Print this page
Saturday, 24 December 2022 15:28

አውሮፓ ህብረት፤ የስምምነቱ ተግባራዊነት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት መልሶ ለመጀመር እንደሚያስችለው አስታወቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

      ከሳምንታት በፊት የተደረገውና በህውሐትና በመንግስት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ መሆኑ ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት መልሶ ለመጀመር የሚያስችለውን ሁኔታ እንደሚፈጥር የአውሮፓ ህብረት ገልጿል፡፡
ህብረቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያና በአፈፃፀሙ ዙሪያ ደግሞ በኬኒያ ናይሮቢ የተደረሱት ስምምነቶችን ማድነቁን የገለፀው ቢቢሲ፤ ከስምምነቱ በኋላ የታዩ ለውጦች የሚደነቁ መሆናቸውንና ለዚህም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን መጠቆሙን አመልክቷል፡፡
የስምምነቱ በዘላቂነት ተግባራዊ መሆን የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት መልሶ ለመጀመር እንደሚያስችለው ማመልከቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትና ለመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት መኖር ህብረቱ ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የልማትና የምጣኔ ሃብት ድጋፍ ቀስ በቀስ ወደነበረበት እንዲመለስ ያደርገዋል ብሏል- በመግለጫው፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ መረጋጋት ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሰላማዊ ልማት ለአካባቢውና ለአውሮፓ ህብረት ቁልፍና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ህብረቱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡   
ኤርትራንም በተመለከተ የድንበር ጦርነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት መካከል የተደረሰውን የአልጀርስ ስምምነት እንዲሁም ከአራት ዓመት በፊት የተደረሰውን የሰላም ስምምነትን ጠቃሚነት የገለፀው ህብረቱ፤ የኤርትረ ሠራዊት በአስቸኳይና ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ በመግለጫው ጠይቋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች የት/ቤቶችና የጤና ተቋማት ግንባታ የሚውል 33 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በቅርቡ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡

Read 11848 times