Saturday, 27 October 2012 10:11

በሜቄዶንያ ማዕከል ያገኘሁትን ድሎት ጤናና ጉልበት በነበረኝ ጊዜ እንኳ አልኖርኩትም

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)

 

እናትም ሆነች ዘመድ የሚፀየፈውን በሽተኛ እሱ ምንም ሳይመስለው ቀርቦ ያገላብጠዋል፡፡ የሚኖረውና የሚበላው ከእኛው ጋር ነው፡፡ ለእሱ የተለየ ወጥ አይሠራለትም - ለእኛ የተሠራውን ወጥ ነው የሚበላው፡፡ ሁላችንም መብላታችንን ካላረጋገጠ ግን አይበላም፡፡ ከዳንኩ በኋላም በገንዘብና በአንዳንድ ነገሮች እየረዳኝ ነው፡፡ “ራስህን የምትችልበትን መንገድ እያመቻችሁ ነው” ብሎኛል፡፡ እኔም ከቤተሰቦቼ ጋር በቅርቡ ለመገናኘት አቅጃለሁ፡፡“ተንከባክበው ነው የያዙኝ፡፡ እንደ ሙሽራ አልጋ ላይ ተኝተን እንደ ልባችን ጥሩ ምግብ በልተን፤ ጥሩ ለብሰን አምሮብን እንኖራለን፡፡ በየቀኑ ገላችንን በሙቅ ውሃ እንታጠባለን፡፡ በቀን ቁርስ፣ ምሳ መክሰስ እራት አራት ጊዜ እንደፈለገን አማርጠን እንበላለን፡፡”በሜቄዶንያ ማዕከል ያገኘሁትን ድሎት ጤናና ጉልበት በነበረኝ ጊዜ እንኳ አልኖርኩትም

ኮተቤ አካባቢ ያለና በጊዜው በጣም ጥሩ የተባለ ቪላ ቤት ነው፡፡ ግቢውን ከፍተው ሲገቡ በግራ በኩል በተተከለ ድንኳን ውስጥ አንድ አሮጌ መኪና ቆማለች፡፡ ከቪላው ፊት-ለፊትና በስተቀኝ በኩል በርከት ያሉ ቢጫ ፕላስቲክ ወንበሮች ይታያሉ፡፡
ጥቂት አረጋውያን ወንበሮቹ ላይ ሆነው የረፋድ ፀሐይ ይሞቃሉ፤ ጥቂቶች ደግሞ የፀሎት መጽሐፍ እያነበቡ ነበር፡፡
አንድ መነኩሴ ደግሞ የቪላውን በረንዳ ተጠግተውና መቋሚያቸውን ተደግፈው ቆመዋል፡፡ ወደ ቪላው ጀርባ ሲሄዱ መኻል ላይ አንድ ሰፋ ያለ መጠለያ ድንኳን አለ፡፡ በርከት ያሉ ሴትና ወንድ ሕሙማንና አቅመ ደካማ አዛውንቶች፣ በመካከለኛ ዕድሜ ያሉ አዋቂዎች፣ ወጣትና ልጆች የአዕምሮ ሕሙማን - ድንኳኑ ውስጥ ሆነው ከአንዱ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ የሚተላለፈውን የእሁድ ፕሮግራም የሚያዳምጡ ይመስላል፡፡ አንድ ወጣት ደግሞ (የአዕምሮ በሽተኛ) ያለማቋረጥ ድምፅ ያሰማል፡፡
ለቪላው ከተሠሩት ሰርቪስ ክፍሎች ውስጥ በሁለተኛ ክፍል በረንዳ ላይ አንድ ሰው የስፌት መኪና አቁሞ ልብስ ይሰፋል፡፡ ከድንኳኑ ፊት-ለፊት ያለው ጠባብ ክፍል እንደ ቢሮ የሚገለገሉበት ነው፡፡ ክፍሉ አሮጌ ሶፋዎችና ሁለት ኮምፒዩተሮች የተቀመጡበት ጠረጴዛ ይዟል፡፡ በጐ ፈቃደኛ ወጣቶች ግማሹ ቆሞ፣ የቀረው ተቀምጦ የተለያዩ ፋይሎች ያገላብጣሉ፡፡ በኤል ቅርፅ የተሠሩት ሰርቪሶች 10 ሲሆኑ፣ 20 አልጋዎች ይዘዋል፡፡
ከቢሮው ጐን ባለው ዘቅዘቅ ያለ ስፍራ ደግሞ 5 አዲስ ክፍሎች ተሠርተው 10 አልጋ ይዘዋል፡፡ ከድንኳኑ ጀርባ ደግሞ ምግብ ማዘጋጃው ማድቤት ውስጥ ከድርጅቱ ባገኙት ድጋፍና ሕክምና የተፈወሱ በጐ ፈቃደኛ ሴቶች ምግብ እያዘጋጁ ነበር፡
በዋናው ቪላ ቤት ሳሎኑን ጨምሮ በተለያዩ ክፍሎች 60 አልጋዎች ተጠጋግተው ተዘርግተዋል፡፡
ከፍ ሲል በዓይነ-ኅሊና ያስጐበኘኋችሁ ግቢ ክፍሎችና አልጋዎች በሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ደጋፊ ጧሪና አስታማሚ ያጡ በየጐዳናውና በየቤተክርስቲያኑ ወድቀው የተገኙ አቅመ ደካማና በሽተኛ አረጋውያን፤ አካለ ስንኩላንና የአዕምሮ በሽተኞች የሚጦሩበትና የሚገለገሉበት ማዕከል ነው፡፡
በዚህ ሠናዬ ምግባር ማዕከል 80 አቅመ ደካማ አረጋውያን የአዕምሮ ሕሙማን እንዲሁም በተደረገላቸው ድጋፍና ሕክምና ተሽሏቸውና ድነው ያለ ምንም ክፍያ በነፃ አገልግሎት የሚሰጡ 20 በጐ ፈቃደኞች በአጠቃላይ መቶ ሰዎች እየኖሩበት ነው፡፡
አቶ ግርማ አሰፋ የ47 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡ ትዳርና ሦስት ልጆች ያፈሩ በሱቅ ንግድ የሚተዳደሩና ጥሩ ኑሮ የነበራቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ አቶ ግርማ ጨርቆስ ገበያ የነበረው ሱቃቸው ሲቃጠል ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህ የተነሳ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸዉን አገር ቤት ልከው እሳቸው ወደ ተለያዩ ክፍለ ሀገሮች እየሄዱ በመሥራት መጠነኛ ገንዘብ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ነገር ግን ጥረታቸው ፍሬ አላፈራም፡፡ ሌቦች ገንዘቡን ዘርፈው ባዶ አስቀሯቸው፡፡ የሚበሉትና የሚቀምሱት ሲያጡ ወደ ጐዳና ወጡ፡፡ በዚህ ዓይነት ልደታ አካባቢ ለ7 ዓመት ታመውና የአልጋ ቁራኛ ሆነው ቆዩ፡፡
ከዚያም የሜቄዶኒያ ማዕከል መሥራች አቶ ቢኒያም በለጠ አገኛቸውና አነጋገራቸው፡፡ አቶ ግርማም ታሪካቸውን ነግረው፣ በዚያ የተነሳ ጐዳና መውደቃቸውንና የአልጋ ቁራኛ መሆናቸውን ገለፁለት፡፡ አቶ ቢኒያምም “ምንም ችግር የለም እኔ አሳክሞታለሁ” ብሎ አንስቷቸው ወደ ማዕከሉ እንዳመጣቸው ተናግረዋል፡፡
“ከጐዳና አንስቶ ጤና ጣቢያ ወሰደኝ፡፡ ጤና ጣቢያውም ለምንሊክ ሆስፒታል ጻፈልኝ፡፡ እዚያ 10ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከኪሱ አውጥቶ አሳከመኝ፡፡
የሚገርመው ደግሞ ገንዘቡን ማውጣት ብቻ ሳይሆን “አይዞህ ትድናለህ፤ እዚህ ካልተሻለህ ውጭ አገር ወስጄ አሳክምሃለሁ” እያለ በሸክም ከወዲያ ወዲህ ሲያመላልሰኝ ቆይቶ አዳነኝ፡፡ ከዚያም የጡረተኝነት ስሜት እንዳይሰማኝ በማሰብ ምን መሥራት እንደምችል ጠይቆኝ ይህን የልብስ ስፌት መኪና ገዛልኝ፡፡ አሁን የአረጋውያንን ጋዋንና ሌላም ከአካባቢው የማገኘውን እየሰፋሁ እጠቀማለሁ፡፡
በጣም የሚገርመው ደግሞ ደጋፊና መጠለያ አጥተን በየጐዳናው የወደቅነውን አንስቶ አሳክሞ ማዳን፣ መጠለያ መስጠት፣ ማብላትና ማጠጣት … ብቻ ሳይሆን፣ ለእኛ ለድሆችና ሕሙማን ያለው አመለካከትና ፍቅር ነው፡፡
እናትም ሆነች ዘመድ የሚፀየፈውን በሽተኛ እሱ ምንም ሳይመስለው ቀርቦ ያገላብጠዋል፡፡ የሚኖረውና የሚበላው ከእኛው ጋር ነው፡፡ ለእሱ የተለየ ወጥ አይሠራለትም - ለእኛ የተሠራውን ወጥ ነው የሚበላው፡፡ ሁላችንም መብላታችንን ካላረጋገጠ ግን አይበላም፡፡ ከዳንኩ በኋላም በገንዘብና በአንዳንድ ነገሮች እየረዳኝ ነው፡፡ “ራስህን የምትችልበትን መንገድ እያመቻችሁ ነው” ብሎኛል፡፡ እኔም ከቤተሰቦቼ ጋር በቅርቡ ለመገናኘት አቅጃለሁ፡፡
“እውነቴን ነው የምለው ወጣት ቢሆንም በአስተሳሰብ፣ በተግባርና በባህርይው በጣም ትልቅ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ይስጠው ከማለት በስተቀር የምለው የለኝም፡፡ ስለ እሱ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ቤተክርስቲያን ለመሳለም ሲሄዱ ለኔ ቢጤ 10 እና 5 ሳንቲም ከሚለግሱ እዚህ መጥተው እሱ ለብቻው የሚሠራውን አይተው የአቅማቸውን ያህል ቢለግሱ፣ ከዚህ በጣም በላቀ ደረጃ ብዙሃን ችግረኞችን መደገፍ ይቻላል” በማለት ስለ ቢኒያም ያላቸውን አድናቆትና ምስክርነት ገልጸዋል፡፡ ወ/ሪት አስካለ ደሴ፣ ዕድሜያቸው 47 ቢደርስም ልጅ ሊኖራቸው ቀርቶ ወንድ ነክቷቸው እንደማያውቅ ይናገራሉ፡፡ ሁለት ወንድሞቻቸው በጦርነት ስለሞቱ ምንም ዘመድ የላቸውም፡፡ ትውልዳቸው ደብረ ሊባኖስ አካባቢ ቢሆንም አዲስ አበባ ሰው ቤት (ፈረንጆች ጋ) እየሠሩ ይተዳደሩ ነበር፡፡ ሥራውን በቋሚነት እንዳይሠሩ የሆድ ውስጥ ሕመማቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ ሲሻላቸው ሲሠሩ፣ ሲያማቸው ሲያቆሙ ቆይተው ሲብስባቸው ሥራውን እርግፍ አድርገው ቢተውትም ዘመድ ስለሌላቸው ማረፊያ አልነበራቸውም፡፡
ኮተቤ አካባቢ ሄደው ለሚያውቁት ቤተሰብ ችግራቸውን ተናግረው እንዲያስጠጓቸው ለመኑ፡፡
የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ሰዎቹ ቅን ነበሩና “ምንም ችግር አይግባዎት፡፡ ባዶ ክፍል ስላለ እዚያ ይኖራሉ” ብለው አስጠጓቸውና 6 ዓመት ኖሩ፡፡ የሆዳቸው ሕመም ሳይለቃቸው አንገታቸው ላይ እባጭ ወጣ፡፡
አንድ ዓመት እንደምንም ተቋቁመው ቢቆዩም አቃታቸውና አልጋ ያዙ፡፡ ሰዎቹ አንድ ዓመት ካስታመሟቸው በኋላ፤ እማማ በሽታዎ አልድን አለ፡፡
እኛም ከአቅማችን ላይ ሆነ” አሏቸውና ወደሜቄዶኒያ ማዕከል ሄደው ስለሁኔታቸው ነገሩ፡፡ የማዕከሉ ሰዎች ሄደው አዩዋቸውና “በቃ እኛ እናሳክማቸዋለን” ብለው ወሰዷቸው፡፡ “ያኔ ሥጋዬ አልቆና ምንምን ብዬ 35 ኪሎ ነበርኩ” ብለዋል - ወ/ሪት አስካለ፡፡
ማዕከሉ አርሾ ወስዶ ሲያስመረምራቸው በሽታቸው ሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ሆኖ ተገኘ፡፡ ከዚያም ምንሊክ ሆስፒታል እያመላለሰ አሳከማቸውና የ6 ወር መድኃኒት ተሰጥቷቸው መዳናቸውን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሪት አስካለ በአሁኑ ወቅት መሄጃና የሚያስጠጋቸው ዘመድ ስለሌላቸው በበጐ ፈቃደኝነት በማዕከሉ ውስጥ እያገለገሉ ነው፡፡
“ተንከባክበው ነው የያዙኝ፡፡ እንደ ሙሽራ አልጋ ላይ ተኝተን እንደ ልባችን ጥሩ ምግብ በልተን፤ ጥሩ ለብሰን አምሮብን እንኖራለን፡፡ በየቀኑ ገላችንን በሙቅ ውሃ እንታጠባለን፡፡ በቀን ቁርስ፣ ምሳ መክሰስ እራት አራት ጊዜ እንደፈለገን አማርጠን እንበላለን፡፡” ብለዋል፡፡
አቶ ኃ/ማርያም ወርቅነህ ዕድሜያቸውን በትክክል አያውቁም፡፡ በኢጣሊያ ወረራ ጊዜ የ5 ዓመት ልጅ እንደነበሩና ከእናታቸው ጋር ዋሻ ውስጥ ያድሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዚያ ስሌት ዛሬ የ82 ዓመት አዛውንት ናቸው ማለት ነው፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ፍቼ አካባቢ ውድሱ ዮሐንስ፣ አረፋምባ ሚካኤል በተባለው ስፍራ ተወልደው እንዳደጉ ይናገራሉ፡፡
በግብርና ይተዳደሩ የነበሩት አቶ ኃ/ማርያም፤ እግራቸው ሲታመሙና ዓይናቸው አላይ ሲላቸው፣ ዘመድ ጠላቸው፡፡ መሬታቸውን እያረሰ የሚጠቀመው ወንድማቸውም ትንሽ ጊዜ ከጦራቸው በኋላ ሚስቱ “ይህንን ሽማግሌ አልቀልብም” አለች፡፡ ካልያዛችሁኝማ በችጋር አልሞትም ብለው አውጡኝ አሉ፡፡ በመኪና ወስዶ ፍቼ ተ/ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አወረዳቸው፡፡
“ከዚያ በኋላ አስፋት ላይ ተኝቼ እጄን እያውለበለብኩ ስለምን የአዲሳባ ጣድቃን ሲዘከረኝና ሲሰጠኝ ዱርዬ እየቀማኝ፣ ከላይ ፀሐይ ከስር ቅዝቃዜ ሲያሰቃየኝ ቆይቼ፣ እኔ ጌታ ሰጠኝ ነው የምለው፣ አምና መጥቶ “ልጅ የለዎትም?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ የለኝም አልኩት፡፡ “ይነሱ፤ እኔ እጦርዎታለሁ” ብሎ አምጥቶኝ ይኼው አልጋ ላይ እንፈላሰሳለሁ፡፡ ጧት ቁርሳችንን ሻይና ዳቦ፣ ቀን ላይ የጠገበ ምሳ፣ ማታ የጠገበም ራት እንበላለን፡፡ ገላችንን እንታጠባለን፤ ንፁህ ልብስ እንለብሳለን፡፡ አንቀባሮ ነው የያዘን፡፡ ጤና ጉልበት በነበረኝ ጊዜ እንኳ እንደዚህ አልኖርኩም”፡፡
ሕይወት ስለሺ የ21 ዓመት ወጣትና የጐዳና ተዳዳሪ ነበረች፡፡ እናቷ በልጅነቷ ስለሞቱ አያቷ ናቸው ያሳደጓት፡፡ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ አያቷ ሲሞቱ አንኮበር የሚያስተምሩት አባቷ ጋ ሄደች፡፡ እዚያ ግን ከእንጀራ እናቷ ጋር መስማማት ስላልቻለች፣ ከአባቷ ገንዘብና የእናቷን ወርቅ ተቀብላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳ ጐዳና መኖር ጀመረች፡፡
ገንዘብና ወርቋን ዱርዬዎች ሲቀሟት አባቷ ጋ ተመለሰች፡፡ አባቷም “ገንዘብና ወርቁን ወስደሽ የዱርዬ ሲሳይ አደረግሽ፡፡ አሁን የመጣሽው ገንዘብ ልትወስጂ ነው? በይ ሂጂልኝ” ብለው አባረሯትና ወደ ጐዳና ሕይወቷ ተመለሰች፡፡ ሕይወት በልጅነት የጀመራት የሚጥል በሽታ አለባት፡፡ አያቷ አማኑኤል ሆስፒታል ወስደው አሳክመዋትና መድኃኒት ተሰጥቷት እየዋጠች ተሽሏት ነበር፡፡ መድኃኒቱ ሲያልቅባት ሆስፒታል ሄዳ አልወሰደችም፡፡ ስለዚህ ይጥላት ጀመር፡፡ በጐዳና ሕይወቷም ዱርዬዎች ብዙ ጊዜ ይደፍሯትና በደሎች ይፈጽሙባት ነበር፡፡ ለአባቱ ሰጠችው እንጂ አንድ ልጅም ወልዳለች፡፡ የጐዳና ኑሮ ሲመራት ቤተክርስቲያን ተጠጋች፡፡ ድርጅቱ ያገኛት እዚያ ነው፡፡
ወደ ማዕከሉ አምጥቶ አሳከማት፣ ጥሩ መኝታ ሰጣት፣ እየመገበ ንፁህ አልብሶ ተንከባከባት፡፡ አሁን ተሽሏታል፡፡ ወደ ማዕከሉ ከመጣች ወዲህ ጥሏት አያውቅም፡፡ ኑሮም እንደተመቻት ተናግራለች፡፡
ድርጅቱ በርካታ ጐዳና ላይ የወደቁ ሕሙማንን አንስቶ እያሳከመና እየተንከባከበ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መሐመድ ይባላል፡፡ መሐመድን አንስተው ያመጡት ከደብረዘይት ነው፡፡
መሐመድ አሁን ቢሻለውም አይናገርም፡፡ ብርድ ልብስ ለብሶና አልጋው ላይ ተቀምጦ ነው ያገኘሁት፡፡ የማዕከሉ መስራች የነገረኝንና ከመንገድ ሲያነሱት ከተቀረፀው ቪዲዮ ያየሁትን ላጫውታችሁ፡፡
መሐመድ መች ወደ ጐዳና እንደወጣ በትክክል አይታወቅም፡፡ ከጐዳና ሲያነሱት በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች አንዳንዱ “ከ4 ወር በፊት እዚህ መጥቶ ተኛ” ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “የለም እዚህ ከወደቀ ሁለትና ሦስት ወር ቢሆነው ነው” ይላሉ፡፡
ቪዲዮውን ብታዩ ከሰው ገላ እንዲህ ዓይነት ነገር ይወጣል ብላችሁ ስለማትገምቱ በጣም ትደነግጣላችሁ፤ ትገረማላችሁ፣ ይዘገንናችኋል፡፡ ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ባይታወቅም ገላውን ታጥቦና የግል ንፅህና የሚባል ነገር ጐብኝቶት እንደማያውቅ መገመት ቀላል ነው፡፡
ለብዙ ጊዜ ተኮራምቶ ከተኛበት ስፍራ አንስተው ሲያጥቡትና ንፁህ ልብስ ሲያለብሱት የሚታየው ትዕይንት በጣም ዘናግኝ ነበር፡፡ ከጭኑ ፀጉር ውስጥ የወጣው በጣም የሚገርምና ለመግለጽም የሚቀፍ ነው፡፡ እንዴት ብዬ ልግለጽላችሁ? የሞተ ውሻ ወይም ድመት … መንገድ ዳር ወድቆና ቆይቶ ሲበሰብስ የሚፈጠሩ ትሎች ሳታዩ እንዳልቀራችሁ እገምታለሁ፡፡ መሐመድ ሲታጠብ ከጭኑ ይወጡ የነበረሩት ትሎች እንደዚያ ዓይነት ነበሩ፡፡
መሐመድን አምጥተው ሲያስመረምሩት በሽታው ሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ሆኖ ተገኘ፡፡ አመላልሰው ስላሳከሙትና መድኃኒቱን በትክክል እንዲወስድ በመደረጉ አሁን ድኗል፡፡
አሁን ያስቸገረው ለብዙ ጊዜ ጉልበቱን አጥፎና ተኮራምቶ የቆየበት እግሩ አልዘረጋ እያለው ነው፡፡
ይህን የመሰለ የተቀደሰ ምግባረ-ሠናይ ተግባር የሚሠራው ማነው? ሳትሉ የቀራችሁ አይመስለኝም፡፡ ቢኒያም በለጠ አዲስ ይባላል፡፡ የ35 ዓመት ጐልማሳ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ (ኤል ኤል ቢ) አለው፡፡ ከአሜሪካ-ሚኒሶታ ሴት ሜሪ ዩኒቨርሲቲ በምግባረሠናይ ተግባር (ፊሊያንትሮፒ) ማስተርስ አለው፡፡
የቢኒያም ቤተሰብ እናትና አባቱ እህት ወንድሞቹ በሙሉ የሚኖሩት አሜሪካ ነው፡፡ እሱም እዚያ 7 ዓመት ሲኖር የተለያዩ ሥራዎች ይሠራ እንደነበር ገልጿል፡፡
ሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በቢኒያምና በቤተሰቡ ድጋፍ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ አባቱ አቶ በለጠ አዲስ ከ30 ዓመት በፊት ሼል ኢትዮጵያ ይሠሩ ነበር፡፡ በወቅቱ ደሞዛቸው 4ሺህ ብር ይደርስ ነበር፣ አሁን አገልግሎት እየሰጠበት ያለውን መኖሪያ ቤት ከመሥራትና ድሆችና አቅመ ደካሞችን ከመርዳት በስተቀር ለግላቸው ምንም እንዳላደረጉበትና ለቤተሰቡ ቅርስ እንዳላቆዩ ቢኒያም ተናግሯል፡፡ “አባቴ አንድ ያለውን ቤት እንድጠቀምበት ፈቀደልኝ፡፡ አገልግሎት መስጫውን በነፃ አገኘሁ ማለት ነው፡፡ አሁን አባቴ ቢመጣ ማረፊያ ቤት የለውም፤ ሆቴል ነው የሚያርፈው” ያለው ቢኒያም፤ ድርጅቱ የሚንቀሳቀሰው እህትና ወንድሞቹ በተለይም እህቱ ፍሬሕይወት በለጠ በየጊዜው በምታደርግለት ድጋፍና ራሱም አሜሪካ በነበረበት ወቅት ባጠራቀመው ገንዘብ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ይህ ማዕከል ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመቱ ነው ያለው አቶ ቢኒያም፣ በ20 ተረጂዎች ጀምረው አሁን 80 መድረሳቸውንና ከበጐ ፈቃደኛ አገልጋዮች ጋር መቶ ሰዎች በግቢው እንደሚኖሩ ገልጿል፡፡ እነዚህ ተረጂዎች አብዛኞቹ ጐዳና ላይ የነበሩ፣ የአልጋ ቁራኛና ራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ነበሩ፡፡ አሁን ከዚያ ሕይወት ተላቀው አልጋ ላይ ይተኛሉ፤ ምግብና ልብስ፣ የጤና ክትትልና ሕክምና … ያገኛሉ፡፡ የአልጋ ቁራኛ የነበሩ ድነው የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጥሩ ሕክምናና ምግብ በቀን አራት ጊዜ ስለሚያገኙ ነው፡፡
መካከለኛ ኑሮና ገቢ ካለው ሰው በተሻለ ደረጃ ይኖራሉ፡፡ የፈውሳቸው ሌላው ምክንያት እንደ ቤተሰብ በመኖራቸው በጣም ደስተኞች አድርጓቸዋል፡፡ ለገንዘብ ብለው ሳይሆን ለነፍሳቸው ብለው የሚንከባከቧቸው ከገዳም የመጡ ሦስት በጐ ፈቃደኞች አሉ፡፡ እዚህ ሲረዱ ቆይተው የዳኑና በበጐ ፈቃደኝነት የሚሠሩ ሰዎችም አሉ፡፡
እነዚህ ተረጂዎች በበጐ ፈቃደኞች እንክብካቤና ፍቅር እያገኙ እንደ ቤተሰብ ይኖራሉ፡፡ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡
ሕክምናን በተመለከተ የአዕምሮ ሕሙማን አማኑኤል ሆስፒታል እንወስዳቸውና ተመርምረው መድኃኒት ይሰጣቸዋል፤ እዚህ ይወስዳሉ፡፡ ሌሎች በሽተኞችን ደግሞ ጤና ጣቢያ እንወስዳቸውና ወደ ሪፈራል ሲጽፉልን ምንሊክ ሆስፒታል ወስደን እናሳክማቸዋለን፡፡ የሆስፒታሉ ሰዎች ስለለመዱን አሁን ብዙ ጊዜ ሪፈራል ወረቀት አይጠይቁንም ብሏል፡፡
በሚዲያ ከተነገረ በኋላ እዚህ እየመጡ የቁስል ፋሻ የሚለውጡ፣ ጉሉኮስ የሚቀጥሉ በጐ ፈቃደኛ ነርሶች አሉ ያለው አቶ ቢኒያም፤ ሜቄዶኒያ የሚንቀሳቀሰው በበጐ ፈቃደኞች እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በየሆስፒታሉ የሚሰጠው ሕክምና መሻሻሉን ጠቅሶ፣ ጥቁር አንበሳም ሆነ ምንሊክ ሆስፒታል እየከፈሉ እንደሚያስተኙ ገልጿል፡፡ “ለምሳሌ መሐመድ አንድ ወር ነው ምንሊክ ሆስፒታል የተኛው፡፡
ሕክምናው ጥሩ ቢሆንም “ውጭ አስመርምር” ብለው የሚልኩት ወጪው ከበድ ይላል፡፡ እኛ ለሕክምና በወር እስከ 80ሺህ ብር እናወጣለን፡፡ ወጪያችን ትንሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ምክንያቱም የቤት ኪራይ ስለሌለብንና የሠራተኛ ደግሞ ስለማንከፍል ነው፡፡ ወደፊት ነፃ ሕክምና ለመጠየቅ አስበናል በማለት አብራርቷል፡፡ የቀን ልብስ ሰው ስለሚሰጣቸው ችግር የለባቸውም፡፡ አልጋ፣ ፍራሽ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ ግን ገዝተው ነው የጀመሩት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ብርድ ልብስ እያገኙ ነው፡፡ 21ኛው የዓለም አረጋውያን ቀን የተከበረው እነሱ ጋ ነበር፡፡ በዚያ በዓል አምስት ብርድ ልብሶች፣ እንዲሁም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የአረጋውያንን ቀን ሲያከብር ብርድ ልብስ ከተሸለሙ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ መሆናቸውን አቶ ቢኒያም ተናግረዋል፡፡
የሜቄዶኒያ ማዕከል የገንዘብ ምንጭ እስካሁን ድረስ ቢኒያምና ቤተሰቡ ናቸው፡፡ ከቤተሰብ ውጭ ማንም ሰው ሳይረዳቸው ነው በራሳቸው የጀመሩት፡፡ “አሁን ግን ዜናው በሚዲያ መተላለፍ ሲጀምር በተለይ በኢ.ቢ.ኤስ ተደጋግሞ ከተላለፈ በኋላ ሰዎች እየመጡ እየጐበኙን ልብስ ያመጡልናል፣ ብርም የሚሰጡን አሉ፡፡ ቋሚ የሆነ ድጋፍ ግን የለም፡፡
አንድ ባለሀብት በተለያዩ ጊዜያት እስካሁን 150ሺህ ብር ረድቶናል፡፡ ዲ ኤች ገዳ አራት ኩንታል የስንዴ ዱቄት ፈቅዶልናል፡፡ መቶ ብርድልብስም ረድቶናል፡፡ ንግድ ባንኮችም ሊረዱን ንግግር ላይ ነን፡፡ እስካሁን ድረስ ቋሚ ድጋፍ ባይኖረንም አሁን ግን ሰዎች ሊረዱን እየመጡ ነው” ብሏል፡፡
አቶ ቢኒያም አሁን ዋነኛ ችግር የሆነባቸው የቦታ ጥበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ መንግሥት ቦታ በነፃ ከሰጣቸው እሰየው ነው፡፡ ነገር ግን ቦታ ባያገኝም አሁን ባሉበት ግቢ ውስጥ በቤተሰቡ ወጪ ባለ 5 ፎቅ ቤት በመሥራት፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ከ300-500 ሰዎች ለመያዝ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር የየካ ክ/ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት የጥናት ዕቅድና በጀት ዋና የሥራ ሂደት፣ ጳጉሜ 2 ቀን 2004 በስፍራው ተገኝቶ ባደረገው የሥራ ግምገማ፣ ድርጅቱ ፕሮጀክቱን በተፈለገው መንገድ ተግባራዊ እያደረገ በመሆኑ መደሰቱን ገልፆ የመሥራቹንና የበጐ ፈቃደኞችን ቁርጠኝነት በማድነቅ የምሥጋና ደብዳቤ ጽፏል፡፡
የገምጋሚው ቡድን በጉብኝቱ ወቅት ተገልጋዮቹ ሲታመሙ ወደ ሐኪም ቤት የሚወስዳቸውና የሚመልሳቸው አንቡላንስ ወይም መኪና እንደሌለው፣ ድርጅቱ ሊገነባ ላቀደው ሕንፃ የቦታ ጥበት (ችግር) እንዳለበት ገልጿል፡፡
ድርጅቱ ቋሚ የገንዘብ ምንጭ ቢኖረው ይሻላል፤ ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ከወረዳው አስተዳደር ጋር ቢሠራ ጥሩ ነው፤ የመጀመሪያ ዕርዳታ መስጫ በጣም አስፈላጊ ነው፤ የአዕምሮ ሕሙማንን የሚረዳ የሥነ-ልቦናና የሥነ-አዕምሮ ባለሙያ ቢኖረው ጥሩ ነው፤ ድርጅቱን የሚያስተዋውቅ በራሪ ወረቀትና ጽሑፍ ቢዘጋጅ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

 

images/stories/667/negedna econome 2.jpg

መካከለኛ ኑሮና ገቢ ካለው ሰው በተሻለ ደረጃ ይኖራሉ፡፡ የፈውሳቸው ሌላው ምክንያት እንደ ቤተሰብ በመኖራቸው በጣም ደስተኞች አድርጓቸዋል፡፡ ለገንዘብ ብለው ሳይሆን ለነፍሳቸው ብለው የሚንከባከቧቸው ከገዳም የመጡ ሦስት በጐ ፈቃደኞች አሉ፡፡ እዚህ ሲረዱ ቆይተው የዳኑና በበጐ ፈቃደኝነት የሚሠሩ ሰዎችም አሉ፡፡

Read 27532 times Last modified on Saturday, 22 December 2012 11:42