹በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ የሚዲያ ጌቶዎች መፈጠር የለባቸውም››

Written by  ግሩም ሰይፉ ከዶሃ ኳታር
Rate this item
(1 Vote)

   ጆቫኒ (“ጂያኒ”) ሜርሎ ጣሊያናዊ የስፖርት ጋዜጠኛ፣ የላ ጋዜታ ዴሎ የስፖርት ፕሬስ አምደኛና የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር AIPS ፕሬዝዳንት ናቸው። ከዓለም  ዋንጫ  ይልቅ  ዘገባውና ትንታኔያቸው በኦሎምፒክ የሚታወቁ ሲሆን 25 ኦሎምፒኮች (12 ኦሎምፒያዶችና 13 የክረምት ኦሎምፒኮች) ላይ ሰርተዋል። በ35 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችም ያገለገሉ ባለሙያ ናቸው፡፡ 76ኛ ዓመታቸውን የያዙት ጂያኒ ሜርሎ፤ የዓለም የስፖርት ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS) ፕሬዝዳንት በመሆን ተቋሙን ሲመሩ 17 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በስፖርት ሪፖርተርነትና ኤዲተርነት ሙያቸው ከ1962 ጀምሮ ለ55 አመታት በስራ ቆይተዋል። በአትሌቲክስ መፅሄት ላይ በ18 ዓመታቸው መስራት የጀመሩት ጂያኒ፤ ከዚያም ላ ጋዜታ ዲሎፖሎ እና ኮሬርዮ ዴሎስፖርት በተባሉ የህትመት ሚዲያዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን፤ በቲቪ ኮሜንታተርነትም ልምድ አላቸው፡፣በታዋቂው የጣሊያን የስፖርት ሚዲያ ላ ጋዜታ ዴሎ ስፖርት ደግሞ ከ1974 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ያለፉትን 48 አመታት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ 2013 (አ.ኤ.አ) ላይ በአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር ምርጥ ጋዜጠኛ ተብለው ልዩ ሽልማት የተቀበሉ ሲሆን በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የፕሬስ ኮሚቴ ቋሚ አባል ሆነው እየሰሩ ናቸው፡፡
ጂያኒ ሜርሎ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS)98 ዓመታትን ያስቆጠረና በዓለም ዙርያ ከ9500 በላይ አባላት ያሉት ነው፡፡ ማህበሩ ተቀማጭነቱን በስዊዘርላንድ ሉዛን ያደረገ ሲሆን በአፍሪካ፤ በኤስያ፤ በአውሮፓና በአሜሪካ በ4 ዞኖች ቅርንጫፎች አሉት። ሲሆን ከ160 በላይ የስፖርት ሚዲያ ማህበራትንም የሚያሰባስብ ነው፡፡  
በኳታር 22ኛው የዓለም ዋንጫ ቆይታዬ ካገኘኋቸው ታላላቅ የስፖርት ባለሙያዎች መካከል ጂያኒ ሜርሎ አንዱ ሲሆኑ በዓለም ዋንጫው የሚዲያ ማዕከል ውስጥ ልዩ ቃለመጠይቅ አድርጌላቸዋለሁ፡፡ ጣሊያን ከዓለም ዋንጫ ስለመቅረቷ፤ ስለኳታር የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ፤ የስፖርት ጋዜጠኝነት ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገራት ስለሚገኝበት ደረጃ፤ ስለ የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር... እና ሌሎችም ጉዳዮችን አውግተውኛል።
ስለ ጣሊያን ከዓለም ዋንጫ መጥፋት
በሁለት የዓለም ዋንጫዎች በተከታታይ አልተሳተፍንም፡፡ ሁላችንም በጣሊያን ይህ አሳዝኖናል፡፡  የሆነ ችግር ያለ ይመስላል። የአውሮፓ ሻምፒዮን ነበርን፤ ማጣርያውን ለማለፍ አልቻልንም፡፡ በጣም የሚያስገርም ነው። በቀጣይ በሚካሄደው 23ኛው የዓለም ዋንጫ እንጠበቅ፡፡ ተሳታፊ ቡድኖች 48 በመሆናቸው ተመልሰን የመካፈል እድል ይኖረናል፡፡ በኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ ጣሊያኖች መኖራቸውን አዘጋጆቹ ይፈልጉ ነበር፡፡ ለምን ቢባል የአለም ዋንጫን ለመታደም  ከጣሊያን  የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥራቸው የበዛ በመሆኑ ነበር፡፡ ከየትኛውም የአውሮፓ ክፍል በተሻለ ጣሊያን የእግር ኳስ ደጋፊ አለ፡፡
ስለ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ
የዓለም ዋንጫው በአረቡ ዓለም መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ታላቁን የስፖርት መድረክ በአንድ ከተማ ውስጥ ማዘጋጀት ተችሏል፡፡ ይህን ለማሳካት የበቃችው ደግሞ  ኳታር ናት፡፡  የዓለም ዋንጫው በአንድ ከተማ የሚካሄድበትን የቆየ ባህል መልሶ ያስገኘ እድል ነው፡፡ በቀጣይ የዓለም ዋንጫ በሶስት የተለያዩ አገራት ማለትም አሜሪካ፤ ካናዳና ሜክሲኮ የሚዘጋጅ ነው፡፡ በርካታ ረጃጅም ጉዞዎች ማድረግ ይጠይቃል። በየከተሞቹ የሰዓት ልዩነት ይኖራል፡፡ በኳታር የዓለም ዋንጫው ሲካሄድ በ48 ደቂቃዎች ልዩነት ስታዲየሞቹ መገኘታቸው ልዩ እድልን ፈጥሯል። በነገራችን ላይ ለዓለም ዋንጫው በዶሃ ከተማ የተዘጋጀው የሚዲያ ማዕከል በጣም ግዙፉና ዘመናዊ ነው፡፡ የኳታር መንግስት ማዕከሉን ለዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ቋሚ መናኸርያ ቢያደርገው እመኛለሁ፡፡ በአጠቃላይ ኳታር የዓለም ዋንጫ መስተንግዶዋ ላይ ለወደፊት የማይደገሙ መሰረተልማቶችን መጠቀሟ  የሚደነቅ ነው፡፡
እኔ ከዓለም ዋንጫ ይልቅ ብዙ ትዝታዎች ያሉኝ በኦሎምፒክ ነው፡፡ 25 ኦሎምፒያዶችን ማለትም ዋናውን ኦሎምፒክና የክረምት ኦሎምፒክን ተሳትፌያለሁ፡፡ በ2006 (እ.ኤ.አ) ጀርመን ባዘጋጀችው 18ኛው የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታን በልዩ መንገድ አስታውሳለሁ፡፡ በርግጥ የዓለም ዋንጫን ማዘጋጀት ከኦሎምፒክ አንፃር ስትመለከተው እጅግ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ የኦሎምፒክ ዝግጅት በጣም የተወሳሰበና ከፍተኛ አደረጃጀትና መሰረተልማቶችን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከ24 በላይ የስፖርት አይነቶች በልዩ እና ውስብስብ የስፖርት መሰረተልማቶች ማካሄድን ይጠይቃል፡፡
ስለ ዓለም ጋዜጠኞች እኩልነት
በዓለም ዋንጫ እና በተለያዩ ግዙፍ የስፖርት መድረኮች ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገራት ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ በሶስተኛው ዓለም የሚገኙ የስፖርት ጋዜጠኞች  በዓለም ዋንጫ አይነት የስፖርት መድረኮች ወጭያቸውን በመሸፈን ዘገባ ለመስራት እንደሚቸገሩ እናውቃለን። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች ምክክር ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ደረጃ በደረጃ ይህን ለማሻሻል እንደሚቻል ሁሉም ያምንበታል፡፡ በሶስተኛው ዓለም የሚሰሩ ጋዜጠኞች የጉዞና የማረፊያ ወጭያቸውን የሚሸፍን ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል። ይህም ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮችን በእኩልነት ለመዘገብ ያስችላቸዋል። ለዚህም በዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርም እየሰራንበት ነው፡፡ ይህ አይነቱ ድጋፍ የጋዜጠኛውን የስራ ነፃነትና ፈቃድ በገንዘብ መግዛት አይደለም፡፡ ልክ እንዳደጉ አገራት ሚዲያዎች በሚሰሩበት ደረጃ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡና የተሻለ እንዲሰሩ ለማስቻል እንደሆነ መታሰብ አለበት፡፡ በጣም ጥሩ የሚሰሩ ጋዜጠኞች  በአፍሪካም ከሌላውም የዓለም ክፍል ይገኛሉ፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ብቻ አይደለም ያሉት፡፡ እኩል እድል ባለመፈጠሩ ነው፡፡ ይህም ሚዛኑን እንዲጠብቅ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ለህትመት ጋዜጠኞች በስራ ምህዳሩ እኩልነት እንዲሰፍን መስራት ይገባል፡፡ በአውሮፓ የሚካሄድን የአንድ ቀን የስፖርት መድረክ ለመዘገብ በጣሊያን የሚገኝ ጋዜጠኛ ከ500 ዶላር ጀምሮ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ ለአፍሪካዊ ግን ከ1000 ዶላር በላይ ነው የሚጠይቀው፡፡ በአፍሪካውያንና በአውሮፓውያን ጋዜጠኞች መካከል ሚዛኑን የጠበቀ አሰራር እንዲኖር ነው በእኛ በኩል የምንታገለው፡፡ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከአዘጋጆቹ ጋር እየተነጋገርን  ነው። ለሁሉም በእኩልነት ለመስራት የሚያስችሉ እድሎች እንዲፈጠሩ እናስባለን፡፡  በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ የሚዲያ ጌቶዎች  መፈጠር የለባቸውም፡፡ ለሁሉም መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ ዋናውና ወሳኙ ተግባር ሙያን ክብርን በጠበቀና በፍፁም መተማመን መስራት ነው፡፡ የዓለም ዋንጫ በከፍተኛ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፤ በካናዳና በሜክሲኮ ነው የሚካሄደው። የህትመት ጋዜጠኝነት  ይህን የመሰለውን የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ በምን መልኩ ሽፋን መስጠት እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል፡፡
ዓለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ከፊፋ ጋር በቅርበትና በጋራ ይሰራል። በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ያሉት የስራ አመራሮች በእኛ በኩል የምናቀርባቸው ሃሳቦችን አክብረው ይቀበላሉ፡፡ የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች በሚዲያው መስክ የመጡትን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ በሚጠቀሙበት ደረጃ ራሳቸውን ማሰልጠን አለባቸው፡፡ አዳዲስ የሚዲያ አውታሮችና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ማለት ነባሩን የስራ ደንብና ግብረገብ መተው ሳይሆን ማጠናከር ነው፡፡ ትክክለኛ፤ ተዓማኒና በጥናትና በምርምር የምናገለግል ባለሙያዎች መሆን አለብን፡፡ የሚዲያን ስራ ለማከናወን ስፖርትን ብቻ ማወቅ በቂ አይደለም፡፡ የዓለም ዋንጫን ራእይ መገንዘብ አለብን፡፡ ሁሉንም ሰፋ አድርገን መመልከት ይኖርብናል፡፡

Read 10856 times