Saturday, 31 December 2022 12:09

የእግር ኳሱን ንጉሰ ነገስት ፔሌ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

     "የተወለድኩት እግር ኳስን ለመጫወት ነው፡፡ ልክ ቤትሆቨን ሙዚቃን ለመፃፍ፤ ማይክል አንጀሎ ለመሳል እንደተወለዱ፡፡ በዓለም ላይ ማንኛውም ልጅ እግር ኳስ ሲጫወት ፔሌን መሆን ይፈልጋል፡፡ ኳስ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን እንዴት ሰው መሆን እንደሚችሉ የማሳየት ትልቅ ኃላፊነት አለብኝ"

          ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉሰ ነገስት ኤዲሰን አረንተስ ዶናሲሜንቶ ፔሌ ከትናንት በስቲያ በ82 ዓመት እድሜው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ፔሌ በተጨዋችነት ዘመኑ በነበረው ልዩ ተሰጥኦ፤ ብቃትና ጥንካሬ እንዲሁም በእግር ኳሱ ዓለም ከ70 ዓመታት በላይ በቆየበት ተወዳጅ ስብዕናው የስፖርቱ  አምባሳደር ሆኖ በመላው ዓለም እንደሚደነቅ ይታወቃል፡፡
ከ21 ዓመታት በላይ በቆየበት የተጨዋችነት ዘመኑ በ1363 ጨዋታዎች ከ1283 ጎሎች በላይ ያስቆጠረው ፔሌ፤ ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን ጋር 3 የዓለም ዋንጫዎችን በ1958፤ በ1962 እና በ1970 እኤአ ላይ በማሸነፍ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡ ፔሌ በታዋቂው የብራዚል ክለብ ሳንቶስ  በ659 ጨዋታዎች 643 ጎሎችን በስሙ ያስመዘገበ፤ በ1 የውድድር ዘመን 127 ጎሎች ያስቆጠረ፤ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ለ14 ዓመታት በመጫወት በ92 ጨዋታዎች 77 ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ፤ በፊፋ የምንግዜም ምርጥ የተባለና ከማራዶና ጋር የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠ፤ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የክፍለዘመኑ ምርጥ አትሌት ተብሎ የተሰየመ፤ በ4 የዓለም ዋንጫዎች የተጫወተና ጎል ያስቆጠረ፤ 7 ግዜ ተፍራንስፉትቦል የወርቅ ኳስ የተሸለመ፤ ከ92 በላይ ሃትሪኮች በመስራት ልዩ ክብረወሰን ያስመዘገበ እና እግር ኳስን በማው ዓለም በማስተዋወቅ የተወደሰ የስፖርቱ ዓለም ባለውለታ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ስለ ፔሌ በተነሳ  ቁጥር የሚታወስ አንድ ታሪክ አለ፡፡ ከክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  በ1970 እኤአ ላይ 13ኛው የዓለም ዋንጫ በሜክሲኮ እየተካሄደ ነበር፡፡ ዓለም ዋንጫውን አስመልክቶ ለኢትዮጲያውያን ትንታኔ ያቀረቡት  ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ ጥያቂያቸውን ለማቅረብ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሚሰራጭ ፕሮግራም ላይ 10 የስፖርት ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡ ደምሴ ዳምጤ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ግርማ ሰይፉ ከአዲስ ዘመን፤ በሃይሉ አስፋው ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ ኢብራሂም ሃጂ ከበሪሳ ጋዜጣ፤ ሰለሞን ገብረእግዚአብሕር ከኢቲቪ፤ ይንበርብሩ ምትኬ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ሃድጉም መስፍን ከዓልአለም ጋዜጣ፤ ገዛህኝ ፄዮን መስቀል ከኢዜአ እና አዋያዩ ፀጋ ቁምላቸው ነበሩ፡፡
90 ደቂቃዎችን በፈጀው መግለጫ ላይ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ ከፔሌና ከማራዶና የቱን ያደንቃሉ? የሚል ነበር፡፡ ክቡር ይድነቃቸው ምላሽ ሲሰጡ ‘’አንድ ያልገባችሁ ነገር ፔሌን አናውቀውም ስትሉ እራሳችሁን ልጅ ማድረጋችሁ ነው? ወጣት ነኝ ለማለት ካልፈለጋችሁ በቀር ፔሌ ሲጫወት አይታችሁታል፡፡ ማራዶና በአሁኑ ትውልድም እንደምናየው ጥሩ ተጫዋች ነው ግን ግራኝ ነው” ብለው ማስረዳታቸውን ሲቀጥሉ ሁለቱን ተጨዋቾች ማነፃፀር  በእጅጉ እንደሚከብድ ሊያመለክቱም ሞክረዋል፡፡ ፔሌ  በሁለቱም እግሮቹ እንደሚጫወት፤ ሰውነቱም የተደላደለ እንደሆነና ኳስን የመቆጣጠር ብቃቱ በጣም የተሻለ መሆኑን ክቡር ይድነቃቸው አስረድተዋል፡፡ ማራዶና ብዙ ጊዜ ኳስን በእራሱ እንደማይነካ ፔሌ በአንፃሩ ብዙ ጎሎችን ያስገባው በጭንቅላቱ ገጭቶ እንደሆነና ፍጥነቱም እንደሚያስደንቅ አብራርተዋል፡፡ ማራዶና ሰባት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ ማግባቱ አለምን ማስደነቁን የጠቀሱት ይድነቃቸው፤ ፔሌ እስከ ዘጠኝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ ማግባቱን ይህን ብቃቱንም ከ30  ጊዜ በላይ እንደደገመው አስቀምጠዋል፡፡

Read 3186 times