Print this page
Saturday, 24 December 2022 15:58

“እነ እሙጢ ጋ እየሄድኩኝ ነው”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

  “ለዛሬ ይበቃኛል” ብሎ ወደ ሰፈር ሊያዞር ሲል አንድ ተጨማሪ ስራ መጣ። “ራይድ ነህ አይደል?” ብሎ ተጠግቶ ጠየቀው። አመኔታ የሚጣልበት አይነት ነው። ቦርጭ እና ቅላት አለው። በተለምዶ ካለ ጥሪ ተሳፈሪ አይጭንም።
“አዎ ነኝ” ከማለቱ “ጠብቃት ትመጣለች… ልጅ ይዛለች” አለው። “ጠሪ አክባሪ” የሚባለው አይነት መሆኑ ነው። የሚሄዱትን ራሱ ሳይሄድ የሚያገናኘው። ልጅቷ መጣች። ህጻኑን ይዛ ከኋላ ወንበር ተሳፈረች። ወደ ኋላ በሚያሳየው መስታወት ሲገመግማት እንዲሁ አልወደዳትም። ወደምትፈልግበት ከደረሰች በኋላ “የምከፍለው የለኝም” ብላ አይኗን ልታፈጥ የምትችለው አይነት ትመስላለች።
ብዙውን ጊዜ መጓጓዣውን ጠርቶ የሚያሳፍረው… ጉዞው ከመጀመሩ በፊት ይከፍላል። እንደ ቅርበቱ። ለተጓዡ እንደሚሰጠው አክብሮቱ። ብዙም ትውውቅ ያላቸው አይመስልም። በጎዳና ላይ ሲያልፍ “ራይድ ጥራልኝ” ብላው ተባብሯት ሊሆን ይችላል።
 ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ነገር በእጇ ታቅፋለች። ያመናት በታቀፈችው ህጻን ምክንያት ነው። የታቀፈችው ህጻን ከታቃፊዋ ወጣት በላይ ንጹህ ይመስላል። በነጭ መታቀፊያ ነው የተጠቀለለው። ብዙም ደስ ሳትለው ነው መኪናውን አስነስቶ ጉዞ የጀመረው።
አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ኋላ አንገቱን አዙሮ በደንብ በአይኑ ከላይ እስከ ታች አዳርሷታል። ከሰላምታ በስተቀር ተሳፋሪን ማየት አይወድም። ዞሮ ማየት ሳያስፈልገው፣ ምን አይነት ሰው እንደተሳፈረ ያውቃል። አንዳንዶቹ ጠረናቸው ማንነታቸውን ይናገርላቸዋል። ሌሎቹ ዝምታቸው። ዝምታቸው የሆኑትን ሳይሆን ምን መስለው መቅረብ እንደሚሹ ይነግረዋል። ራሳቸውን ስለሚያከብሩ፣ መዋረድ ስለማይፈልጉ… የተጠየቁትን መክፈላቸው አይቀርም።
ከመነሳቱ በፊት መዳረሻዋን እና ስልክ ቁጥሯን ጠየቃት። ስልክ ቁጥርም የቁጥሩን ባለቤት ማንነት ለማሳየት ይጠቅማል። ተደብቆ ሰው ለመሳደብ የፈለገ ሰው፣ የሚደውልበት አይነት ቁጥር ነው። 0911 ወይንም ሁለት፣ ወይንም በአንድ ሶስት የሚጀምሩ አድራሻ ያላቸው ስልኮች ናቸው። ስልኳን ነገረችው እና ሞላው። ፈረሱ ስራውን ጀመረ።
በመሰረቱ ማንንም ማዋራት አይፈልግም። እቺኛዋ ልታወራው ስትሞክር ተቆጣት።
“መንገድ የተዘጋጋው ምን ሆኖ ነው?” ብላ የሆነ የወሬመግቢያ ልታመቻች ሞከረች።
“እኔ ምናውቃለሁ” ብሎ ለመክፈት የሞከረችውን ዘጋው። ወዲያው መልሶ ጸጸተው። ግን በትራንስፖርት ስራ ላይ ለጸጸት ጊዜ የለም። እሱ ማን እንደሆነ እንዲያውቁም ሆነ እነሱም ማን መሆናቸውን እንዲያሳውቁት አይፈልግም። እቺ ግን ጋጠ-ወጥ መሆኗን ጠርጥሯል። መጠርጠር የሚያስፈልግበት ሰዐት አይደለም። ገና አልመሸም። ከቀኑ ስምንት ሰዐት ተኩል ገደማ ነው። በቅርብ ነው እሱም ሱሰኝነቱን የተወው። ሲተው ያገኘው ነገር ጥላቻ ብቻ ነው። ሱሰኛ የመሰለውን ችክ ብሎ መጥላት። እርግጠኛ ነው ሱሰኛ መሆኗን የተጠራጠረው፣ ሴተኛ አዳሪ በሚመስለው አለባበሷ ነው። ትንሽ እንደተጓዙ በስልኳ በከፈተችው ሙዚቃ የጠረጠረውን ስለመሆኗ እርግጠኛ ሆነ። አብራ ከሙዚቃው ጋር ታዜማለች። ድምጿ የጎረና ነው። በምሽት ቤቶች የማይጠፉ ሴቶች ላይ የሚያስታውሰው አይነት ድምጽ ነው ያላት፤ የጎረና። እግሯን አንፈራጣ ነው የተቀመጠችው። በማቀፊያ የተጠቀለለውን ህጻን በአግድም ጭኗ ላይ አጋድማዋለች። አያለቅስም። ጠረንም አያመነጭም። ህጻናት የሚያመነጩት ጠረን አለ። ይኸኛው የለውም። እናትየዋ ግን የማይረባ ሽቶ ተቀብታለች። በሃይል ይሰነፍጣል። የተጫማችው ጫማ ማንነቷን የበለጠ ያብራራል። ከስክስ ቡትስ ጫማ ነው::  ወርቃማ ዘለበት እና ረጅም ለጃኬት የሚመጥን ዚፕ ያለው ቡትስ ጫማ ነው።  አፍንጫዋ ላይ ሁለቱን ቀዳዳዎች በሚለየው ስጋ ላይ ቀለበት አንጠልጥላለች። እንደ ፈረንጅ ከብት ቀለበቱን ይዞ የሚነዳት ሳይኖር አይቀርም- ብሎ አሰበ። ጆሮዋ ከአንድ በላይ ጌጥ በመደዳ ይዟል፤ ሊፒስቲክ ግን አልተቀባችም።
ያለሙዚቃ አንድ እርምጃ መንቀሳቀስ የማይችሉ  አይነት ሰዎች አሉ። የምትሰማው ሙዚቃ ሰው ጭፈራ ቤት ገብቶ ሲሰክርና ራሱን ሲረሳ ብቻ የሚሰማው አይነት ነው። በቀን ከተከፈተ ከሽቶው ጋር ተደባልቆ የሚያጥወለውል። በቀን በራስ ፍላጎት ከፍቶ ያውም አራስ ህጻን ታቅፎ ለመስማት እንደሚመርጠው አያውቅም ነበር። ደግሞ አብራ ታዜማለች። አንዳንዱን ትደጋግመዋለች። ድግምቱ ከራሷ በስተቀር ለማንም ትርጉም  የሚሰጥ አይደለም።
መሄድ የፈለገችው ወደ ሃያ ሁለት ስለሆነ፣ ቶሎ የሚገላገልበትን  መንገድ መርጦ መምዘግዘግ ጀመረ።
“አባቱ!... በሀያ አራት ልትሄድ ትችላለህ” ስትለው በድጋሚ ተበሳጨ። መጓዝ ከጀመሩ በኋላ አቅጣጫ የሚለዋውጡ ወይንም “እግረ መንገድህን እንትን ጋር  ቆም ታደርግልኛለህ” የሚሉትን አይወድም። ከሁሉ የሚጠላው ግን “ገንዘብ ይዘውልኝ እስኪመጡ…” ብለው ከደረሱ በኋላ የትዕግስቱን መንገድ እንደገና ወዳላሰበበት አቅጣጫ የሚነዱትን ነው። በራይድ ስራ ላይ ብዙ የሚገርሙት ነገሮች አሉ። ለግርምቱ መጠን ተወዳዳሪ የሚያጣለት ግን… ሁሉም ተሳፋሪ የሚሄድበትን አድራሻ ከስም በስተቀር ያለማወቁ ታኢብ ነው። የሚሄዱበትን እሱ እንዲያውቅላቸው የሚፈልጉት ነገር…።
ተሳፋሪዎቹ ይገቡታል። ወሬ የሚፈልጉ እና የማይፈልጉት ብሎ ይከፍላቸዋል። የወሬ መነሻው “ስራ እንዴት ነው?” የሚል ነው። እሱን ሲመልስ… “በቀን ስንት ታገኛለህ?” ይከተላል። ይከታተላል። “መኪናው ያንተ ነው ወይስ… ለገቢ ነው የምትሰራው?”
በተቻለው መጠን ፊቱን ቅጭም አድርጎ ገና ከመነሻው “ጥያቄ አልፈልግም” የሚል ማስታወቂያ ይሰራል። ግን ከፋይ ስለሆኑ የሱን ፊት መልዕክት ቢያውቁም፣ በራሳቸው ፍላጎት እሱን ባሪያ አድርገው የሚቀጥሉ ይበዛሉ። የሱን ያለማድመጥ ፍላጎት በራሳቸው የማውራት ፍላጎት ይገለብጡታል።  የባጥ የቋጡን አውርተው ተንፈስ ብለው ይወርዳሉ። እንደ ልብ ጓደኛ ሚስታቸውን የሚያሙለት አሉ። ልክ እመውረጃቸው ሲደርሱ በቅጽበት ባዳ ይሆናሉ። በወሬ ያጋሉትን ጆሮውን መልሰው ባይተዋር አድርገው ፍሪጅ ይከቱታል። ያንን ሁሉ አውርተው “በቃ እዚህ ጋ” ብለው ሲያዙት ሌላ ሰው ሆነው ነው። “አላውቅህ አታውቀኝ” የሚለው የመለያያ ዜማ፣ ድምጽ አልባ ሆኖ የመኪናውን ድባብ ይቆጣጠረዋል።
መጀመሪያ ሰሞን…ገና ለሥራው አዲስ እያለ… ካደረሰው ሰው ሁሉ ጋር ዝምድና የመሰረተ ይመስለው ነበር። “ለስራ ከፈለጋችሁ ስልኬን ሴቭ አድርጉና ደውሉልኝ” ይል ነበር። ቲፕ የሰጠውን ከማመስገን አልፎ ይሳለም ነበር። በኋላ ቲፑን እየጠበቀ የመቋመጥ ልምድ ሲጠናወተው በራሱ አፈረ። ከተቻለ እቅጩን ለመቀበል እንጂ አልፎ የሚመጣውን በመጠበቅ መቁለጭለጭ እርም ብሎ ተወ። መጣ ቀረ ብዙ ለውጥ አያመጣም። ለማይረባ ነገር ሱሰኛ መሆን ነው ትርፉ። እንዲያውም አንዳንዴ ዝርዝር የለንም ሲሉ ይተውላቸዋል። ዝርዝር በመፈለግ የሚባክነው ጊዜ ይባስ ያበሽቀዋል። እስከ ሀያ ብር ድረስ የራሱን ጥቅም አሳልፎ ይሰጣል። ከሀያ ብር በላይ ግን “አሁንስ በዛ” ብሎ ያበሳጨዋል። እሩብ  ጉዳይ ነገር ነው አቋሙ። እሩብ ጉዳይ ከሙሉው ክፍያ ቢጎድል ችግር የለውም። ግማሽ ካሉት ግን አሻፈረኝ ይላል።
እቺኛዋ ግን ግማሹን እንኳን ከሰጠችው አመስጋኝ ነው። ልክ አሮጊት አሳፍሮ እንደማድረስ በመሰለ አኳኋን። የሆነ በምድር ሳይሆን በሰማይ የሚከፈል አይነት ስሜት የሚሰጥ አገልግሎት አለ። እቺኛዋ ለሰማይ እድሜዋም ማንነቷም አያቀራርባትም። ምናልባት ያቀፈችው ህጻን ሌላ ሚዛን ላይ ካላስቀመጣት በስተቀር። ህጻን ታቅፈው እንደሚለምኑት የምስኪንነት ደረጃ ያስጠጋት ይሆናል። ጠቅልላ የታቀፈችው ህጻን መሆኑም ግን ያጠያይቃል። ህጻኑ ሽታም ለቅሶም የለውም።
ሁሉም ነገር ከአሽከርካሪው አንጻር ከታየ የመአት ጥርጣሬ ውስብስብ ክምችት ነው። ማረጋገጥም አይፈልግም። የሚረጋገጥም ነገር የለም። ሲደርሱ ሁሉም ግልጽ ሆኖ ይወጣል።
ስልክ ጠቃሚ ነገር ነው። በተለይ ከኋላ ከተሳፋሪ መቀመጫ ሲመጣ። ያ የሚያስጠላ የሁከት ሙዚቃ በስልኩ ጥሪ ምክንያት ተቋረጠ። ከወንድ ጋር ነው የምታወራው፤ የምትናገራቸው ቃላት ተደጋጋሚ ናቸው። ከድግምግሞሹ ጋር የለቅሶ ሳግ እና መቃተት እየተጨመረበት መጣ። ለቅሶዋ እና የምትናፈጠው ንፍጥ ተደጋጋሚ ቃላቶቿን ወደ ሌላ የጥልቀት ወንበር ወስደው አነገሱት። አለቃቀሷ፣ በሳግ የሚቆራረጠው ድምጿ እና በድምጿ የሚናጠው አንድ ፍሬ ልጅነቷ፣ ሾፌሩ ወደ ኋላ በድጋሚ ዞሮ እንዲያያት ምክንያት ሆነው። መጠየቅም ሆነ ጣልቃ መግባት ግን አልፈለገም። ምድር የአሳር እና መከራ ቋት ናት። የስንቱ ታሪክ ተሰምቶ የስንቱ ይቀራል። ከተሰማ በኋላስ ከንፈር ከመምጠጥ ባሻገር ምን መፍትሄ ያስገኛል?
በስልክ የምታወራውን በፍጥነት በመገጣጠም ግርድፍ ነገሩ ገብቶታል።
“… እነ እሙጢ ጋር እየሄድኩ ነው… ብቻዬን ከበደኝ… አንተ ከጎኔ የለህም …. ባዶ ቤት ውስጥ ብቻዬን ከበደኝ… እነ እሙጢ ጋር እየሄድኩ ነው… በቃ ከሰው ጋር ማውራት ናፈቀኝ… አንተ ትናፍቀኛለህ… ጓደኞቼ ይናፍቁኛል… ብዙ ደስ የማይል ነገር እያሰብኩኝ ነው… ማታ አልተኛም… ቀን ይጨንቀኛል… ተቀየምከኝ?... እዛ ስለሄድኩ?... ምን ላድርግ ሰለቸኝ… እኔ ጩጬ ምናምን ነገር አይገባኝም… ግራ ገባኝ… አንተ የለህም… ማንም የለም… ትርሲት አንዴ ብቻ መጥታ በዛው ጠፋች… ስራ ትገባለች…. ብቻዬን አልችልም… አንተ የለህም… እኔ ባዶ ሰፊ ቤት ውስጥ መቀመጥ አልለመድኩም… ብታዝንም ምንም ማድረግ አልችልም… መጥፎ ነገር ነው ቀኑን ሙሉ የማስበው… ጩጬው ደህና ነው… እኔ ግን ከበደኝ…”
መልእክቱ ይሄው ነው። ቅደም ተከተሉ ይለዋወጣል እንጂ አዲስ የሚጨመር መረጃ የለም። ከውጭ ስትታይ ቅርጿ የተሳዳቢ ዱርዬ ሴት ነው። ስትናገር ከአራዳ ቋንቋ ጋር ቀላቅላ የምትሳደብ። አፏን ያዝ ያደርጋታል። አማርኛ የመጀመሪያ ቋንቋዋ አይደለም። ግን ይህ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው፤ እናት ስትሆን። ሃያ አመት አይሞላትም። አጭሳና ስባ የማታውቀው ነገር ለም። ቀረብ  ብሎ የአፏን ጠረን ያሸተተ፣ በማስቲካው ሽታ ላይ የማስቲሹን ሊለየው ይችላል።
መኪናውን እየነዳ በአንድ እጁ ጭንቅላቱን አከከ። ግራ ሲገባው ሳይታወቀው የሚያደርገው ነገር ነው። አሁን በነጻ ቢወስዳትና ብትጽናና ደስ የሚለው መሰለው። የሴቶች ለቅሶ በሰውነቱ ላይ የሚፈጥርበት ነገር አለ። በዋና ሀገር ጥለህ … ባህር አቋርጠህ ሽሽ የሚለው ድንጋጤ ከውስጡ ይቀሰቀሳል።
ለመድረስ ብዙ ይቀራቸዋል። ሃያ ሁለት መጀመሪያ… ከዛ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሆስፒታል ቁልቁል ወደ ሀያ አራት…። በእሷ በኩል እንጂ በስልክ በሚያናግራት ወንድ በኩል ለለቅሶዋ ምን ምላሽ እንደቀረበ መስማት አይችልም። ጥቅሉ ነገር ይገባዋል። ጥቅሉ ነገር ልጁን  ይዛባት እሙጢ ጋ እንድትሄድ አለመፈለጉ ብቻ ነው፡፡ ለማባበያ ምን አይነት ምክንያት እንደደረደረ ወይንም የተጠቀመው ብልሀት አድብቶ ለሚያደምጠው ሾፌር ባይገለጥለትም… የእናትየዋን የጉዞ  አቅጣጫ ግን ሊለውጠው አልቻለም፡፡   
“ወደመጣንበት ልመለስ…” ብሎ መጠየቅ የእርጎ ዝንብነት ነው። በራሱ ጭንቅላት በሰራው ካርታ እነ እሙጢ የሚወክሉት የቀድሞ ህይወቷን ነው። ሲ.ኤም.ሲ የሚባል የሀብታም ሰፈር ልጅ ታቅፋ ከመቀመጧ በፊት ለምዳ የኖረችውን የቀድሞ ታሪኳን--- አለባበሷን አልቀየረውም፤ አዲሱ ህይወቷ፡፡ በጉዞ ለመመለስ የተሳፈረችበት አቅጣጫ በምትሰማው ሙዚቃ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ሾፌሩን ታየው።
የልጁ አባት ላይ በስልክ አልጮኸችም። ወቀሰችው እንጂ አልኮነነችውም።  የደወለው አባትዬው መሆኑ እርግጥ ነው። በስራ ምክንያት ራቅ ያለ ይመስላል፡፡ የመሰለ ሁሉ ግን ነው ማለት አይቻልም፡፡ በስሜቱ ማሰብ ከጀመረ በቀላሉ ሊጭበረበር እንደሚችል ሹፌሩን ታሰበው፡፡
መዳረሻው የሆነ የሴተኛ አዳሪዋን መንደር ማታ ማታ ለመበጥበጥ ጮሆ የሚነሳ፣ ቀን ቀን ድምፁን አጥፍቶ በሩን ቆልፎ የሚሰወር አንድ ቤት ሊሆን ይችላል። በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ወደ ታች መውረድ ሲጀምሩ፣ “በዚህ ግባ” ብላ ቅያስ አሳየችው። በውስጥ ልትንሸራሸር ፈልጋ እንጂ መልሰው ሲወጡ መደበኛውን የሀያ ሁለት ቦሌ መንገድ ያዙ።
መልሳ እነዛኑ የድምፅ ሀጢአት ዘፈኖችን ከፍታለች። በውስጥ መንገድ ከተንሸራሸሩ በኋላ የተበጠበጠው መንፈሷ ረግቷል፡፡ ሀቅታው፤ ስቅታው ቆሟል። መጠነ ቁራጭ ወጥቶላታል። ሾፌሩ ሊጠይቃት አልፈለገም። በጥቅሉ የሚሰማው የጉዳዩ አሳዛኝነት በዝርዝሩ ውስጥ ተራ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ የተሰማውን ርህራሄ በግዴለሽነት ለብጦ ዝም ማለት ተሻለው፡፡
“ውይ ትራፊኩ እንዳይቀጣህ” ብላ በርህራሄ እጇን በደረቷ ላይ ጫነች። ቀጥሎ ደግሞ “እንዴት ትራፊክ እፈራለሁ መሰለህ!” ብላ እጇን ትከሻው ላይ ሳታስበው አሳረፈች። መስላ የምትታየውን እንዳልሆነች ያለ አንደበት መሰከረለት። በእጇ ንክኪ ውስጥ ባገኘው መልዕክት እርግጠኛ ሆነ። ቢያንስ ባል አላት ብሎ ትንሽ ከፍታ ሰጣት። መጀመሪያም ያልሆነችውን አባዝቶ ነበር የኮነናት። ወዲያው አሁን ደግሞ ትንንሽ ብልጭታዎችን አጋኖ ሊያዳንቃት ፈልጓል፡፡
“እኔ ስራ አለኝ እንጂ ሌላ ምን አለኝ” ብሎ የንቀቱን አቅጣጫ ወደ ራሱ መለሰው። አንድ የሚንቀው ነገር ሁሌ በቅርብ ያስፈልገዋል። መጀመሪያ ተሳፋሪዋን ነበረ። ቀጥሎ ደግሞ እሷ በለቅሶ እና ለእሱ በጥቂቱ ባሳየችው አሳቢነቷ፣ እሷን አክብሮ ራሱን አርክሶ ቁጭ አለ።
“እሷ ባል አላት … እኔ ሚስት የለኝም።  እሷ ልጅ አላት…እኔ ልጅም በህይወቴ ላይ በቅርብ ርቀት አይታየኝም። ልጅነቴንም በፍጥነት አጥቻለሁኝ። ድንገት ከመሬት ተነስታ ከበረችብኝ እያለ አሰበ። ወደ ታች መውረድ ቀጠልን። መንገዱ ወደ ሁለት እንደሚሰነጠቅ ረስቷል። ሁለተኛውን ቅያስ ማንም የሚጠቀመው የለም። በታች የሚሄደውን ማንም የሚያዘወትረውን ቅያስ እንዲይዝላት ደጋግማ አስጠነቀቀችው። ቆሻሻው መንገድ ነው፡፡
የሀይላንድ ፕላስቲክ በአንድ ላይ ተከማችቶ በዚህ ቅያስ ጥጋጥግ ላይ ተከምሯል። የቆሻሻው መግፊያ ጋሪዎች ተደርድረው ክብደታቸውን ወደ ፊት ዘንበል አድርገው ቆመዋል። ቆሻሻ ገንዳ ያለበት አካባቢ የተለመደ እይታ ነው። ከቆሻሻ ገንዳው ትንሽ ፈቀቅ ብሎ የላስቲክ ቤቶች አሉ። ሁለት ሊሆኑም ብዙ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ከተነሳችበት የዛ አይነት ርቀት የመጣችው ለዚህ መዳረሻ ይሆናል ብሎ ፈፅሞ አልጠረጠረም፡፡
መኪናውን ዳሩ ላይ ከላስቲኩ ቤት አጠገብ አቆመ።  እነ እሙጢ መአት ሆነው እየተሯሯጡ ወጡ። አንድ ጥርሷ የጎደላት፣ ያልጎደሉት ደግሞ ተዛንፈው የተበላሹባት፣ ትንሽ ከሌሎች በእድሜ ከፍ የምትለው ሴትዮ ልትሆን ትችላለች፤ እሙጢ፡፡ ደጋግማ በሥሟ ጠራቻትና ታቅፋ የቆየችውን ነገር ተቀበለቻት። እሙጢ በአስተቃቀፏ እንደዛ አይነት ህጻን ለመታቀፍ የመጀመሪያዋ እንዳልሆነ ግልፅ ነበር፡፡
ከበው ተቀበሏት፤ ወደ ላስቲክ ቤታቸው አጅበው አስገቧት። ከማስገባታቸው በፊት ግን የጉዞ ተመኑን ጠይቃ ለሾፌሩ ከፍላዋለች። አልቀበልም ብሎ ለመግደርደርም አልተመቸውም። የናቃት እንዳይመስል ተመኑን በልኩ ወሰደ። ቲፑን ግን እንቢ አለ።  ሊያዝንላት የጀመረው ሰው፣ በተቃራኒው አዝናለት ጨምድዳ አስጨበጠችው፡፡
የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ቤት አጅበዋት እስኪገቡ ድረስ እንደ ሰላይ በጥንቃቄ ተከታትሎ፣ ለመሄድ ተነሳ። በእሙጢ ስም ፋንታ የእሷን የእናትየውን ቢያውቀው የበለጠ ደስ ይለው እንደነበር እያሰበ ጎዳናውን ተያያዘው፡፡  

Read 921 times