Saturday, 17 December 2022 14:01

በከተማ አመራር ስኬት ያስመዘገቡ ከንቲባ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(4 votes)

 • “አመራሩን በንቅለ ተከላም በቆረጣም ነው ያስተካከልነው”
     • “ዓለም ስትሰለጥን ወሎን ትመስላለች


    በ1999 ዓ.ም ከሀረማያ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ተቀብለው ከ2000 ዓ.ም  ጀምሮ በሰሜን ወሎ ዋድላ ወረዳ የወረዳውን ገንዘብና ኢኮኖሚ ዘርፍ ለአራት ዓመታት መርተዋል። ከዚያ በኋላ በህዝቡ ፍላጎት በወጣትነት እድሜያቸው የዋድላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ለአምስት ዓመት በሰሩበት ወቅት በሳዩት የስራ ብቃትና አፈጻጸም የትምህርት ዕድል አግኝተው ሁለተኛ ድግሪያቸውን በዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ ከባህዳር ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል - የዛሬው እንግዳችን የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ።
ሁለተኛ ድግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ከወረዳ ወደ ክልል ተዛውረው በክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በማገልገል ላይ እያሉ የዓለም ባንክ ፕሮጀክት በሆነው “የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋት ፕሮግራም” የተሰኘ የከተሞች ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ሰሞኑን ለሥራ ወደ ደሴ ያቀናችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከንቲባው አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ፣ የወርልድ ባንኩ የከተሞች ፕሮግራም ላይ ምን አስተዋጽኦ አበረከቱ? እንዴት ወደ ደሴ ከተማ ከንቲባነት መጡ? በጦርነት ስትታመስ የነበረችን ከተማ በአስተዳዳሪነት መረከብ ምን ያህል ፈታኝ ነበር? አሁን ደሴ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች? የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎችን በማቅረብ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-          ከክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ እንዴት ወደ ዓለም ባንኩ የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማትና ማስፋፊያ ፕሮግራም ተዘዋወሩ? እግረመንገድዎን የዓለም ባንክ የከተሞች ፕሮግራም ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸውን ዘርፎች ቢያብራሩልኝ?
ፕሮግራሙ በጣም ትልቅና ዓለም አቀፍ ፕሮግራም ሆኖ ከተሞች ላይ በስፋት የሚሰራ ፕሮግራም ነው፡፡ ይሄ ፕሮግራም በርካታ ዘርፎች አሉት፡፡ ክልሉ ይህን ዘርፍ የመምራት አቅም አለው በሚል ነው የመደበኝ፡፡ በዚህ መሰረት የፕሮግራሙ የምስራቅ አማራ ማስተባበሪያ አስተባባሪ ሆንኩኝ፡፡ ይህንን ፕሮግራም ከተረከብኩ በኋላ እውነት ለመናገር አንደኛ ፕሮግራሙ ሳይንስ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን ሳይንስ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለማስፈፀም የሚያስችል አቅም ነው ያገኘሁት፡፡
እንዳልኩሽ ባህሪው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ከከተማ መሰረተ ልማት ጋር ይያያዛል፤ የጥገና ፕሮጀክት የሁኔታዎችን ትንታኔ ሰርቶ እንዴት ማውጣት እንደሚቻል ማወቅን ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዱ መሬት በዳታ ቤዝ ተመዝግቦ መሬትን ከተማ ላይ እንዴት ሀብት አድርጎ መኖር እንደሚቻል፤ የሎካል ኢኮኖሚክ ዴቬሎፕመንት ፕሮግራም፤ የስራ ዕድል ፈጠራና ፆታን አካታች ያደረገ የስራ ዕድል ሁሉ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ የአካባቢ ሁኔታ እና ችግርና አደጋን መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ እንዴት መፍጠር ይቻላል የሚል ትልቅ እሳቤን የያዘ ነበር-ፕሮግራሙ። በሌላ በኩል፤ መሬትን ከዘረፋ ለማዳን በሲስተም የመታገል ማለትም እያንዳንዷ መሬት የመንግስትም ሆነ የግል በዳታ ቤዝ ይዞ ማስተዳደር፤ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻን የአወጋገድ ሥርዓት ሁሉ በፕሮግራሙ አለ፡፡ የከተማ አመራር ለመሆን፤ መጀመሪያ የአሰራር ስርዓት ልማት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ከተማ ላይ አዳዲስ አሰራሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የከተማን ፅዳትና ውበት ለመቆጣጠር ምን ሥርዓት መዘርጋት አለብን የሚል በጣም ዘርፈ ብዙ ሀሳብ ያለው ነው የዓለም ባንክ ፕሮግራም፡፡
ይህን ሀላፊነት እንዴት ተወጡት? በዚህ ስራስ  ምን ውጤት አስመዘገቡ?
እንግዲህ ሥራው ከላይ በዘረዘርኳቸው ዘርፎች አግባብ ከተሞችን ማስተባበር ነው። ከተሞችን ለማስተባበር የተሻለ እውቀት ይጠይቃል፡፡ የተሻለ ዕውቀት ብቻም ሳይሆን የተሻለ ክህሎትም አስፈላጊ ነው፡፡ በአምስት ስድስት ዞኖች ያሉ በርካታ ከተሞችን ነበር የምመራው፡፡ በዚህ ፕሮግራም እውነት ለመናገር ትልቅ አቅም ነው የፈጠርኩት፡፡ ከተሞችን በማስተባበር በኢትዮጵያ ደረጃ እኔ የማስተባብራቸው ከተሞች አንደኛ መውጣት የቻሉበትን አቅም ነበር የፈጠርኩት፡፡ ለምሳሌ ወልዲያ አንደኛ ወጥቷል፤ሰቆጣ ሁለተኛ ወጥቷል፤ ሸዋሮቢት ፤ ኮምቦልቻ፤ ደብረ ብርሃን ሌላው ቀርቶ ደሴ በኢትዮጵያ ደረጃ ሁለተኛ ወጥቶ ያውቃል፡፡ በፊት በነበረው በአጠቃላይ ምስራቅ ቀጠና ውስጥ ያሉ ከተሞች የተሻለ ቁመና ላይ እንዲሆኑ ካደረግን በኋላ፣ የምዕራቡ ቀጠናም በአጭር  ጊዜ ወደ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲገቡ እንደ ክልል ውጤታማ የሚያደርገንን ሥራ ሰርተናል፡፡ በሁለተኛው ዓመት የምዕራቡ ቀጠና የምስራቁን ተምሳሌት እያደረገ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ ሆነ፡፡ በዚህ አካሄድ የከተሞችን የእርስ በእርስ ትብብር እያጠናከርነው ስንመጣ፤ እውቀትን እያጋራን ስንሄድ፤ የከተማ አመራርን መፍጠር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ስንገባ በተፈጠረ ትልቅ ንቅንቄ ክልላችን በኢትዮጵያ አንደኛ ወጣ፡፡ አስታውሳለሁ ገና ስራ ስንጀምር የነበረው የበጀት ድጋፍ 600 ሚሊዮን ብር አካበቢ ነበረ፡፡ በፕሮግራሙ ድጋፍ በተሰራ የስራ ውጤት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ እኛ በአንድ ዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ነው ያስጨመርነው፡፡ ይህን ያገኘንበት ዋና ምክንያት 70 እና 80 በመቶ የነበረው አፈፃፀማችን በአንድ ጊዜ ወደ 98 እና 99 በመቶ በመግባቱ ነው፡፡ ስለዚህ በእውቀትም በክህሎትም ሆነ በከተሞች አካባቢ ንቅናቄ በመፍጠርም የተሻለ ውጤትና አፈፃፀም በማሳየታችን ከተሞችም የተሻለ በጀት አግኝተው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ችለናል፡፡ በዚህ ስራ የራሴ የሆነ ሊጨበጥ ሊለካ ሊታይ የሚችል የተለየ አስተዋፅኦ ማበርከት ችያለሁ፡፡ በዚህ ደግሞ በጣም ደስ ይለኛል። በዚያ ፕሮግራም ጥሩ የከተማ አመራር ለመሆን የሚያስችል ልምድ ክህሎትና አቅም አግኝቼበታለሁ፡፡
በምን መልኩ ነው ወደ ደሴ ከተማ አስተዳደርነት የመጡት? እርስዎ የመጡት ከተማዋ በጦርነት ቀውስ ውስጥ በነበረችበትና እምብዛም ከጦርነት መንፈስ ባልወጣችበት ወቅት ነበርና ደሴን እንዴት አገኟት? በምንስ ሁኔታ ተረከቧት?
እውነት ነው! እንዴት ተረከቧት ከሚለው ጥያቄሽ ብጀምር ደስ ይለኛል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ወደ ደሴ ከተማ በከንቲባነት እመጣለሁ ብዬ አስቤውም አልሜውም አላውቅም፡፡ የስነ -ልቦና ዝግጅትም የለኝም፡፡ የነበርኩበት ቦታም እውነት ለመናገር ወደ እዚህ የሚያመጣ አልነበረም፡፡
እንዴት ማለት?
ሰው እንዴት ተጠቃሚነቱን ቀንሶ ወደዚህ ይመጣል፡፡ ማንም ይሄንን አይቀበልም። ምክንያቱም ቀደም ሲል የተሻለ ቦታ ነው ያለሁት፤ የተሻለ ተጠቃሚ ነኝ፤ ብዙ ከተማ ነው የማስተባብረው፤ ከብዙ ከተማ ወደ አንድ ከተማ ነው እየመጣሁ ያለሁት፡፡ በየትኛውም መንገድ ለታሪክ ካልሆነ ለተጠቃሚነት ማንም እሺ ብሎ አይመጣም፡፡ የክልሉ መንግስት ድንገት ነው ጥያቄውን ያቀረበው፡፡ ክልሉ ጥያቄውን ሲያቀርብልኝ ለተወሰነ ጊዜ በራሴ የማመዛዘንና የማሰላሰል ሥራ ሰራሁ፡፡ ከዚያ በኋላ እሺ ብዬ ጥያቄውን ተቀበልኩ፡፡ ምክንያቱም ታሪክ ይበልጣል፡፡ ገንዘብ የትም አያደርስም። ታሪክ ለመስራት ግን አቅም ቢኖርሽ እንኳን ዕድል አታገኚም፡፡ ዕድሉን አግኝቶ ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ካወቁበት ትልቅ ነገር ነው። ሁለተኛው እንድመጣ የገፋፋኝና ያስወሰነኝ ነገር፣ ያው ደሴ የወሎ የሁላችንም መዲና ናት፤ ማረፊያችን ናት፡፡ የትም ዞረን ዞረን ተመልሰን እዚህችው ከተማ ነው የምናርፈው፡፡ ስለዚህ በደሴ ወደ ኋላ መቅረት ትልቅ ቁጭት በውስጤ ነበረ። ትልቅ ቁጭት ነው የነበረብኝ፡፡ ስለዚህ ለምንድነው አቅሜ በቻለው መጠን አስተዋፅኦ የማላደርገው፤ እድሉ ከተገኘ ከማህበረሰቡ ጋር ከተማውን መቀየር እንችላለን የሚል ተስፋ በውስጤ አደረና ሀላፊነቱን ተቀበልኩኝ፡፡
እንዴት ተረከቧት ከሚለው ጥያቄሽ ቀጥሎ በምን ሁኔታ ከተማዋን አገኟት የሚል ይመስለኛል፡፡ ይህም ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ከተማ እንደመጣሁ የነበረው የአመራር ኮሚቴ እንደገና እንዲስተካከል ለማድረግ ወደ አራት መሰረታዊ ነገሮችን አስቀመጥን፡፡ አንደኛው፡- የአመራር ኮሚቴው ከምንም በላይ ይሄንን ማህበረሰብ ለማገልገል በመርህና በመርህ መቆም እንዳለብን ተስማማን፡፡ መርህ አልባ ግንኙነት በፍፁም አይፈቀድም፡፡ የጥቅም ትስስርና ሌሎች አሳስፈላጊ ግንኙነቶች አይፈቀዱም፡፡ በመርህና በመርህ ላይ ብቻ የተመሰረተ ግንኙነት፤ ጠንካራ አንድነት ያለው አመራር ኮሚቴ በመሆን፤ ይህንን ህዝብ በንፅህና ማገልገል እንዳለብን ተስማማን፡፡ ሁለተኛው፡- መወሰን መቻል፡፡ በበርካታ ሁኔታ ተውሰብስበው የተቀመጡ የማህበረሰቡ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የሚያያዙ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱት በቆራጥ ውሳኔ ሰጪነት ነውና የውሳኔ ሰው መሆን እንዳለብን ተስማማን፡፡ ሦስተኛው፡- አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ ነው፡፡ በነበረ፤በተለመደና በዘፈቀደ አካሄድ ይሄን ከተማ መለወጥና አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሸከም ስለማይቻል፣ አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅና አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡን፤ እኛ ቀድመን እንዲከተለን የማድረግ አሰራር ያስፈልጋል። ስለሆነም መወሰን ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አዳዲስ አሰራር መዘርጋት አለብን በሚለው ላይ ተስማማን፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁበትና ለአገልግሎት ብቁ የሚሆኑበት፤ የተለያዩ አሰራሮችን መሬት ላይ የምናሳርፍበት፤ ህብረተሰቡን ሰርተን በተግባር እያሳየን እንዲከተለን ማድረግ እንጂ በመልካም ንግግርና አንደበትን በማሳመር ላይ ብቻ መጠመድ እንደሌለብን ተነጋግረን፤ በተግባር ይህን ማህበረሰብ መካስ አለብን በሚለው ሀሳብ ላይ ተስማምተን ወደ ስራ ገባን፡፡ ወደ ስራ ስንገባ ውጥንቅጡ የበዛ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ወቅት ነው የነበረው፡፡ የህግ የበላይነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የገባበት፤ የሰው ልጅ በጠራራ ፀሀይ ከዚሁ ከተማ ታፍኖ የሚወሰድበት፤ ወርቅ ቤቶች በጠራራ ፀሀይ የሚዘረፉበት፤ የትኛው አካል ህግ እንደሚያስከብር የማይለይበትና በርካታ ችግሮችን የተጋፈጥንበት ወቅት ነበር። በአጠቃላይ በብዙ መልኩ በከተማው የህግ የበላይነት አደጋ ውስጥ የገባበት ጊዜ ነበር፡፡
ሁለተኛው የአካባቢው ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የገባበት ነበር፡፡ ምክንያቱም ተወርረናል። ህውሃት ወሮናል፡፡ በማህበረሰቡ ላይ የስነ ልቦና ስብራት አድርሶብናል፤ ንብረቶች ተዘርፈዋል። ቢሮዎች ሆን ተብሎ እቃዎችና ንብረቶች ወድመዋል፤ አገልግሎት መስጠት አይቻልም፤ ምክንያቱም ንብረት ወድሟል፡፡ መቼም በእስክሪብቶ እየፃፍሽ አገልግሎት መስጠት አይሞከርም፡፡ ለምን ብትይኝ ይህ ከተማ ትልቅ ከተማ ነው፤ ብዙ ህዝብ የሚኖርበት ነው። ኮምፒውተሮች በሙሉ ተዘርፈዋል፤ የንግድ ድርጅቶች ስለተዘረፉ የንግድ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል፤ ሆቴሎች ተዘግተዋል፤ አልጋ ቤቶች አይሰሩም፤ የስራ ዕድል ፈጠራ ችግር ውስጥ ነው ያለው፤ ይሄ ሁሉ ፈተና የተጋረጠበት ሁኔታ ነበር የገጠመን፡፡
እኒህ  ሁሉ ተግዳሮቶች ከፊትዎ ሲደቀኑ ተስፋ አልቆረጡም?
በጭራሽ! አንድ አመራር አመራር የሚባለው ያልተመቸ ከባቢን ወደ ምቹ ሁኔታ መቀየር ሲችል ነው፡፡ እኔ ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ ጉዳዩ ተስፋ የሚያስቆርጥ ስላልሆነ አይደለም፡፡ በመልካም ጊዜማ ሁሉም አመራር ይሆናል፡፡ ከላይ ችግሮቹን የገለፅኩልሽ የነበረው ሁኔታ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር ለማሳየት ነው፡፡ የሆኖ  ሆኖ ምንም የፕሮጀክት እንቅስቃሴ ስላልነበር በአጭር ጊዜ እንዲጀመሩ የሚያስችል ሥርዓት ዘረጋን፡፡ ገንዘብ የለም ግን የሰራተኛውን ደሞዝና የከተማ አስተዳደሩን በጀት በሙሉ አዙረን አባይ ባንክ አስገባነው፡፡ አባይ ባንክ ደግሞ ብር እንዲያበድረን አደረግንና ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ አደረግን፡፡
ከአባይ ባንክ ምን ያህል ብር ብድር አገኛችሁ?
200 ሚሊዮን ብር አገኘን፡፡ ከዚያ በኋላ የገቢ መሰብሰብ ስራ በአጭር ጊዜ እንዲጀመር አደረግን፡፡ የተለያዩ የክልልም የፌደራልም ተቋማት ስብሰባዎችን ወደ ደሴ እንዲያመጡልን አደረግን፡፡ ይህን ያደረግነው በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው፡፡ ወዲያው ሆቴሎች፤ ምግብ ቤቶች፤ ቡቲኮች፤ ሊስትሮዎች፤ ባልትናና ቡና ጠጡ ቤቶች ሁሉ ተከፈቱ፡፡ የገበያ ትስስሩ ህይወት መዝራት ጀመረ፡፡ የፀጥታ አካላትን ሁሉን ገምግመን የፀጥታውን ሁኔታ ሥርዓት የማስያዝና ሰላም የማስፈን ሥራ ሰራን፡፡ አንድም ነፍስ ሳይጠፋብን ግን ሥርዓት አስያዝነው። አንድም ደም ሳይፈስ ነው የፀጥታ ስራው የተሰራው፡፡ “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” አይደል የሚሉት አባቶቻችን፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ አገዘን፡፡ ከጎናችን ቆመ፡፡ የነበረው ሁኔታ አስፈሪ ቢሆንም ፤እኛ ታጋሽ በመሆንና በያዝነው አቋም በመፅናት ብዙዎቹን ነገሮች መስመር አስያዝናቸው ማለት ነው፡፡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ነፍስ እየዘራ ሲመጣ ደሴ ደግሞ የንግድ ሁኔታዋ የተሻለ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ወደ ማገገም ሄድን፡፡
በዘጠኝ ወር የአመራርነት ጊዜ ውስጥ ይህን  ሁሉ ውስብስብ ሁኔታ ማስተካከል የሚደነቅ ነው፡፡ ቀደም ብለው እንደነገሩኝ ወደ ስራ ከመግባታችሁ በፊት አራት ጉዳዮችን አስቀምጣችሁ ነበር፡፡ አንዱና ዋነኛው አመራሩ በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖረው ማድረግ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በቀደመው ሥርዓት ውስጥ በጥቅም የተሳሰሩ፤ በሙሰኝነት ማህበረሰብ የሚያንገላቱና በአጠቃላይ ብልሹ አሰራር ላይ የተጠመዱ አመራሮች አላጋጠሟችሁም? እንዲህ አይነት አመራሮች ከነበሩ፤ እርስዎ የአመራሩ ግንኙነት መርህ ላይ ይመስረት ሲሉ  ነገሮችን ወደ ማበላሸትና ወደ ተንኮል ገብተው አላስቸገሯችሁም? እርስዎ ይህን ችግር  በምን መልኩ ፈቱት?
ጥሩና ወሳኝ ጥያቄ ነው! ትክክል ነሽ፡፡ ይህንን አደረጃጀት በሁለት መልኩ ነው የሰራነው፤ አንዳንዱን በንቅለ ተከላ ነው፡፡
ንቅለ ተከላ ማለት?
አንዳንዱን ከነአካቴው ነቅለን ሌላ ነው የተከልነው፡፡ በአዲስ ነው የተካነው ማለቴ ነው። አንዳንዱን በቆረጣ ነው፡፡ የተቆረጠ ይኖራል፡፡ የችግሩ አግባብ መለስተኛ የሆነ፣ በግምገማና በማስጠንቀቂያ የታለፈ አለ። ሁሉንም አንዴ ነቅለሽ መጣል ከባድ ነው። ምክንያቱም አመራር በአንዴ መፍጠር አትችይም፡፡ አመራር በሂደት ኢንቨስት እየተደረገበት ነው መፍጠር የሚቻለው፡፡ ይህቺ ከተማ ብቻዋን መቅረት አትችልም፡፡ በተለይ ወጣቶች ደሴ ላይ በለውጡ ምክንያት የመጡ ሆነው ስራ ሲገቡ የትኛው ነው ጥሩ፤ የትኛው ነው ስህተት የሚለውን አያገናዝቡም፤ ሄደው ማኖ ይነኩብሻል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ሆን ብለውም ብቻ ሳይሆን ከልጅነት አንፃር ስሜታዊ በመሆንና ከመሳሰሉት ሁኔታዎች ነው። እነዚህን ልጆች እየቆረጥን ብንጨርሳቸው፣ ይሄ ከተማ መሪ አልባ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ መዳን የሚችሉትን በቆረጣ አስተካክልን፤ አንዳንዱን በንቅለ ተከላ መስመር አስያዝነው፡፡ መውጣት ያለበትን ውልቅ አድርገን ከአመራር ሥርዓቱ አስወጥተናል፡፡ እንዳልኩሽ አንዳንዱን እየሞረድን ቅርፅ እያስያዝን፣  ለስራው ተገቢ እንዲሆን አድርገናል፡፡ ምን መሰለሽ ዋናው ነገር? በመጀመሪያ መስተካከል ያለበት አናቱ ነው፡፡ ከንቲባው ከተስተካከለ ሌላውን ያድናል፡፡ ከንቲባው ጠንካራ ከሆነ ብዙ አመራር ያወጣል፡፡ ከንቲባው ደካማና ከመርህ የወጣ ከሆነ፣ ብዙዎችን ይዞ ይጠፋል፡፡ ስለዚህ ከላይ በጠቀስኩልሽ መንገድ ሄደን የአመራር ኮሚቴውን ካስተካከልን በኋላ ሲስተሙን እንደ አዲስ ኢንስቶል ማድረግ ጀመርን፡፡ ለምሳሌ ማሽነሪዎችን ብንወስድ ኤክስካቫተር፣ ሎደር፣ ግሬደር የተባለ በሙሉ በህውሃት ተወስዶብናል፡፡ ስለዚህ ማሽን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ያስፈልገናል፡፡ እንደ ከተማ አስፓልት ፕላንት አልነበረንም፡፡ ይሄ ከበፊቱም አልነበረም አይታሰብምም፡፡ ነገር ግን እኛ አስፓልት ፕላንትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ችለናል፡፡ በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን በዲፕሎማሲያዊ ውይይት ተፈፃሚ ሆኖ ገራዶ ላይ ተተክሏል፡፡ አስፓልት ፕላንት እንግዲህ አስፓልት መንገድ ስትሰሪ ሬንጁን እያስተካከለ እየሰራ የሚያቀርብ ማሽነሪ ነው፡፡ እኛ ስለተወረርንና ሥለተዘረፍን የክልሉን መንግስት አስፈቅደን ከቀረጥ ነፃ በራሳችን ግዢ፣ በፍጥነት ማሽነሪ እንዲቀርብልን አደረግን፡፡ እነዚህ ሁሉ ተፋጥነው የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴያችን በአጭር ጊዜ ወደነበረበት እንዲመለስ አደረግን ማለት ነው፡፡ የተወሰነውን በግዢ የተወሰነውን ደግሞ በኪራይ ወስደን ስራ ጀምረናል፡፡ ለእያንዳንዱ ሴክተር ኮምፒዩተሮችን በዓለም ባንክ ገዝተን፣ ቶሎ አስገብተን አገልግሎቱን በፍጥነት አስጀመርን፡፡
እርስዎ በዓለም ባንክ የከተሞች ፕሮግራም ውስጥ መስራትዎ ነገሮችን ቀላል ሳያደርግልዎት አልቀረም አይደል?...
ትክክል ነው፡፡ ዓለም ባንክ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ስለማውቀውና እንዴት መሄድ እንዳለበት ስለምረዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንን አስተካክለን ወደ ስራ ገባን፡፡ ስለዚህ ከተማው አይደለም ወደ ነበረበት መመለስ ከቀጠናው ብሎም ከክልሉም ጭምር ተወዳዳሪ የሚሆንበትን አሰራር መፍጠር ቻልን፡፡ የነገርኩሽ ሁሉ ወሬ ብቻ ሳይሆን የሚታይ የሚጨበጥ የሚዳሰስ እውነት ነው፡፡
እስኪ ቀደም ብሎ ተጀምረው በጦርነቱ ተቋርጠው የነበሩና አዳዲስ ተጀመሩ የተባሉትን የመሰረተ ልማት የግንባታ ሂደቶች አንድ ሁለት ብለን እንጥቀሳቸው…
አሁን ላይ በከተማው የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ሁለት መልክ አላቸው፡፡ አንደኛው በራሳችን በከተማው የምንሰራው ሲሆኑ፤ ሁለተኛው በፌደራል መንግስት የሚሰሩልን ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ በከተማው የሚሰሩትን በተመለከተ አስፋልትም እንሰራለን፤ ለምሳሌ፡- ኮሸምበር ገረዶ አካባቢ ከ4 ኪ.ሜ ያላነሰ አስፓልት እየሰራን ነው፡፡ በዚህ የበጀት ዓመት አጋማሽ (ጥር መጨረሻ ላይ) ይጠናቀቃል፡፡ ለዚህም ቀንም ሌሊትም እየሰራን ነው፡፡ ሌላው ከመዘጋጃ ቤት ወደ ወሎ ሆቴል ዘቅዝቆ የሚሄደውም ሌላ ሁለተኛው አስፓልት ነው፡፡ እስከ ጥር 30 ይጠናቀቃል፡፡ ሶስተኛው ከመላኩ ወደ ሆስፒታል የሚወርድ አስፋልት አለ፡፡ እስከ ጥር 30 የሚጠናቀቅ ነው፡፡ አራተኛ ከመናፈሻ ተቋም ወደ ሚባለው አካባቢ የሚሄደው አስፓልት ቀደም ሲል ተጀምሮ ሳያልቅ የቀረ ነበር፡፡ አሁን በተመሳሳይ በጥር ከሚጠናቀቁት አንዱ ነው፡፡ ለዚህም በፍጥነት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ከየካቲት እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ተግተን የምንሰራቸው ከቧንቧ ውሃ እስከ ሮቢት እስከ ወሎ ባህል አምባ ያለውን አስፓልት መንገድ ዘንድሮ ለማጠናቀቅ ለአስፓልት ዝግጁ የማድረጉን ስራ ዘንድሮ እንጨርሳለን። ይሄ በጣም ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሁለተኛው ከገብርኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ ወደ ቁርቁር የሚወጣ ሰፊና ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ለአስፓልት ዝግጁ የማድረግ ስራው እስከ ሰኔ 30 ይጠናቀቃል፡፡ ከፍተኛ በጀት ተይዞለታል። ከመንገድ ፕሮጀክት ሳንወጣ መግለፅ የምፈልገው አራዳ ላይ ከኔትወርክ ህንፃ በቡና ተራ አድርጎ የሚወጣ ሌላ የመንገድ ሥራ አለ። ይህም ለአስፓልት ዝግጁ የማድረጉ ሥራ እስከ ሰኔ 30 ያልቅና በቀጣይ አመት አስፓልት ይሆናል፡፡ ሌላው ከፋሲካ ሆቴል ወደ እቴጌ መነን የሚወጣው የጠጠር መንገድ ለአስፋልት ዝግጁ የማድረግ ስራው እስከ ሰኔ ይጠናቀቃል፡፡ ሌላው በመነኃሪያ በኩል አድርጎ ወደ ጤና ጣቢያ ወደ ቄራ የሚወርደውም እንዲሁ በተመሳሳይ የመንገድ ሥራ ነው፤ ሰሞኑን ይጀመራል። ለአስፓልት ዝግጁ አድርገን እናከርመውና በቀጣይ አመት አስፋልት ይሆናል፡፡ በብሉ ናይል ቁልቁል የሚወርደውም መንገድ እንዲሁ ሌላው የጠጠር መንገድ ስራ ነው፤ እስከ ሰኔ 30 ይጠናቀቃል፡፡ በሌላ በኩል ደረጃቸውን የጠበቁ የመናኸሪያ ግንባታዎችን እያካሄድን ነው። አንዱ ከተማ መሃል የሚገኘው የኮንትራት ውሉ ተወስዷል፡፡ እስከ ሰኔ 30 የመጀመሪያው ምዕራፍ የምንለውን ስራ ለመጨረስ ሰኞ ይጀመራል (ባለፈው ሰኞ ማለት ነው)፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት 71 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል። ሁለተኛው ገራዶ ላይ የሚገነባው መናኸሪያ ነው፡፡ በዚህ በጀት አመት ይጠናቀቃል፡፡ ሰባት የሚሆኑ የኮብልስቶን መንገዶች የግዢ ስርዓት አልቆ ወደ ውል ሥርዓት እየገባን እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ሶስት ሴፕቲክ ታንኮች ሶስት ቦታዎች ላይ በዚህ በጀት ዓመት ለመስራት ትልልቅ በጀቶች ይዘናል፡፡ ሁለት ሼዶችን ለመገንባትም አቅደናል፡፡ በአጠቃላይ የከተማዋን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማፍጠን ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ ቀን ከሌት ርብርብ ላይ እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል በፌዴራል የሚሰራው የመጀመሪያው ፕሮጀክት የአስፓልት ጥገና ነው፡፡ ቅድም ስታነሽው የነበረውና በዝናብ ወቅት አስፓልቱ በሙሉ ጎርፍ እየሆነ፣ ግሳንግሱ ሁሉ አስፓልት ላይ እየተከመረ የከተማው ነዋሪ ሲሰቃይ ቆይቷል፡፡ በተለይ ከፒያሳ አራዳ ሳር ተራ ጀምሮ በፒያሳ ላዩን በከበደ አበጋዛ ሆቴል ወደ መዘጋጃ የሚያልፈው መንገድ እጅግ በጣም አስቸጋሪና ከእኛ አቅም በላይ ስለሆነ በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የሚሰራ የነሱ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከአሁን በፊትም ተናግረናል የፊታችን ክረምት ሳይመጣ ተጠግኖ ማለቅ እንዳለበት ከነ ኢ/ር ሀብታሙ ጋር ተነጋግረን ነበር እስካሁን አልተጀመረም፡፡ በዚህ ቅሬታ ላይ ነን፡፡
ሁለተኛው በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የሚሰራው የአስፓልት ባይፓስ መንገድ ነው። በመንበረ ፀሀይ ከዚያም በቄራ አድርጎ በሆስፒታል በኩል ይመጣና ከዚያ ወደ አሬራ ከተሻገረ በኋላ በቧንቧ ውሃ ይወጣል። ይህ በጣም ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ አሁንም የግዢ ሂደት ላይ ነው ያለው ነገር ግን የግዢ ሂደቱ ውል ባለው አገላለፅ ተጠናቅቆ ስራ ላይ ውሏል ማለት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ በጀት የተያዘለት በመንግስት እቅድም በይፋ ለሕዝብ የተገለፀ ነው፡፡ አሁንም ከሂደት የዘለለ መሬት የነካ ነገር እንደሌለ ነው የሚታወቀው፡፡ እነዚህ ሁለት በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የተያዙ ፕሮጀክቶች እስካልተሰሩ ድረስ የጎርፍ ችግር በቀጣዩም ክረምት በእጅጉ ያሰጋናል፡፡ እኛም አዲስ አበባ ድረስ እየሄድን እባካችሁ ተግባራዊ አድርጉልን እያልን እየጠየቅን ነው የምንገኘው፡፡
ደሴ በጦርነት ውጥንቅጥ ውስጥ ነበረች፣ ብዙ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች አሉ፣ ህዝቡም በጦርነት መንፈስ ውስጥ አሁንም እንዳለ ታዝቤያለሁ፡፡ ከተማዋ ታሪክ ያላት ጥንታዊት ከተማ እንደመሆኗ ያላትን ታሪክና ሀብት ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ምን የታቀደ ነገር አለ?
እኛ በመጀመሪያ ህዝቡን በልማት ተደራሽ ወደ ማድረጉ እንቅስቃሴ ነው የገባነው። በዚህ ረገድ እንደገለፅኩልሽ የተሻለ ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ሊሰሩ የታሰቡ ስራዎችን ቅድመ ዝግጅት የካሳ ክፍያ፤ የሶስተኛ ወገን ጉዳይ ቁሳቁሶችን ገዝቶ ወደ አገር ቤት የማስገባቱን ለምሳሌ፡- ሬንጅ ለዓመቱ የሚበቃንን ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተን ገዝተን አጠናቀናል፡፡ ጠጠርና ሌሎችንም አዘጋጅተን ከመስከረም 30 በፊት አልቀው ጥቅምት 1 ቀን ወደ ትግበራ ነው የገባነው፡፡ ሁሉም ፕሮጀክት በታቀደላቸው ጊዜ ላይ እየሄዱ ነው፡፡ መስራትና መስራት ብቻ ነው የምንፈልገው፡፡ ወደ አገልግሎት አሰጣጥ ስንመጣ ህዝቡ በነፃ አገልግሎት ማግኘት ነው ያለበት፡፡ ይህንን እረስተው ህዝቡን ክፍያና ጉቦ በመጠየቅ የሚያጉላሉ አመራሮች ይኖራሉ፡፡ ይሄ የሙስና ትግል ነው፡፡ በዚህ የሙስና ትግል ብዙ ተጠያቂ አመራሮች ብዙ ተጠያቂ ባለሙያዎች ብዙ ተጠያቂ የፍትህ አካላትና ደላላዎች አሉ። ይህን ለማጥራት በሰራነው ስራ የታሰረ አለ፤ በፍርድ ሂደት ላይ ያለ አለ፤ የመንግስትን መሬት ፎርጅድ ዶክመንት አዘጋጅቶ የሸጠ አለ ብዙ ብዙ ነገር አለ፡፡ ገና እየታደነ ያለም አለ፡፡ እያጠራን ነው ያለነው፡፡
በዚህም ህገ ወጥ ቤቶችንም ጭምር  እያፈረሳችሁ ነው?
እውነት ነው እያፈረስን ነው፡፡ ህዝቡም በዚህ እያገዘን ነው፡፡ አሁን ይህን እየሰሩ ያሉ አመራሮችና ደላሎች እየተመነጠሩ ነው፡፡ ደላላ ከአንዳንድ ሀላፊነት ከጎደላቸው የመንግስት ሰራተኞች ጋር ኔትወርክ ፈጥረው የሚሰሩትን ህገ ወጥ ስራ እያፈራረስን ነው፡፡ ህገ ወጦቹ ጥቂት ናቸው እናጠራቸዋለን፡፡ እጃችን ላይ ሰነድ አለ፡፡ ለምሳሌ፡- አንዲት የ89 ዓመት እናት ከአያት ከቅድመ አያት ይዘውት የመጡትን መሬት ምንም በማያውቁት ነገር የመንግስት ሰራተኛና ደላላ ተመሳጥረው ይዞታቸው ሊቀማ ሲል አስመልሰናል። ብዙ ታሪክ ነው ያለው። በሌላ በኩል የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ለማበረታታትና አካባቢውን ለማስተዋወቅ በፋሲካ አካባቢ ትልቅ ዓለም አቀፍ የባዛርና የኤግዚቢሽን እንዲሁም የገቢ ማሰባሰቢያ ስራ እያዘጋጀን ነው። ለዚህ ኮሚቴ ተዋቅሮ አልቋል። በተረፈ ደሴ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ያለ ልዩነት በፍቅር የሚኖርባት ተምሳሌት ትልቅ ከተማ ናት። ዓለም ሲሰለጥን ወሎን ይመስላል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ህዝቡ ዘረኝነትን ይጠየፋል በዚህ ምክንያት የደሴ ህዝብ በ1997 ዓ.ምም ሆነ ከዚያ በፊት ያለውን ምርጫ መርጦ አያውቅም ዘረኝነትን ስለሚያወግዝ። በዚህ ምክንት ከልማት ተጠቃሚነትም ተገልሎ መቆየቱ ግልጽ ነው። ደሴ መልከ ብዙ ታሪክ ብዙ ከተማ ናት፡፡ አፀደማርያም ተብላ ሙስሊም ፤መሃመድ የሚል ስም ይዞ ክርስቲያን የምታገኚባት ተዓምረኛ ከተማ ናት፡፡ ህዝቡ አሁን ባለው አመራር ግን ደስተኛ በመሆኑ ደስታውን ለመግለጽ የከተማ አስተዳደሩን ቢሮ (የከንቲባውን) ፅ/ቤት በራሱ ወጪ በዘመናዊ መንገድ ሰርቶ አጠናቅቋል፤ ጥር ላይ ይመረቃል። በጣም ከፍተኛ በጀት ነው የወጣው ሲመረቅ በሪፖርት ያቀርቡታል። ህዝብ ሲምን ተዓምር ይሰራል። አንተ ውጣና ልቀቅ ስንጨርስ ትመጣለህ ብለውኝ ቢሮዬ ሌላ ቦታ ነው። ይሄ የሚገርም ነው። እንዳልኩሽ በሚያዚያ ወር በምናካሄደው ትልቅ ዓለም አቀፍ ባዛርና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የደሴና የዙሪያዋ ፍሬዎች፣ ወዳጆቿና የደሴ አድናቂዎች ይሰባሰባሉ። ታሪክና ቅርሷ እንዴት ተጠብቆ መቆየት እንዳለበትና ለዓለም ቱሪስቶች በምን መልክ ይተዋወቅ የሚለው ጉዳይ ላይም ይመክራሉ። በዚህ ዝግጅት ደሴን ወደ ቀደመ ልዕልናዋ እንመልሳታለን። ለዚህ የእናንተም የሚዲያዎች እገዛ ያስፈልገናል። አመሰግናለሁ።

Read 13335 times