Saturday, 17 December 2022 13:47

“ሥር አልባው ግንድ” እና ቤተሰብ፡፡

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     “ሥር አልባው ግንድ” የተሰኘው የአጭር ልብወለድ መድብል፣ የወጣቶች ሕይወት ላይ ያተኮሩ ትረካዎችን የያዘ ነው፡፡ ግን ከቤተሰብ ጋር ያስተሳስራቸዋል፡፡ ህዳር 24/2015 ዓ.ም በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት በተመረቀበት አጋጣሚ የቀረበ አስተያየትም ፣ይህን የሚያጎላ ነው፡፡
ፍቅርና ፀብ፣ ቅንነትና መጠላለፍ፣ ወንጀልና መተሳሰብ፤ ሱስና ማንነት ቀውስ የወጣቶች ሕይወት መልክዐ ምድርና ጅረት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ውስጥ የቤተሰቦችን ትስስር፣ የወላጆችና የልጆች የሥርና የግንድ ግንኙነትን በትረካዎቹ እንደተዳሰሰ ተጠቅሷል፡፡
የወላጅ ወይም የአሳዳጊ ተገቢ ትኩረት ማጣት ልጆች እድሜያቸውን ያላገናዘበ ስብዕና  እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ በራስ የመተማመን ስሜት በውስጣቸው እንዳይፈጠር በተራ ስሜት ብቻ ቤተሰብን እንዲጎዱ ይገፋፋቸዋል ይላል አስተያየቱ፡፡ የቤተሰብ ግንባታ እንዴት መሆን አለበት? የሚል ጥያቄም አእምሮአችን ውስጥ ይኖራል ሲል አክሏል፡፡
ደራሲው ደረጀ ኃይሌ ሥላሴ ከዚህ አስተያየት ጋር የሚስማማ ሃሳብ የያዙ ይመስላል፡፡ በመፅሃፍ መግቢያ ላይ ያቀረቡት የምስጋና ማስታወሻ እንዲህ ይላል፡፡   
የዚህ መፅሐፍ ማስታወሻነቱ፣ በሕይወት ዘመናቸው ለውድ አገራቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ላገለገሉ እና ላልተዘመረላቸው በንጉስ ሥርዓተ ዘመን፣ የወለጋ ገዢ ለነበሩት ለቅድመ አያቴ ኩምሳ ምርዳ (ገ/እግዚአብሔር)።
ከጠላት ወረራ በፊት፣ በትምህርት ሚኒስቴር የለቀመት ት/ቤት ዳይሬክተር፣ በፅህፈት ሚኒስቴር፣ በሀገር ግዛት ሚኒስቴር እንዲሁም የጋምቤላ አውራጃ ገዢ፣ በመጨረሻም የኢሊባቡር ጠቅላይ ግዛት ዋና ዳይሬክተር ለነበሩት አያቴ ብላታ ብዙወርቅ ሣህሌ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቅየሳ እና የንግድ ስራ ትምህርት ምሩቅ በመሆን፣ ወደ ስራ አለም ከተሰማሩም በኋላ በአስራ አራቱም ጠቅላይ ግዛቶች በመዘዋወር… ሲያገለግል ቆይቶ፣ ወደ የተለያዩ የሥልጣን ዕርከኖች በመሸጋገር፣ በኢትዮጵያ የመንግስት መሬቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሐገሩን እና ሕዝቡን ላለገለው፣…
ከሌሎች የሥራ ባልደረቦች ጋር በመሆን የናዝሬት፣ የሻሸመኔ እና የሐዋሳ ከተሞችን ማስተር ፕላን በመቀየስ ለከተሞቹ መመስረት ከፍተኛ አስዋፅኦ አድርጎ ባስመዘገበው ውጤት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነውን የፈረሰኛ ወርቅ ኒሻን እና ዲፕሎማ ተሸላሚ ለሆነው አባቴ አቶ ኃይለሥላሴ ግዛው፤
ለውድ ልጆቿ ስትል በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ብዙ መስዋዕትነት ለከፈለችው ለውድና ለጀግናዋ እናቴ ወ/ሮ ሰናይት ብዙወርቅ ይሁንልኝ።…ብሏል ደራሲው።



Read 21028 times