Saturday, 17 December 2022 13:58

ስለ ሕገ-መንግስት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ሕገ መንግሥት ማለት መንግሥቱ በምን ዓይነት አስተያየትና ሐሳብ የተመራ ሆኖ እንደ ተመሠረተ የሚያስረዳ፣ በመንግሥቱና በሕዝቡ መካከል ያለውንም ግንኙነት ከናስተዳደሩ ለይቶ የሚያመለክት ቀዋሚ ደንብ ነው።
ይህም ሕግ ንጉሠ ነገሥቱን ወይም መንግሥቱን ከበላይ  ሆኖ የሚያዝና የሚመራ ነው።
ሕግ ለሰው ልጅ አዲስ ነገር አይደለም፤ ዓለም ሲፈጠር አብሮ የተመሰረተ ነው፤ ለአዳምና ለሔዋን ዕፀ በለስን እንዳትበሉ ሲል ጌታችን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል።
ለሙሴም ሕዝቡን እንዲያስተዳድርበት መሪ ይሆነው ዘንድ ከእብነ በረድ ላይ የተቀረጹ ዐሥር  ትእዛዞች (፲ቱ ቃላተ ኦሪትን) ሰጥቷል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ዓለም በኛ በወገኖቹ መካከል ሲኖር ፲ቱ ቃላት ኦሪትን ሳይሽር ዳግም ተጨማሪ ፮ ትእዛዞች (፮ቱ ቃላተ ወንጌልን) ሠርቷል።
እነዚህንም ሁሉ የሚፈጽም የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ፣ የተቃወመ ግን በዘላለም እሳት እንደሚቀጣ ሕጉን ሲሰራ ፍርዱንም አስቀድሞ ለፍጥረቱ አስታውቋል።
እነዚህም የማይዛቡና የማይቃወሱ ጽኑ የሆኑ ሰማያዊ ትእዛዞች በወረቀት ላይ ብቻ ሳይሆን በልባችን የተቀረጹ ለመሆናቸው፣ ራሱ ኅሊናችን በየጊዜው አስታዋሽና ወቃሽ ሆኖ ይነግረናል።
ደንብም በመጠበቁ ወይም በመፍረሱ በሰማይ ክብር ወይም መከራ እንደሚሰጥና እንደሚያመጣ እንደዚሁ ሁሉ፣ በዚህም ዓለም ህግ በመፈጸም መከበርና መጠቀም ይገኛል፤ ሕግ ባለመጠበቅና በማጓደል ከመዋረድና ከመጎዳት ይደረሳል።
ስለዚህ የሚበጀውንና የሚከፋውን ለይቶ ለማወቅ አእምሮ ስለተሰጠን፣ የምንሰራውን ሁሉ ከተቀየሰው መንገድ ሳንወጣ መፈጸም አለብን፤ ይገባናልም።
ንጉሥም የእግዚአብሔር እንደራሴ ስለሆነ ይኸንን ሰማያዊ ሕግ ፈጽሞ ማስፈጸምና ደግሞ ለሚገዛው ህዝብ መልካም አኗኗር የሚስማማውን ያስተዳደር ደንብ በየጊዜው እያሻሻለ መስጠት ግዴታ ይሆንበታል።
እግዚአብሔር ከሰው ፍጥረት ጋራ አከታትሎ ስርዐት መስራቱ፤ የርሱ እንደራሴዎች የሆኑ ምድራውያን ንጉሦች ይኸንኑ ምሳሌ ተከትለው፤ለመንግስታቸውና ለህዝባቸው አስተዳደር ጽኑ መሠረት ማቆም ተቀዳሚ ስራቸው እንደሆነ ሲያስረዳ ነው።
ነገር ግን ሰው በባህርዩ በጥርጊያ ጎዳና (ደንብ) ከመጓዝ መንገድ በሌለበት ጫካ ተሹለክልኮ መሄድ ያደላበታል።
እንደዚሁም ሁሉ ይህ መንፈስ ያደረባቸው ገዥዎችና መሪዎች ህዝብን በደንብና በሥራት እንዲተዳደር በማድረግ ፈንታ የራሳቸው ፈቃድ የሚያዛቸውን ብቻ እንደ ሕግ ቆጥረው እንደፈጸሙና እንዳስፈጸሙ በታሪክ እንመለከታለን።
ይህም መሰረት የሌለው፤ ያልተተካከለ አስተዳደር ምንም ለጊዜው ገዥዎችን ቢያስደስት፤ በመጨረሻው ህዝብ እየሠለጠነ በመሄዱ መነቀፉና መለወጡ አልቀረም።
ሕግንም ከነገሥታት ፈቃድ አውጥቶ አንድ የተለየ መልክ ሰጥቶ ለማቋቋም በታሰበ ጊዜ በዓለም ላይ ምን ያኽል ሁከት እንደ ተነሣና ደምም እንደፈሰሰ በሐሳባችን ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመራመር ልንረዳው እንችላለን።
የሆነ ሆኖ ዛሬ ባለንበት ሰዓት በዓለም ላይ ካሉ መንግስቶች የሠለጠኑት ሁሉ በህግ የተመሠረቱና የተመሩ ናቸው ለማለት ይቻላል።
በሀገራችንም በኢትዮጵያ የነገሡት ነገሥታት ከቀዳማዊ ምኒልክ ዠምሮ እስከ ንግሥት ዘውዲቱ ቁጥራቸው ሁለት መቶ ኻያ አራት (፪፻፳፬) ሆኖ፤ እነዚህም ሕዝቡን በወደዱትና በፈቀዱት ሲያስተዳድሩት ቆይተዋል። (በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን ነገሥታት ዝርዝር ለማወቅ ለሚፈልጉ ማስረጃውን አባሪ ሦስት በማድረግ አግብቻለሁ)።
ስለ ሆነ ዐፄ ምኒልክ ከሳቸው በፊት ከነበሩት ገዥዎች ተለይተው የመንግሥታቸውን ስራ ለማሻሻል ረዳት ይኖራቸው ዘንድ ሚኒስትሮችን ሹመዋል።
ነገር ግን ምንም ሥራው ቢከፋፈልና ይህ አዲስ ስም በሀገራችን ቢገባ፣ በዓለም ላይ እንደሚደረገው ሁሉ  ሕገ መንግሥትና የሕዝብ እንደራሴዎች የሚመክሩባቸው ምክር ቤቶች (ሲናተርና ፓርላማ) ባለመቆማቸው፣ ሐሳቡ መልካም ሆኖ ሳለ ሥራው ተጓድሎ ይታይ ነበር።



Read 1310 times