Saturday, 24 December 2022 15:26

መስከረም አበራ በአስቸኳይ ከእስር እንድትለቀቅ ሲፒጄ ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ)፣ በእስር ላይ የምትገኘው የ”ኢትዮ ንቃት” ዩቲዩብ ሚዲያ መሥራችና ባለቤት መስከረም አበራ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ከእስር እንድትለቀቅና የፕሬስ አባላትን ማዋከብ እንዲቆም አሳሰበ፡፡
ባለፈው ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋለችው መስከረም አበራ፣ ታህሳስ 5 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የቀረበች ሲሆን  የፌደራል ፖሊስ የጠየቀው 14 የምርመራ ቀናት በፍ/ቤት ተፈቅዶለታል፡፡
የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቀናቱን በጠየቀበት ወቅት መስከረም በተጠረጠረችበት “የሽብር ወንጀል ድርጊት መነሻነት የተሰባሰቡ መረጃዎች መኖራቸውን” ለችሎቱ አስታውቋል።
“መስከረም ከዚህ ቀደም ለሳምንታት በእሥር ስትማቅቅ አሳልፋለች፡፡ አሁን በድጋሚ ከሥራዋ ጋር በተያያዘ መታሰሯ በእጅጉ ያሳዝናል” ብለዋል የሲፒጄ የአፍሪካ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ፣ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፡፡
“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መስከረምን በአፋጣኝ ከእስር መልቀቅና የተመሰረተባትን ማንኛውንም ክስ ማቋረጥ አለባቸው” ያሉት የሲፒጄ ተወካይ፤ “ያለ ተጨማሪ ጣልቃ ገብነት ሥራውን እንድትቀጥልም ሊፈቀድላት ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ መስከረም አበራ ለእስር ስትዳረግ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር ውላ ነበር፡፡ ለ23 ቀናት በእስር ያሳለፈችው መስከረም፤ ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ነበር  ከእስር የተለቀቀችው፡፡  

Read 12185 times