Saturday, 27 October 2012 10:20

ትንሽ እውቀትና ጭፍን አመለካከት

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

ፕሪንስ ጆንሰን እና ፓውሊን ንይራማሱሁኮ
በ2011 ዓ.ም በላይቤሪያ በተካሄደው የፕሬዚዳንትነት ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ ተቀናቃኞቻቸውን በተቀላሉ በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው ይመረጣሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ የምርጫው የመጀመሪያ ውጤት ግን ተቃራኒውን አመለከተ፡፡ ፕሬዚዳንት ሲርሊፍና ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ዊንስተን ተብማን አንዳቸውም ከሃምሳ በመቶ በላይ ውጤት ሳያስመዘግቡ አንገት ለአንገት እንደተናነቁ መፎካከራቸው በይፋ ተገለፀ፡፡ በወቅቱ ከእጩ ተፎካካሪዎች ውስጥ በሶስተኝነት ስለሚከተሉት እጩ ማንም ነገሬ ያለው አልነበረም፡፡ ሁሉም ስለዚህ እጩ ማንነት ለማወቅ ጆሮውን የቀሰረው ፕሬዚዳንት ሲርሊፍና ተቀናቃኛቸው ዊንስተን ተብማን ለሁለተኛ ዙር መፎካከራቸው እንደማይቀር የላይቤሪያ የምርጫ ቦርድ ካስታወቀ በኋላ ነበር፡፡ 

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ላይቤሪያውያን በተለይ ደግሞ የእርስ በርሱ ጦርነት ሠለባ የሆኑትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድንገት በድንጋጤ ክው ያሉት በሶስተኛ ደረጃ የሚከተሉትና የሁለቱን ተፎካካሪዎች የማሸነፍ እድል በእጃቸው የያዙት እጩ ተወዳዳሪ ፖለቲከኛ ፕሪንስ ጆንሰን መሆናቸው እንደታወቀ ነበር፡፡ 
የሀምሳ አለቃ ሳሙኤል ዶ በመሩት የመፈንቅለ መንግስት በተኙበት በጥይት ተደብድበው የተገደሉት የፕሬዚዳንት ቶልበርት ተብማን የበኩር ወንድ ልጅ የሆኑት ዊኒስተን ተብማን “ከዚህ ሰውዬ ጋር ከምደራደርስ ሁሉም ነገር ጥንቅር ይበል” ብለው ተውት፡፡ ፕሬዚዳነት ሲርሊፍን ግን ስልጣን በእጅጉ አጓጓቸው፡፡
እናም አዲሱ የላይቤሪያ ንጉስ ሿሚና ሻሪ ሆነው ድንገት ብቅ ካሉት ፕሪንስ ጆንሰን ጋር ለድርድር ተቀመጡ፡፡ እናም ፕሪንስ ጆንሰን ከመራጩ አስር በመቶ የሚሆነው ደጋፊያቸው ድምፁን ለፕሬዚዳንት ሲርሊፍ እንዲሰጥ ለማድረግ፣ በአንፃሩ ደግሞ ፕሬዚዳንት ሲርሊፍ ከሚያቋቁሙት አዲስ መንግስት ሠላሳ በመቶውን ቦታ ለፕሪንስ ጆንሰን ፓርቲ ለመስጠት በመስማማት ድርድራቸውን አጠናቀቁ፡፡
ይህንን ያዩ የላይቤሪያውን የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ሲያውቁ “ነገርዬው ለላይቤሪያ እርቅና አንድነት አወንታዊ ሚና ይጫወታል በማለት የሀፍረታቸው መሸፈኛ ድጋፍ ሲሰጡ በሊወን የሚቆጠሩት ደግሞ “ድሮውንም ሰው የሚጐዳኘው ከቢጤው ነው፡፡ የዚያ ደም ጠማሽ ወንጀለኛ የቻርለስ ቴለር ቀንደኛ ወዳጅና ደጋፊ የነበረችው ኤለን ሲርሊፍ የቻርለስ ቴለር ቀኝ እጅ ከነበረው ቀንደኛ ነፍሰ ገዳይ ከፕሪንስ ጆንሰን ጋር ብትጐዳኝ ምን ያስገርማል ይልቅስ ወዬ ለላይቤሪያና ላይቤሪያውያን” በማለት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ደረታቸውን አየደቁ በምሬትና በከፍተኛ ስጋት ጮኹ፡፡ ይሁን እንጂ ድርድሩን በተግባር ከመተርጐም ለማስቀረት የሚያስችል አቅም የነበረው ወገን አልነበረውም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ድርድሩ ለሁለቱም ወገን ድል ያስገኘ ነበር፡፡ ለኤለን ሲርሊፍ እንዲያ የቋመጡለትን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን በድጋሚ አስገኝቶላቸዋል፡፡ በምንም አይነት ተአምር የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን ማግኘት ለማይችሉት ፕሪንስ ጆንሰን ደግሞ ከአዲሱ መንግስት የሰላሳ በመቶ የስልጣን ቦታ ማግኘት ከሰማይ እንደወረደላቸው መና የሚቆጠር ነበር፡፡ “ይህ ለጭቁኑ የጉዮ ብሔረሰብ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በዜሮ ባዶ እጅን አጨብጭቦ ከመቅረት ይሻላል፡፡ የያዙትን እየጠቡ ማልቀስም ቢሆን ክፉ አይደለም፡፡” በማለት ሰፊ ፊታቸውን አለመጠን አኮሳትረው መግለጫ ሰጡ፡፡
ፕሪንስ ጆንሰን ይህን መግለጫ የሰጡት በቁጭትና በደስታ በተደበላለቀ ስሜት መሃል ሆነው ነበር፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የእርሳቸው የጉዮ ብሔረሰብ አባላት በሆኑ ወታደሮች በፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ላይ ተሞክሮ ለጥቂት የከሸፈውን የመንፈቅለ መንግስት ሲያስቡ በእጅጉ ይቆጫሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አስተሳሰብ ያኔ ስልጣን በእርሳቸው የጉዮ ብሔሰብ አባላት እጅ ልትወድቅ እጅግ በጣም ተቃርባ ነበር፡፡
ነገር ግን እነዚያ የተረገሙ “አሜሪኮ ላይቤሪያን” እንዳልሆነ አድርገው አከሸፉት፡፡ የእርሳቸው የላይቤሪያ የጦር ሃይል አባልነት ህይወት እህል ውሃው ያለቀውም ከዚህ የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ ነበር፡፡
የፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ወታደሮችና የብሔር አባላት ሚሊሺያዎች የጐዮ ብሔረሰብ አባላት የሆኑትን ወታደሮችና ሌሎች የብሔረሰቡ አባላት በዋናነነት የሚኖሩበትን የማኖና የሂምባ ክልልን በመውረር የእውር ድንብር ግድያ ሲጀምሩ ፕሪንስ ጆንሰን ነፍሴ አውጭኝ ብለው ሀገር ለቀው ተሰደዱ፡፡
የዚህ ቁጭት ዛሬም ድረስ ሲያስቡት ያንገበግባቸዋል፡፡ ለፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ብሔር አባላትና አሜሪኮ ላይቤሪያን ለሚባሉት “ያንኪዎች” ያላቸው ወደርየለሽ ጥላቻም ነፍስ ዘርቶ እንደ አዲስ በውስጣቸው መገላበጥ ይጀምራል፡፡
የደስታ ስሜታቸው መሠረቱ ግን በድርድሩ ያገኙት የሰላሳ በመቶ የስልጣን ቦታ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ፤ በዚያ በሚያምረው ጥርሳቸው ብቻ ሳይሆን በአይናቸውም በአፋቸውም ጭምር እየሳቁ ነው፡፡ እንዲህ ሲስቁ ላያቸው ደግና ሩህሩህ እንጂ ነፍስ ገዳይ ነው ብሎ ማንም ሊጠረጥራቸው አይቻለውም፡፡ ደስ በሚለውና ለሌሎችም በቀላሉ በሚጋባው የሞቀ ሳቃቸው ውስጥ ግን እጅግ አደገኛ የጥፋት ዛር ተደብቋል፡፡
በፕሪንስ ጆንሰን ውስጥ ያደፈጠው አደገኛ ዛር፣ ለናምባ ብሔረሰብ ራሳቸውን እንደ ላይቤሪያውያን ሳይሆን ልክ እንደ አሜሪካዊ አድርገው በመቁጠር የላይቤሪያን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ለዘመናት ተቆጣጥረውታል ለሚባሉትና “አሜሪኮ ላይቤሪያን” በሚል የተለየ መጠሪያ ለሚጠሩት እንዲሁም ለምሁራን ያለው ጥላቻ አያድርስ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሌላ ሳይሆን በትምህርት አለመግፋታቸውና በጭፍን ጥላቻ መታወራቸው ነው፡፡
የአሜሪኮ ላይቤሪያን ነገር ሲነሳ ያን አጭርና ሰፊ ፊታቸውን በአስፈሪ ሁኔታ አኮሳትረው “ተመልከቱ እስከዛሬ ድረስ በሃያ ሁለት አሜሪኮ ላይቤሪያን ፕሬዚዳንቶች ተገዝተናል፡፡ የጉዮ ብሔረሰብ አባል የሆነ ግን ለሞት መድሃኒት ነው ብላችሁ ብትፈልጉ እንኳ አንድ አታገኙም፡፡ ቆይ ለመሆኑ በእነዚህ ውዳቂ ያንኪዎች የምንገዛው እድሜልካችንን ነው እንዴ? ደግሞ አመራራቸውንና አገሪቱን እንዴት እንዳደረጓት አይታችሁልኛል? እየውላችሁ! ለዚህ መፍትሔው አንድና በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ ሁሉንም አንድ ላይ ሰብሰብ አድርጐ ወደ አምላካቸው መላክ ብቻ” በማለት ስሜታቸውን ያስረዳሉ፡፡
ስለምሁራን ሲናገሩም የስሜታቸው መምረር ሳይቀየር ነው፡፡ “አሉ የተባሉትን ምሁራን የፓርቲዬ አባል እንዲሆኑና የፕሬዚዳንት የምርጫ ዘመቻዬን እንዲደግፉ ራሴን ዝቅ አድርጌ ለምኛቸው ነበር፡፡ ኧረ እንዲያውም ተማጽኛቸው ነበር፡፡ ሁሉም እምቢ አሉኝ! ትዕቢተኛና ጉረኛ ነገሮች ናቸው፡፡ ራሳቸውን ከሁሉም የበለጡ አድርገው ይቆጥራሉ!” በማለት አዘውትረው ያማራሉ፡፡
ፕሪንስ ጆንሰን የተማሩትን እንዲህ ሲያማርሩና ሲራገሙ፣ ራሳቸው ማንበብና መፃፍ በቅጡ የማይችሉ መሆናቸውን ግን እንኳ ሊናገሩ ቀርቶ የተናገረባቸውን ሰው ከመግደል ጨርሶ አያመነቱም፡፡
ፕሪንስ ጆንሰን ከሁሉም ነገር ይልቅ ለናምባ ብሔር ያላቸው ጥላቻ ግን መግለጫ ቃላት የለውም፡፡ “ስለ እነሱ ሳስብ ሁልጊዜም አፌን ደም ደም ይለዋል፤ እነሱ ነቀርሳ ናቸው፡፡ ከነቀርሳ ለመገላገል ደግሞ የሚያስፈልገው ቆርጦ መጣል ነው፡፡ ቆርጦ መጣል ብቻ!” ይላሉ ያ ግዙፍ ሰውነታቸው እየተንቀጠቀጠ፡፡
በ1952 ዓ.ም በኒምባ ክልል በምትገኝ ታፔታ በተባለ ቀበሌ የተወለዱት ፕሪንስ ጆንስን፤ የላይቤሪያን የጦር ሃይል የተቀላቀሉት በሃያ ሶስት አመታቸው ነበር፡፡
የመቶ አለቅነት ማዕረግ ያገኙት ጦሩን ለአስር አመት ካገለገሉ በኋላ ነበር፡፡ በዚህ የአስር አመት ጊዜ ውስጥ ከአዕምሮአቸው ጠፍቶ የማያውቅ አንድ ሃሳብ ነበራቸው፡፡ የመፈንቅለ መንግስት ማካሄድና የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን መጨበጥ ለአስር አመታት ቀንና ሌሊት ያልሙት የነበረው ህልም ነው፡፡
ይህ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የመያዝ ህልማቸው በቀላሉ እንደማይሳካ ሲረዱና በ1989 ዓ.ም ቻርለስ ቴለር የሚመሩት የአማፂ ቡድን ጦሩን ሰብቆ ዘገሩን ነቅንቆ የናምባ ብሔረሰብ አባል በሆኑት ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ኪንየን ዶ ላይ መነሳቱን እንደሰሙ የራሳቸውን ጥቂት የጐዮ ብሔር አባላት አስከትለው ሲቀላቀሉ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር፡፡
አማፂያኑን ተቀላቅለው ይዋጉ በነበረበት ጊዜ ዋነኛው መሪ ቻርለስ ቴለር አምርረው ከሚጠሏቸው አሜሪኮ ላይቤሪያን አንዱ መሆናቸውን ሲረዱ ከሞላ ጐደል የጐዮ ብሔር አባላት የሆኑ የራሳቸውን አማፂ ታጣቂ ማደራጀት ጀመሩ፡፡ አማፂያኑ በለስ ቀንቷቸው በ1990 ዓ.ም ዋና ከተማዋን ሞንሮቪያን ሲቆጣጠሩ፣ የፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶን ቤተመንግስት ቀድመው በመቆጣጠር ፕሬዚዳንት ዶን መማረክ የቻሉት ዋነኛው የአማፂያኑ መሪ ቻርለስ ቴለር ሳይሆኑ ፕሪንስ ጆንሰንና የሚመሩት ቡድን ነበር፡፡
ከከባድ ህዝብ ጨራሽ የእርስበርስ ጦርነት በኋላ በአማፂያን ጠላቶቻቸው እጅ የሚወድቁ ፕሬዚዳንቶች እንደ እድለ ቢስ ሰዎች ይቆጠራሉ፡፡ ምክንያቱም የማታ ማታ መጨረሻቸው በፍርድም ይሁን ያለ ፍርድ በሞት ቅጣት የሚደመደም ስለሆነ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶም ከእነዚሁ እድለቢሶች አንዱ ናቸው፡፡ እናም በመጨረሻው የተጋፈጡት የማይቀረውን ሞት ነው፡፡ ለመሆኑ የፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ አሟሟት እንዴት ነው ብላችሁ ብትጠይቁ የምታገኙት ታሪክ የተለየ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ከሞታቸው አሟሟታቸው ተብሎ ከተለቀሰላቸው መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ የእኒህ ሰው አሟሟት እስከዛሬም ድረስ ከላይቤሪያ “ጥቁር ታሪኮች” እንደ አንዱ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ከቤተመንግስታቸው ሳይወጡ በማረኳቸው የፕሪንስ ጆንሰን ታጣቂ አማፂያን እጅ ከተገደሉ ሃያ ሁለት አመታት አልፈዋል፡፡ የተገደሉበት ሁኔታ ግን ዛሬም እንደ አዲስ ይወሳል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ የመጨረሻ እጣ ፈንታቸውን እንዴት እንደተጋፈጡት የሚያሳይ የቪዲዮ መረጃ በኢንተርኔት አማካኝነት እንደልብ ይገኛል፡፡ ከበርካታ የቪዲዮ ፊልሞች በአንዱ ብቻ የአሟሟታቸውን ሁኔታና ከአሟሟታቸው ጀርባ ማን እንደነበረ ራሳችሁ አይታችሁ በቀላሉ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ መርጣችሁ የተመለከታችሁት የቪዲዮ ፊልም ሁለት ነገሮችን በሚገባ ያረጋግጥላችኋል፡፡ ፕሪንስ ጆንሰንንና “ስለናምባ ብሔረሰብ ሳስብ አፌን ደም ደም ይለኛል” ያሉት የውሸታቸው አለመሆኑን፡፡ በቡድናቸው አባላት የተማረኩትን የፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶን ቃል የተቀበሉት ፕሪንስ ጆንሰን ነበሩ፡፡ መጀመሪያ እንዳዩዋቸው ያወረዱባቸው ብሔረሰባቸውን መሠረት ያደረገ እጅግ ክብረ ነክና ፀያፍ የሆኑ ስድቦችን ነበር፡፡
ከዚያ እርቃናቸውን በማስቀረት እጅና እግራቸውን የፊጢኝ በማሰር፣ የላይቤሪያን ገንዘብ ምን እንዳደረጉበትና የት እንዳደረሱት እንዲናዘዙ በአማፂያኑ የምድር ላይ ፍዳ እንዲቀበሉ አስደረጉ፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ የሰጡት መልስና የደረሰባቸው ቶርች ፕሪንስ ጆንሰንን ሊያረካቸው ወይም የጥላቻቸውን ዛር ሊያበርድላቸው አልቻለም፡፡
ከቤተመንግስቱ ማድ ቤት ከተገኙት የተለያዩ የመጠጥ አይነቶች የአሜሪካ ጥምቅ የሆነውን የበድዋይዘር ቢራ እንዲቀርብላቸው አስደርገው፣ እሱን እየቀመቀሙ አንዱን ወታደራቸውን ጠሩና በምልክት አንድ ትዕዛዝ ሰጡት፡፡ አማፂው ወታደርም ጊዜ አላጠፋም፡፡ በወገቡ የታጠቀውን የውጊያ ጩቤ በቅጽበት መዥረጥ አደረገና፣ የፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶንን የቀኝ ጆሮ ቀርድዶ ጣለው፡፡ ፕሪንስ ጆንሰንና ሌሎቹ ታጣቂዎች በሳቅ አውካኩ፡፡ በተለይ ፕሪንስ ጆንሰን ቢራቸውን እየተጐነጩ “የተከበሩት ፕሬዚዳንት፤ ጆሮዎት ስለተቆረጠ አመመዎት እንዴ? አሁንስ የጠየቅንዎትን ጥያቄ እውነቱን አይመልሱልንም?” አሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ በከፍተኛ ስቃይ፣ ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ እየቃተቱ የደበቁት ገንዘብ እንደሌለ ለመናገር ሞከሩ፡፡ ነገር ግን ፕሪንስ ጆንሰንን ማርካት ሳይችሉ ቀሩ፡፡
ይህን ጊዜ ፕሪንስ ጆንሰን ከተቀመጡበት ድንገት ቱር ብለው ተነሱና፣ የፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶን በደም የተበከለ አንገት በግራ እግራቸው ረግጠው በመያዝና ቁልቁል አፍጥጠው እያዩዋቸው “አንተ ጥምብ አንሳ! ባንተ ላይ የነበረኝ ትዕግስት አልቋል! እንዳንተ ላለ አሳማና ጥንብ አንሳ ለሆነ ሰው የሚገባው ምን እንደሆነ አሁኑኑ አሳይሀለሁ!” በማለት አምባረቁና በብሔራቸው ቋንቋ ጩቤውን መዞ ፊትለፊታቸው ትዕዛዛቸውን ለሚጠባበቀው ታጣቂ አንድ አጭር ትዕዛዝ ሰጡት፡፡ ታጣቂውም በሚያስገርም ፍጥነት ቀደም ብሎ በጩቤው የቆረጠውን የፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶን ጆሮ አንስቶ፣ አጠገቡ ከነበረና የእድር ወንበር ከሚመስል ረጅም የብረት ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ፣ ልክ እንደ አሪፍ የወጥቤት ባለሙያ ጐረድ ጐረድ አድርጐ በመክተፍ የጋዜጣ ቅዳጅ በሚመስል ወረቀት ላይ አድርጐ፣ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ፊት አቀረበው፡፡ ፕሪንስ ጆንሰንም ግቢ የሚበጠብጥ ወፍራም ሳቃቸውን ጮክ ብለው እየሳቁ “አንተ ሰው በላ! የሰው ስጋ እንዴት ጣፋጭ እንደሆነ መቸም ሳታውቅ አትቀርም፡፡ ይሄው አቅርቤልሃለሁ፡፡ ብላ!” አሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ስሜቱንና አይነቱን ለመግለጽ ከቶውንም በማይቻል የጣዕር ድምጽ አቃሰቱ፡፡ እጃቸው የፊጢኝ በሽቦ ስለታሰረ አንስተው ሊበሉ አይችሉም፡፡ እናም ታጣቂው ልክ የፖሊዮ ክትባት እንደሚወስድ ህፃን ልጅ፣ አፋቸውን በግድ በመክፈት የከተፈውን የገዛ ጆሮአቸውን እንዲበሉ አስገደዳቸው፡፡
በወቅቱ የነበረው ሁኔታና የተፈፀመው ድርጊት ከሰውነት የወጣና ጤነኛ አዕምሮ ላለው ለማንም ሰው ሊያስቅ የሚችል አልነበረም፡፡ ፕሪንስ ጆንሰን ግን ሲጠጡት የነበረው ቢራ ከልብሳቸው ላይ እስኪደፋ ድረስ እንደ ህፃን ልጅ በከፍተኛ ደስታና የእርካታ ስሜት ሆዳቸውን ይዘው በሳቅ ይንፈቀፈቁ ነበር፡፡ ይህንን አይነት በአውሬነት የተሞላ አሰቃቂ ስቃይ አድርሰውባቸውም እንኳ የፕሪንስ ጆንሰን ጭፍን የዘር ጥላቻ ቅም ሊለው አልቻለም፡፡ ታጣቂ ወታደሮቻቸውን ያሻቸውን እንዲያደርጓቸው ነገሯቸውና የተቀመጡበትን ወንበር ወደ ግድግዳው አስጠግተው ቢራቸውን መቀምቀማቸውን ቀጠሉ፡፡ ታጣቂ ወታደሮቹም ከጳጳሱ ደቀ መዝሙሩ እንደሚባለው ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶን እንደ አደን ስጋ ተናጠቋቸው፡፡ ከዚህ በሁዋላ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ እንዴት ሆኑ ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ለምን ቢባል በሌላ ምክንያት ሳይሆን መግለጽ ስለማይቻል ነው፡፡ ፕሪንስ ጆንሰን በቁጥር በማይገለጽ አይነት የተበጣጠሰውን የሳሙኤል ዶን ሰውነት በከፍተኛ የጥላቻና የመጠየፍ ስሜት ወገባቸውን በእጆቻቸው ይዘው ቁልቁል አዩና ምራቃቸውን ጢቅ አድርገው ተፉ፡፡ ከዚያ ታጣቂ ወታደሮቻቸውን ቀና ብለው አዩና “ይህን ተባይ ጥምብ አንሳ ልከኛ ዋጋውን ሠጣችሁት፡፡
ይህ ያለንበት ግቢ የእኛ የጉዮዎች መሬት ነው፡፡ እንደ ሳሙኤል አይነት ጥምብ አንሳ በመቅበር መሬታችንን ማርከስ ይገባናል እንዴ?” በማለት ጠየቁዋቸው፡፡ ሁሉም የታጠቁትን ክላሸንኮቭ ጠመንጃ ወደ ላይ በማንሳት “Never!” አሉ፡፡ በጭራሽ! ይሄኔ ፕሪንስ ጆንሰን ያን የሚያምረውን ፈገግታቸውን ፈገግ አሉ፡፡ ከፍተኛው ጭፍን የዘር ጥላቻቸውም የቀን ምሱን ያገኘና ተግ ያለ መሰለ፡፡
ይህ ከሆነ ከስድስት አመት በኋላ የእርስበርስ ጦርነቱ ቆመ፡፡ በዓመቱ ከ1997 ዓ.ም በላይቤሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሄደ፡፡ ዋነኛው የአማፂያኑ መሪ የነበሩት አሜሪኮ ላይቤሪያኑ ቻርለስ ቴለርም አዲሱ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት በመሆን ለመመረጥ ቻሉ፡፡
ይህ ሁኔታ የፕሪንስ ጆንሰንን በአሜሪኮ ላይቤሪያ ላይ ያላቸውን ጭፍን ጥላቻ ክፉኛ ቀሰቀሰው፡፡ ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴለርን ግን ልክ እንደ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ዶ ውጊያ መግጠምና በመማረክ አሰቃይቶ መግደል የሚቻላቸው ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ በዚሁ አመት ጨርቄን ቅሌን ሳይሉ ወደ ናይጀሪያ ኮበለሉ፡፡ ከሠባት አመት የናይጀሪያ ስደት በሁዋላ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በ2005 ዓ.ም የትውልድ አካባቢያቸው የኒምባ ክልል ሴነተር በመሆን የተመረጡትና በ2011 ዓ.ም በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አዲሱ የላይቤሪያ ንጉስ ሿሚና ሻሪ ፖለቲከኛ ሆነው ከች ያሉት ሰውዬ እንግዲህ ይህን የመሰለ በደም የጨቀየ የ”አስከፊ ጥቁር ታሪክ” ባለቤት የሆኑ ናቸው፡፡
ፕሬዚዳንት ኤለን ሲርሊፍና ፕሪንስ ጆንሰን ያደረጉትን ድርድርና ስምምነት አስመልክቶ የፖለቲካ ተንታኞችና የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች፡ አዲሱ መንግስት እክል ይገጥመዋል በማለት ገና ድሮ ግምታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ ግምታቸው ሁሉም የተሞኙ ይመስላሉ፡፡
አዲሱ የሲርለፍና የጆንሰን ጥምር መንግስት ከተመሠረተበት ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ ህልውናውን አደጋ ላይ የሚጥል እክል አላጋጠመውም፡፡ እዚህ ላይ ግምቱን የሠጡት ሰዎች አንድ አብይ ጉዳይ ያላወቁ ወይም የዘነጉ ይመስላሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ኤለን ሲርለፍ እኮ በሰብአዊነት ላይ በፈፀሙት ከባድ ወንጀል የተነሳ በአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሀምሳ አመታት ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው፣ የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት የቻርለስ ቴለር ጨርቃቸውን የጣሉ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ታዲያ፣ ፕሪንስ ጆንሰን እንዴት ቢሆኑ ሊከብዷቸው ይችላሉ?
ይህንን ጥያቄ ለፕሬዚዳንቷ ለኤለን ሲርሊፍና ለህዝባቸው በመተው ምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር ላይቤሪያን ለቀን ፊታችንን ወደ ምስራቅ አፍሪካ በማዞር ወደዚያው እናቅና - ወደሩዋንዳ፡፡
በመላው አለም ዘንድ የምትታወቀው እርስበርስ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት እልቂት ነው፡፡ ለአንድ መቶ ቀናት በተካሄደው የእርስበርስ ጦርነት የሀገሪቱን ህዝብ አብዛኛውን ቁጥር የያዙት ብዙሀኖች የሁቱ ብሔረሠብ አባላት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የአናሳዎቹ የቱትሲ ብሔረሰብ አባሎችን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ ባልታወቀና ተነግሮ በማያልቅ እጅግ አሰቃቂ ጭካኔ ፈጅተዋቸዋል፡፡ የሩዋንዳ አስከፊ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ መዝገብ፣ ለቁጥር የሚያታክቱና ለማመን የሚያዳግቱ የፍጅትና የፍጅቱ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ታሪክ ታጭቆበታል፡፡ በሺዎች ከሚቆጠረው የዚህ መዝገብ ገጾች ውስጥ የተወሰኑት ስለ ፓውሊን ንይራማሱሁኮ ይተርካሉ፡፡ ለመሆኑ ይህች ወይዘሮ ማን ናት?

Read 5284 times