Print this page
Saturday, 17 December 2022 14:14

“የዘሩት ሲያፈራ” መጽሐፍ ሲዳሰስ

Written by  በፕ/ር አበበ ዘገዬ
Rate this item
(0 votes)

  መግቢያ
“የዘሩት ሲያፈራ” በሚል አርእስት የቀረበው የደራሲ ደመቀ ዘነበ መጽሐፍ፣ በደርግ ዘመን የኩባ መንግስት ለኢትዮጵያ ካደረገው  አስተዋጽኦ ዋነኛውን ከትቦ፣ በሚያምር አቀራረብና ትውስታን ባዘለ አገላለጽ ለአንባቢ አቅርቦልናል፡፡ ይህ መጽሐፍ በዋነኛነት የኩባ መንግስት ለኢትዮጵያ ያደረገውን ድጋፍ የሚገልጽ ሲሆን በዘመኑ በኩባ የተማሩ ኢትዮጵያውያን የነበራቸውን የሀገር ፍቅር እንዲሁም  ዘመናዊና ቅምጥል ኑሮ ሳያማልላቸው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ያደረጉትን ወገናዊ አስተዋጽኦ  በብዙው ይነግረናል፡፡
የኩባ መንግስት እድሜያቸው ከ9-16  አመት የነበሩ ልጆችን ከኢትዮጵያ በመውሰድ እንደ እናትና አባት ተንከባክቦ በማስተማር ለቁምነገር ማድረሱ ታሪክ የማይረሳው ውለታ መሆኑን መጭው ትውልድ እንዲረዳ ይህ መጽሐፍ  ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ በውጭ ሀገር ተምሮ ወደ እናት ሀገር ተመልሶ ሀገራዊ ግዴታን መወጣት ከቀድሞ የኩባ ተማሪዎች የምንማረው  ትልቅ የዜግነት ግዴታ ነው፡፡
የመጽሐፉ ዘውግ ግለ ታሪክ (ማስታወሻ) ሲሆን በ17 አነስተኛ ምእራፎች የተከፋፈለና የሕይወት ዘመን ትዝታ ላይ የሚያጠነጥን ነው። ጸሐፊው  አቶ ደመቀ ዘነበ በመምህርነት ሙያ ኩባ ሀገር በነበሩበት ወቅት በሥራ ስለነበራቸው ተሳትፎ፣ ስለ ኢትዮጵያውያን የኩባ ተማሪዎች፣ ስለ ኢትዮ-ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትና ወታደራዊ ድጋፍ ውለታ  ይተርካል፤ መጽሐፉ፡፡
ደራሲው በተወለዱበት የወሎዋ ደሴ ከተማ ከቄስ ትምህርት ፊደል ጥናትና ግብረገብነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት መዝለቅና በመምህርነት ሙያ ተሰማርተው ሀገራቸውን ማገልገላቸውን በመጽሐፋቸው ያወሳሉ። በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ስሙ ጎልቶ የሚነገርለት የወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት ካፈራቸው ተማሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡ ቀጥለውም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የአማርኛ ቋንቋ መምህር ሆነው እያስተማሩ ሳለ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ ምክንያት ሥራቸውን ለመልቀቅ እንደተገደዱ  ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም የኩባ መንግሥት ባመቻቸው እድል ወደ ኩባ ሄደው እንዲማሩ የተመለመሉትን አንድ ሺ ሁለት መቶ ተማሪዎች ይዘው በሚወዱት የማስተማር ሙያ እንዲሳተፉ ከደርግ መንግስት ጥሪ ተቀብለው፣ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ግዳጃቸውን ተወጥተዋል። በዚያ ስለነበሩ የኩባ ተማሪዎችና መምህራን ማኅበራዊ ትስስርና ውጣ ውረድ፣ በሱማሊያ ወረራ ወቅት መስዋዕትነት ስለከፈሉት የኩባ ወታደሮች ያልተቆጠበ ውለታ  በመጽሐፋቸው አካፍለዋል፡፡
ምዕራፍ አንድ፡-  ከኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ ሥልጣኔ ታላቅነት ባሻገር በየጊዜው የተካሄዱ አሰልቺ ጦርነቶች ለአስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት መጋለጥ፣ ከመካከለኛው ዘመን የፖርቱጊዝ ጣልቃ ገብነት እስከ ሶማሊያው ሰይድ ባሬ የእብሪት ወረራና የኩባ ሶሻሊስት ወታደራዊ ድጋፍ በአጭሩ ያትታል፡፡
ምዕራፍ ሁለት፡-  ስለ ኩባ እና ሕዝቧ ታሪክ፣ ባሕል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ኢኮኖሚ  እንዲሁም ቀደም ሲል ከስፔን አፓርታይድ ቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ እ.ኤ.አ በ1898 ዓ.ም የተደረገው  የነጻነት ትግል ሂደት ወደ ብሔርተኝነት መሸጋገሩ ያስገኘው ውጤት፣ ከአሜሪካ አፍንጫ ስር ስለተወለደው የኩባ አብዮተኞችና የነጻነት ታጋዮች ሆ ማርቲ፣ ፊደል ካስትሮ እና ቼ ጉቬራ ዓይነተኛ ሚና በሰፊው ይተርካል፡፡
ምዕራፍ ሦስት፡- የኢትዮጵያ እና ኩባ ወዳጅነት፣ የባሕል ትስስር መጠናከሩ በተለይም አምባሳደር ካሳ ከበደ የሕጻናትና ጀግኖች አምባ በመልካም እሴት እንዲደራጅ በማድረግ በሱማሊያ ወረራ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት ወደ ማሳደጊያ አምባው እንዲገቡና በኋላም ተመልምለው ወደ ኩባ ጭምር እንዲላኩ የነበራቸውን ጉልኅ አስተዋጽዖ ዘርዘር አድረጎ ያስረዳል፡፡
ከምዕራፍ አራት እስከ ስምንት ያለው የመጽሐፉ ይዘት በአጠቃላይ ወደ ኩባ ሀገር ለትምህርት የተላኩ ወጣት ተማሪዎችና መምህራኖቻቸው  የጉዞ ሁኔታ፣ ውጣ ውረድና ገጠመኞች፣ የኩባ የሥራ ባሕል እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት ተማሪዎች ጋር የነበረው  መስተጋብር ምን እንደሚመስል በደምሳሳው የተመላከተበት ነው፡፡
ምዕራፍ ዘጠኝ እና አስር፡- በኩባ ለኢትዮጵያውን ተማሪዎች ስለ መደበኛ ትምህርት አሰጣጥ፣ የትምህር ቤቶቹ ሥነ ሥርዓት፣ ንድፈ ሃሳብ፣ የሙያ ክህሎት፣ የሰውነት ማጎልመሻ፣ የእርሻ ትምህርት፣ ሁለገብ እውቀት፣ ወታደራዊ ስልጠና፣ ባሕልና ስፖርት ነክ እንቅስቃሴ ተሳትፎን ለሀገራችን የሚኖረውን ፋይዳ ያስረዳል፡፡
ምዕራፍ አስራ አንድ ደግሞ በምዕራፍ ዘጠኝ ከተብራራው ስፖርትና የባሕል ነክ እንቅስቃሴ ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ምዕራፍ አስራ ሁለት እና አስራ ሦስት በኩባ ተማሪዎች እና መምህራን ቆይታ በማኀበራዊ ግንኙነት ረገድ ያጋጠማቸው ያለመግባባት ውዝግቦችን በተለይም የቡድን መሪ የነበሩትን ኮሎኔል አሰፋ በርሔ ጊላይን የአያያዝ ድክመት እንዲሁም ችግሮች እንዲስተካከሉ ለአምባሳደሩና ለፕሬዝዳንት መንግስቱ በማሳወቅ ጭምር የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ ያብራራል።
ምዕራፍ አስራ አራት እና አስራ አምስት፡- የፕሬዝዳንት መንግስቱ በኩባ ያልተጠበቀ ጉብኝት በተማሪዎችና መምህራን ሠራተኞች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖርና ችግሮች እንዳይቀጥሉ ስለማገዙ እንዲሁም መምህራኖቹ ተማሪዎችን እንደ ወላጅ ሆነው በማነጽና በመንከባከብ ተሰጥአዋቸውን እንዲያጎለብቱ ያበረከቱትን ጉልኅ አስተዋጽዖ እንዲሁም የእውቅና አሰጣጥ ሁኔታ በሰፊው ይገልጻል፡፡
ምዕራፍ አስራ ስድስት፡- የቤተሰብ ሕይወትን  በተመለከተ እንዲሁም የኩባ ተማሪዎች የተዋጣላቸው ስፔሻሊስት ሀኪም ሆነው በኢትዮጵያ ዝነኛ ሆስፒታሎች እያበረከቱት ስላለው አስተዋጽኦ በምሳሌነት ጥቂቶቹን (እነ ዶክተር ሙሉዓለም ገሠሠ፣ ዶክተር መብራቱ ጀምበሬ፣ ዶክተር ሸዋዓለም ነጋሽ፣ ዶክተር ስዩም ካሳ፣ ዶክተር ዓለማየሁ ተገኝ የመሳሰሉትን) ጠቅሶ፤ ቀደም ሲል ሲነዛ የነበረውን የትምህርት ጥራት ችግር  ገጽታ ለመቀየር ይሞግታል፡፡
በመጽሐፉ በገጽ 168 ላይ የቀ.ኃ.ሥ  የቤተ ዛታ ሆስፒታል ተብሎ የተጠቀሰው በአርትኦት ክፍተት ምክንያት ሲሆን የቀ.ኃ.ሥ ቤተሳይዳ ሆስፒታል፣ የአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል በሚል ታሪኩን አንባቢ እግረ መንገዱን ቢገነዘበው መልካም ይሆናል፡፡
የመጨረሻው ምዕራፍ አስራ ሰባት፣ የመጽሐፉ ማገባደጃ፣ ዋና ፍሬ ሃሳቡ የሚገኝበት ነው፡፡ በአጠቃላይ የኩባ መንግስት ለኢትዮጵያ የዋለውን ዘርፈ ብዙ ውለታ ይዘክራል፡፡ በኩባ የትምህርት እድል አማካኝነት በልዩ ልዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለማገልገል ቢፈልጉም፣ ለምስራቁ የሶሻሊስት  ርዕዮተ ዓለም በነበረ የተዛባ አመለካከት የተነሳ ሥራ ሳይመደቡ መጉላላት ቢያጋጥማቸውም፣ በሀገር ፍቅር ሚዛን አርአያነታቸውን በኩራት ይገልጻል፡፡ ለኩባ ተማሪዎች አሉታዊ እይታ ሊፈጠር የቻለው ሀገራችን በሰሜኑ የጸረ-ተገንጣይ ጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት የሀኪሞች እጥረት በማጋጠሙ  ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ከኩባ በመጡ ተማሪዎች በተፈጠረ የህክምና ስህተት ምክንያት መሆኑን ደራሲው  በመጽሐፋቸው  አልሸሸጉም፡፡
መደምደሚያ
ይህ የግለ ታሪክ ማስታወሻ በሁለቱ ሀገራት ላይ  ያጠነጠነ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ታሪክ አጠናን የሚኖረው ድርሻ ቀላል አይሆንም፡፡ በተጨማሪም በኩባ የተማሩ ድንቅ ኢትዮጵያውያን  ተግባር  ለአሁኑ የኢትዮጵያውያን ፍልሰት የሚያስተምረው ትልቅ ቁምነገር አለ፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያሉ ዜጎችን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያኖች  ወደ አሜሪካ፤ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ይፈልሳሉ። በመሆኑም እነዚህ ኢትዮጵያዊያን በዚህ መጽሐፍ ከተገለጸው የቀድሞ የኩባ ተማሪዎች ሀገር ወዳድነት ተምረው፣ ወደ እናት ሀገራቸው  ተመልሰው  ያበረከቱትን አስተዋጽኦ  አርአያ ቢያደርጉ ለትውልድ ሀገራቸው የሚኖረው ፋይዳ ብዙ ነው፡፡


Read 6739 times