Saturday, 24 December 2022 16:01

የመሻገር ሲቃ - (ከዐውሎ ነፋስ ጋር መደነስ)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከመጽሐፉ ላይ ጥቂት አንቀጾች ለቅምሻ
‹‹እህስ... መሰጠትስ እንዳንተ ነበር፡፡ ነፋሱን መከተል መሰጠት እንጂ መባከን አይሆንም፡፡ ደግሞም እራስህን እንጂ ነፋሱን አታሳድደውም፤ ራስህን እንጂ ነፋሱን ልትለውጠው አትችልም። በእውነታው ሊያጠምቅህ፣ ሊያላምድህ ያባብልሃል እንጂ ነፋስን ልታሳድደው ወይ ልትከተለው የማይሆን ነገር ነው፡፡ የምዕራብ ነፋስ ሲጠነሰስ ከባህር ልብ ከጥልቁ እንደማዕበል ይጀምራል፡፡ ነፋሱ ንጹህ፣ ፍጹም፣ የሚያድስ (nourisher) እና የሚገነድስ (destroyer)፣ የማምነው ረቂቅ ልሳን፣ እስትንፋስ፣ አሻራ ነው... ደግሞ የሆነ ጊዜ ከዚያ ወዲያ ነፋስን መከተል ወይ ማሳደድ አስፈላጊ የማይሆንብት ጊዜ ይመጣል፡፡  ነፋስ አወኩት የምትልበት ገጽ፣ ያዝኩት የምትለው አካል የለውምና፡፡ ይህ ሲገባህ ያኔ መማረክ፣ ሁለመናን ማስረከብ (surrender) ይከተላል፡፡ ራስህን ካስረከብክ በኋላ ነፋሱን፣ ሁለንተናን ትሆናለህ እንጂ ቀትረ-ሰብህ አይቀጥልም፡፡
ሆኖም ነፋስን መከተል እንዲሁ ቀላል አይምሰልህ፡፡ አንድ ቀን የሆነ ቀን የሆነ ቦታ አጥንቶችህ ወላልቀው እስኪገኙ ድረስ የነፋሱን አዙሪት ተከትለህ ወደ ተራሮች ጫፍ መውጣት ወይም ወደ ወንዞች ጥልቅ መውረድ ሊኖርብህ ይችላል፡፡ ነፋስን መታዘዝ ባህሪው እሱ ነው። እናም አንድ ቀን የሆነ ቀን እንደ ሉባጃ ጢስ አሊያም እንደ ብናኝ አመድ የትም እስኪበትንህ፣ ከሁሉም ጋር እስኪቀይጥህ ለነፋሱ እፍኝ እና መዳፍ መታዘዝን ትታዘዛለህ...››
ቀጥሎ ዝም እንዲልም ፈቀድኩለት፡፡ ሌሊቱን በመሰጠት ሰማነው፡፡ ሌሊቱን እንደ ረቂቅ ሙዚቃ አደመጥነው፡፡ ሕይወት ነበር፡፡ በእያንዳንዷ የነፋስ ሹክሹክታ ውስጥ የማምነው ልሳን ነበር፡፡ ባሻገር አልፎ አልፎ የሚሰማው የቀበሮ፣ የጉጉት፣ የኩኩ መለኮቴ፣ የምሽት ወፍ (ፈረንጆች Nightjar የሚሏት) የጁንጅላቴ ወፍ (ፈረንጆች Hoope bird ይሏታል) ድምጽ እንኳን ከዚህ ረቂቅ ሙዚቃ ጋር የሚናበብ ነበር። ይህ ኹሉ በእርግጥ ልዩነት የሚያመጣ ነበር፡፡
ቢሆንልኝ ወፎችን በቋንቋቸው ላናግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ ወፍ የመሆን ትግሉን ፈተና ቢነግሩኝ እወዳለሁ፡፡ ወፍ የመሆን መፍገምገም ምን እንደሚመስል ባውቅ ምኞቴ ነው፡፡ ወፍ መሆንን የመረጥኩት ሰው መሆንን ጠልቼ አይደለም፡፡ ሰው በመሆን ከሚታሰስ የምናብ ነጻነት ይልቅ በወፏ ክንፎች የሚዳሰስ ገቢር ነጻነት ቢበልጥብኝ እንጂ…
ከሰው ልጅ በስተቀር ሁሉም ተንቀሳቃሽ፣ እና ኢ-ተንቀሳቃሽ ሕይወታዊ ራሱን ለተፈጥሮ ህጎች ማስገዛቱ ይገርማል፡፡ ሰው ‹መስማትን ይሰማል፤ አያስተውልም፤ ማየትን ያያል፡፡ አይመለከትም፡፡› የተባለው ዓይነት ሆኗል፡፡ ሰው እንደሚድህ ጨቅላ ወይ እንደ ዓይነስውር ዳዴ የሚያስቆጥረው ያስፈልገዋል፡፡
ከጀርባችን የተንሰራፋችው ዘርፋፋ ዛፍ ላይ ሆና የጅንጂላቴ ወፍ ደጋግማ ባዜመች ጊዜ ስለዚህችው ረቂቅ ወፍ ያውቅ እንደሁ እንግዳውን ሰው ጠየቅኩት፡፡
መልሱ አጭር ነበረች...
‹‹አዬ... ጌታዬ ወታደር ባሩድ እንጂ ሌላ ምን ሊያውቅ ብለው?...››
ቆጣ ብዬ መልስ ሰጠሁት....
‹‹ወታደርማ ነው እንጂ ኹሉንም የሚያውቅ! መኖር እና መሞት መንታ ሀቅ ሆኖበት እንደ ምድር ማሚቴ መሬትን በርብሮ ገብቶ አፈር ለብሶ በልቡ እየተሳበ ተፈጥሮን የሚወዳጃት፣ እንደ መሲህ ለሌሎች መሞትን የሚኖራት፣ የወታደር መጠራቱ ሞቶ ማዳን እንጂ መግደል እኮ አይደለም... የጀግና ጀግንነቱ መማረኩ ሳይሆን ለማረካቸው ነፍሳት ርህራሄ ማሳየቱ አይደለምን? ለማንኛውም ይህቺ የጁንጅላቴ ወፍ ወይም ‹አንድርማሚት› ትባላለች፡፡ ለየት ያለ ሾጣጣ ጉትዬ ያላት ሆና አንገቷ ገብስማ ክንፏና ጅራቷ ግን ጥቁርና ነጭ ቡራቡሬ ነገር ናት፡፡ በሀገራችን በብዙ ቦታዎች ትገኛለች፡፡
እንደ ቅዱስ ቁርዓን አንቀጾች በንጉሥ ሱሌይማን (ሶሎሞን) ትዕዛዝ፣ ለንግሥት ሳባ (በቅዱስ ቁርአን ብልቂሰ ትባላለች) በጸሐይ የጣዖት አምላክ ማምለኳን ትታ ወደ አላህ መንገድ እንድትገባ የግብዣ ደብዳቤ ያመጣችላት ይህችው የጁንጅላቴ ወፍ ናት፡፡ ይህች ወፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪዘት ዘሌዋዊያን ምዕራፍ 11 ቁጥር 19 ላይም ተጠቅሳለች፡፡››  
‹‹ጌታዬ ይቅርታ ያድርጉልኝና ትሩፍ ነዎትን?››
አሁን ጥቂት ቃላት ከእኔ ጋር መለዋወጥ በመቻሉ የሰለለ ጉሮሮው እየሰላ ይመስላል፡፡ ‹ትሩፍ› ያላት ቃል ስላልገባችኝ ስቁነጠነጥ...
‹‹ጠይብ ነዎትን?›› ብሎ አከለ፡፡
‹‹መሆኔስ አለመሆኔስ ምን ልዩነት ያመጣል?!›› አልኩት፡፡
ምላሽ አልነበረውም፡፡ ዝም እንጂ ጥያቄውስ ምን ምላሽ ያስፈልገዋል?
‹‹ይሄን ግን ልንገርህ... አንተ ከመምጣትህ በፊት እዚህች አንተ የተቀመጥክባት ድንጋይ ላይ ጥንት ከሚመስሉ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ወደ ምድረ ኑድ ሲራመድ ቃየን ተቀምጦ ነበር፡፡ በቀኝ በኩል የምታያት የግራር ዛፍ አድባር ነች፡፡ እሜቴ አይከል ትባላለች፡፡ የኖህ ሚስት አይከል የተቀበረችው ከዚህችው ዛፍ ስር ነው በሚል ትርክት መነሻነት ቅማንቶች በዙሪያዋ አምልኮ ያከናውናሉ፡፡ የተቀመጥነው አይከል ሚካኤልና እሜቴ አይከል እኩል የሚመለኩበት ቦታ ላይ ነው፡፡››
‹‹ይሰሙኛል... ይኸ የሚሉት ኹሉ እኮ አይገባኝም፡፡ ይኸው ሁለት ወሬ ነው አልኹዎት እኮ፡፡ እኔ የተማርኹ አይደለኹም ብየዎታለሁ... ብቻ ንፋስን እከተላለሁ... ወደየት ትግሰግሳለህ ቢሉኝ ‹የትማኒያዬን› ይሆናል መልሴ... እኸዳለሁ እንጂ መድረሻየንስ እንጃ... ሸምበቁማ ሚካኤልን እልዎታለሁ ጅል አይደለሁም፡፡ አይምሰልዎት ንፋሱ ይመራኛል፡፡ እኸዳለሁ... ንፋሱን ተከትዬ... የትማኒያዬን ወደ ምሥራቅ... እኸዳለሁ... እንደ ጧፍ፣ እንደ ኩበት ንድድድ ብዬ፣ ተቃጥዬ እስክጠፋ...››
መሰጠትን ይሄ ሰው ተሰጣት! በንጹህ ልቦና እጣፋታንውን የተፈጥሮ ሰሌዳ ላይ ይጽፋታል። ስንኩል በሆኑ ቃላት ሊገለጽ የማይችል ረቂቅ የተፈጥሮን ጥሪ ተከትሎ ማንም ለመሆን፣ ወደ ምንም ይገሰግሳል፡፡ ማንም ለመሆን ከመቋመጥስ በላይ መሰጠትን አላውቅም!
አሁንም አሁንም ወደተተገንናት ዛፍ እየዞረ ይመለከታል፡፡ እኔ ደግሞ ስለእሜቴ አይከል ዛፍ አስባለሁ፡፡ ሔርማን ሔሰ የሚከተለውን ጽሁፍ የጻፈው እሜቴ አይከልን የመሳሰሉ ዛፎችን እያሰበ ይሆን? እላለሁ፡፡
‹‹Trees have always been for me the most intense preachers. I revere them when they are alive in the forests and groves. And I revere them even more when they stand alone. They are like solitary people. They are like hermits. Who because of some kind of weakness left society, but are like a great, lonesome people, like Beethoven and Nietzsche… nothing is more sacred, more exemplary than a beautiful, strong tree…. Trees are temples. Who ever knows how to talk to them will know the truth.›› (The Seasons of the Soul: The Poetic Guidance and Spiritual Wisdom of Herman Hesse)
ከልጅነቴ ጀምሮ በዙሪያዬ የማያቸው ዛፎች ሁኔታ ይገርመኛል፡፡ የሌሉ ያህል ጭምት፣ ትዝታን፣ ቁዛሜን የሚጠሩ ንጹህ ፍጥረታት... በተለምዶ ውኃ ቅዱስ እንላለን አይደል? በቅድስና ዛፎቹን የሚስተካከል ነገር አለ እንዴ? ዛፎች የሚሰጡ፣ የሚያበረክቱ፣ የሚያስጠልሉ እንጂ ከማንም ምንም የማይጠብቁ ጽኑ ፍጥረታት ናቸው፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን እንዳሉት፤ የሰው ልጅ ከሆነ ያለማወቅ ድንግርግር ወደ ፍዝ ንቃት ሲንደረደር መጀመሪያ የተቀበሉት፣ ያስጠለሉት፣ የመገቡት ዛፎች ነበሩ፡፡ ዛሬም ቢሆን!
በሂደት ሰው የሆነ መንፈሳዊ ምሰላውን የሚሸከም ምልክት ሲፈልግ በቅርብ የተገኙት ጽኑ እና ገታራ ዛፎች ሆኑ፡፡ አመለካቸውም፡፡ አድባር ሆኑት፡፡ ልክ እንደዚህችው እንደ እሜቴ አይከል…
ሱዛን ሲማርድ የተሰኘች ካናዳዊት ሳይንቲስት ያጠናችውን ጥናት ያነበብኩ ጊዜ ደግሞ እንደ ልጅ ቦርቄያለሁ፡፡ ዛፎች ያወጋሉ፡፡ ታላላቆቹ ዛፎች በሥራቸው ለተጠለሉት ትንንሽ ችግኞች ግራ እና ቀኝ በሚናኟቸው ሥሮቻቸው አማካኝነት ምግብ፣ መልዕክት፣ ማስጠንቀቂያ ያቀብላሉ፡፡
እውነት ነው... ዛፎች ይናገራሉ፡፡ ድንቁርናችን ዲዳ አስመስሎ ያሳየናል እንጂ ዛፎች ከሁላችንም በላይ እልፍ ታሪኮችን ያውቃሉ። ከሁላችንም በላይ በዝምታ ይመለከታሉ፡፡ የሰው ልጅ ከጠለሳቸው በታች ለሺህ ዓመታት ያካሄዳቸውን የጭካኔ ምክክሮች አዳምጠዋል፡፡ የሰው ልጅ ከጠለሳቸው በታች ፈሪ ሆኖ፣ ድንጉጥ መድረሻ ቢስ ሆኖ ሲነፋረቅ ታዝበዋል፡፡
ተጓዡ ሰው የተረጋጋ መስሎ ባሻገር የተዘረጋውን የኦሪት ትረካ ውስጥ የምናነበው የተስፋይቱን ምድር የሚመስል ገጸ ምድር ይመለከታል፡፡ አቀማመጡ እንደዛ ስለሆነ አተያዩን ገመትኩ እንጂ የዓይኖቹን እንቅስቃሴማ በጨለማው ምክንያት ለማየት አይቻለኝም፡፡ ወጣት ይሁን ጎልማሳ፣ ጥቁር ይሁን ቀይ እንኳን መናገር ያስቸግራል፡፡  
ብዙ የዝምታ አፍታዎች ተከናወኑ፡፡ ነፋስ ነበር፡፡ የማምነውን ትንፋሽ የተሸከመ የምዕራብ ነፋስ ከክራር ክሮች ጋር እንደሚደንሱ ጣቶች፣ ከሳር ከቅጠሉ በጠቅላላው ከሁለንታ ጋር ይጫወታል፡፡ ሌሊቱ ሙዚቃ ነበር፡፡ በመላው ሕይወታዊ ረቂቅ እስትንፋስ የተቃኘ ዝምታን የሚስተካከል ሙዚቃ... ሌሊትን የምወደው እኮ ለዚህ ነው፡፡ እንደ ቀኑ ግልብ ሳይሆን፣ ገር፣ ረቂቅ እና ምስጢር ስለሆነ...
ሌሊቱ እንደሰ መመን እንዲያባብለን ፈቀድንለት፡፡ ሌሊቱን እንዲያቅፈን፣ እንዲያንሳፍፈን ተሰጠንለት፡፡ ሌሊቱ እንደተስረቅራቂ ሙዚቃ ሁለመናችን ተቆጣጠረ። ከተፈጥሮ ጋር ተመሳጠርን። ከማምነው ጋር ተነጋገርን፡፡ ሌሊቱን እንደ ረቂቅ ሙዚቃ አደመጥነው፡፡ መላውን በሌሊቱ የልብ ትርታ በኩል የሚተነፍስ ስነፍጥረት እንደ አንድ ሲንፎኒ ሰማነው፡፡ የማምነውም ልሳን በዚያ ነበር፡፡ ነፍስ የቱንም ያህል ረቂቅ ብትሆን በሁለንታ ፊት እንደ ሚጢጢ ሞገድ ናት፡፡ ፈረንጆች ripple የሚሏት የውኃ ንቅናቄ ዓይነት... ሌሊቱ ደግሞ ራሱ ሁለንታ ነው፡፡ ይህ ኹሉ በእርግጥ ልዩነት የሚፈጥር ነበር፡፡ ጸሎት፣ አርምሞ ነበር፡፡
ደግሞም ረሀብ ነበር፡፡ ብዙ ማፋሸግ ነበር። ግን ቀትረ-ሰባችንን ማረቅ እስኪቻል ድረስ መሰጠትም ሆኗል፡፡ ሌሊቱን እንደ ረቂቅ ሙዚቃ እያደመጥኩ በተቀመጥኩበት ዓይኖቼን ገርበብ  አደረኩ፡፡ ሌሊቱን በሰመመን ሰማሁት። አደመጥኩት፡፡ ይሄ ቅኝት ውበት መሆኑ ግን እሙን ነው፡፡ አሜሪካዊቷ አፈንጋጭ ሰዓሊ አግነስ ማርቲን እንዳለችው፤ ውበቱ በዚህ ውድቅት ሌሊት ኹሉንም በነፍስ ሊገናኝ፣ ሊያተጋ ይኳትናል እንጂ የማንም አይደለም፡፡ (beauty is unattached, it’s inspiration – it’s inspiration. -Agnes Martin)
ዓይኖቼን ከድኜ ምን ያህል እንደቆየሁ አላወቅኩም፡፡ ምናልባት ነግቶ እንደገና መሽቶም ሊሆን ይችላል... እንዳላንቀፋሁ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡  የሌሊቱ ልሳን በስኩን ዜማ አባበለኝ። ረቂቅነቱ ልክ እንደ ሲንፎኒ ሙዚቃ ሕብር ያለው ሆነ፡፡ ነፋሱ በሌሊቱ ልሳን ቅኝት ስልት ልክ በስሱ ይነፍሳል፡፡ ነፋሱ ራሱ ናፍቆትን የተራበ ይመስላል፡፡ ዘመዱን ጉንጩ እስኪረጥብ እንደሚጮመጩም አዝማድ፣ ሁለመናን የሚያወረዛ እርጥብ ትንፋሽ ተሸክሟል፡፡ ፊቴ ላይ የሚርመሰመሰው የነፋሱ መደባበስ ልክ እንደ ሕጻን ልጅ እጅ ንክኪ ሀሴት የሚዘራ ስሜትም ነበረው፡፡ እናስ ያ የሕጻን የመሰለኝ እጅ የማምነው አለመሆኑን በምን አውቃለሁ?
ሌሊቱን ዓይኖቼን ገርበብ  አድርጌ እንደሰ መመን በማደምጥበት ቅጽበት ከንፈሮቼ ላይ እንደ ሕልም ያለ ቀላል ንክኪ ተሰማኝ። በቅጽበት ዓይኖቼን ገልጬ አንገቴን በቀስታ ሳንቀሳቅስ ብቸኛ ንብ ከከንፈሮቼ ላይ ተነስታ በረረች፡፡
 ምልክት ይሆን?
ሞገስ የማግኘቴ ምልክት?...
ዓይኖቼን ስገልጥ እንግዳው ሰው አጠገቤ አልነበረም፡፡
መቼ እንደ ሄደ ጭራሹኑ አልመጣ እንደሆነ እንኳን የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡
ሆኖም ጠብመንጃውን የተቀመጠበትን ድንጋይ አስደግፎት መሄዱን አየሁ፡፡ ምን  ጠመንጃውን ብቻ... የወታደር ልብሱን እና ጫማውን ጭምር አውልቆ ጥሎታል። አልደነቀኝም፡፡ ቢያንስ መምጣቱ እውን እንደነበር በዚህ ማረጋገጥ አይቻል ይሆን? በዛለ ስሜት እየተጎተትኩ ሄጄ ጠብመንጃውን በግዴለሽነት አንስቼ እጄ ላይ እያንከላወስኩ ተመለከትኩት፡፡ ቤልጂግ ይሁን፣ ክላሽንኮቭ፣ ዲሽቃ፣ መውዜር፣ ቆመህ ጠብቀኝ... የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ብቻ ለሆነች ሽራፊ ሳድሲት ዝም ብዬ አግድሜ መተኮስ ውል ብሎኛል። ወዲያው ግን በሁኔታዬ አፍሬ እንደ ጤፍ ቅንጣት አነስኩ፡፡ ይሄ አፈሙዝና ባሩድ ይሉት ጉድ ግን አዚሙ ምንድን ነው?
ነፋሱ ወደ ምሥራቅ ይነፍሳል፡፡ እንግዳ የሆነ ፈገግታም ይነበብበታል፡፡ ፈገግታው የሚቀበል ነበር፡፡ ለአዲሱ ምርኮኛው እንኳን ደህና መጣህ ይሆን? ይህ ሰው ስያሜውን በቅጡ አይወቀው እንጂ መጠራቱን ተቀብሎ እየተከተለው መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሲጠራ (ጠ - ሲነበብ ይላላል) እንዲህ ነው፡፡ ሲጠራ ይህን ሰው በጉምጀት ምራቅ እንደሚያዝረበርብ የደራጎን ላንቃ፣ ሊውጠው የሚያዛጋ የፍጅት ቱማታ መሀል አነቃው፡፡ ለሌላ የላቀ ግዳጅ አሰማራው። ሊያስፈራራበት ሲችል ጠብመንጃውን እንዲመረኮዝ፣ እንዲለምንበት አሰከነው፡፡
ምናልባት  ‹እሄዳለሁ - ነፋሱን እከተላለሁ› እንዳለ ነፋሱን ተከትሎ ወደ ምሥራቅ መንኖ ይሆናል፡፡ ምናልባት ይህ መጠራት እንግሊዛዊው ደራሲ C.S. Lewis ‹‹Sehnsucht - inconsolable longing for we know not what›› ያለው ዓይነት ይሆን? Sehnsucht ሌዊስ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ይሄን እንግዳ ናፍቆትና መጠራት በምልዓት የሚገልጽለት ቃል ሲያጣ ከጀርመንኛ የተዋሳት ነጠላ ቃል ናት፡፡
የሰውዬው ታሪክ ግን ለሰሚም፣ ለተራኪም እንግዳ ነገር ሆነ፡፡ አዎና የዚህን ሰው ሕመም ያላካተተ የዓለም ታሪክ ከጎደሎነት ያመልጣልን? አርጀንቲናዊው ደራሲ ቦርጌስ አንድ ደራሲ አራት ዓይነት ታሪኮችን ብቻ መተረክ ይችላል ይላል፡፡
‹‹There are only four stories to tell: a love story between two people, a love story between three people, the struggle for power, and the voyage. All of us writers rewrite these same stories ad infinitum.››
እና ይሄ ሰው ገጸባህሪይ ቢሆን ኖሮ ታሪኩ ከአራቱ አንጓዎች በየትኛው ሊተረክ ኖሯል?... Just a mere Voyage? እእእ... ለመሆኑ የነፋሳት ማሰሪያ ውል የት ነው? ምሥራቅስ ጥጉ ከወዴት ነው? ምሥራቅን የሚወስነው አቋቋም አይደለምን?
ራሴን እስክታዘብ ድረስ የአራስ ድመት ዓይነት አስደንጋጭ ረሀቡን የመቋቋም አቅም ነበረኝ፡፡ እናስ ረፋድ ላይ እዚህች ከተማ ውስጥ ዳቦ ሰርቆ ተያዘ... ደበደቡት... ታሰረም ሲባል ብሰማስ ይደንቀኛልን?
ሰምቼም ይሆናል እኮ...
ቢሆንም ቢታሰር እንኳን ለመጠየቅ ዝግጁ መሆኔን አላውቅም፡፡
መተው ነበር የፈለኩት...
ለእጣፋንታው መተው...
‹No short cut route to the top of the palm tree.› እንዲሉ ፈረንጆች፣ የራሱን ትግል ለብቻው እንዲጋፈጣት መተው...
ይሄ ኹሉ ተብሎም አልተባለም፣ ተፈጽሞም፣ አልተከናወነምም፣ ጨረቃ ጠፍ አልነበረች፣ ይሄን ሰው ምናልባት አልመጣ፣ ጭራሽኑ አላገኘሁትስ እንደሆነ በምን አውቃለሁ?
ግን እንዴትስ ቢከወን ምን ልዩነት ያመጣል?
...
እየነጋ ነበር...
ንጋቱ የፍጥረት የመጀመሪያዋን ዕለት ንጋት ይመስል ነበር...
ወደ ምሥራቅ የሚነፍስ የምዕራብ ነፋስም ነበር...
በአንዳች በልበል የሚል ስሜት ተወትውቼ ተነሳሁ...
በአንዳች በልበል የሚል ስሜት ተገፋፍቼ ነፋሱን ተከትዬ ጥቂት እርምጃዎች ወደ ምሥራቅ ተራመድኩ...
እየተራመድኩ ከሳሙኤል ቤኬት The Unnamable የተሰኘ መጽሐፍ የወሰድኳቸውን ጥቂት መስመሮች ደጋግሜ አጉተመተምኩ፡፡
‹‹Lets us go on As I were the only one in the world. Whereas I am the only one absent from it.... You must go on, I can’t go on, I’ll go on... where I am, I don’t know, I’ll never know, in the silence you don’t know... When speaking of others, when speaking of things, how could I know? I can’t know if  I spoken of him, I can only speak of me, no, I can’t speak of anything,  and yet I speak, perhaps it is of him, I will never know, How could I know? who could know?...››

Read 4669 times