Saturday, 31 December 2022 12:33

መንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ መንግስት ከእነ ደብረፂዮን ቡድን ጋር ለመደራደር ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዘው መቀሌ ከተማ በራፍ ላይ ደርሶ ምናልባትም ከተማዋን በሶስትና በአራት ቀን ውስጥ መቆጣጠር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ይገኝ በነበረበት ጊዜ መሆኑ  ይታወሳል፡፡
“ምታ በዝምታ” የሚል ስያሜ የተሰጠው በዛ እንቅስቃሴው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሀይል አማፂው ቡድን ላይ እጅግ ከፍተኛ የበላይነት ያስገኘለት ጉዞና ተጋድሎ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዛው ሰሞን የመንግስት አካል የሆኑ የመረጃ አጣሪ  “የትግራይ ጦር የሚባል ነገር የለም፣ የትግራይ መንግስት ብሎ ነገርም የለም፤ ያለው አንድ አመፀኛ ቡድን ነው” የሚል መግለጫ በመስጠት ትክክለኛ መልክ አሳይቶም ነበር፡፡
በደቡብ አፍሪካው ድርድር፣ የእነ ደብረፂዮን ቡድን፣ የኢትዮጵያ መንግስትንና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ተቀብሎ ትጥቁን እንዲያወርድ በማድረግ በመንግስት አሸናፊነት ስምምነቱ እንዲጠናቀቅ ሆኖ ነበር፡፡
የእነ ደብረፂዮን ቡድን በየጊዜው በሚሰጠው የተምታታ መረጃ ምክንያትም ከተደራዳሪዎች አንዱ የሆኑት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የስምምነቱን ዝርዝር ይዘት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ይፋ እስከ ማድረግም ተገድደዋል፡፡
በስምምነቱ በመንግስትም ሆነ በታጣቂው መከናወን ያለባቸው ተግባሮች እንደ ቅደም ተከተላቸው የተዘረዘሩ ቢሆንም፣ በተግባር እየዋሉ ያሉት ግን በመንግስት በኩል ሊፈፀሙ የታሰቡ ብቻ ናቸው፡፡ አንድም አይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ያልፈለገውና ያላደረገው የእነ ደብረፂዮን ቡድን በዚህ ጊዜ ስራዬ ብሎ  ያሰራጭ የነበረው በመንግስት ላይ ክስና ወቀሳ ብቻ ነበር፡፡
በትጥቅ አፈታት ዝርዝር አፈፃፀም ላይ ለመምከር ወደ ናይሮቢ ያመራው በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው የመከላከያ ቡድን፣ የትኛው መሳሪያ ቀድሞ የትኛው መከተል አለበት ከሚል የአፈፃፀም መመሪያ ከማዘጋጀት ወጥቶ ተደራዳሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡  “ቡድኑ መሳሪያ የሚያወርደው በትግራይ ክልል የሚገኙ የውጭ ሀይሎች ሲወጡ ነው” ሲል መስማማቱ ለአማፂው ቡድን የፈለግከው ይሁንልህ ማለት እንደሆነ እንዴት እንዳልተረዳው ገርሞኛል፡፡
በስምምነቱ እየተገዛ ያለው መንግስት ወደ ትግራይ የሚያስገቡትን ሶስቱንም በሮች እንዲከፈቱ፤ የመብራት፣ የስልክና የባንክ አገልግሎቶች መቀሌን ጨምሮ በክልሉ ብዙ ቦታዎች ላይ ስራ እንዲቀጥሉ በማድረግ ብቻ አልቆመም፡፡ ከታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መደበኛ በረራውን ወደ መቀሌ እንዲያካሄድም አድርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን መንግስት በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ተቋርጠው የቆዩ አገልግሎቶችን ወደ ቦታቸው እየመለሰ የሚጠበቅበትን ግዴታ እያሟላ ነው፡፡ በአጭሩ የአስቀረው ነገር የለም ለማለት የሚያስደፍር ሆኗል፡፡
ታህሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በአፈ ጉባኤ ታደሰ ጫፎ የሚመራ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቡድን ወደ መቀሌ ተጉዞ ከእነ ደብረፂዮን ጋር ተነጋግረዋል፡፡ በምን በምን ጉዳዮች ላይ እንደተነጋገሩ በዝርዝር የተገለፀ ነገር ባይኖርም፣ ተጓዡ  ቡድን ስለ አንድ ቀን ውሎው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሪፖርት ማድረጉ ታውቋል፡፡ የሪፖርቱ ይዘት አሁንም ይፋ አልወጣም፡፡
“ሶስተኛ ወገኖች ጣልቃ ያልገቡበት” ተብሎ የተወደሰው ይህ ጉዞ እና ውይይት ወደ ትግራይ የሚደረገውን የአየር በረራ ከታቀደው ጊዜ በፊት እንዲፈፀም ከማድረግ ውጪ ያስገኘው ነገር ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ከውይይቱ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን፣ የእነ ደብረፂዮን ቡድን ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም የከባድ መሳሪያ ትጥቁን እንደሚያስረክብ ቢናገሩም፣ ይህ ፅሁፍ እየተዘጋጀ ባለበት ጊዜ ስለርክክቡ መጠናቀቅ አይደለም ስለመጀመሩም የተሰማ ነገር የለም፡፡
በዚህ አጋጣሚ ሁለት ነገሮችን አስታውሼ አጥብቄ ማሳሰብን መርጫለሁ፡፡ የመጀመሪያው መከላከያ ወደ መቀሌ ከተማ መግባትና ጊዜያዊ ወይም የሽግግር አስተዳደር የማቋቋሙ ጉዳይ ነው፡፡ እንደኔ የሚቋቋመው አስተዳደር ወታደራዊ አስተዳደር ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ መንግስት አንድ ጊዜ አደለም አንድ መቶ አንድ ጊዜ ማሰብ ያለበት የትግራይ ህዝብ በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቀ ያለው ሰላም እግር እየተከለና እየፀና የሚሄድበትን መንገድ በማመቻቸት ነው፡፡ ይህን ወደ እውነትነት ማምጣት የሚቻለው ደግሞ በፌዴራል መንግስት የሚቋቋመው የሽግግር አስተዳደር በትክክል የተቋቋመ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ አስተዳደር እንደከዚህ ቀደሙ የጊዜያዊ አስተዳደር ሁሉ በእነ ደብረፂዮን ቡድን እንዳይጠለፍ መንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ያልተቋረጠ ክትትልም ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከመጠንቀቅ በላይም መጠንቀቅ  ያለበት ደግሞ የእነ ደብረፂዮን የአስተሳሰብ ቫይረስ የተጫነባቸው ሰዎች፣ በለውጥ ደጋፊነት ስም ተግተልትለው እንዳይገቡ በማድረግም ነው፡፡
ሁለተኛው በገፍ ወደ ትግራይ እየገባ ስላለው የእርዳታ እህልና ቁሳቁስ ነው፡፡ የእነ ደብረፂዮን ቡድን የመሳሪያና የገንዘብ ምንጭ አድርጎ ሲገለገልበት የቆየው ይህን መንገድ ነው። ይህ መስመር መንግስት አጥብቆ ሊቆጣጠረው ይገባል፡፡ በዚህ መንገድ የሚታየው መላላት ሌላ ጦርነት ሌላ መተላለቅ አያስከትልም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን!

Read 1573 times