Saturday, 24 December 2022 16:13

የእኛ ሰው በኳታር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ30 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በመሳብ

        ኳታር ባዘጋጀችው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ  ከ1.4 ሚሊዮን  በላይ ዓለምቀፍ ጎብኝዎችን አስተናግዳለች። የዓለም ዋንጫው 64 ግጥሚያዎች በዓለም ዙሪያ ከ5 ቢሊዮን በላይ ተመልካች ነበራቸው። 12ሺ ጋዜጠኞችና የስፖርት ባለሙያዎች የዓለም ዋንጫውን የተሳተፉበት ሲሆን ኢትዮጵያን በመወከል በሙያ ዘመኔ ታላቁን ስኬትና ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቻለሁ። ከምድብ ማጣሪያ እስከ ፍጻሜው ድረስ 30  የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን  በስምንቱ ዘመናዊ ስታድየሞች  የመታደም ዕድል አግኝቼ 29 ለመመልከት ችያለሁ። የዓለም ዋንጫ ታሪኬን ከ15 በላይ የተለያዩ አገራትን የሚወክሉ ከ30 በላይ ሚዲያዎች  ዘግበውታል። ከዚህ በታች የቀረበው ጽሁፍ ይህን የሚዳስስ ነው።
የምንጊዜም ምርጥ የዓለም ዋንጫ
22ኛው የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ከፈረንሳይ ባደረጉት የፍፃሜ ፍልሚያ ከተጠናቀቀ በኋላ አዘጋጇ ኳታር ብሄራዊ ቀኗን አክብራለች። የዓለም ዋንጫው መስተንግዶ የምንግዜም ምርጥ በመባሉ ክብረበዓሉን አሳምሮላታል፡፡ የዋንጫ ጨዋታው  ከ88696 በላይ ተመልካች በሚይዘው በግዙፉ የሉሲየል ስቴዲየም ከተካሄደ በኋላ ሁሉም  64 ጨዋታዎችን ከ3.5 ሚሊዮን ስፖርት አፍቃሪዎች በስታድዬም መመልከታቸው ክብረወሰን ነው። የዓለም ዋንጫው የምንግዜም ምርጥ የተባለው ከፍተኛ የስታድዬም ተመልካች በመመዝገቡ ብቻ አይደለም፡፡ ከምድብ አንስቶ እስከ ፍፃሜው በታየበት አስደናቂ ፉክክርና የውጤት ድራማ ነው። ሁሉንም አህጉራት የወከሉ ቡድኖች ጥሎ ማለፍ ገብተዋል። የአፍሪካ ቡድን በሞሮኮ አማካኝነት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍጻሜ በመግባትና 4ኛ ደረጃ በማስመዝገብ አዲስ ታሪክ ተሰርቷል። የአረቡን ዓለም ባህል ባስተዋወቁ ዘመናዊና አስደናቂ ስታድዬሞች እያንዳንዱ ጨዋታ በማይረሳ መስተንግዶ፣ ፉክክርና የተመልካች ድባብ ተከናውኗል። ከ12ሺ በላይ የዓለም ሚዲያዎች በምቹ መስተንግዶና መሰረተልማት በመስራታቸው በኳታር በሙያ ዘመናቸው የላቀውን ልምድ አግኝተውበታል።  ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ለጉብኝት ኳታር ገብተዋል። ይህም የዓለም ዋንጫውን ገቢ ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ያመለከተ ሲሆን በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ኳታርን ከ40 ቢሊዮን በላይ ጎብኚዎች እንደሚያጥለቀልቋት አስገምቷል።  ከአርጀንቲና ድል በኋላ ደቡብ አሜሪካ  ከ22 የዓለም ዋንጫዎች 10ሩን መውሰዷ ተረጋግጧል።  አርጀንቲና ከ36 ዓመታት በኋላ ዓለም ዋንጫውን በመውሰድ የዓለም ዋንጫ ድልን ለሶስተኛ ጊዜ የወሰደች ሲሆን በ1978 እና በ1986 ሁለት ዓለም ዋንጫዎችን ማሸነፏ ይታወሳል። የፈረንሳዩ ክሊያን ምባፔ በኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ ሲሸለም አርጀንቲናውያኑ ሊዮኔል ሜሲ በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ፣ ማርቲኔዝ በኮከብ በረኝነት የወርቅ ጓንት ተሸልመዋል።
የ33 ቀናት ቆይታዬ ምን ይመስላል?
ከ22ኛው የዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ በኳታር ዋና ከተማ ዶሐና ሌሎች አጎራባች ከተሞች ያደረጉት የ33 ቀናት ቆይታ በዘመናዊ ስታዲየሞች ጨዋታዎችን በመከታተል የተወሰነ አልነበረም። የአዘጋጇን ኳታር ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶች፤ የተለያዩ አገሪቱን የሚወክሉ ማህበረሰቦች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ያካልላል።ስለ ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎቹ በማያያዝ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በቀጥታ ከዶሐ ከተማ  4 ሳምንት ልዩ ዘገባዎች በመላክ ለህትመት በቅተዋል። ባሻገር ከየጨዋታዎቹ በፊትና በኋላ በፌስቡክና ኢንስታግራም ገጾች የቪዲዮ ምስሎችን፣ የቀጥታ ዘገባዎችን፣ የጽሑፍና የፎቶግራፍ ማስታዎሻዎችን በማዘጋጀት ሰፊ ሽፋን መስጠት ተችሏል። በአራዳ ኤፍ ኤም ሳምንታዊ የራዲዮ ዝግጅትና፣ ለቀጥታ ስርጭት ኳስ በሚተላለፉ ልዩ ፕሮግራሞች የስልክ ውይይቶች ተደርገዋል። በዓለም ዋንጫዎቹ የእረፍት ቀናት ከኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ የተለያዩ አካላትና፣ ስራ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን ጋር  “የእኛ ሰው በኳታር” በሚል ርዕስ ከፍተኛ ልምድ የምንቀስማቸው ቃለመጠይቆች ተሰርተዋል። በኳታር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጉብኝት በማድረግ በኳታር የቱሪዝም አድራሻዎች በመዘዋወር ተጨማሪ የጉዞ ማስታወሻዎች ተዘጋጅተዋል። የዓለም ዋንጫ የቴክኒክ ቡድን በሰጠው መግለጫ፣የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ፣ በኳታር ፋውንዴሽን በተዘጋጀ የከተማ ጉብኝት፣ በካታሯ ቪሌጅ በተካሄደ የውይይት መድረክ፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ባዘጋጀው የባህልና የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መድረክ በአካል፣ በመገኘትና ክትትል በማድረግ ልዩ ማስታወሻዎች ተከትበዋል። ለምሳሌ ያህልም በኳታር ፋውንዴሽን በተዘጋጀው ልዩ የጋዜጠኞች ጉብኝት በዶሐ የሚገኘውን የትምህርት ከተማ ተዟዙሮ የመመልከት ዕድል መፈጠሩን መጥቀስ ይቻላል። ከፖላንድ፣ ከቻይና፣ ከፍልስጤም፣ ከካሜሮን ጋዜጠኞች ጋር ባደረግነው ጉብኝት በትምህርት ከተማው ውስጥ በትምህርት፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ ልማት የተገነቡ ተቋማትን አይተናል። በዲሬሻ የስነ-ጥበብ ፌስቲቫል የፋውንዴሽኑ ፌልሃርማኒክ ኦርኬስተራ ግዙፍ ሙዚቃ ዝግጅት ታድመናል።
ከ64 ጨዋታዎች፣ 29 በመታደም
በዓለም ዋንጫው ከተደረጉት 64 ግጥሚያዎች 30 ጨዋታዎችን የመመልከት እድል በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ተስጥቶኝ 29 ጨዋታዎችን ስታድየም ገብቼ ተከታትያለሁ። ከብራዚልና ደቡብ ኮሪያ ጨዋታ በቀር። በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች 30 ጨዋታዎችን በመመልከት ባለክብረወሰኑ በኳታር የሚገኘው ግርማቸው ከበደ ነው።  ዶሐ በስፖርት  ማኔጅመንት እያጠና  በመክፈቻውና በምድቡ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች የሊግ ስፖርት ጋዜጣን ከወከለው አለምሰገድ ሰይፉ ጋር በዶሐ  ስታድዬሞችና የሚዲያ ማዕከል ላይ አስደናቂ ጊዜዎችን አሳልፈን በአርትስ ቲቪ ለዕይታ ቀርቧል። ታች  ከጥሎ ማለፍ  ጀምሮ ዓለም ዋንጫውን ያጣጣምነው ደግሞ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ከፍተኛ ልምድ ካለው  ከይስሐቅ  በላይ ጋር ነው። አስደናቂ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በሚዲያ ትሪቡን ጎን ለጎን ተቀምጠን ተመልክተናል። የማስታወሻ ፎቶ እየተነሳን የዓለም ዋንጫውን በመዘገብም ልዩ ተሞክሮ አግኝተናል ከይስሐቅ ጋር። በየሚዲያ ማዕከሉ ከትላልቅ የእግር ኳስ ሰዎች ጋር ተገናኝተናል። ጆተኒ ተጫውተናል። ከሌሎች የዓለም ጋዜጠኞች ጋር በአውቶብስ ጉዞዎች፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎች የሚዲያ ማዕከሎችና ስታዲየሞች ተቀላቅለን  አድራሻዎችን ተለዋውጠናል።
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ከተሰለፍኩላቸው 30 ጨዋታዎች መካከል  ከ9 በላይ ለሚሆኑት ከጨዋታ በኋላ በተዘጋጁ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ተሳትፌያለሁ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ለካሜሮን፣ ለጋና፣  ለሞሮኮ፣… ዋና አሰልጣኞችና ዋና አምበሎች ያቀረብኳቸው ጥያቄዎችና ምላሻቸው ይገኙበታል። ከ29 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በግዙፉ የሉሴይል ስታድየም 7፤ በአልጃኑብ ስታድየም 6፣ በአልባዬት ስታድየም 5፣ በአልቱ ማማ ስታድየም 5፣  በኤሱኬሽን ሲቲ ስታድየም 3፣ በካሊፋ ኢንተርናሽናል  ስታድየም 2፣ በስታየም 974 እንዲሁም በአህመድ ቢን አሊ ስታድየም አንድ ጨዋታን በእያንዳንዳቸው ተመልክቻለሁ።
ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በመሳብ
ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የዓለም ዋንጫ ታሪኬን በተለያየ መንገድ ዘግበውታል። በኮስታሪካ፣ በስሎቫኪያ፣ በኡዝ ቤኪስታን፣ በፖላንድ፣ በዮክሬን፣ በአርጀንቲና፣ በጃፓን፣ በሜክሲኮ፣ በቻይና፣ በሞሮኮ፣ በአልጄርያ፣ በግብፅ፣ በአረብ ኢምሬትስ፣ በፔሩ...ወዘተ የህትመት፤ድረገፅና ብሮድካስት ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ ናቸው። በዓለም ዋንጫው ማግስት ደግሞ በኳታር ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኳታር ቲቪ ለመቅረብ በቅቻለሁ። የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዬ የዓለም ሚዲያዎችን ትኩረት የሳበው በተለያዩ ምክንያቶች ነው።  በሙያና የእግር ኳስ ፍቅር  ባገኘሁት አድናቆት፤ ልዩ የስፖንሰርሲፕ ድጋፍ ሳልይዝ በዓለም ዋንጫው ላይ ለመስራት በመገኘቴ፤ በዓለም ዋንጫው  ሬጌና ስነጥበብ ለማስተዋወቅ ባደረኩት እንቅስቃሴና በራስታ ስብዕናዬ፤ በሚዲያ ማዕከል በነበረኝ ዝነኝነትና የነቃ ተሳትፎ፤ በአስደናቂዎቹ ስታድየሞች በተመልካችና ሚዲያዎች በሳብኩት ትኩረት፤ ስለ ኳታር የዓለም ዋንጫ ስኬታማነት በምሰጣቸው ቅን አስተያየቶችና ሌሎች ሁኔታዎች ነበር ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲዎች ጋር ባደረግኳቸው ቃለምልልሶች፣ ውይይቶችና ልዩ አስተያየቶች የዓለምን ትኩረት የሚስቡ አዳዲስ  ሃሳቦች ተንጸባርቀዋል። የኳታር ምንጊዜም ምርጥ የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ተደንቋል። የስነ-ጥበብ ዲፕሎማሲ በስፖርቱ ላይ የሚጫወተው ሚና ተዋውቋል። የሬጌ ሙዚቃ  ዓለማቀፋዊነት ተንጸባርቋል። ስፖርት ለሰው ልጆች አንድነት የሚጫወተው ሚና በእማኝ  ለመመስከር ተችሏል። ሚዲያ በዓለም አቀፍ ስፖርት ያለውን  አቅምና አስተዋጽኦ በልዩ መልኩ ተገልጿል። የአገር፣ አህጉር፣ የዓለም ገጽታ በበጎ መልኩ ተናፍሷል።
የዓለም ዋንጫ ታሪኬን ከዳሰሱ ዘገባዎች መካከል በቀን 1.5 ሚሊዮን ኮፒ  በሚታተመውና በቻይናው ሻንግዶንግ ግዛት በሚሰራጨው ኪሉ አቪኒንግ ኒውስ፤ ሌላው የቻይና የማህበረሰብ ጋዜጣ “ዳይዞንግ ዴይሊ” (3605ሺ ቅጂ በቀን ይታተማል) የቀረቡት ይጠቀሳሉ።ቻይና በ2030 ወይ በ2034 የዓለም ዋንጫ በማዘጋጀት የሚኖራትን ዕድል  የሚያነቃቁ ናቸው። በአርጀንቲና ሚዲያዎች ደግሞ ሰፊውን ሽፋን አግኝቻለሁ። በዓለም ዋንጫው ያለስፖንሰር በመከሰቴ፣ ለሙያው ባሳየሁት ትጋና በከፈልኩት መስዕዋትነት፣ በዓለም ዋንጫው የአርጀንቲና ተስፋ በምሰጣቸው አስተያየቶች ዙሪያ በርካታ ዘገባዎቹ ተሰርተዋል። ላቮዝ፣ ኢንፎቢ፣ ለሪፐብሊካን፣ በተባሉት የአርጀንቲና ሚዲያዎች የቀረቡት ይጠቀሳሉ። ከስሎቫኪያው ጋዜጣ ፕራቭዳ፣ ከኡዝቤኪስታን ትልቅ ሚዲያ ተቋም ሻምፒዮናት፤ ከዩክሬኑ ፉትቦል ዩክሬን፣ ከኮስታሪካ የራዲዮ ጣቢያ፣ ከጣሊያኑ ዕውቅ ጋዜጠኛ ታንኬርዲ ፓሌርሚ ጋር በፉትቦል ኢታልያ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ግዙፍ የሚዲያ ተቋም አሻራቅ እንዲሁም ከቱርኩ አናዱሉ ኤጀንሲ ጋር ልዩ ቃለ-ምልልሶችን አድርጌያለሁ። በኳታር ቲቪ ክብር እንግድነት በመቅረብ  የዓለም ዋንጫውን ስኬታማነት በሚያረጋግጡ ሃሳቦች ዙሪያ በክብር እንግድነት ተወያይቻለሁ።
በመጨረሻም ልዩ ምስጋና በመጀመሪያ ደረጃ ልዩ ምስጋናዬን የማቀርበው ለኳታር መንግስት፣ ለዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ኮሚቴ፣ ለዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ እንዲሁም በኳታር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ በተለይ በ33 ቀናት የዓለም ዋንጫ ቆይታዬ በመኖሪያ ቤቱ ማረፊያዬን በማመቻቸት ከፍተኛ ድጋፍ ለሰጠኝ ስንታዬው ተፈራ አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለ5 ዓመታት ያገለገለውና በኳታር 9 ዓመታት በሚዲያና ዲፕሎማሲ ስራዎች የሚንቀሳቀሰው ስንታየሁ የዓለም ዋንጫ ታሪኬን ለማዘጋጀት ሙያዊ ድጋፍ ሰጥቶኛል። በዓለም ዋንጫው በአስደናቂ የስዕል ስራዎቹ ስነ-ጥበባዊ ዲፕሎማሲ በመጫወት ዝነኛ ለሆነው ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ ተሰማ አስራቴ ተምትሜ ልዩ አክብሮትና ምስጋናዬን መግለጽ እፈልጋለሁ። ሰዓሊና የሥነ-ጥበብ ዲፕሎማቱ ተሰማ የዓለም ዋንጫ ቆይታዬን አስደሳች አድርጎታል። በመጨረሻም ዓለማቀፉን የኳታር አርት ኢንተርናሽናል ፌስቲቫል ህንዳዊቷ ራሺሚ አግራዋል  የተገናኘን ሲሆን ከ22ኛው ዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ልዩ ድጋፍ ላደረገልኝ  ለመደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራ የ2022 QIAF የተሳትፎ  ልዩ ሽልማት ተበርክቶልናል። የስነጥበብ ስፍራ በ2023 በሚካሄደው ኳታር ኢንተርናሽናል አርት ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክ እንዲሳተፍ ተጋብዟል።


Read 10621 times