Saturday, 24 December 2022 15:30

በመንግስትና በሕውሃት መካከል በናይሮቢ የተካሄደው ውይይት ከፍተኛ ውጤት የታየበት ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

  - የህብረቱ የአደራዳሪዎች ቡድን በቅርቡ ወደ መቀሌ ያመራሉ
   - በስምምነቱ መሰረት የፌዴራል መንግስቱ ሰራዊት መቀሌ ከተማ በመግባት ዋና ዋና ተቋማትን መቆጣጠር ቢገባውም፣ እስከ አሁን  ወደ ከተማዋ አልገባም
           
        በህውሐትና በፌዴራል መንግስቱ መካከል በናይሮቢ ከተማ ታህሳስ 12 እና 13 ቀን 2015 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ውይይት ተጠናቋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በውይይቱ ላይ ስለተነሱ ጉዳዮችና ስምምነት ስለተደረሰባቸው ነገሮች እውነተኛ መግለጫ የሚሰጡት በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ለመከታተል መቀሌ ላይ ስንገናኝ ይሆናል” ሲሉ የአደራዳሪው ቡድን አባልና የቀድሞው የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች በሌሉበት በናይሮቢ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ በአደራዳሪዎቹ በተሰጠው በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኡሁሩ ኬኒያታ እንደተናገሩት፣ የሰላም ስምምነቱን ተፈፃሚነት የሚከታተልና የሚገመግም ቡድን ከሁለቱም ወገን ተደራዳሪዎች ጋር በቀጣዮቹ ቅርብ ቀናት መቀሌ ከተማ ላይ ይገናኛል፡፡ የቡድኑ በመቀሌ መገኘት በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው የህውሃት ሃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትና፣ የውጪ ሃይሎችን ከመቀሌ የማስወጣት ሂደት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሚከታተልና የሚገመግም ይሆናል ተብሏል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ በናይሮቢ ያካሄዱት ውይይት ተከታይ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ የናይሮቢው ውይይት ላይ፣ የሁለቱ ወገን ወታደራዊ አመራሮች በዝግ ውይይቱን ያደረጉ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግስታት ተቋም (ኢጋድ)እና የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች ተሳታፊ እንደሆኑበት ታውቋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለ3ኛ ጊዜ ናይሮቢ ላይ የተደረገው ይኸው ውይይት ሲጠናቀቅ፣ ድርድሩን በመምራት ላይ የሚገኙት አሸማጋዮች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ መቀሌ እንደሚያመሩና ይህም የሚሆነው በሁለቱ ወገኖች መካከል ከሳምንታት በፊት በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈፃፀምን ለመታዘብና ለመገምገም ነው ተብሏል፡፡ የጉዞውን ትክክለኛ ቀን መናገር ያልፈለጉት አሸማጋዮቹ፣ ከፈረንጆች አዲስ አመት መግባት በፊት ወደ ስፍራው እንደሚያመሩ ገልፀዋል ፡፡
ባለፉት ሁለት ቀናት የሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ አመራሮች ናይሮቢ ላይ ተገናኝተው ከተወያዩባቸውና ስምምነት ላይ ከደረሱባቸው ጉዳዮች መካከል ከሳምንታት በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተገዥ በመሆን አፈፃፀሙን ለመቆጣጠርና ይህንኑ የአፈፃፀም ሂደት መከታተያ ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን አሸማጋዮቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ የስምምነት ሰነድ ላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከልም ከፌዴራል መንግስትና ከህውሃት ሃይሎች የተወጣጡ አባላት ያሉበት ኮሚቴ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የባለሙያዎች ቡድንን ያካተተ አንድ ቡድን ወደ መቀሌ የሚያመራ ሲሆን፤ የቡድኑ ተግባርም ሁለቱም ወገኖች በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት እየተገበሩ መሆኑን ማረጋገጥና በየትኛውም ወገን ተግባራዊ ያልተደረገና በስምምነቱ ላይ የተገለፀ ነገር ካለ ለእርማት ሪፖርት ማድረግ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ መቀሌ ያመራል በተባለው በዚህ ቡድን ውስጥ የፌዴራል መንግስት ተወካይ፣ የህውሃት ሃይሎች ተወካይ፣ ድርድሩን ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ቡድንና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ተቋም (ኢጋድ) አንደ አንደ ትወካዮች እንደሚገኙና የአፍሪካ ህብረት ተወካዩ የቡድኑ ሊቀመንበር እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በደቡብ አፍሪካና በናይሮቢያ የተደረጉ ስምምነቶች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረግ ቀዳሚ አላማው ነው የተባለው ጥምር ቡድኑ፣ መንግስትና ህውሃት የደረሱበትን የሰላም ስምምነት እንዲሁም የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ አመራሮች የተፈራረሙትን የአፈፃፀም ስምምነትን የሚጥስ ተግባር ተፈፅሞ ሪፖርት ሲያደርግለት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ መፍትሔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጥምር ቡድኑ የህውሃት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት መጠናቀቁን ማረጋገጥ፤ የህውሃት ተዋጊዎች ዳግም የጦር መሳሪያና ተተኳሽ መሳሪያዎችን እንዳይዙና ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳያደርጉ የመቆጣጠር፣ የህውሃት ሃይሎች የሚፈቱት ትጥቅ የሚቀመጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በለያቸው ቦታዎች ላይ ብቻ መሆኑን የማረጋገጥ ሃላፊነትም ለጥምር ቡድኑ ተሰጥቷል፡፡
በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ቡድኑ በመቀሌ ከተማ ውስጥ ሲገናኝ በሰላም ስምምነቱ እስከ አሁን ድረስ ምን እንደተከናወነና ስምምነቱ የደረሰበትን ደረጃ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለት ወራትን ሊደፍን ቀናት የቀረው ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነት መሰረት፤ ህውሐት በ30 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንደሚፈታ የተገለፀ ቢሆንም፤ ይህ ሁኔታ ተፈፃሚ አልሆነም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመከላከያ ሰራዊት መቀሌ ከተማ በመግባት ዋና ዋና ተቋማትን እንደሚቆጣጠር የስምምነቱ ሰነድ ቢያስረዳም፣ የመከላከያ ሰራዊት እስከ አሁን መቀሌ ከተማ አልገባም፡፡ ይህንን ተከትሎም በመቀሌ ከተማና መከላከያ ባልገባባቸው የትግራይ ክልል አንዳንድ ከተሞች ከባድ ዝርፊያ እየተካሄደ መሆኑን መንግስት መጠቆሙ ይታወሳል፡፡  


Read 11853 times