Saturday, 17 December 2022 14:07

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በኢትዮጵያ ከግማሽ የሚበልጡ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ በጥናት ተረጋገጠ


      በኢትዮጵያ ከግማሽ የሚበልጡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ማንበብ እንደማይችሉ አዲስ የተሰራ ጥናት አመላክቷል።  ራይዝ ኢትዮጵያዊ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን የጥናት ውጤት ከትናንት በስቲያ  ይፋ ማድረጉን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።
ራይዝ ኢትዮጵያዊ በሰራው ጥናትም፤ 68 በመቶ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች እና 51 በመቶ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ ማረጋገጡን አስታውቋል።
በኢትዮጽያ በ168 የተለያዩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ በ9 ሺ ተማሪዎች በተደረገው ጥናት መሰረት ፤ 68 በመቶ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች እና 51 በመቶ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ ተገልጿል።
በተጨማሪም በቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ለይ እና ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መፃፍ፣ ሂሳብ ማስላት፣ የተረጋጋ ስነ-ልቦና እና መልካም ማህበራዊ መስተጋብርን የመሰሉ መሰረታዊ ክሎት እንዲኖራቸው መሰራት አለበት ተብሏል።
የተማሪዎችን የትምህርት ዉጤት ለማሻሻል የትምህርት ስርዓቱ የተናበበና የተቀናጀ ትግበራ እንደሚያስፈልገው በጥናቱ ላይ ተመልክቷል።
በጥናቱ ላይ የትምህርት ስርዓቱ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ እንደሚገባ መጠቆሙን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማህበራዊ የትስስር ገጹ አስታውቋል። እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ፣ ለምንድን ነው በአዲስ አበባ በት/ቤቶች በሚሰቀል ባንዲራና መዝሙር አደገኛ ውዝግብ ውስጥ የገባነው? በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
__________________________________________

               አዲስ አበባ የሁላችንም ናት!
                 ሙክታሮቪች ኡስማኖቫ


      ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም አንዴ ምን አሉ?
“እኔ የጥበብ ሰው ብዬ የምገልፀው አንድ ሰው ጥቀስ ብባል ቴዲ አፍሮን ነው”
የቴዲ የጥበብ መነፅር ሁሌ ይገርመኛል። ትልቅ ሀሳብን በአጭርና በሚገርም አገላለፅ ቁጭ ያደርገዋል።
ለምሳሌ USA Live ኮንስርት ላይ ስለ አዲስ አበባ እንዲህ ብሎ አዜመ
አፍሪካን አክሎ የተሰፋው ልብሱ
ኢትዮጵያን አክሎ የተሰፋው ልብሱ
ከምኔው ከምኔው ጠበበሽ ቀሚሱ
አዲሳባ ነበር የጥንቱ ስምሽ
ሁሉ አገርሽ ነበር የጥንቱ ስምሽ
አሁን ከምንጊዜው የኔነሽ አሉሽ::
ወዳጄ አዲስ አበባ ስትመሰረት አፄ ሚኒልክ ባወጁት አዋጅ ላይ እንዲህ የሚል አገላለፅ ነበረ፤
“አበልጄ ሆይ ናና ጎሮቤት ሁነኝ”
በዚህ መሰረት ከአራቱም አቅጣጫ ብሔር ብሔረሰቦች አዲስ አበባን ሁሉ ሐገርሽ አደረጓት።
አዲስ አበባ የሁሉ አፍሪካዊ መዲና ናት። የአለም የዲፕሎማሲ ከተማ ናት። ይህ ሊሆን የቻለው ኢትዮጵያን እንድታክል ደምና አጥንት የተከሰከሰባት የመስዋዕትነት ከተማ ስለሆነች ነው።
ቴዲ የገባው ይህ ታላቅ ሚስጢርን ነው። ለሚገባው ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል።
ሐገር የሁላችን ናት። አዲስ አበባ የሁላችንም ናት። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

______________________________________________

                   “world Monkey Day”
                       ተጓዡ ጋዜጠኛ /ሄኖክ ስዩም/


         ዛሬ በመላው ዓለም “world Monkey Day” ይከበራል። እኛም ዓለም የሌለውን ጭላዳ እያሰብን ከዓለም ጋር እናከብራለን። ዕለቱ ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት መከበር ሲጀምር ጦጣን ብቻ ታሳቢ አድርጎ ነበር። አሁን ዝንጀሮና ኤፕን ጭምር በመዘከር ስለጥበቃቸው ይመክራል።
በዚህ ቀን ከዝንጀሮ ተገኘሁ ያለውን ዳርዊንን ሳይኾን፤ ከአዳም መጣሁ ያሉትን እና ሰውና ዝንጀሮ ያስታረቁትን አቡነ ዮሴፍን አስባለሁ። እንግዲህ ለጦጣ እና ለዝንጀሮ መኖሪያ የምንጨነቀው፤ ከጦጣ እና ከዝንጀሮ የተሻለ የምናስብ የሰው ልጅ ነን በሚል ለራሳችን ስንል ነው።

__________________________________________________


                 ከሼክስፒር ቃለ ተውኔት ተመዝዞ ያጠረ
                     ኤፍሬም ሶልያና

ከናንተ መካከል
የቄሣር
የልብ ወዳጁ ነኝ:የሚል እርሱ ማንነው ?
እነሆኝ አንድ እውነት
እነግረው ዘንድ አለሁ:”እኔ’’ ነኝ ለሚል ሰው።
እርሱም
እኔ ከርሱ በላይ
ያገሪቷን ቄሣር አብልጬ እወዳለሁ።
ነገር ግን መልሼ
ይህንኑ ቄሣር እቃወመዋለሁ።
አሁን
አመክንዮ እንድሰጥ
ምክንያት እንዳስቀምጥ
ለምን ?ለሚለኝ ሰው
የኔ-መልስ ሚሆነው ....?...
ከቄሣሩ በላይ
ታላቂቷን አገር ስለምወዳት ነው።
ማስታወሻ
ግን?
ብሩተስም ቢሆን ?
ይህንን መሰል ቃል ሊናገር የቻለው
ለሥልጣን ጥቅሙና
ለፖለቲካዊ ፍላጎቱ ሲል ነው።

_________________________________________

                   “የአፍሪካ አገራት ክብርን ለማግኘት ምዕራባውያንን ሊለምኑ አይገባም”



         የአፍሪካ አገራት አለም አቀፋዊ ክብርን ለማግኘትና ስለ አህጉሪቱ ያለውን ደካማ አመለካከት ለመቀየር ምዕራባውያንን ከመለመን ራሳቸውን ሊያላቅቁ ይገባል ሲሉ የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ ተናገሩ።
“ልመናችንን አቁመን የአህጉሪቱን ሃብትና ጥሪት እዚሁ ከተጠቀምንበት እኛ አፍሪካውያን ከማንም ክብር መጠየቅ አይኖርብንም። የሚገባንን ክብር እናገኛለን። አህጉሪቷንም መድረስ ወደምትችልበት ብልጽግና ማድረስ  ከቻልን ክብር ይከተላል” በማለት የጋናው ፕሬዚዳንት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት በዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በተከፈተበት ወቅት ነው።
ፕሬዚዳንት አኩፎ፤ በጋራ ለማደግም በአፍሪካውያን መካከል የላቀ ትብብር እንዲኖር አሳስበዋል። “አፍሪካውያን በሃገሮቻቸው ከሚኖሩበት በላቀ በሌሎች አህጉራት ላይ አይበገሬነትን አሳይተዋል። ለውጭው ዓለም እንደ ናይጄሪያዊ፣ ጋናዊ፣ ወይም ኬንያዊ ሳይሆን የጋራ ማንነታችንን፣ አፍሪካዊነትን መዘንጋት የለብንም። እንደ አህጉሪቷ ዜጎች እጣ ፈንታችን እርስ በርስ የተሳሰረ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት፤ አህጉሪቱ ክህሎትና የሰው ሃይል ቢኖራትም የተቀናጀ የፖለቲካ ፍላጎትና ቀናነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንቱ አኩፎ አዶ አስተያየት የተሰማው አገራቸው ያለችበትን የኢኮኖሚ ድቀት ለመቅረፍ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት በተስማማበት ቀን ነው።

____________________________________________________


                  የምንገድ ላይ ቀለህ
                    በድሉ ዋቅጅራ

መቼም እኛ
ከየትኛው ዘመን መለስ÷
ከየትኛው ትውልድ ጀምሮ
ከባህላችን ተጋምዶ÷
ከሕይወታችን ተሳስሮ
እንደተገኘ ባላውቅም
ከልደት እስከ ሞታችን÷
ከነፍጥ እርቀን አናውቅም::
ስንወልድ ተኩሰን
ስንድር ተኩሰን
ባሩድ ባሩድ ሸትተን::
ስንገድል ተኩሰን
አናት ደረት ገምሰን
ስንሞት ጥይት ጎርሰን
ድንጋይ ተንተርሰን
ጎዳና ላይ ወድቀን::
የመስክ ላይ ቀለህ÷
ባድማ የወደቅከው
ያፍርከው የዛግከው
እባክህ ንገረኝ እውነቱን ልወቀው::

Read 1579 times