Saturday, 31 December 2022 12:13

መከላከያና ፌደራል ፖሊስ መቀሌ ገብተዋል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(9 votes)

  • የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ከተሞች እየወጣ ነው ተባለ
     • “ለሰላም ተብሎ ነው በሚል ሰበብ ስምምነቱ የአገሪቱን ህግ እየጨፈለቀ መፈፀም የለበትም”
         
         የመንግስትና የህወሓት ከፍተኛ የጦር አመራሮች በናይሮቢ ያካሄዱትን ውይይትና የደረሱበትን ስምምነት ተከትሎ፣በያዝነው ሳምንት የሰላም ስምምነት ሂደቱን የሚያፋጥኑ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በዚሁ ስምምነት መሰረትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መቀሌ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አጉላና የሰፈረ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ ደግሞ መቀሌ ከተማ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ሰፍሯል። የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት የህወሓት ታጣቂዎች የፈቱትን ጦርና ከባድ መሳሪያ እስከ ትላንት በስቲያ ሐሙስ ይረከባል የተባለ ቢሆንም፣ የህወሓት ታጣቂ ሃይሎች ከባድ መሣሪያዎቻቸውን ስለማስረከባቸው የተገለጸ ነገር የለም፡፡  
የዚሁ ስምምነት አካል የሆነውና በፌዴራል መንግስቱ ከተፈፀሙ ጉዳዮች መካከል መቀሌ ከተማን ጨምሮ በሌሎች የትግራይ ክልል ዋና ዋና ከተሞች የስልክ፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎቶችን የማስጀመሩ ሂደትም ተፈፃሚ ሆኗል፡፡ ከ3 ቀናት በፊት በተጀመረው የመቀሌ ከተማ የስልክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ በጀመረው የበረራ አገልግሎት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸው ችለዋል፡፡  
ታህሳስ 19 ቀን2015 ዓ.ም ከ18 ወራት መቋረጥ በኋላ በተጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ በርካቶች ከዓመት ተኩል በላይ ከተለያዩአቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተዋል፡፡ የስልክ አገልግሎት በመቀሌ በተጀመረ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ220 ሺህ በላይ ጥሪዎች ወደ መቀሌ መደረጉን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በክልሉ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ከ27 የሚበልጡት የስልክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል፡፡
ድርድሩን በበላይነት ሲመሩ ከቆዩት የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አደራዳሪዎች መካከል የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሶንጆና የቀድሞው የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ተቋም(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ሂደት ለመመልከት ከትላንት በስቲያ መቀሌ ከተማ ገብተዋል፡፡
ይህንኑ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለመቋጨት በህወሓት ታጣቂ ሃይሎችና በመንግስት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ሂደት የሚቃወሙ  ወገኖች፤ “ለሰላም ተብሎ ነው በሚል ሰበብ ስምምነቱ የአገሪቱን ህግ እየጨፈለቀ ሊፈፀም አይገባውም” ይላሉ፡፡
ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡት የፖለቲካ ምሁሩና የህግ ባለሙያው ዶ/ር ተስፋዬ አጥናፉ፤ “እንደ አንድ ሰላም ፈላጊ ዜጋ የተደረገውን የሰላም ስምምነት እደግፋለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን እየተካሄደበት ባለው የስምምነት አፈፃፀሙ ላይ ብርቱ ተቃውሞ አለኝ፡፡ አፈፃፀሙ የአገሪቱን ህጎችና ህገ መንግስቱን በራሱ የሚፃረር፣ የዜጎችን መብት የሚጥስ ነው“ ብለዋል፡፡
ሲጀመር ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት ግጭት የማስቆም ስምምነት በጦርነቱ ወቅት ለደረሱት የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ተጠያቂ የሆኑ ወገኖችን ለህግ ስለማቅረብ ምንም ያለው ነገር የለም ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለስደት የዳረጉ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሃብትና ንብረት ያወደሙ፤ ሴቶችና ህፃናትን ሳይቀር የደፈሩ ወንጀለኞች በምንም አይነት ህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ባልተገለፀበት መንገድ የሰላም ስምምነት አድርገናል ማለቱ በዜጎች ሰብአዊ መብቶች ላይ መቀለድ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም፣ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር ላይ ህውሐትን በአሸባሪነት የፈረጀ ሆኖ እያለ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ እንዲሁም የህውሐት ቁንጮ አመራሮች ላይ የክስ መዝገብ የከፈተው የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህውሐትን አሸባሪነት በምክር ቤቱ ሳያነሳና የተከፈተባቸው የወንጀል ክስ መዝገብ ሳያዘጋ ወይም ክሱ ሳይቋረጥ ከአሸባሪ ቡድኑ አመራሮች ጋር እየተቃቀፉ ፎቶግራፍ መነሳት ለዜጎች የሚሰጠው መልዕክት ፈፅሞ የተዘነጋ ይመስላል፡፡ ይህ ሁኔታ ግልፅ የህግ ጥሰት የተፈፀመበት ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ሰብአዊ መብት ያላከበረና በሺዎች በሚቆጠሩ በጦርነቱ መስዋዕት በሆኑ ወገኖች ላይ መቀለድ ነው” ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዜጎች ለተቋማቱ የሚኖራቸውን እምነትና በተቋሙ ላይ የሚጥሉትን ተስፋ የሚያሳጣ አደገኛ አካሄድ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ሰለሞን መስፍን፤ “ከቀናት በፊት ፍርድ ቤቱ በእነዚህ ተከሳሾች ላይ በከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል የተከፈተውን መዝገብ እየተመለከተ ባለበት፤ የፍርድ ሂደቱን ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ በሰጠበትና ተከሳሾቹ ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማዘዣ በወጣበት ሁኔታ የክስ መዝገቡ መቋረጡ ወይም መዘጋቱ ሳይነገር የአገሪቱን ህግ የሚጠብቅ ትልቅ ተቋምን የሚመሩት ሰው ተከሳሽ ተብለው የመያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው ሰዎች ጋር በዚህ ደረጃ ሲተቃቀፉ ማየት የአገራችን የፍትህ ስርዓት ከምን ደረጃ እንደደረሰ ማሳያ ነው፡፡ ህግ ሃይለኞች ሲስማሙ የሚወዳጁበት ሲጣሉ የሚያፈርሱት መጫወቻ አይደለም፡፡ ይህ በሚሊዮኖች ደምና አጥንት ላይ የተቀለደ እጅግ አሳዛኝ ቀልድ ነው” ብለዋል፡፡
የህግ የበላይነት የሀገር ህልውና መሰረት መሆኑ ፈፅሞ ሊዘናጋ አይገባም ያሉት ዶ/ር ሰለሞም፤ ቢያንስ የስምምነቱ አፈፃፀም ህጋዊ ሥርዓትን የተከተለ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በመንግስትና በህውሃት መካከል የተደረሰውን ስምምነት እያከበሩ አይደለም የሚል ወቀሳ የሚቀርብባቸው የህውሐት ሀይሎች ከሰላም ስምምነቱ ውጪ የሆኑ ተግባራትን እያከናወኑ ቢሆንም ማንም ሃይ ባይና ከልካይ አለማግኘታቸውንም ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ የህውሃት ሃይሎች በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ራሳቸው ባወጡት የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ለመንግስት ተባባሪ ነበር የሚሉትን ወገን የተለያዩ ክሶችን በመመስረትና በራሳቸው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በመቅጣት ዜጎችን ለእስር እየዳረጉ መሆኑን የሚገልፁት ምንጮች፤ ክልሎች የራሳቸውነ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሚያወጡት በምን አግባብ ነው ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
የህውሃት አመራሮች በአሁኑ ሰዓት እንኳን የመቀሌ ከተማ መሬትን በሊዝ እየቸበቸቡ፣ የራሳቸውን ህቡዕ አደረጃጀት እየፈጠሩና በውጪ አገር ከሚኖሩ ደጋፊዎቻቸው ጋር የዲያስፖራ ኮሚቴ አቋቁመው  ውስጥ ለውስጥ እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ የሰላም ስምምነቱ በህውሃት በኩል እኩል ተቀባይነት አግኝቷል ለማለት አያስደፍርም ብለዋል፡፡
ይህ በመንግስትና በህውሃት ታጣቂ ሃይሎች መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘ ጉዳይ ቢሆንም አፈፃፀሙ ህግና ስርዓትን በተከተለና የዜጎችን ሰብአዊ መብት ባከበረ መልኩ እንዲሆን መደረግ እንዳለበትም ተገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤የኤርትራ ሰራዊት ላለፉት 18 ወራት ከቆየባቸው የትግራይ ክልል ከተሞች ትናንት መውጣት መጀመሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ሮይተርስ በዘገባው እንዳመለከተው፤ የኤርትራ ወታደሮችን የጫኑ በርካታ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከአክሱም ከተማ አቅጣጫ በመምጣት ወደ ሽራሮ ማለፋቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡  
የህውሃት ሃይሎች የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ላለመፈፀማቸው ከሚጠቅሷቸው ምክንያቶች አንዱ የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ክልል አለመውጣቱ መሆኑ ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ህብረትም የኤርትራ ሠራዊትን ከትግራይ መውጣት ደጋግመው ሲጠይቁ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

Read 5483 times