Monday, 26 December 2022 00:00

የአገራችን መፍትሄ፣… ፅድቅ ብቻ ይሆን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(5 votes)

 የአገራችን “የሀይማኖት ፖለቲካ” እና “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ”፣… ማለትም “የጭፍን እምነትና የዘረኝነት ስካር”፣… እንዲሁ የሚያባራ አልሆነም። ለዚያውምኮ፣ ይሄ ሁሉ አጥፊ ኋላቀርነትን ያራባነው፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነው።
ከሰሞኑ በዓል ጋር የተዛመደ አንድ አባባል ብንጠቀም ሳይሻል አይቀርም። ጥንታዊ አባባል ቢሆንም፣ “የተትረፈረፈ እውቀትና የተሳከረ ሃሳብ ተቀላቀለበት የዘመናችንን ቀውስ” የሚገልፅ ይመስላል።
ሰራተኛ ጠፋ እንጂ እርሻው (አዝመራው) ብዙ ነው ይላቸዋል ኢየሱስ - ለተከታዮቹ፣ ለተማሪዎቹ፣ ማለትም ለደቀመዛሙርቱ።
እውነትን ለማየት፣ እውቀትን ለመማር፣ ጥበብን ለመቅመስ የሚፈልጉ እልፍና እልፍ ሰዎች ወደ ቦታው መጥተዋል። የያኔው ዘመን፣… የመከራ ሸክም ሆኖባቸዋል። የአገሬው ነባር እምነትና አስተሳሰብ የተቃወሰበት ዘመን ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን፣… ኑሮ የተናጋበት፣ ሰላም የደፈረሰበትም ጊዜ ነው።
ከዛሬው ዘመን ጋር አይመሳሰልም? ከኢትዮጵያም ጋር ይቀራረባል።
ለማንኛውም፣ የአገሬዎች ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበዋል። ስብከቱን ለመስማት፣ ተዓምረኛ ሥራዎቹንን ለማየት፣ ማንነቱንም በአካል ለመመልከት የሚመጡ ሰዎች እጅግ በርክተዋል።
እውነትና ሐሰት፣ ትክክልና ስህተት የተደበላለቀባቸው፣ በተምታቱ ሃሳቦች ብዛት ሳቢያ ግራ የተጋቡ፣ የሕይወት መንገድ የጨለመባቸውና ትርጉሙ የጠፋባቸው፣ ተስፋ የራቃቸውና “አርአያ” ያጡ ሰዎች፣… ምን ያድርጉ?
“ሁሉም ከንቱ ነው” ብለው ለድንዛዜ እጅ ሰጥተው ይቀመጡ?
በዘፈቀደ እንደየስሜታቸው ወይም በሆታ እንደመንጋ፣… እንደ ሌሎች እንስሳት በደመነፍስ እየተደናበሩ ወይም እየተንጋጉ፣ እንደ አውሬ የመጠፋፋትና የመበላላት ውርደት ነው መጨረሻቸው?
እውነት፣ ሕይወትና መንገድ እኔ ነኝ… ወደሚለው አስተማሪ በብዛት መምጣታቸው ይገርማል? እውቀትን የሚያስጨብጥ፣ ትክክለኛውን መንገድ የሚያሳይ፣ ትርጉም ላለው ሕይወትም አርአያ የሚሆን አስተማሪ ተገኝቶ ነው?
ብዙ ሕዝብ በተስፋ፣ በፈቃደኝነትና በጉጉት ከየአቅጣጫው መጥቷል። አዝመራውስ ብዙ ነው የተባለው ይህንን ለመግለፅ ነው። እውነትንና እውቀትን፣ የተቃና መንገድንና ጥሩ የኑሮ ተግባርን፣ የስነ ምግባር መርህን ለመማር፣… እንዲሁም መልካም ስብዕናን በአካል ከአርአያ ለመመልከት የሚናፍቁ ሰዎች ከተበራከቱ፣… ጥሩ ምልክት ነው። ይሄ ነው እንደ አዝመራ የተገለፀው።
አዝመራውን ለፍሬ የሚያበቃ ጥበብና ጥበበኛ ግን በቀላሉ የሚገኝ አይሆንም። እውቀት እንደዋዛ ይገኛል? አስተዋይ አስተማሪስ እንደዘበት ከየት ይመጣል?
ከ2000 ዓመታት በፊት፣ ብዙ እውቀት ብዙ መፅሐፍ አልነበረም። በማንኛውም የሙያ መስክ፣ ተዝቆ የማያልቅና የተትረፈረፈ የእውቀት ባሕር ውስጥ የሚዋኙበት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ያኔ አልነበረም።
ዛሬስ?
ዛሬም እንደያኔው፣ ግራ መጋባት የበዛበት ዘመን ነው። ግን ደግሞ እውቀት በየቦታው ተትረፍርፏል። የማወቅ ጉጉትና ጥረት ግን በቀላሉ የሚገኝ አልሆነም። “አዝመራውስ ብዙ ነው” ከተባለ፣ የእውቀት መትረፍረፍን ለማሳየት እንጂ፣ የማወቅ ፍላጎትንና ጉጉትን ለመግለጽ አይሆንም።
አዎ፣ የጥበበኞች እውቀት በዓለም ዙሪያ ከመብዛቱ የተነሳ፣ በሽ በሽ ሆኗል። ከምንተነፍሰው አየር አይተናነስም።
እንዲያም ሆኖ፣ ለእያንዳንዱ እውነተኛ መረጃ ዘጠና የውሸት መረጃ የሚዛመት ከሆነ፣ ፍሬና ገለባውን መለየት ቀላል አይደለም።
እውነትና ሐሰት፣ ትክክልና ስህተት፣ ጥሩና መጥፎ፣ መልካምና ክፉ የተምታቱበት ዘመን ነው - ዛሬ። ከመምታታትም አልፈው ትርጉም እስከማጣት ደርሰዋል።
ሁሉም ነገር በጭፍን ስሜትና ጩኸት፣ በጉልበትና በሽሚያ፣ በጥላቻና በመንጋ እየሆነ ነው።
እውነትን የሚጨብጥ፣ ሕይወትን የሚያከብር፤ ትክክለኛ መርሆችን የሚይዝ፣ ብቃትና ጥረትን የሚያዋሕድ ምሉዕ አስተሳሰብና ስብዕና፣… ጨርሶ የማይታለም መስሏል።
መርህ ይቅርና፣… የጨዋነት ወይም የይሉኝታ ልጓሞችምና ምርኩዞችም እየተበጣጠሱ እየተሰባበሩ መሆናቸውን እያየን ነው።
ማስመሰልም እንኳ እየቀረ ነው።
ለይስሙላና ለይሉኝታ፣ ለይምሰልና ለታይታ… ሕይወት ላይ መተወን ቀሽምነት ቢሆንም፤ ለኑሮ ባያዛልቅም፣ ነፍስን ቢያረክስም፣… እንደ ሮቦት ወይም እንደ አውሬ ከመሆን ግን ይሻላል።
የጨዋነት ልማድ፣ የይሉኝታ ልጓም እስካለ ድረስ…
ቢያንስ ቢያንስ፣... ለእውነት፣ ለውጤታማ ጥረት፣ ለተቃና መንገድ፣ ለመልካም ስብዕና ዋጋ ባይሰጥም እንኳ፤… ዋጋ መስጠት እንደሚያስፈልግ በግላጭ አይክድም።
ለመሸወድ፣ ለመሸፈን፣ ለመሸንገል ይሞክራል እንጂ፣… ለይቶለት ከእውነት ጋር ወደ መጣላት፣ በተቃና መንገድ ላይ ወደ ማመፅ፣ በመልካምነት ላይ ወደ መሸፈት አይደርስም - የጨዋነትን ምርኩዝ፣ የይሉኝታን ልጓም ያልጣለ ሰው።
በትክክለኛ መርህ፣… ሃሳቡን፤ ተግባሩንና መንፈሱን የመምራት ፍላጎት፤ እንዲሁም ጥረትና ፅናት ባይኖረውም፣ “ትክክለኛ መርህ” የሚሉት ነገር መኖሩን በግላጭ አይክድም። ለማፍረስና ለማርከስ ፊት ለፊት አይዘምትበትም።
ለእውነት ባይቆምም፣ በይሉኝታ ከውሸት ይታቀባል።
የተቃና ፍሬያማ የጥረት መንገድን ባይመርጥም፣… “ያዩኛል፣ ይታዘቡኛል” በሚል ሃሳብና ስሜት፣… “በጨዋነት ልማድ” አደብ ይገዛል። ወዳፈጠጠ የምቀኝነትና የጥፋት ዘመቻ ከመግባት ይቆጠባል።
እያንዳንዱን ሰው፣ እንደየ ተግባሩ፣ እንደየ ባሕርይው የመዳኘትና የመመዘን የፍትህ መርህን ባይከተልም፣ በዘፈቀደ ሰዎችን ከመስደብና ከማዋረድ ይርቃል። ባይርቅም፣ አያዘወትርም። የጨዋነት ልማድ፣ የይሉኝታ ልጓም እስካለ ድረስ ማለት ነው። እነዚህ የተበጣጠሱና የተሰባበሩ ጊዜ፣ መያዣ መጨበጫ ያጣል።
ደግሞም ሲያጣ እያየን ነው። የኑሮ ድህነትና እጦት ያህል፣ በመርህ ድህነት ላይ የጨዋነት እጦት እየጨመርንበት ትርምስ አብዝተናል።
እውነት ይሁን ውሸት፣… አንዱን ለማሞገስ ሌላውን ለመስደብ እስካገለገለ ድረስ፣ ያለ ቅንጣት ይሉኝታ፣ እስከ ጥግ ድረስ የሚያስጮኹ የብሽሽቅ ፊታውራሪዎችና ረዳት ጋጠወጦች በርክተዋል። ገናናም ሆነዋል። ከየጎራው አውራ የአሉባልታ ወሬ እየተቀበሉ በእልፍ አባዝተው የሚያስተጋቡና የሚያዛምቱ የብሽሽቅ አጃቢዎችም ሞልተዋል። የውሸት ወሬ እንደሆነ ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ ችግር አይቆጥሩትም።
አዎ፣ የውሸት ወሬና ስድብ፣ ብሽሽቅና ወንጀል፣… የጥላቻ ዘመቻን ያቀጣጥላል። ለጅምላ ግድያዎች መንገድ ይከፍታል። ኑሮን ያጎሳቁላል። ጦርነትን ይፈጥራል። ይሄ ሁሉ በተግባር ከበቂ በላይ ታይቷል። ቢሆንም ግን፣…
ያሰኛቸውን በጭፍን ለማወደስ፣ ያሻቸውን በጭፍን ለማንኳሰስ እስካገለገለ ድረሰ… የውሸት ወሬ ችግር የለውም፤ እንዲያውም ጠቃሚ ነው ብለው ያስባሉ። ምን ይሄ ብቻ?
“ምንም የማይፈራ ቆራጥ ተቃዋሚ” የሚል ሹመት ወይም…
“በታማኝነት የላቀ ሃይለኛ ቲፎዞ” የሚል ማዕረግ የሚያስገኝ ይመስላቸዋል። ደግሞ ሊያስገኝ ይችላል።
ከዚህኛው ጎራ በኩል የመጣ መግለጫ፣ ከዚህኛው የብሽሽቅ አውራ ከስድ አንደበት የወጣ ንግግር፣… ምንም ይሁን ምን፣… ውሸትም ቢሆን በጭፍን ማስተጋባትና ማወደስ፣…
ከወዲያኛው ጎራ በኩል፣ ከሌላ ተቀናቃኝ የመጣ ንግግር፣… ምን ይሁን ምን፣… እውነት ቢሆንኳ፣ በጭፍን ማብጠልጠልና ማንቋሸሽ… ሆኗል - የየጎራው ጩኸት።
ምንም ቢል፤ የውሸት መረጃና የተሳሳተ ሃሳብ ቢናገር፣…
ምንም ቢያደርግ፣ አክሳሪና አጥፊ እቅድ፣ ጎጂና አውዳሚ ተግባር ቢፈፅም፣…
የትኛውም አይነት ብልሹ ስብዕና ቢታይበት፣… መጥፎ ልማድና ክፉ ባህርይ ገንኖ ቢወጣበት፣.. የወዲህኛውን ጎራ ለማዳነቅ ከሆነ፣… የወዲያኛውን ተቀናቃኝ ጎራ ለማጥላላት እስካገለገለ፣…
እሰዬው “ይበል፤ ይበል” ብሎ የሚያስተጋባለት እንጂ እርማትና ማስተካከያ የሚሰነዝር አያጋጥምም።
“ደግ አደረገ፣ አበጀ!” ብሎ የሚደግፍ እንጂ ለማቃናት የሚሞክር አይኖርም።
የሚያዳንቅ እንጂ የሚገስፅ አይመጣበትም።
ሃሳብ፣ እቅድና ልማድ፣… ንግግር፣ ተግባርና ባሕርይ፣… እንዲህ አንድ ላይ እርስ በርስ ተያይዘው ሲበላሹ… ነገር ዓለሙ ሁሉ እየተዘበራረቀና እየጨላለመ ግራ ያጋባል።
የአእምሮ፣ የአካልና የመንፈስ ገፅታዎች ሁሉ፣ አንድ ላይ አብረው ሲለመልሙና ሲያምርባቸውም፣ ድምቀታቸው የዚያኑ ያህል ነው። ሁሉንም መልካም ገፅታዎች ለማጣመርና ለማዋሀድ የሚችል ቃል መኖሩ ታዲያ ያስገርማል? ደግሞም ያስፈልጋል።
ከተሟላ ትክክለኛ አስተሳሰብ ውጭ፤… ማለትም ከእውነትና ከመርህ፣ ከብቃትና ከጥረት ውጭ የሚገኝ ቅንጣት መፍትሔ የለም።
በማሸጋሸግ፣ በመበወዝ፣ በመከለስ፣ መልሶ መላልሶ በማገላበጥ፣ ለጭፍን እምነትና ለዘረኝነት መፍትሄ የሚገኝ ይመስለን ይሆናል። ግን ከንቱ ምኞት ነው።
የውሸት፣ የጥፋትና የክፋት መንገዶች ናቸውና፣ እነዚያኑን በማሸጋሸግ ከመከራ መዳን አይቻልም። በየትኛው ሰው አንደበት፣ ውሸትን እልፍ ጊዜ ቢበውዙት፣ “እውነት” አወጣውም። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካም በእልፍ አቅጣጫ ቢያገላብጡት ቢያሸጋሽጉት አያለማም።
በሌላ አነጋገር፣…
1. ጭፍን እምነትን በአንዴ ባይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሸነፈ የሚጓዝ የእውነትና የእውቀት ብሩህ መንገድ ከወዲሁ ያስፈልጋል።
2. እየማገዱና እየተማገዱ ከሚጠፋፋበት ጉራንጉር የሚወጣው፣ ወደ ከፍታ የሚወሰድ፣ የግል ጥረትንና ፍሬያማነትን የሚያከብር የተቃና መንገድ ከወዲሁ ሊቀየስ ይገባል።
3. በመንጋና በጅምላ ሳይሆን እያንዳንዱን ሰው በግል ተግባሩ የሚመዝን የፍቅርና የፍትህ መርህም ከወዲሁ መታሰብ አለበት።
በአጠቃላይ፣… የተሟላ መፍትሄ አሁን ያስፈልጋል።
በአንድ ዓመት በአስር ዓመት ተከናውኖ አያልቅም።
ነገር ግን ከወዲሁ የተሟላ የመፍትሄ ሃሳብና መርህ ያስፈልጋል። አለበለዚያ፣ ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ እንኳ ለይተን ማወቅ ያቅተናል። እናም፣ ወደ ውጤታማ ስኬት የሚወስደንን የዓመታት የጉዞ አቅጣጫ ዛሬውኑ መጨበጥ ይኖርብናል።
ፅድቅ የሚለው ቃል ይህንንም የሚጨምር መሆን አለበት። የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት አተረጓጎሙ ማለቴ አይደለም። በመደበኛ ዓለማዊና መንፈሳዊ ትርጉሙ ማለቴ ነው።
የቃሉ ትርጉም፣ በአንድ በኩል… በጥሬው እውነት ማለት ነው። እውነትን መናገርና መመስከር፣ ሰምቶና አይቶ እውነትን አረጋግጦ መቀበል… ማለት ነው የቃሉ ትርጉም።
በሌላ በኩልም፤ ትክክለኛ ሃሳብና ጠቃሚ እቅድን ተገንዝቦ መደገፍ፤ ማፅደቅ፣ ተግባራዊ ማድረግ ማለት ነው - ሁለተኛ ትርጉሙ።
ሦስተኛው፣ ሕያውነትንና ልምላሜን፣ የተቃና ባሕርይና መልካም ስብዕናን፣… የተቀደሰ የግል ማንነትና ብቃትን የሚገልፅ ነው - የቃሉ ትርጉም።
የተሟላ መፍትሔ የሚሆነን፣ ፅድቅ ብቻ ይሆን?
ፅድቅ ማለት በጥሬው እውነት ማለት ነው። እውነትን መናገርና መመሰከር ነው ፅድቅ።
የሰውን ንግግር ሰምተው፣ ትክክለኛና ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበው ሃሳቡንና እቅዱን አጸደቁ እንላለን፣… ተግባራዊ እንዲሆን በመስማማትና በመደገፍ።
“ችግኝ ፀደቀ፣ አፀደቁ” ይባላል። መጠውለግን ሳይሆን መለምለምን፣ መክሰምን ሳይሆን ሕያውነትን የሚያከብር ትርጉም አለው።
“ጻድቅ ናት። እነሱ ጸደቁ”… ብለንም ቃሉን እንጠቀማለን።
እያንዳንዱን ሰው በግል፣…እንደየተግባራቸው እንደየባህሪያቸው፤ የግል ብቃትና የግል ማንነታቸው፣ በትክክል ተለይቶ፣ ከዚያም ሚዛኑና መጠኑ ተለክቶ፣ የነፍሳቸውን፣ የመንፈሳቸውን፣ የግል ማንነትና የስብዕና ክብራቸውን የሚገልፅ ፍሬ ሃሳብ ነው - ፅድቅ።
በአጠቃላይ፣ እውነት ከመናገርና ለእውነት በቅንነት ከመቆም ጀምሮ…
ትክክለኛ ሃሳብን የመቀበልና ጠቃሚ እቅድን የማፅደቅ ወይም የመደገፍ ቀናነትን ጨምሮ፣…
ፍሬያማና ሕያው ስራ በተግባር የመፈፀምና ኮትኩቶ የማፅደቅ፣…
ይህን ሁሉ ከእለት ኑሮና ከሕይወት ጋር፣ ከማንነትና ከባህርይ ጋር የማዋሃድ ትርጉም አለው-ጽድቅ።
ወይስ በድምፅ ተመሳሳይ የሆኑ የተለያዩ ቃላት ናቸው?
ቢሆኑም እንኳ፣ ሁሉንም ማዋሃድ ያስፈልጋል - መፍትሔ ከፈለግን።

Read 9081 times