Print this page
Sunday, 01 January 2023 00:00

መሰንጠቅ ለማገዶ ነው፤ መጨፍለቅ ደግሞ ለፍንዳታ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

 - የአገራችን እንዲሁም የራሺያና የዩክሬን ጦርነቶች የዓመቱ ዜና ነበሩ፡፡
   - በአንድ ኪሎ ግራም ሃይድሮጅን 50 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን የመተካት ሙከራስ?
           

       የየእለቱ ዋና ዜና፣ የጦርነትና የአደጋ ወሬ እንጂ፣… “አዲስ የሳይንስ ግኝት” ወይም “አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ” አይደለም። ብዙ ጊዜ አያጋጥምም።
ወሬዎችን ሁሉ የሚያስንቅ አዲስ የጦርነትና የቅራኔ መረጃ ጠፍቶ አያውቅም። ውዝግብና ውንጀላ እየተወራወሩ፣ ሁሌም የዜና ርዕስ የሚሆኑ ተቀናቃኞችም ብዙ ናቸው። በዚያ ላይ፣ አስፈሪና አሳዛኝ አደጋዎች ሞልተዋል። ይህም ብቻ አይደለም።
የጦርነትና የወረርሽኝ መረጃ በየእለቱ እየበረከተና እየሰፋ፣ ዓይነቱና ቁጥሩ ይጨምራል። ለበርካታ ወራት ላይረግብ ይችላል። የክትባት ወይም የሰላም ስምምነት ግን፣ የአንድ ቀን ዜና ነው። ከሳምንት በኋላ፣ ዜናነቱ ይበርዳል።
ደግሞስ፣ ጦርነትና በሽታ እንጂ፣ እንዴት ሰላምና ጤና እንደ ጉድ እንደ ዜና ይወራለታል? “ዛሬም በርካታ የዓለም አገራት፣ እንደትናንቱ ሰላም ናቸው” የሚል ዜና ተሰምቶ አይታወቅም።
“ሰላም” መደበኛ የኑሮ ሁኔታ እንጂ፣ እንደ ብርቅ መታየት የለበትማ። ከዚህ አንፃር፣ የጦርነትና የአደጋ ዜናዎች በየቀኑ እየተደራረቡ መግነናቸው ላይገርም ይችላል።
ግን፣ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶችና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች፤ ለምን ከዓለም የዜና ተርታ ውስጥ ጠፉ? “የመሬት ስበት እንደትናንቱና እንደቀድሞው፣ ዛሬም ሕግና ሥርዓቱን ሳያዛንፍ ቀጥሏል” ተብሎ ይወራ ማለት አይደለም።
የኤሌክትሪክና የስልክ፣ የቴሌቪዥንና የኮምፒዩተር ፈጠራዎች፣… የመኪናና የአውሮፕላን ቴክኖሎጂዎችም ጭምር፣ ድንገት ብን ብለው እንዳልጠፉና፣ ዛሬም በህልውና እየቀጠሉ መሆናቸውን በዜና ይነገር ለማለትም አይደለም።
አዳዲስ የሳይንስና የቴክኖሎጂ መረጃዎች ግን አልጠፉም። ታዲያ ለምን ዜና አይሆኑም?
በእርግጥ፣ የክትባት ፈጠራዎች የዓለማችን ዋና ዜና የሆኑበት አጋጣሚ አይተናል። ዜና ለመሆን የበቁት ግን፣ ከኮሮና ወረርሽ ጋር ስለተዛመዱ ብቻ ነው - ማለትም ከአደጋና ከበሽታ ጋር ስለተዳበሉ ብቻ።
በቅርቡ የተሰራጨ የአመቱ ትልቅ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዜና ደግሞ አለ። የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል። ለምን? በመረጃው ክብደት ነው? ድንቅ የሳይንስ ግኝት፣ ግሩም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በየሚዲያው ቅድሚያ እየተሰጠው በየአገሩ ዜናው እየተሰራጨ የዓለም መነጋገሪያ የሆነው ግሩም ድንቅ መረጃ ስለሆነ ብቻ ነው ወይ?
እንግዲህ፣ አፈትልኮ እንደወጣ “ትልቅ ምስጢር” ተደርጎ ነበር የተወራው፤… በግዙፎቹ የዜና ተቋማትም የተዘገበው።
ከዋናው የአሜሪካ የኒዩክሌር ተቋም የመጣ መረጃ፣ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የተገኘ ወሬ እንደሆነም ተጠቅሷል። የተቋሙ ሃላፊዎች ግን ወዲያውኑ የማስተባበያም ሆነ የማረጋገጫ ቃል አልተነፈሱም። ከጋዜጠኞች የሚጎርፍ እልፍ ጥያቄዎች በስልክና በኢንተርኔት ተቋሙን ለማጥለቅለቅ ጊዜ አልፈጀባቸው። በብርሃን ፍጥነት ነው የዘመናችን ወሬ።
የተቋሙ ሃላፊዎች ግን፣ ቀጥተኛ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ቢሆንም ግን በፋይናንሻል ታይምስ የተለኮሰው ቁራጭ ዜና፣ እንደ ሰደድ እሳት መቀጣጠሉ አልቀረም። ሲኤንኤን፣ ቢቢሲ፣ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ኒው ዮርክ ታይምስ… ገናናዎቹ የሚዲያ ተቋማት፣ የተለያዩ ምንጮችንና ባለሙያዎችን በማነጋገር መረጃውን እየተቀባባሉ ሲዘግቡት ውለዋል፤ አድረዋል።
የሳይንስ ሊቃውንትና የቴክኖሎጂ ጠበብት፣ ለ50 ዓመታት ሲመራመሩበትና ሲሞክሩት የነበረ፣ እስከዛሬ ያልተሳካ የሃይል ማመንጫ ዘዴ፣… ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተሳካና የሚጨበጥ ውጤት እንዳሳየ የሚገልፅ ነው - መረጃው።
በዓለም ዙሪያ እጅግ የተራቀቁና ዝና ያተረፉ የፊዚክስ ጠበብት፣ በመረጃው እንደተደነቁ ተናግረዋል። በተለይ የኒዩክሌር ተመራማሪዎች፣ በዘገባው በጣም እንደተደሰቱ በመግለፅ በአግራሞት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
መረጃው እውነት ከሆነ፣ የዓለማችንና የሰው ልጅ ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደተሸጋገረ ወይም የመዳረሻ በር እንደተከፈተ ይቆጠራል በማለት ተናግረዋል። ዝርዝር መረጃዎችን በጉጉት እንደሚጠብቁም ጠቅሰዋል።
“ለውረንስ ሊቨርሙር” የተሰኘው ግዙፍ የኒዩክሌር ተቋም፣ ለአንድ ቀን መረጃ ሳይሰጥ ማደር ይችል ይሆናል። ከዚህ በላይ ለማዘግየት ግን ይቸገራል።
ወይ ማስተባበበል አለበት።
ወይ ማረጋገጫና ማብራሪያ መረጃዎችን መስጠት ይኖርበታል።
ወይም ደግሞ፣ “ጉዳዩ ምስጢር ስለሆነ፣ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ምላሽ መስጠት አልችልም” ብሎ አሳማኝ ምክንያት ለማቅረብ ይሞክራል።
በእርግጥም፣ ተቋሙ የምስጢሮች አምባ ነው። የአሜሪካ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን፣… የአተም ቦምብና የሃይድሮጅን ቦምብን ጨምሮ፣ ተዛማጅ የጦር መሳሪያዎችን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ተቋም ነው። የወታደራዊ ምስጢሮች መነሃሪያ ስለሆነ፣… ሰው ዝር የማይልባቸው፣ በታጠቁ ወታደሮች የተከበቡ ሰፈሮች አሉት። የኒዩክሌር መሳሪያዎች ጉዳይ ነዋ ነገሩ።
ግን ደግሞ፣ ወታደራዊ ያልሆኑ ሰፈሮችንም ያካትታል። ከኒዩክሌር ቦምብ የራቁ የምርምር ማዕከላትን በውስጡ ይዟል።
“Star builders” የተሰኘው መጽሐፍ፣ ይህን “ባለ ሁለት ፊት ተቋም” ያስቃኘናል። በቀጥታ ከጦር መሳሪያ ጋር የተቆራኘ የኒዩክሌር ምርምር አለ። ለዚያውም በአለምና በታሪክ ወደ የሌላቸው ቦምቦች ላይ የሚያተኩር ነው ምርምሩ። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የኒዩክሌር የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ምርምርና ቴክኖሎጂ አብሮት ይካሄዳል።
የጦር ሰፈር ከዩኒቨርስቲ ጋር የተጎራበቱበት፣ ወይም የጦር መሳሪያ ማምረቻ ከግል የቴክኖሎጂ ፋብሪካ ጋር፣ ወይም የመከላከያ ሚኒስቴር ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የተዳበሉበት ማዕከል ይመስላል። ደግሞም ነው።
የሆነ ሆኖ፣ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የተገኘው መረጃ፣ ከምርምር ማዕከል አፈትልኮ እንደወጣ ትልቅ ምስጢር በመላው ዓለም ሲሰራጭ ውሎ አመሸ።
በማግስቱ፣ “ታሪካዊና ይፋዊ የመግለጫ ድግስ” ተዘጋጀ። ጋዜጠኞች ከየአቅጣጫው መጡ።
የጋዜጣዊ መግለጫው ዋና ባለቤት የአሜሪካ የኢነርጂ ሚኒስቴር ነው።
የኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ባለብዙ ቅርንጫፍ ነው። በአንድ በኩል በነዳጅ ምርትና በኤሌክትሪክ ሃይል ዙሪያ የ50ዎቹ ግዛቶችና ጠቅላላ የአሜሪካ አገራዊ መረጃዎችን የሚመዘግብና የሚያጠና ዘርፍ አለው።… የእያንዳንዱን አገር ዝርዝር መረጃዎች፣ ከድፍድፍ ነዳጅ እስከ ቤንዚን ፍጆታ፣ ከሃይል ማመንጫ አቅም እስከ ሽያጭ፣… ዓለምን ሁሉ የሚያካትቱ መረጃዎችን ያሰባስባል፤ ያጠናቅራል፤ ያሰራጫል።
በኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ ጣቢያዎች የሚመነጭ ኃይል፣ በመሃል የሚባክንና ለአገልግሎት የሚውል የኤልክትሪክ ፍጆታ ምን ያህል እንደሆነ… የየዓመቱን መረጃ በሰፊው ለማግኘት፣… የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ ድረገጽን ማሰስ፣ የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን አትጠራጠሩ።
የነዳጅ ቁፋሮ፣ የማጣሪያ ፋብሪካ፣ የማስተላለፊያ ቱቦ፣ የሀይል ማመንጫ በመሳሰሉት ስራዎች ላይ የንግድ ምዝገባ ያካሂዳል። ፈቃጅና ከልካይ ልሁን ማለቱም አልቀረም። አገሬው የነፃ ገበያ መዲና የነበረ ቢሆንም።
ለማንኛውም፣ የኢነርጂ ሚኒስቴር በነዳጅና በኤሌክትሪክ ላይ ያተኮሩ ቢሮዎችን ከማስተባበር በተጨማሪ፣ የምርምር ተቋማትንም ይቅፋል።
እናም የኢነርጂ ሚኒስቴር ነው የጋዜጣዊ መግለጫው አዘጋጅ።
ሚኒስትሯ ናቸው ዋናዋ የመግለጫው መሪ።
መቼም… ዜናው ትልቅ ቢሆን ነው።
ሚኒስትሯ ጀኒፈር ግራንሆልም ወደ መድረክ የወጡበት መንፈስ የጀብድ ነው። የመግለጫ ንግግራቸው የሚያሻማ አይደለም። የብስራትና የድል አዋጅ ይመስላል።
አዲሱ የምርምር ስኬት በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ሲተረክ ይኖራል ብለዋል ሚኒስትሯ። የዓመቱ ምርጥ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዜና ነው አላሉም።
የመቶ ዓመታት ምርጥ ዜና እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከተመዘገቡት ድንቅ የሳይንስ ግኝቶችና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መሃል በቀዳሚዎቹ ተርታ ላይ የሚቀመጥ ነው፣ ትልቅ ታሪክ ተሰርቷል ሲሉ ተናግረዋል።
የምርምር ተቋሙ ዋና ዳይሬክተርም፣ አሜሪካ ከሌሎች አገራት እጅግ እንደቀደመች፣ ፈርቀዳጅ ውጤት እንደተመዘገበ ገልጸዋል።
የኒዩክሌር ምርምሮችን የሚመሩ፣ የጦር መሳሪያ ፈጠራና የዲዛይን ዋና ሃላፊም፣ ዛሬ የተገኘው ውጤት፣ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል። የመላው ዓለም ሳይንቲስቶች ለሃያ ለሰላሳ ዓመታት የደከሙለትና ሳይሳካ የቆየ አስደናቂ እመርታ ነው ሲሉ ክስተቱን አድንቀዋል።
ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ውዳሴና የሽርጉዱ መነሻ ምንድን ነው?
“የኒዩክሌር ፊዩዥን ቴክኖሎጂ… ከወጪ ቀሪ ያለው ኃይል አመነጨ” የሚል ነው ዜናው።
በቃ። ይሄው ነው ዋናው ፍሬ ነገር።
እንዲሁ ሲታይ፣ ትልቅ ዜና አይመስልም።
በእርግጥ ውስጠ ሚስጢሩን አብጠርጥረው ለሚመራመሩ ሳይንቲስቶች፣… ወይም በጥቅሉ ዙሪያ ገባውን ለሚከታተሉ ሰዎችም ጭምር፣… ዜናው ትልቅ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ለታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ ቀርቦ የነበረ አንድ ጥያቄ እናስተውስ።
በሚቀጥሉት መቶ ዓመታት የትኛው ምርምር እንዲሳካ ትመኛለህ ተብሎ ተጠየቀ - ስቴቨን ሆኪንግ።
“በ21ኛው ክፍለ ዘመን በኒዩክሌር ፊዮዥን አማካኝነት እጅግ ርካሽና የተትረፈረፈ የኃይል ምንጭ መፍጠር” የሚል ነበር የታዋቂው ሊቅ ምኞት።
ምኞቱ እስከ ዛሬ አልተሳካም። ለ80 ዓመታት ተሞክሮ አልተሳካም። አሁን የስኬት ጭምጭምታ እየሰማን ይሆን?
በእርግጥ የኒዩክሌር ኃይል አዲስ ነገር አይደለም። የኒዩክሌር ምርምር ከመቶ ዓመታት የበለጠ ታሪክ አለው።
ምርምሩ የተሳካውና የኒዩክሌር ኃይል ቴክኖሎጂ የተፈጠረው ደግሞ የዛሬ 80 ዓመት ነው። በጥቂት ዓመታት ውስጥም የኒዩክሌር ቦምብ ተሰራ (አቶሚክ ቦምብ ይሉታል)።
ከዚያም በኒዩክሌር ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ቴክሎጂዎች፣ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
ዛሬ፣ ከዓለማችን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ውስጥ፣ ከስድሳ እስከ ሰባ በመቶ ያህል ከከሰል ድንጋይ፤ 10 በመቶ ደግሞ ከኒዩክሌር ሃይል የሚመነጭ ነው።
እና ታዲያ አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?
“ታሪካዊ ውጤት ተመዘገበ” የሚያስብል ነገር ከየት መጣ?
እንግዲህ፣… የኒዩክሌር ኃይል አዲስ ነገር ባይሆንም፣… ዓይነት አለው። የኒዩክሌር ሀይል ሁሉ፣ እኩል አይደለም።
ነባሩ “አተም ሰንጣቂ” ቴክኖሎጂ - (Fission)።
የእስከዛሬዎቹ የኒዩክሌር ሃይል ቴክኖሎጂዎች፣ “ኒዩክሌር ፊዥን” የሚባሉት ነው።
የትልቅ አተም አስኳል፣ ለምሳሌ የዩራኒየም አተም አስኳል ለሁለት ወይም ለሶስት በመሰንጠቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ - ነባሮቹ ቴክሎጂዎች። የአተሞቹ አስኳል ሲሰነጠቅ እንደ ፍንዳታ ነው።
በአንድ ጊዜ 10 ኪሎ ግራም አተሞች በቅፅበት እየተሰነጣጠቁ ከፈነዱ፣ ትልቁ ከተማ አመድ ይሆናል። ነገር ግን፣ እንደ መኪና ነዳጅ በጥቂት በጥቂቱ እያነደደ በትንሽ በትንሹ እያፈነዳ መጠቀም ከቻለ፣ ጠቃሚ የሀይል ምንጭ ይሆናል።
እንደ ሲሊንደር ጋዝ ነው። የምድጃ ማብሰያ ዘዴ ሊሆንልን ይችላል። ከፈነዳ ደግሞ ያጠፋናል። የኒዩክለር ሀይልም እንደዛው ነው። በጥቂት በጥቂት የአተሞችን አስኳል ለመሰንጠቅ የመቆጣጠሪያ ዘዴ የተበጀለት ቴክኖሎጂ፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ቴክኖሎጂ ይሆናል።
የአተሞች አስኳል እየተሰነጠቀ በፍንጥርጣሪ ቅንጣቶችና በጨረሮች አማካኝነት ከፍተኛ የሙቀት ኃይል ይፈጠራል። በዚሁ ሙቀት ውሃ ማፍላት፣ በእንፋሎቱም ተርባይኖችን ማሽከርከርና ኤሌክትሪክ ማመንጨት ማለት ነው።
ለቅጽበታዊ ፍንዳታ ሲያውሉት ደግሞ የጦር መሳሪያ ይሆናል።
ገና ያልተሳካው “አተም ጨፍላቂ” የኒዩክሌር ሃይል - (Fusion)።
ሌላኛው የኒዩክሌር ኃይል፣ ትናንሽ አተሞችን፣ በተለይም የሃይድሮጅን አተሞችን ወይም አስኳሎችን በመጨፍለቅ፣ ተለቅ ወዳለ አስኳል በማጨቅ የሚፈጠር ኃይል ነው።
ታዲያ፣ሁለት አተሞችን ወይም አስኳሎችን ወደ አንድ መጨፍለቅ ማለት፣ ተደፍጥጠው አንድ አስኳል ይሆናሉ ማለት እንጂ፣ ሁለት አተሞች ይጣመራሉ ማለት አይደለም።
አስኳል መሰንጠቅ ማለትም የተጣመሩ አተሞችን የመለየት ጉዳይ አይደለም።
“ኒዩክሌር ፈዥን”፣ አንዱን አተም በመሰንጠቅ ወደሌላ አይነት አተሞች የሚቀይር ነው።
“ኒዩክሌር ፊዩዥን” ደግሞ፣ ሁለት አተሞችን ወይም አስኳሎችን ጨፍልቆ፣ በዓይነት የተለየ ሌላ አንድ አተም ወይም ሌላ አንድ አስኳል እንደመፍጠር ነው።
የአተሞችን አስኳል በመሰንጠቅ ወይም በመጨፍለቅ የሚፈጠረው የሙቀት ኃይል እጅግ ከፍተኛ ነው። ለሂሳብ ቢያስቸግርም፣ ከማገዶና ከቤንዚን ጋር ያነጻጽሩታል።
አንድ ኪሎ የከሰል ድንጋይ፣ ከአንድ ኪሎ እንጨት በእጥፍ እና ከዚያ የሚበልጥ የሙቀት ኃይል ይሰጣል።
እነ ቤንዚን እና ናፍታ፣ ከከሰል ድንጋይ ትንሽ ይበልጣሉ።
የአተም አስኳሎችን በመሰንጠቅ የሚገኘው የሙቀት ኃይል ግን፣ ከከሰል ድንጋይና ከናፍታ ጋር ሲነጻጸር፣ 10 ሚሊዮን እጥፍ ነው።
የአተም አስኳሎችን በመጨፍለቅ የሚገኘው ኃይል ደግሞ ወደ 40 ሚሊዮን እጥፍ ይደርሳል።
ልዩነቱ የትና የት እንደሆነ ለማወቅ ርቀቱን ማስላት አያስፈልግም ቢባል አይሻልም?
በእርግጥ፣ ችግሮች አሉ። የአተም አስኳሎችን መሰንጠቅ፣ ወይም መጨፍለቅ ቀላል አይደለም። ማገዶ ለማንደድ፣… ትንሽ ጭድ፣ አንድ ክብሪት በቂ ሊሆን ይችላል። ቤንዚንና ናፍታም እንዲሁ። አተሞችን ለመሰንጠቅና ለመጨፍለቅ ግን… መከራ ነው።
ግን ዘዴ አልጠፋም። ሊቃውንትና ጠቢባን መላ ፈጥረዋል።
አተም በመሰንጠቅ፣ ሰማይ ምድሩን የሚያደባዩ ቦምቦች በገፍ ተሰርተዋል። የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችም ተገንብተዋል።
አተሞችን በመጨፍለቅስ? ቦምብ ተሰርቶበታል። ሃይድሮጅን ቦምብ እንዲሉ። የኤሌክትሪክ ማመንጫ ዘዴ ግን አልተፈጠረለትም።
አሁን እንደምንሰማው ዘዴ ከተገኘለትስ?
ያው፤ ቴክኖሎጂ እንደማንኛውም መሳሪያ፣ ጥቅሙና ጉዳቱ እንደአያያዛችን ነው። ከቤንዚን 40 ሚሊዮን እጥፍ ጉልበት ያለው ቴክኖሎጂ ደግሞ፤ ጥቅሙና ጉዳቱ የዚያኑ ያህል ብዙ ሚሊዮን እጥፍ ይሆናል።
ይሄ ሁሉ ልዩነት በ120 ዓመታት ርቀት።
በ1900 ዓም፤… በግዙፉ የዓለማችን መድፍ የሚፈጠረው የዘመኑ ከባድ ፍንዳታ፣ “2.6 ሜጋ ጁል” ጉልበት ነበረው። ደግሞ “ሜጋ ጁል” ምንድነው? ግድየለም ከቤንዚን ጋር በሊትር እናነፃፅረዋለን። ያኔ፣ ከ120 ዓመታት በፊት፣ “4 ሜጋ ጁል” በሚደርስ ጉልበት የሚፈነዱ የመድፍ አረሮች ተሰርው ነበር ብላችሁ አስቡት።
በእርግጥ፣ በሜጋ ጁል ከሚገለፀው “የኢነርጂ መጠን” ጋር፣ የፍንዳታው ቅፅበታዊ ፍጥነት ነው መዘዙን የሚያባብሰው።
አልያማ፣ አንድ ሊትር ቤንዚል በማቀጣጠል፣ ከስምንት እጥፍ በላይ የሙቀት ሃይል ማግኘት ይቻላል - ከ35 ሜጋ ጁል በላይ። ከዚህ ያነሰ ነበር የድሮው የፍንዳታ ጉልበት።
በ1945፣… ከጦር አውሮፕላን የሚዘንቡ ትልልቅ ቦምቦች ተሰርተዋል። 3800 ሜጋ ጁል ሀይል ነበራቸው። ከ100 ሊትር ቤንዚን የሚበልጥ የፍንዳታ ጉልበት ነበራቸው እንደማለት ነው።
በዚያው አመት፣ በ1945 የተሰራውና በጃፓን የፈነዳውን የመጀመሪያው የአተም ቦምብ ተመልከቱ። በዘመኑ ከተሰሩ ሌሎች ትልልቅ ቦምቦች ጋር ሲነጻጸር፣ 15ሺ እጥፍ ጉልበት ነበረው።
63 ሚሊዮን ሜጋ ጁል ነው፤ ሄሮሺማ ላይ የፈነዳው የአተም ቦምብ ጉልበት።
የቦምቡ፣ ከተጣራ ዩራንዬም ነው (60 ኪሎ ግራም ዩራኒዬም)።
ከአንድ ኪሎ ግራም ዩራኒዬ፣… “አንድ ሚሊዮን ሜጋ ጁል” ማለት ነው።
ከ1960 በኋላ የተሰሩ አተም ቦምቦች ግን፣… ከዚህም ይብሳሉ።
አንድ ኪሎ የተጣራ ዩራኒየም፣ “የአስር ሚሊዮን ኪሎ ግራም ቤንዚን” ያህል ነው ጉልበቱ።
የኢትዮጵያ የቤት መኪኖች የዕለት ፍጆታ ከዚህ ያንሳል። ከአንድ ኪሎም ዩራኒዬም በታች ነው - የአገራችን ዕለታዊ የቤንዚን ፍጆታ።
ይሄ “የዩራኒዬም አተሞችን በመሰንጠቅ” (በኒዩክሌር ፊዥን) የሚገኝ ቅፅበታዊ የፍንዳታ ኃይል ነው። የፍንዳታውን ፍጥነት ለመቆጣጠርና በቀስታ ለማከናወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ደግሞ፣ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት እያገለገለ ነው - በኒዩክሌር ፊዥን (አተሞችን በመሰንጠቅ)።
የዩኒክሌር ፊዩዥን ቴክኖሎጂ ከተሳካ ደግሞ፣…
አንድ ኪሎ የተጣራ ሀይድሮጅን፣… 40 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ቤንዚንን የሚተካ ሀይል ያመነጫል።
50 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን፣ በአንድ ኪሎ ሃይድሮጅን እንደመተካት ማለት ነው። ለዚያውም የዩራኒዬም አይነት አደጋ የለውም። ድንቅ ነው፤ ተዓምር ነው።
ለጊዜው በሙከራ የተሳካው ግን፣ ከቁጥር የሚገባ አይደለም።
3 ሜጋ ጁል ብቻ ነው - በስኬታማው ምርምርና ሙከራ የተገኘው ውጤት።
ከአንድ ሊትር ቤንዚን በታች ማለት ነው።
ኢምንት ነው።
ቢሆንም ግን፣ ፈርቀዳጅ ጭላንጭል ነው። እስከዛሬ እንደታየው፣ አተሞችን የመጨፍለቅ ዘዴ፣ ወደር የለሽ ፍንዳታ ለመፍጠር፣ መዓተኛ ቦምቦችን ለመስራት አገልግሏል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያገለግል ዘዴ መፍጠር እንደሚቻል ተጨባጭ የሙከራ ውጤት የተገኘው ግን፣ ገና ዘንድሮ ነው። ለዚህም ነው፣ “ታሪካዊ እመርታ” የሚል ማዕረግ የተሰጠው።

Read 3300 times