Monday, 26 December 2022 00:00

ለወጣቶች ዲስፕሊንና ተስፋን የሚያስታጥቀው “ድሬዳዋ ሰርከስ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “እኛ ትርኢታችንን ለማሳየት ወደ ባህር ማዶ እንጓዛለን፡፡ ወጣቶቹ ከዚያ በሚያገኙት ገንዘብ ህይወታቸውን ያሻሽላሉ፡፡ ሌሎች ቤተሰቦች ይሄንን ሲያዩ ወደኛ ይመጡና ልጆቻቸው እኛ ጋ እንዲገቡላቸው ይጠይቃሉ፡፡”

           እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተቋቋመው “ድሬዳዋ ሰርከስ”፤ እዚህ ግባ የሚባል የገንዘብ አቅምና ሃብት ባይኖረውም፤ ለወጣቶች ዲስፕሊንና ተግቶ መሥራትን እያስተማረ ይገኛል፡፡ በተከበሩና ታዋቂ ዓለማቀፍ ፌስቲቫሎችም መልካም ስምና ዝናን ተቀዳጅቷል፡፡
ከድሬዳዋ ሰርከስ መሥራቾች አንዱ የሆነው እንዳለ ሃይሌ በሚመራው ቡድን ውስጥ 35 ጀማሪና ፕሮፌሽናል የጥበቡ ከዋኞች ይገኛሉ። በዕድሜ ትንሹ የቡድኑ አባል የ5 ዓመት ህፃን ሲሆን፤ አብዛኞቹ ግን በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
ከእነዚህም መካከል በሰርከስ ውስጥ ስላሳለፈችው በርካታ ዓመታት በፍቅር የምትናገረው የ18 ዓመቷ ናርዶስ አዊሊቱ ትገኝበታለች፡፡
“ሰርከስን የተቀላቀልኩት በ7 ዓመቴ ነው” የምትለው ናርዶስ፤ ቡድኑን መቀላቀል የሚያስገኘውን ጠቀሜታ እንዲህ ታብራራለች፡-
“አንደኛ፤ በጎ አመለካከት እንዲኖረን ያግዘናል፤ ሁለተኛ በት/ቤት የተሻለ እንድንሰራ ያደርገናል፡፡ በአጠቃላይ በህይወታችን በሁሉም ነገር ውስጥ  ይጠቅመናል፡፡”
በአንድ ወቅት የኢኮኖሚ ማዕከልና ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ ለነበረችው ለድሬዳዋ ወጣቶች ዋነኛ የህይወታቸው መሰረት ነው - ድሬዳዋ ሰርከስ፡፡
የቡድኑ መሪ እንዳለ ሃይሌ ራዕይ ቀላልና ግልፅ ነው - ዋልጌ ወጣቶችን በስፖርት አማካኝነት መታደግ ነው፡፡
“ወጣቶች ጊዜያቸውን በሱስ ውስጥ ተዘፍቀው እንዳያጠፉ አግዘናቸዋል፡፡ እዚህ እንደሚታየው አብዛኛው ሰው ጫት የሚቅምና አደንዛዥ ዕፅ የሚወስድ ነው፡፡ እኛ ግን ዲስፕሊን ከጅምናስቲክ ጋር እናስተምራቸዋለን።” ብሏል እንዳለ፡፡ ድሬዳዋ ሰርከስ ገብተው መሰልጠን የሚፈልጉ ህፃናት ቁጥር ከአቅማቸው በላይ መሆኑንም እንዳለ ይናገራል፡፡
“እኛ ትርኢታችንን ለማሳየት ወደ ባህር ማዶ እንጓዛለን፡፡ ወጣቶቹ ከዚያ በሚያገኙት ገንዘብ ህይወታቸውን ያሻሽላሉ፡፡ ሌሎች ቤተሰቦች ይሄንን ሲያዩ ወደኛ ይመጡና ልጆቻቸው እኛ ጋ እንዲገቡላቸው ይጠይቃሉ፡፡” ብሏል፡፡
ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ በሰርከስ ሲሳተፍ የቆየው የ24 ዓመቱ አብዱልደፋር ራመቶ፤ በበርካታ የሰርከስ ዘርፎችና በከፍተኛ  ጂምናስቲክ የሰለጠነ የእጅ-ለእጅ አክሮባቲስት ነው፡፡
“ሌሎች ህፃናት ኳስ ሲጫወቱ እኔ ይበልጥ የማተኩረው አክሮባት ላይ ነበር፡፡” ይላል አብዱልደፍር፡፡
አሁን ታዲያ በአክሮባት ትርኢት ነው የኑሮ መተዳደሪያውን የሚያገኘው፡፡ የስኬት መንገዱ ግን አልጋ ባልጋ አልነበረም፤ ረዥምና ውጣ ውረድ የበዛበት እንደነበር አልሸሸገም።
“ዲስፕሊን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በጂምናስቲክ በጣም ጎበዝ ልትሆን ትችላለህ፤ ያለ ዲስፕሊን ግን ትርጉም የለውም፡፡ ሁለተኛው ነገር ተግቶ መስራት ነው፡፡ በአንድ የሰርከስ ዘርፍ ብቁ ለመሆን ቢያንስ ለ3 ዓመታት መለማመድ አለብህ፡፡” ብሏል፡፡
ድሬዳዋ ሰርከስ በታወቁ የተለያዩ ፌስቲቫሎች ላይ ሽልማቶችን አሸንፏል - የሩስያና ቻይናን ጨምሮ፡፡
እ.ኤ.አ በ2019 ዓ.ም አብዱራሂምና አበለ በእጅ -ለእጅ ትርኢት ሰባት ሽልማቶችን ወደ አገራቸው ያስገቡ ሲሆን፤ ይህም በሞንቴ ካርሎ ዓለማቀፍ የሰርከስ ፌስቲቫል- ”ኒው ጀነሬሽን” ውድድር ላይ ያገኙትን እጅግ የተከበረ ሽልማት ይጨምራል፡፡
ከዚህ አራት ዓመት ቀደም ብሎ ደግሞ ረመዳንና ቢንያም በተመሳሳይ ዘርፍ በፓሪስ በተካሄደው 36ኛው የሰርከስ ፌስቲቫል፣ የነሐስ ሜዳልያ ለአገራቸው አስገኝተዋል፡፡
ዓለማቀፍ የትርኢት ጉዞዎች የድሬዳዋ ሰርከስ ቡድን ብቸኛ የገቢ ምንጭ ሲሆን-፤ እስካሁን ስኬታቸው ወደ አጥጋቢ የገንዘብ አቅም አልተለወጠም፡፡
“ይህ አዳራሽ የተሰጠን በከተማዋ ባለሥልጣናት ነው፡፡ በአንዳንድ ቁሳቁሶችም ደግፈውናል፤ ነገር ግን መደበኛ በጀት የለንም።” ብሏል፤እንዳለ፡፡
“የኛ ዋነኛው ችግር ብዙ ውድ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከባህር ማዶ የምንፈልግ መሆናችን ነው፡፡” የሚለው እንዳለ፤ “ድሬዳዋ ሰርከስ ሲመሰረት ከስፖርት ኮሚሽን የተሰጡን ቁሳቁሶች አርጅተዋል፤ አዲስ ለመግዛት ደግሞ አቅም የለንም፡፡” ብሏል፡፡
(ምንጭ፡- AFP)

Read 9328 times