Saturday, 24 December 2022 15:37

የ‘ቆረጣ ግልበጣ!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንደምን ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንዴት ነህ? በቀጠሮ ከች አልክ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ደህና ነኝ አንድዬ! ደህና ነኝ! ግን አንድዬ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
አንድዬ፡- ገና ከመገናኘታችን ምን ተነጋገርንና፣ ምን አልኩህና ነው ደስ የሚልህ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በአንድ ጊዜ አወቅኸኛ፣ አንድዬ! ድጋሚ እንኳን ሳልጣራ ነው እኮ ምስኪኑ ሀበሻ ያልከኝ፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ ዛሬ በእውነትም ሆድ እንደባሳችሁ አወቅሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንዴት አንድዬ?
አንድዬ፡- ደስ እንዲላችሁ ትንሽ ሰበብ ነዋ የምትፈልጉት! አሁን እኔ አንትን ወይም እናንተን ቶሎ ማወቄ ምኑ ነው የሚያስደስተው! ይኸው ስንትና ስንት ዘመን ስትፈልጉ ስታነሱኝ፣ ስትፈልጉ ጀርባችሁን ስታዞሩብኝ ኖራችሁ እንዴት ነው እናንተን መርሳት የምችለው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ኸረ እኛ አንተ ላይ ጀርባችንን አዙረን አናውቅም!
አንድዬ፡- ተው እንጂ ምስኪኑ ሀበሻ! ተው እንጂ! አሁን ቆስቁሰህ አናግረኸኝ በኋላ እንዲህ ብሎን፣ እንደዛ ተናግሮን እያላችሁ ልታማርሩኝ ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደሱ ሳይሆን...
አንድዬ፡- ተወው ግዴለም፡፡ ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ እኔ ላይ ጀርባ ማዞር ማለት እኮ ይሄ በትንሽ ትልቁ በከፋችሁ ቁጥር ልመና ሳይሆን አንዳንዴም አንደማስፈራሪያ “ወይ ፍረድ፣ ወይ ውረድ፣” የምትሉን ብቻ ሳይሆን  እኔን የሚያስከፉ ነገሮች ስታደርጉ እኮ ጀርባ ማዞር ማለት ነው፡፡ ማንም ሆነ ማንም ላይ ተንኮል ስትሠሩ፣ ምንም አይነት ተንኮል በማይፈጽሙና አስበውም በማያውቁ  ላይ ግፍ ስትፈጽሙ፣ ሰውን በፍጡረነቱ ብቻ ማክበር ሲገባችሁ ጠባችሁ፣ ጠባችሁ፣ ጠባችሁ የእናንተ መንደር ሰው ስላልሆነ ብቻ ቁም ስቅሉን ስታሳዩ እኮ እኔ ላይ ጀርባ ማዞር ነው፡፡ ልቀጥል እንዴ ምስኪኑ ሀበሻ?   
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ ይበቃል፡፡
አንድዬ፡- ለነገሩ እኔስ አንተን እንዲህ ብዬ መጠየቄ ምን ይሉታል! ቀጥል ብትለኝስ ምኑን አንስቼ ምኑን ልተወው ነው! አንደኛችንን እዚሁ እንከርማት ነበር። አይመስልህም?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ልክ ነህ አንድዬ! ልከ ነህ፡፡ የእኛ ነገር ምኑ ተነግሮ ያልቃል ብለህ ነው!
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንደው ግራ ግብት ያለኝና የሚከነክነኝ ነገር አለ፡፡ እዛ እናንተ ዘንድ እንደው ሹክሹክታ ነገር ሰምተህ አታውቅም?!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ሹክሹክታ አንድዬ?
አንድዬ፡- ብቻ አንድ ነገር ቃል ግባልኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ቃል፣ አንድዬ?
አንድዬ፡- አሁን በምለው ነገር አትታዘብኝም!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ተው አንድዬ፣ እንደ እሱ....
አንድዬ፡- እሺ፣ እሺ!  እንደው ከተማ ዞር፣ ዞር ስትል በእኔ ላይ እየተጎነጎነ ስላለ ነገር ሰምተህ አታውቅም? 
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምንድነው የሚጎነጎነው አንድዬ? አንድዬ አስፈራራኸኝ እኮ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ ደግሞ አሁን እንደዚህ ይባላል! እኔ ባለጉዳዩ ፈራሁ ያላልኩትን  ጭራሽ አንተ ትፈራለህ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ አንተ ምን ትፈራለህና ነው እንደሱ የምትለው! እና ስንፈራ ታስጠጋናለህ፣ ትከልለናለህ እንጂ አንተ ከፈራህ እኛስ ምን እንሁን!
አንድዬ፡- እናንተማ ምን ትሆናላችሁ! አስፈራሪዎቼ እኮ እናንተው ናችሁ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ቆይ አትደንግጥ፣ አንተና የአንተ ቢጤዎችማ ምኑን አውቃችሁት! ልጠይቅህ የፈለግሁትን እያስረሳኸኝ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ...
አንድዬ፡- ሹክሹክታ ያልኩህማ እንደው ለግልበጣ እየመከሩ ነው የሚባል ነገር ሰምተህ እንደሆነ ብዬ ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የምን ግልበጣ አንድዬ! ያው መሰዳደብ፣ መፎካከር...
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ የምልህ አልገባህም! እኔ ስለ ምድር ጣጣችሁ አይደለም የማወራው። እሱን እንደ ፍጥርጥራችሁ ልል ትንሽ ነው የቀረኝ። ልልህ የፈልግሁት እኔን ከስልጣኔ ለማውረድ የሚ....
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ! እኔ ይሄን አልሰማም! ተቆጣኝ አንጂ እኔ እንዲህ ስትል አልሰማም!  
አንድዬ፡- አንተንማ ለራስህ ምስኪን ምን በወጣህ ነው የምቆጣህ! ግን ሌላ ጥያቄ ብጠይቅህ ትፈቅድልኛለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ፈቅደህልኛል ማለት ነው። እንደው ፊት ለፊት የሚወጣው ነገርማ ጥሩ፤ እንኳ እናንተ በዕድሜ ወደ ላይ እየወጣችሁ በአእምሮ ብስለት እኩል አንወጣ ብላችሁ ያስቸገራችሁኝ ቀርቶ አራስ ልጆችም ያውቁታል፡፡ ግን ምስኪኑ ሀበሻ እንደው በየጓዳው፣ በየስርቻው፣ በየጉራጉሩ በየምናምኑ ስለሚደረገው ነገር ሁሉ ታውቃለህ? 
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በጭራሽ አንድዬ! በጭራሽ። እኛን እንደዛ አይነት ቦታዎች ማን አድርሶን! 
አንድዬ፡- ስለዚህ የማታውቀው ብዙ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በጣም ብዙ ነገር አንድዬ? እንደውም ከምናውቀው እኮ የማናውቀው በብዙ እጥፍ ነው የሚበልጠው፡፡ ሁልጊዜ አንተ ትጠብቀናለህ እያልን ነው እንጂ ብዙ ጉድ አለ አንድዬ!
አንድዬ፡- አየህ እኔ ደግሞ ደስ የሚለኝ እንደዚህ ያለውን ችግር መኖሩን ስታምኑልኝ ነው፡፡ ስለዚህ ከጀርባ ስለሚካሄዱ ነገሮች  ካላወቃችሁ እኔ ላይ ግልበጣ እየተጎነጎነ ነው ወይ ስልህ ምነ አስደነገጠህ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ የፈለገ ይሁን እንጂ አንተ ላይ እንደዚህ አይነት ነገር በጭራሽ ሊታሰብ አይችልም፡፡
አንድዬ፡- ብዬ ነበር፡፡ አንዳንዴ ልበሳጭባችሁ እደርስና ደግሞ ታሳዝኑኛላችሁ፡፡ የብዙዎቻችሁ የዋህነት በጣም ስለሚበዛ ይህን እያዩ ነው እኮ ተንኮለኞቹ የሚጫወቱባችሁ፡፡ ትስማማለህ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በደንብ ነው የምስማማው አንድዬ!
አንድዬ፡- እሺ አሁን ደግሞ ግልበጣ የሚለውን ነገር ለምን አነሳህ በለኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ፣ ግልበጣ የሚለውን ነገር ለምን አነሳህ?
አንድዬ፡- የሚደረገውን ብቻ ሳይሆን አሁን፣ አሁን የሚባለውን ነገር ሁሉ ስሰማ የሚከነክነኝ ነገር አለ፡፡ እነኚህ አገሩን ሙሉ የሞሉት ከእኔ ጋር እንካ ስላንትያ ለመግጠም ምንም የማይቀራቸው ክፍሎች የሆነ3 ነገር ቢያስቡ እንጂ እንዲህ የሚያደርጋቸው በጤናማ አይደለም እያልኩ ነው፡፡ ወይ አንደኛውን ጭርሱን የለህም ብለውኝ አይለይላቸው፣ ወይ አፍ አውጥተው በአደባባይ ስልጣን ለሰፊው ህዝብ ብለው ሰልፍ አይወጡብኝ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ኸረ መሰማቱ እየከበደኝ ነው!
አንድዬ፡- ቆየኝማ... ምስኪኑ ሀበሻ፣ ምድር ላይ እኔን እየጠቀሱ ትናንት ማታ አናግሮኝ ሲሉ፣ እንዲህ ብለህ አስጠንቅቃቸው ብሎኛል ሲሉ አሁን ከበደኝ እንደምትለው መስማቱ ይከብደሀል?  
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ግን እኮ አንዳንዴ እነሱ የሚናገሩት ነገር እውነት እንደሚሉት አናግሯቸው ይሆን እንዴ ብዬ እንደምጠራጠር አልደብቅህም፡፡
አንድዬ፡- በምን ምክንያት ነው እንደሱ የምትጠራጠረው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በቃ አንድዬ ምን ልበልህ! እኔ የማስበውን  ነው የሚነግሩኝ!
አንድዬ፡- ለምሳሌ..
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምሳሌ አንድዬ፣ ለምሳሌ ነገሩ ሁሉ ሲደባላለቅብኝ፣ ኖሮ ሲያስጠላኝ በቃ የዓለም መጥፊያ መድረሱን ነግሮኛል ሲሉ፣ የምጸአቱ ቀን ለመቃረቡ ራዕይ ታይቶኛል ሲሉ እኔ ከማስበው ጋር ይገጥምለኛል፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ! እስቲ አንድ ነገር መልስልኝ፣ ሰዉ ሁሉ እንዳንተ የዋህ ነው እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን መሰለህ አንድዬ...ለነገሩ እኮ ኑሯችን...
አንድዬ፡- እኔ የምለው ኑሯችሁ የፈለገው ቢሆን አንደው የተቸለሰባችሁን ሁሉ ያለ ጥያቄ መቀበል አለባችሁ! ስማኝ..እንዳያያዛችን ማደራችን ነው፡፡ ለሌላ ጊዜ እሱ ትናንት ማታ በተኛሁበት መጥቶ አናግሮኝ ሲሏችሁ ምን አድርጉ መሰለህ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን እናድርግ አንድዬ?
አንድዬ፡- ማስረጃ ጠይቁታ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ብለን አንድዬ!
አንድዬ፡- መቼም ማንም መኝታ ቤትህ ድረስ ገብቶ ሲያዋራህ ታየዋለህ፡፡ እና  አንደዛ ሲሏችሁ ምንድነው የለበሰው? ምንድነው....
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- በቃ ትቸዋለሁ፡፡ ዛሬ የአንተን  ወሬ ልናወራ ነበር፡፡ እኔ በቆረጣ ገባሁብህ፡፡ ደግሞ ቆረጣ የሚለውን ቃል የሰማሁት ከእናንተ ነው። ቆይኝማ ዶልተው፣ ዶልተው በቆረጣ ከወንበሬ ሊያነሱኝ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ!
አንድዬ፡- በል በሚቀጥለው ጊዜ የአንተን ወሬ እናወራለን! ሰላም ግባ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1356 times