Saturday, 24 December 2022 16:05

በትግራይ ሰላም የማምጣቱ ነገር!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  “--ከዚህ በኋላ ትግራይ የጦር ነት ምድር እንድትሆን አልፈልግም። አጎራባች የአማራና የአፋር አካባቢዎች ተመልሰው የውጊያ ክልል ሲሆኑ ማየት ጨርሶ አልሻም፡፡ በቦሌም ይሁን በባሌ በአካባቢው ሰላም መስፈን አለበት።--”
          
       ከስልሳ ዓመት በፊት፣ አንድ የአምስት አመት ያርበኝነት ተጋድሎአቸው ክብር ያስገኘላቸው  ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ሰው፣ የአንድ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ይሠሩ ነበር። እሳቸውን እንዲረዳም አንድ ጸሐፊ ተመድቦላቸው ነበር።
ጠቅላይ ግዛቱ በየጊዜው መፈጸም አለባቸው የሚላቸውን ሥራዎች እየዘረዘረ ትእዛዝ ይልካል። ከምን ደረሰ ብሎ ሪፖርት ይጠይቃል። “ይኸ ይኸ ለምን አልተደረገም?” ብሎ መልሶ የደረሰውን ሪፖርት ይልካል። ተጓደለ የተባለው በእሳቸው እምነት እንዲሟላ ተደርጎ አሁንም ሪፖርት ይደረጋል። የሚደርሰው መግለጫ ከአንጀቱ ጠብ ሊል ያልቻለው ጠቅላይ ግዛቱ፣ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ማስጠንቀቂያ ይልካል። ሰውየው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ሲነበብላቸው እንደ ሌላው ጊዜ ሃሳባቸው እንዲበታተን አያደርጉም። የሚያዳምጡት አፍ ከልብ ሆነው ነው። በዚህ ጊዜ ሥራዬ ብለው የሚፈልጓቸው ቃላት አሉ። እነሱም “ነገር ግን”፣ “ይሁን እንጂ”፣ “ቢሆንም ወዘተ” የሚሉ የቀደመውን ሃሳብ የሚያፈርሱ ቃላት ናቸው። እነሱ ከአሉ ይረጋጋሉ። “ግዴለም እንደርስበታለን” ይላሉ። እና ሁልጊዜ ጸሐፊያቸውን የሚጠይቁት “ደብዳቤው ቢሆንም፣ ይሁንና” የሚሉ ቃላትን ይዟል ወይ” ብለው  ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ጋር በደቡብ አፍሪካ ባደረገው ድርድር፣ ቡድኑ በአንድ አገር ሁለት የታጠቀ ኃይል ሊኖር እንደማይችል፣ በአገር ውስጥ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥራ የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን ተቀብሎ፣ ትጥቅ  ለመፍታት መስማማቱ ይታወቃል፡፡ በሳምንት ውስጥ የፌዴራሉ መንግሥት መቀሌ ገብቶ አስተዳደሩን ሊዘረጋ ታቅዶ እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም።
ሁለቱ የጦር አዛዦች ኬኒያ ላይ በደረሱት ስምምነት ውስጥ፤ “የእነ ደብረጽዮን ቡድን ትጥቅ መፍታት፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ የውጭ ኃይሎች መውጣት ጋር ጎን ለጎን ይፈጸማል” የሚል ሃሳብ መካተቱ፣ ልክ የአውራጃ ገዢው የሚጠብቁት “ነገር ግን” ሆኖ ተገኝቷል።
የመጀመሪያው የዚህ ስምምነት ጉዳት፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ ያልተረጋገጠው የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኝ የሚያስረዳ መሆኑ ነው። ለረጅም ጊዜ አለሁም የለሁም ሳትል የቆየችውን ኤርትራን አንድ ጥግ ይዛ እንድትቆም ማስገደዱም አልቀረም። ኤርትራ በእነ ደብረጽዮን ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት የደረሰባትና የግንባር ጦርነት የተከፈተባት አገር በመሆኗ፤ ለራሷ ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና እስካላገኘች ድረስ ጦሯን ከትግራይ መሬት ማስወጣት ትፈልጋለች ብሎ ማሰብ ይከብዳል።
ሌላው ችግር ወልቃይት ጠገዴና የራያ አላማጣ ነው። ሁለቱም አካባቢዎች በጉልበት ወደ ትግራይ ክልል እንዲጠቀለሉ የተደረጉ መሆናቸው ይታወቃል። ወደ አማራ ክልል መመለስ አለባቸው የሚል የቆየ ጥያቄ ያለባቸውም ናቸው። እነዚህን አካባቢዎች የእነ ደብረጽዮን ቡድን የራሱ አድርጎ ስለሚቆጥራቸው፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኘው የአማራ ልዩ ኃይል በእነሱ ዓይን የሚታየው እንደ ውጭ ኃይል ነው። ነገር ግን ከዚህም አካባቢ የአማራ ልዩ ኃይል ይወጣል ተብሎ አይታሰብም። ይህ ሌላው የእነ ደብረጽዮን ቡድን ትጥቅ ላለመፍታት በምክንያትነት የሚያቀርበው ነው።
የፌዴራል መንግሥቱ ደቡብ አፍሪካ በገባው ስምምነት መሠረት፤ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የመብራት አገልግሎት መቀሌን ጨምሮ 50 ከተሞች እንዲያገኙ አድርጓል። በብዙ አካባቢዎች  ባንኮች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን  የአፋር፣ የወልድያና የማይ ጸብሪ መንገዶች ተከፍተው መድኃኒትና የምግብ እርዳታ እየገባ ነው። እርዳታ በአየርም ጭምር  እየገባ መሆኑም ይታወቃል፡፡  
ከዚህ ተነስተን የእነ ደብረ ጽዮን ቡድን፣ ስምምነቱን ለመተግበር እየሰራ ነው ወይ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ የለም። አንድ የተሰማ ነገር ቢኖር፣ ተዋጊዎቹን ከጦር ግንባር መሳቡ ብቻ ነው።
 በሌላ በኩል፤ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት፤ ቡድኑ ሠራዊት እየመለመለና ሥልጠና እየሰጠ፣ መፍታትና ለመከላከያ ማስረከብ የነበረበትን ከባድ መሣሪያ እንደ ከዚህ ቀደሙ  እያሸሸና እየቀበረ፣ እንዲያውም  የስለላ ቡድኑን ወደ አላማጣ እየላከ፣ በቁጥጥሩ ስር በሚገኘው በአበርገሌ ግንባር ምሽግ እየቆፈረና ሠራዊት እያስጠጋ መሆኑን  ነው። የአላማጣና የአካባቢው ሕዝብ፤ “አራተኛ ዙር ጦርነት ይከፈት ይሆን?” ብሎ በስጋት ላይ መሆኑም ተሰምቷል።
   እስካሁን ባደረገው ጦርነት ያለቁ የሠራዊቱ አባላትን ሞት፣ የስሚ ስሚ የሰሙ ወላጆች ሐዘናቸውን በአደባባይ እንዳይገልጹ የከለከለው የደብረ ጽዮን ቡድን፤ ከሞት የተረፉት በሕይወት ይቆዩ ዘንድ ይጨነቃል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ለእነርሱ “ሠራዊት በጦር ሜዳ ሊማገድ የተዘጋጀ እንጨት እንጂ ሰው  አይደለም።”  በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ያመጸ የወንበዴ ስብስብ ከመሆኑም አንጻር፣ ለሕግም ሆነ ለሞራል የሚገዛ እንዳልሆነ እኔ በግሌ አምናለሁ። ስለዚህ  በግሌ ከቡድኑ  የምጠብቀው በጎ ነገር የለም።
ይልቅስ በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ያለበትን  ኃላፊነትና ተጠያቂነት  በቅጡ እንዲረዳ ለማስታወስና ለማሳሰብ  እወዳለሁ፡፡  ጊዜና እድል ተሰጥቶት ቡድኑ ወደ ጦርነት ተመልሶ  ከገባ  ተጠያቂው ሌላ ማንም ሳይሆን  እራሱ መንግስት መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል።
ከዚህ በኋላ  ትግራይ የጦርነት ምድር እንድትሆን አልፈልግም። አጎራባች የአማራና የአፋር አካባቢዎች ተመልሰው የውጊያ  ክልል ሲሆኑ ማየት  ጨርሶ አልሻም፡፡  በቦሌም ይሁን በባሌ በአካባቢው ሰላም መስፈን አለበት።
በትግራይ ሰላም የማምጣቱ ነገር  እንደ ቀላል ጉዳይ መታየት የለበትም። መንግሥት እግር በእግር እየተከተለ ቡድኑን “ከዚህ ታልፍና” ብሎ ማስቆም አለበት። “የምን የትግራይ መንግሥት!!! የምን የትግራይ የመከላከያ ኃይል!! ወዘተ” እያለ አደብ ሊያስገዛውም ይገባል፡፡ በቃ ማለት በዚህ ጊዜ ነው፤ ነገሩ አመል ሳይለውጥ!!

Read 2659 times