Saturday, 31 December 2022 12:03

መንግስት በህገወጥ መንገድ ወርቅና ማዕድን የሚዘርፉ የውጭ ዜጎችን አደብ እንዲያስገዛ ባለሀብቱ ጥሪ አቀረቡ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

             ባለሀብቱ በራሳቸው ጥረትና ትግል 35 ህገ ወጥ ቻይናውያንን ለመንግስት አስረክበዋል
              
        መንግስት በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን በህገወጥ መንገድ የወርቅና የማዕድናት ዘረፋ ላይ የተሰማሩ ህገ-ወጥ የውጭ ዜጎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግና አደብ እንዲያሲዝ የታይም ጀነራል ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መኩሪያ ባሳዬ ጥሪ አቀረቡ፡፡ ባለሀብቱ በጉጂ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የውጭ ዜጎች የስደተኛ መታወቂያ ይዘው በመግባት ያለ መንግስት እውቅና የሀገርን ወርቅ እየዘረፉ ከብሄራዊ ባንክ ውጭ በጥቁር ገበያ እንደሚሸጡና ከሀገር እንደሚያስወጡ ገልፀዋል፡፡
ባለሀብቱ ይህንን ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ለማሳወቅ ቢመላለሱም የሚያስገባቸው እንዳጡና በመጨረሻም ከኦሮሚያ መንግስት፣ ከጉጂ ዞንና ከእናሶራ ወረዳ ሀላፊዎች እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ታጣቂዎችን ይዘው ከተሰማሩ በኋላ ህዳር 18 ቀን 2015 ዓ.ም 35 ቻይናዊያንን በህገወጥ የወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ እያሉ እጅ ከፍንጅ ይዘው ለመንግስት ማስረከባቸውንም አብራርተዋል፡፡
በህገወጥ የወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩት ቻይናውያን ብቻ ሳይሆኑ ወደ 135 የሚደርሱ የህንድ፣ የሱዳን፣ የሶማሊያና የሌላም አገር ዜጎች ናቸው ያሉት አቶ መኩሪያ፤ በተለይ 35ቱን ቻይናውያን ስንይዝ ሌሎቹ ከህገወጥ ደላሎችና ጉዳዩ በውል ካልገባቸው አንዳንድ የአካባቢው ወጣቶች ጋር በመነጋገር ከጉጂ ሸሸተው ወደ ጋምቤላና ሌሎች አካባቢዎች መግባታቸውን በቁጭት ተናግረዋል፡፡
“በዶላር እጥረት እየተቸገርን፣ በጦርነት እየታመስንና በረሃብ እየተጎዳን ያለነው ሀገራችን ደሀ ስለሆነች አይደለም” ያሉት ባለሀብቱ፤ “እኛ እርስ በርሳችን በዘርና በሀይማኖት ተከፋፍለን ስንበላላና ስንቧጨቅ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ወርቅና ማዕድናችን በባዕዳን ስለሚዘረፍ ነው” በማለት ገልፀዋል፡፡
“ህገወጦችን ለመያዝ ስነሳም፣ ታጣቂ ከመንግስት ስጠይቅም ሆነ ቻይናዎቹን ስንይዝ በራሴ መኪና በራሴ ነዳጅ እንጂ ከመንግስት ምንም የጠየቅኩት ነገር የለም” ያሉት ባለሀብቱ፤ ይህን የማደርገው ለሀገሬና ለወገኔ ካለኝ ቁጭት ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ የውጪ ህገ-ወጦች ከደላላ ጋር በመነጋገር የገበሬውን መሬት በአነስተኛ ገንዘብ በመውሰድ በሀገራቸን የምድር እምብርት ያለውን ውድ ወርቅ እየተቀራመቱ ነው የሚሉት የታይም ማዕድን መሥራችና ባለቤት አቶ መኩሪያ፤ እነዚህ ህገ-ወጦች 20 በ30 ከሆነ የአንድ አርሶ አደር መሬት ላይ ቆፍረው 8 ኪሎ ወርቅ ካወጡ በኋላ ለአርሶ አደሩ ደረቅ ቼክ ሰጥተው እስከ ማምለጥ የደረሱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ህገ-ወጥ የውጭ ዜጎች ሳተላይቶች የውጭ መገናኛ ሬዲዮኖችና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ባለሀብቱ ጠቅሰው፤የግለሰቦቹ ፎቶዎችና ህገ ወጥ መታወቂያዎቻቸው በእጃቸው በማስረጃነት እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ከኦሮሚያ መንግስትና የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ህገ ወጦችን የማፅዳት ሥራ በሚሰሩበት ወቅት ጥቅማቸው የተነካባቸው ህገ-ወጥ ደላሎች ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርሱባቸው እንደነበር የተናገሩት አቶ መኩሪያ፤ በአዶላ ወረዳም በህገወጦቹ የተሰበሰበ በርካታ ወርቅ፣ የተለያዩ ማዕድናትና ኬሚካሎች በአንድ ክፍል ቤት ሞልተው አስቀምጠው መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡
ባለሀብቱ አክለውም፤ መንግስት እነዚህን ህገ-ወጦች አድኖ በመያዝ የሀገሪቱን ሀብት ከዘራፊዎች እንዲጠብቅ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ከጉጂ ሸሽተው ጋምቤላና ሌሎች አካባቢዎች የገቡትን በተለይ ተከታትሎ ለህግ እንዲያቀርብ መንግስትን በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡
በ2 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል በወርቅና ማዕድን ማውጣት ሥራ የተሰማራውን ታይም ማዕድን” ጨምሮ 32 ኩባንያዎችን ያቋቋሙት ባለሃብቱ፤ ለ3ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል መክፈታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

Read 4975 times Last modified on Saturday, 31 December 2022 12:12