Saturday, 31 December 2022 12:44

ከሸንኮራ ንግድ እስከ ቢሊዮኖች ዶላር ኢንቨስትመንት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    የ32 ኩባንያዎች ባለቤትና የ3 ሺ ሰራተኞች አስተዳዳሪ ሆነዋል

      በኦሮሚያ ክልል ቦሬ ወረዳ፣ ኮቲኮ ቀበሌ፣ በ1964 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ አርሶ አደርና  ከፊል አርብቶ አደር አባታቸው ከአራት ሚስቶቻቸው ከወለዷቸው 44 ልጆች 39ኛ ልጅ ናቸው፡፡ በቦሬ ከተማ በካቶሊክ ሚሽነሪዎች በተከፈተው “ጎሳ” የተሰኘ ት/ቤት ለመማር ከአባታቸው እርሻ ላይ ቃርሚያ እየለቀሙና ደብተር እየገዙ ለሰባት ዓመታት ትምህርት ቢጀምሩም፣ አባታቸው ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ እያደረጉ ወደ ከብት እረኝነት ስለመለሷቸው የመማር እድል ሳያገኙ እስከ 13 ዓመት እድሜያቸው በከብት እረኝነትና ቤተሰብን  በማገልገል ቆይተዋል፡፡
የትምህርት እድል እንደማያገኙ ያወቁት የዛኔው ታዳጊ የአሁኑ ጎልማሳ ከመኖሪያ ቀያቸው ጠፍተው በቦሬ ከተማ የሸንኮራ አገዳ  ንግድ ቢጀምሩም፣ አባታቸው በታላላቅ ልጆቻቸው አሳድደው ወደ ቤታቸው መልሰዋቸዋል፡፡ ሆኖም  እምቢተኛውና አልበገር ባዩ ታዳጊ ድጋሚ ጠፍተው ወደ ሸንኮራ ንግዳቸው ተመልሰው መሥራት ጀመሩ - የዛሬው እንግዳችን ዝምተኛው ጀግና አቶ መኩሪያ ባሳዬ፡፡ ከዚያስ? አሁን የ32 ኩባንያዎች ባለቤትና የ3 ሺ ሰራተኞች አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ እንዴት? መልሱን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት  ዮሴፍ፣ በጉጂ ዞን የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሥራቸውን ባስጀመሩበት አናሶራ ወረዳ ተገኝታ ካደረገችው አስደማሚ ቃለምልልስ ታገኙታላችሁ፡፡ እነሆ፡-


          እንዴት ግን የሸንኮራ ንግድ ጀመሩ ማለቴ ለምን መረጡት? ከየትስ ወዴት እየወሰዱ ነበር የሚሸጡት?
ከፍተኛ የመማር ፍላጎት ነበረኝ፡፡ አባቴ ደግሞ ፍላጎቱ ከብት እንድጠብቅ ስለነበር፣ ሰባት ዓመት ሙሉ ትምህርት እየጀመርኩ አቋርጬ ወደ ከብት እረኝነት እንድመለስ አደረገኝ፡፡ ለመማር ካለኝ ጉጉት የተነሳ ከአባቴ እርሻ ላይ ቃርሚያ ለቅሜ እህል ሸጬ ነበር ደብተር የምገዛው፡፡ ይህ ሁሉ ፍላጎቴ መና ሲቀር ከቤቴ ጠፍቼ ቦሬ ከተማ ሄጄ ሸንኮራ መነገድ ጀመርኩ:: ይሁን እንጂ አባቴ በወንድሞቼ አሳድዶ ይዞ መለሰኝ፡፡ አሁንም ጠፍቼ ወጣሁ። በወቅቱ እናቴ ከሌሎቹ ልጆቿ በጣም ትወደኝ ስለነበር፣ አባቴን “ይሄ ልጅ እራቅ ወዳለ ቦታ ጠፍቶ ሄዶ ይሞትብኛል፤ እባክህ ተወው ይነግድ ትምህርትም ስራም ከልክለነዋል፤ እዚህ አይቀመጥም” በማለት ለመነችልኝ፤ አባቴም በቃ ተወኝ፡፡ እንደፈለግህ ሁን አለኝ፡፡
እናቴ ከሌሎች ልጆች በተለየ መልኩ ትወደኝ ነበር ብለውኛል፡፡ ለምን ነበር ከሌሎቹ የበለጠ የሚወዱዎት?
እናቴ እኔን በተለየ የምትወድበት ብዙ ምክንያት አላት፡፡ አንደኛ፤ የኔ ታላቅ ሞቶባት በመሪር ሀዘን ውስጥ ነበረች፡፡ ሁሌ ከቤት እየወጣች ስታለቅስ ስታዝን እየዋለች ትመለስ ነበር፡፡ አንድ ቀን በህልሟ “ሀዘን አቁሚ ወንድ ልጅ እሰጥሻለሁ፤ መኩሪያና መከታ የሆነ ልጅ ነው የምሰጥሽ” የሚል ህልም  አይታ እንደነበር ነግራኛለች፡፡ አምላክ እኔን ለመካስ የሰጠኝ ልጅ ነው ብላ ስለምታምን ነው በተለየ መልኩ የምትወደኝ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት እኔ ከተወለድኩበት ቀን ጀምሮ ለ3 ወራት ሙሉ አልተኛችም፡፡ ምክንያቱም በጣም የማለቅስ የምረብሽ ልጅ ነበርኩ፡፡ ከፍ እያልኩ ስሄድም አስቸጋሪ ነበርኩኝ፡፡ እናቴ ሁለት ሞግዚት ተጨምሮላትም አልቻሉኝም ነበር፡፡ አባቴ እንዲያውም “ይሄ ልጅ በግ ቢሆን አርጄው እገላገል ነበር” ብሎ እስኪማረር ድረስ ነበር የማስቸግረው፡፡ በዚህ እናቴ ለእኔ መስዋዕትነት ከፍላለችና ትወደኛለች፡፡
አባትዎ ሀብት ነበራቸው?
አዎ፤ እኔ ከብት እረኝነት በጀመርኩበት ጊዜ በትንሹ ወደ አራት ሺህ ከብትና 14 ጋሻ መሬት ነበረው፡፡ ይህ 14 ጋሻ መሬት ግማሹ በሰብል የተሸፈነ ሲሆን ግማሹ የከብት ማሰማሪያ፣ የግጦሽ ቦታ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ ብቻ እኔን ወደ መጥፋትና ወደ ሸንኮራ ንግድ ያስገባኝ ችግር ሳይሆን ትምህርት መከልከሌ ነበር፡፡ ንግዱን ሲከለክለኝ እናቴ ከላይ በገለፅኩልሽ መልኩ አስፈቀደችልኝና ቀጠልኩ ማለት ነው፡፡
መቼ ነበር  የሸንኮራ ንግድ የጀመሩት?
በ1979 ዓ.ም ነው  የጀመርኩት፡፡ ሸንኮራውን እኔ ከተወለድኩበት 14 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሱኬ ከሚባል ቦታ ገዝቼ፣ ቦሬ ከተማ ሌላ 16 ኪ.ሜ በድምሩ 30 ኪሎ ሜትር በእግሬ እየተመላለስኩ ነበር የምሸጠው፡፡ ሆኖም  የሸንኮራ ንግዱ አላዋጣ አለኝና ወደ ጨው ንግድ ገባሁ፡፡ ያን ጊዜ ከተማ ውስጥ ጨው የሚነግዱ ትልልቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አሸናፊ ደርሰህ የሚባል ሰው የ10 ብር ጨው ያበድረኛል፡፡ እሱን እየቸረቸርኩ 20 ሳንቲም ሳተርፍ፣ ያን ጊዜ “ገፉማ” የሚባል ምግብ ነበር። በአምስት ሳንቲም ገፉማ በልቼ 15 ሳንቲም እቆጥባለሁ፡፡ ያላተረፍኩ ቀን ወይም 10 ሳንቲም ብቻ ያተረፍኩ ቀን ከዚህ ላይ ገፉማ ከበላሁ የምቆጥበው ያንሳል በማለት ሳልበላ በእግሬ ወደ ቤት እሄድ ነበር፡፡ በዚህ አይነት እኔን እያዩ የሰፈሬ ልጆች ከኔ ጋር ንግድ ጀመሩ፡፡ ከነዚህ መካከል ነፍሱን ይማረውና ገዳቾ የሚባል ጓደኛዬ፣ ካሳ የሚባል ታላቅ ወንድሜና በቀለ የሚባል የወንድሜ ልጅ ሆነን መነገድ ቀጠልን። ብቻ የእኔን ፈለግ እየተከተሉ በጨው ንግድ 8 ደረስን፡፡
በዚያን ጊዜ ትልቁ ችግራችን ቋንቋ ነበር። እኛ ከገጠር ወደ ከተማ ስንመጣ አማርኛ አንችልም። እሱ ትንሽ ተፅዕኖ ቢፈጥርብንም ከከተማ ልጆች ጋር ጓደኝነት መሰረትን፡፡ ከእነዚህ ጓደኞቻችን ከድር መሃመድ የሚባል የጉራጌ ልጅ ተቀብሎ ከተማ አለማመደን፡፡ አሁን ወልቂጤ ነው ያለው፡፡ ሌላው ሲዳማ ውስጥ ማንም ንግድ ሳይጀምር ነጋዴ የነበሩት፣ በአሁኑ ወቅት ባለቤቴ የሆነችው የትዳር አጋሬ አባት ሲነግዱ እያየን እየተበረታታን ቀጠልን፡፡ እኔ በቀላሉ ከሰው ጋር የመግባባት ተሰጥኦ አለኝ፡፡ በዚህ አይነት ከከተማው ሰው ጋር መግባባቴን ቀጠልኩ፤ ሰውም እየወደደኝ መጣ ማለት ነው። ጨው እየነገድኩ ያጠራቀምኩት ካፒታሌ 25 ብር ሲደርስ ወደ እህል ንግድ ገባሁ፡፡ የእህል ንግድ እናንተ ካያችሁት ከአናሶራ ወረዳ ከቲቻ ቀበሌና ጎንቢሶ ቀበሌ እየገዛሁ፣ 54 ኪሎ ሜትር ድረስ በመምጣት ቦሬ ከተማ ነበር የምሸጠው፡፡ ያን ጊዜ ፈረስም ሰውም እከራያለሁ፡፡
ፈረስ የሚከራዩት መቼስ ለእህል መጫኛ ነው፤ ሰው የሚከራዩት ለምንድን ነው?
የሚገርምሽ በወቅቱ ቁመቴ ፈረስ ላይ እህል ለመጫን ስለማልደርስ ነበር ሰው እየተከራየሁ የማስጭነው፡፡ እህሉ በአግባቡና ሚዛኑን ጠብቆ ካልተጫነ ሩቅ መንገድ ስለሚጓዝ በጣም ያስቸግራል፡፡ እና በዚህ አይነት ከጠቀስኩልሽ ቀበሌዎች እህል ወደ ቦሬ እየጫንኩ ስነግድ ከቆየሁ በኋላ በ1980 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ከቦሬ ከተማ ከእኛ እየገዙ ወደ አለታ ወንዶና ወደ ነገሌ ቦረና ሲሸጡ አስተዋልኩ፡፡ አሃ እኔም በቀጥታ ወደ አለታ ወንዶና ወደ ነጌሌ መጫን እችላለሁ አልኩና፣ ሳልፈራ በድፍረት ወደዚያ ስራ ገባሁ፡፡ ይህንን ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመስራት ስድስት ፈረስ እህል ጭኜ ወደ ከተማ ስገባ፣ አንድ ሰብስቤ የሚባሉ ትልቅ ነጋዴ አዩና “በቃ እኔ  ነኝ የምገዛው” አሉና እዚህ አስገባ አሉኝ፡፡ “አይ ጋሼ ራሴ ነጌሌ ልጭን ነው” ስላቸው፤ “አንተ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ነገሌ የምትጭነው” ብለው በጥፊ መቱኝ፡፡ በግራ ፊቴ በኩል በሀይል በጥፊ ሲመቱኝ በቀኝ ጆሮዬ ደም ፈሰሰ፡፡ እንዴት ለእኛ ሳታስረክብ ቀጥታ ለነገሌ ነጋዴ ታስረክባለህ፣ ብለው ነው የመቱኝ። መምታት ብቻ አይደለም፤ እህሌን ከነፈረሶቼ ቀሙኝ፡፡ እየሮጥኩ ፖሊስ ጣቢያ ሄድኩኝ፤ ደም በደም ሆኜ ፖሊስ ጣቢያ ስደርስ ሃምሳ አለቃ ክብረት የሚባሉ የጣቢያው ፖሊስ አዩኝና፤ “ማነው የመታህ?” አሉኝ፡፡ የተፈጠረውን ነገርኳቸው፡፡ በጣም ተናድደው፣ ሁለት ፖሊስ አስከትለው መጥተው፣ የመታኝ ሰው ጋ ሲደርሱ አቶ ሰብስቤ ነው፡፡ ይህ ነጋዴ በወቅቱ በአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ ስለነበር “ኦ ሰብስቤ አንተ ነህ እንዴ የመታኸው? ለምን እንደዚህ ታደርጋለህ?” ብለው ብቻ ዳኝነትም ሳይሰጡኝ ተመልሰው ሄዱ፡፡ እኒህ ሰው የመቱኝ ለአስራ ምናምን ዓመት የጆሮ ታማሚ አድርጎኝ ነበር፡፡ እህሌን እንደምንም ከሰብስቤ አስመልሼ በአንድ ጥፊማ አልቆምም ብዬ ወደ ነገሌ ጫንኩኝ፡፡ ከነገሌ ወደ መጨረሻዋ የኢትዮጵያ ድንበር ወደ ዶሎ መጫን ጀመርኩኝ፡፡ ወደ ሱፍቱ ከተማና ማንኢራ ወደሚባል የኬንያ ከተማም  መጫን ጀመርኩኝ፡፡ ከዚህ እህል ጭኜ ሸጬ ከዚያ ደግሞ የቆራሊዮ እቃ ይዤ እመጣለሁ፡፡ በዚህ ስራ ላይ እያለሁ በ1982 አጋማሽ ላይ ደግሞ አናሶራ ወረዳና ቦሬ ወረዳ የወርቅ ማዕድን ተገኘ ተባለ፡፡ ከዚያ በባህላዊ መንገድ ወርቅ ማውጣት ጀመርኩ፡፡ አንድ ጉድጓድ 3 ሜትር ወደ ታች ለመቆፈር ሰባት ቀን ፈጀብኝ፡፡ ልጅነትም ልፋትም ስላለ አቅም የለኝም፡፡ ልክ ቆፍሬ ወርቁ ጋ ስደርስ አሸዋው በሙሉ ወርቅ ነው፡፡ ባቢቾ ቀበሌ ልጁ ወርቅ ሲያጥብበት የነበረው ባቲያ የሚባለው ገበቴ ላይ አሸዋውን አፍሼ ሳጣራው ግማሹ ወርቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያኔ ግራሙ 40 እና 50 ብር ነበር፡፡ አወጣሁና 22 ሺህ ብር ሸጥኩት፡፡
የወርቅ ስራ ቀደም ብለው ነዋ የጀመሩት?
አዎ! ያኔ አንድ እያሱ የሚባል የደርግ ሊቀ መንበር ነበር ጉድጓዴን ቀምቶ ደብድቦ ያባረረኝ፡፡ በዚያን ጊዜ ቢያንስ ከዚያ ጉድጓድ የ1 ሚሊዮን ብር ወርቅ ወጥቷል፡፡ ምን መሰለሽ? አባቴ ከአራት ሚስቶች 44 ልጅ ወልዷል፡፡ የእኔ እናት ብቻ 15  ልጆች ወልዳለች፤ የኔ ታላቅ ሲሞት 14 ልጆች ነበርን፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ብዙ ነን፡፡ ምግብ ሲቀርብልን ምግቤን ሲጋፉኝና ሲወስዱብኝ ለምን ወሰዳችሁብኝ ብዬ አልጣላም፤ ጥዬ ነው የምሄደው፡፡ ጉድጓዴን ደብድበው ሲቀሙኝ ጥዬ ሄድኩና በዚያ ብር እዚያው የወርቅ ንግድ ጀመርኩኝ፡፡ ያኔ ዘመናዊ የወርቅ ሚዛን ስላልነበር በዚህም በዚያም በኩል ቆርኪ አስረን ነበር የምንመዝነውና የምንገበያየው፡፡ የቆርኪው ሚዛን ሳይሳካ ሲቀር ሰፊ አፍንጫ ያለው ሰው እንፈልግና ለሰውየው የልኬት እንከፍላለን፡፡ ከዚያም በሰውየው አፍንጫ እንለካለን፡፡
እስኪ በሰፊ አፍንጫ ለክታችሁ እንዴት እንደምትገበያዩ በደንብ ያብራሩልኝ?
እንዴት መሰለሽ -- ያ ሰፊ አፍንጫ ያለው  ሰው ይፈለግና ወርቅ ቋጥረን በሰፊው አፍንጫው ስንከተው ከገባ ይህን ያህል ብር ነው እንላለን፡፡ በሰፊው አፍንጫ ካልገባ አይ ይሄ ወርቅ ትልቅ ነው ብለን ዋጋ ጨምረን እንናገራለን፡፡ ያው ከሚዛኑ አፍንጫ ይቀድማል፡፡ እስከ መቼ በሰው አፍንጫ እንገበያያለን፤ ለምንስ ሌላ መፍትሄ አልፈልግም ብለን ሚዛን መስራት ጀመርን። ሚዛኑ ተሳካልን፡፡ እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ሁሉም ሰው በዚያ ሚዛን ነበር የሚገለገለው። ከዚያ ኢህአዴግ ሲገባ እኔ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ነበረኝ፡፡ የጦፍኩ ነጋዴ ሆንኩኝ፡፡ ኬንያ እሄዳለሁ፤ አዲስ አበባ እሄዳለሁ፤ እነግዳለሁ። በነገራችን ላይ አፍሪካ ወርቅ ቤትን እኛ ነን ያሳደግነው፡፡
የፒያሳውን?
አዎ የፒያሳውን አፍሪካ ወርቅ ቤት ነው የምልሽ፡፡ ሌላ ደግሞ ገብረ ህይወት የሚባሉ ባለወርቅ ቤት፣ በጣም ታማኝ ትግሬ ሰውዬ ነበሩ፡፡ አሁን ይኑሩ አይኑሩ አላወቅሁም። በጣም ታማኝ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ወርቅ ቤቶች ይሰርቁን ነበር፡፡ እሳቸው ግን በታማኝነት ከእኛ ይረከቡና 25 ሳንቲም አትርፈው የእኛን ብር ይመልሱልናል፡፡ በዚህ አይነት ከእሳቸው ጋር መስራት ጀመርን፡፡ ከዚያም ትልቅ ነጋዴ እየሆንኩ መጣሁ፡፡ በ1987 ዓ.ም ሚስት ማግባት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡
ሚስትዎን ጠልፈው ነው ያገቧት የሚባለው እውነት ነው እንዴ?
ምን መሰለሽ --- ጠለፋ ነው አይደለም የሚለውን ለመፈረጅ እንዲመች በመጀመሪያ ሁኔታውን ልንገርሽ፡፡ የልጅቷ አባት ያኔ በሲዳማ ነጋዴ ሳይኖር ይነግዱ የነበሩ ትልቅ ባለሀብት ናቸው፡፡ ዮሃንስ ኦታቻ ይባላሉ፡፡ የኒህ ሰው ልጅ በጣም ቆንጆና በጣም ጎበዝ ተማሪ አለች፡፡ እሷን ካላገባሁ ስል “አይ አይሆንም” ተባለ፡፡ ለምን? እኔ ተራ የገበሬ ልጅ ነኝ፤ እሷ ደግሞ የሚሊየነር ልጅ ናት፡፡ እንዴት ይሆናል ሲባል፣ “እንዴት አይሆንም፤ እኔ እንዴት ከሰው አንሳለሁ?” አልኩኝ፡፡ ዋናው ነገር ልጅቷ እኔን በጣም ነው የምትወደኝ፣ እኔም እወዳታለሁ፡፡ ከዚያ ጠልፌ ወሰድኳት፡፡
በዚያን ጊዜ ሴትን መጥለፍ አያስከስስም ነበር እንዴ?
በእኛ ጊዜ አያስከስስም፤ ጉዳዩን የሚፈታው የአገር ሽማግሌ ነው፡፡ በወቅቱ የአገር ሽማግሌ ተሰብስቦ የልጅቷ አባት ጋ  ሄዱ፡፡ “እንዴት የድሃ ልጅ ያልተማረ ሰው ልጄን ያገባል፤ እራሴን አጠፋለሁ” ብለው በአንድ ክፍል ውስጥ ገብተው ቆልፈው እምቢ አሉ፡፡ የመንግስት ሹማምንት ቢሄዱ የአገር ሽማግሌዎች ቢለምኑ አባትየው አሻፈረኝ አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የመካነ ኢየሱስ ቄስ የሆኑ ቄስ ዮሃንስ የሚባሉ ጓደኛ አሏቸውና እሳቸው ተጠርተው መጡና ተቆጧቸው፡፡ “ምን ማለትህ ነው ልጅህን አንተ አታገባም፤ ለወንድሞቿ አታጋባም ስለዚህ ተው” ብለው ተቆጡ፡፡ “እኔ ካናዳ ልኬ ላስተምራት ፕሮሰስ ጨርሻለሁ” ብለው ተቆጡ። ነገሩ እየተጋጋለ ሲሄድ “ለማንኛውም የልጅቷ ፍላጎት ይታወቅ፤ ካልወደደችው በግድ አፍኖ ሊያኖራት ስለማይችል እንመልሳታለን” አሉ፤ የኔ ጎሳዎች። ከዚያ በኋላ አንድ የእሷ አጎትና ሌሎች ሽማግሌዎች ተመርጠው ተላኩና እሷን ጠየቋት። “እኔ የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ አግብቻለሁ ደግሞ እወደዋለሁ፤ ወደ ቤት መመለስ አልፈልግም። ለአባቴ ንገሩት፤ በጣም እንደሚወደኝ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በቃ ከምወደው ሰው ጋር ነው ያለሁት” የሚል ምላሽ ሰጠች፡፡ አባቷ ሰሙና “በቃ በትክክል ልጄ እንደዚህ አለች?” ብለው ጠየቁ፡፡ ሽማግሌዎቹ ይህንኑ አረጋገጡላቸው፡፡ ነገሩ እዚህ ላይ አበቃ፡፡
ከዚህ በኋላ በአጋጣሚ በሲዳማና በጉጂ መካከል ግጭት ተነሳ፡፡ በዚህ ግጭት አባቷ ወደ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት ተዘረፉ። እነሱንም ለመጨረስ ቀለበት ውስጥ አስገቧቸው፡፡ ይህ ሲሆን ከአባቷ ጋር ገና አልታረቅንም፤ አልተገናኘንም፡፡ በወቅቱ እግዚአብሔር ከኔ ጋር ሆኖ ቦሬ ከተማ ነዋሪ  የሆኑ 560 የሲዳማ ሰዎችን ሰብስቤ ቤት አምጥቼ አዳኗቸው፡፡ በአካባቢዬ እኔም የትልቅ ቤተሰብ ልጅ ነኝ፡፡ አባቴ የተከበሩና ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ እንደነገርኩሽ ከአራት ሚስቶች 44 ልጆች የወለዱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በውጭ የተወለደ ልጅ በአካባቢው ባህል አይቆጠርም እንጂ ቢቆጠር ወደ መቶ ሳንጠጋ አንቀርም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንድ የሀዋርያት ቤተክርስቲያን መሪ “እኔ የእናንተ ወንድም ነኝ፤ አባታችሁ መቶ በመቶ የራሴ ልጅ ነህ ብሎኛል” ብሎ መጣ፡፡ እውነትም ይህ ሰው መቶ በመቶ አባቴን ነው የሚመስለው፡፡ እንደሱ በውጪ ያሉ ልጆች ሳይቆጠሩ እኛ 44 ነን፡፡ አባቴ ሲሞቱ የስጋ ዝምድና ያለን ብቻ ከ 3ሺህ በላይ ሰው ነው ለቅሶ ላይ የወጣው፡፡ ወደ ዋናው ስመለስ በአካባቢው ቤተሰቤ የተከበረ ስለሆነ፣ እነዛን 560 ሲዳማዎች ቤቴ ድረስ መጥተው ሊያጠቋቸው አልቻሉምና እኔ በሰላም ወደ ሲዳማ አሻገርኳቸው። እግዚአብሄር መቼም ሁሉንም ለበጎ ነው የሚያደርገው፡፡
(ይቀጥላል)


Read 1202 times