Saturday, 31 December 2022 13:08

የእኛ ሰው በኳታር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ‹‹ምግብን የምሰራው እንደ ሰዓሊ ተጠብቤ በመሆኑ የምግብ ጠበብት ብባል አይደንቅም›› መስከረም ዘውዴ ‹‹ፕሮፌሽናል ለሆኑ ዜጎቻችን የሚሆኑ የስራ እድሎች በመካከለኛው ምስራቅ ለመፍጠር እፈልጋለሁ፡፡›› - ሔኖክ ተሾመ
 
        ሄኖክ ተሾመና መስከረም ዘውዴ በኳታሯ መዲና ዶሃ ታዋቂ የሆነው የአቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት ባለቤቶች ናቸው፡፡ የትዳር አጋሮቹ በዶሃ ከተማ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር እየኖሩና እየሰሩ ናቸው፡፡ በ22ኛው የዓለም ዋንጫ  በኳታር በነበረን ቆይታ ለመጀመርያ ጊዜ የጎበኘነው የኢትዮጵያውያን መናኸርያ ነው - ሬስቶራንቱ፡፡ ምግብ ቤቱ ሚዘር በተባለውና በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ንግድና ሌሎች ስራዎች በከተሙበት ሰፈር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ሬስቶራንቱ  በዶሐ ከተማ ውስጥ ከ24 ዓመት በፊት የተመሰረተ ሲሆን የተለያዩ ስያሜዎችና የተለያዩ ባለቤቶች ሲፈራረቁበት ቆይቶ በመጨረሻም ኢትዮጵያውያኑ  ባለቤቶቹ ሄኖክና መስከረም ሆነው፣ አቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት በሚል ስያሜ አገልግሎት እየሰጠ  ይገኛል፡፡
ስለ ሬስቶራንቱ
ሔኖክ ተሾመ እንደሚለው፤ ሬስቶራንታቸው በኢትዮጵያውያን ኳታር ውስጥ ከተከፈቱ የንግድ ስራዎች ቀደምትና የመጀመርያው የሚባል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ አገር ቤትን ባማከለ መንገድ ለኢትዮጵያውያን ለማቅረብ እንደተመሰረተና ዛሬም ድረስ ይህን አገልግሎት በመስጠት መቀጠሉንም ይናገራል። የሬስቶራንቱ ስያሜ መጀመርያ ላይ አቢሲኒያ፣ በኋላ ላይ ደግሞ ቢሾፍቱ ተብሎም ነበር፡፡ በመጨረሻም ሁለቱን  ስያሜዎች በማዋሃድ አቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡
ከ24 ዓመታት በፊት ምግብ ቤቱ ሲከፈት ብቸኛው እንደነበር የሚያስታውሰው ሔኖክ፤ በወቅቱ ኢትዮጵያውያን እንደ አሁኑ ሳይበዙ ጥቂት እንደነበሩ ጠቅሶ፣ ባህላዊ ምግብና የኢትዮጵያ ቡና  ይሸጥበት ነበር ብሏል፡፡ ከመነሻው እንደነበረው ሬስቶራንቱ የአገርን ባህላዊ ምግብ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን  እንደ መገናኛ ስፍራም እያገለገለም ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያውያንና የሌላ አገራት ዜጎች በቀጠሮ የሚገናኙበት፤ አንዳንዶች እንደውም እንደ ቢሯቸው የሚሰሩበት ምቹ ስፍራ ሆኖላቸዋል።  ሬስቶራንቱን በልዩ ፍቅር የምታስተዳድረው መስከረም ዘውዴ እንደገለፀችው፤ ደንበኞቻቸው ዛሬም ድረስ እንደ ምግብ ቤት ብቻ ሳይሆን መገናኛም ሥፍራ  እየተጠቀሙበት ነው። ‹‹ኢትዮጵያውያን ወደ ሬስቶራንቱ ሲመጡ ከምግብ በላይ የሚፈልጉት ነገር አላቸው፡፡ ቡና፤ ቆሎ፤ ዳቦ ቆሎና ሌላውን ባልትና ይጠይቃሉ፤ እሱንም አብረን እንሸጥላቸዋለን፡፡ ወገኖቻችን እኛ ጋ መጥተው አገራቸውን እንዲያስታውሱ፤ ቤተሰባዊነት እንዲሰማቸው እንፈልጋለን›› ብላለች መስከረም፡፡
አቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት፤ የተለያየ ዜግነት ያላቸው ደንበኞችም የሚስተናገዱበት ሥፍራ ነው፡፡  የኤርትራ፤ የሱዳንና ሌሎች የኤሽያ አገራት ዜጎች እንደ ስራ ቦታቸው እንደሚመላለሱበት፤ ከትልልቅ ሚዲያዎች የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ደንበኞቻቸው እንደሆኑ መስከረም በኩራት ትናገራለች፡፡ መስከረም የሬስቶራንቱ ባለቤትና ዋና አስተዳዳሪ ብቻ አይደለችም፡፡ የቤቱ ዋነኛ ሼፍና ሁለተኛ ሜኑ እኔው ነኝ ትላለች፡፡ ምግቦቻቸውን የሚያሰናዱት ከኢትዮጵያ በሚያስመጧቸው ምርጥ የባልትና ውጤቶች በመሆኑ   ኢትዮጵያዊ ጣዕሙን ጠብቆ የሚዘጋጅ ነው፡፡ መስከረም በሬስቶራንቱ ስለሚሰሯቸው ምግቦች ስትናገር መጀመርያ የጠቀሰችው አቢሲኒያ ስፔሻል የተባለውን ሲሆን ጥብሳጥብሶችን የሚያካትት የቤቱ መለያ ምግብ ነው፡፡ ክትፎ፣ ሸክላ ጥብስ፣ መረቅ፣ አይብ፣ ዱለት.. ይዞ በሚያምር ሁኔታ ይቀርባል፡፡ በተጨማሪም፣ ማህበራዊ፤ አገልግል፤ ቤተሰብ፤ ምኒልክ፤ በየአይነት የተባሉ ምግቦች አላቸው፡፡ ኮርኒሽ የተባለው ምግባቸው በዶሐ ውስጥ በታወቀ ጎዳና መታሰቢያነት የተሰየመ ነው፡፡ ሬስቶራንታቸው በሚገኝበት ስፍራ ስያሜ ‹‹ሚዜር ስፔሻል›› የሚለውን ምግብ ፈጥረዋል፡፡ ቤተሰብ ብለው የሚያዘጋጁት ምግብ ለሰባት ሰው እንዲበቃ ተደርጎ የሚሰራ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ምግቦች ሁሉ የተካተቱበት ይህን ምግብ ቴክአዌይ ስንታዘዝ ሳናሽግ ከእነ ትሪው ነው የምንልከው” ብላለች መስከረም፡፡ በተረፈ  ሽሮ፤ ፍርፍር፣ ሰላጣዎች፤ አትክልቶች ሁሉንም ዓይነት  ምግብ ይሰራሉ። መስከረም ለአዲስ አድማስ እንደገለፀችው፤ ደንበኛ በሬስቶራንታቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ምግብና መስተንግዶ ፈልጎ የሚያጣው ነገር የለም፡፡
መስከረም ምግብን የምሰራው እንደ ሰዓሊ ተጠብቤ በመሆኑ የምግብ ጠበብት ብባል አይደንቅም ትላለች፡፡ በምግብ ቤቱ አብሯት የሚሰሩ ምርጥ ሼፎች ቢኖሩም፣ በሚቀርበው ምግብ ላይ የራሷን ሃሳብ፤ እይታና ቅመማ ቅመም በመጨመር መስራት ያስደስታታል። ለሰዎች የሚቀርበው ምግብ በመጀመርያ ራስንም ማስደሰት አለበት ብላ ታምናለች፡፡ ለሬስቶራንቱ አጠቃላይ ገፅታ እንደ ምግቡ ሁሉ ትጨነቃለች፡፡ “በፍላጎት የምሰራውና ትልቅ ደረጃ መድረስ የምፈልግበት ንግድ በመሆኑ፣ ሁልጊዜ የቤቱን ውበት ከመጠበቅ ቦዝኜ አላውቅም፡፡ የሬስቶራንቱ ገፅታ እንግዶችን የሚስብ እንዲሆን፤ ባህልን እንዲጠብቅና እንዲያንፀባርቅ ፤ በየጊዜው ደስ በሚለኝ መንገድ እቀያይረዋለሁ” ትላለች፡፡
በአቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት በተለያዩ አጋጣሚዎች ዝግጅቶች ይካሄዳሉ፡፡ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አርቲስቶች፤ ሚዲያዎችና ሌሎች ልዑካኖች ሲመጡ ልዩ መስተንግዶ ይደረግላቸዋል፡፡ በልዩ ምክንያት የሚዘጋጁ የባህል ምሽቶችንም ማካሄድ ጀምረዋል፡፡ በሬስቶራንቱ ውስጥና አዳራሾችን ተከራይተው የተለያዩ የሰርግ ስነስርዓቶችንም ያሰናዳሉ። የበዓል ዝግጅቶችንም ይሰራሉ፡፡ ሐሙስ፤ አርብና ቅዳሜ ሬስቶራንቱን በርካታ በዶሃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይስተናገዱበታል። ከኢትዮጵያውያኑ ባሻገር የሌሎች አገራት እንግዶችም ይስተናገዳሉ፡፡ ‹‹ሞሮኮዎች፤ ሱዳኖች፤ ሱማሌዎች የሬስቶራንቱ ደንበኞች ናቸው፡፡ ምግብ ባይመገቡ እንኳን ቡና ይጠጣሉ፡፡ ሞሮኮዎች በተለይ ቡናውን በጣም ስለሚወዱ ደንበኞቻችን ናቸው፡፡ ምግባችንንም መሞከር ማየት ይፈልጋሉ፡፡ በሆነ አጋጣሚ ሲቀምሱት ይወዱታል፡፡›› የምትለው መስከረም፤ “ኳታሮችና የመኖች  በኢትዮጵያ ባህል እንደሚገረሙና እንደሚደሰቱ ይነግሩኛል” ብላለች፡፡
መነሻው የቤት ሰራተኝነት ቢሆንም
መስከረም ዘውዴ ኳታር ከገባች ከ15 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡ በቆይታዋ የተለያዩ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ እንደ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን መስከረምም ወደ ኳታር የገባችው በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ነው። በኳታር  ከተቀጠረችበት ቤተሰብ ጋር በመልካም ግንኙነት ለስምንት ዓመታት ሰርታለች። አሰሪዎቿ ባደረጉላት ድጋፍ ባለቤቷን ወደ ኳታር እንዲመጣ አደረገች፤ ኳታር ውስጥ የራሷን ሬስቶራንት ለመክፈት እንደምትፈልግ ለኳታሪ አሰሪዎቿ ትነግራቸው ስለነበርም ይህን ህልሟን እንድታሳካ ድጋፍ አድርገውላታል፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚገባ ኢትዮጵያዊ በአብዛኛው መነሻው የቤት ሰራተኝነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የራስን ንግድ ከፍቶ ለመስራት ብዙ መስዋዕትነት፤ ብዙ ትጋት ይጠይቃል  ያለችው መስከረም፤ ኳታር ውስጥ በዚህ ረገድ በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ ጀግና ሴቶች መኖራቸውን ትናገራለች፡፡ ሰብለ እንጀራ፤ ዮርዳኖስ ከሀባሻዊ ትሬዲንግ፤ ፕሮሚስና አፍሪካ የተባሉ ሬስቶራንቶችን የከፈቱ ኢትዮጵያውያን እንስቶች የተሻለ ቦታ ለመድረስ በአርአያነት እንደሚታዩም ትገልጻለች፡፡
‹‹በኳታር ውስጥ የራስን ስራ ለመስራት ገንዘብ ብቻውን የትም አያደርስም፡፡ ፍላጎትንና አቅምን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ማንም ሰው መስራት ለሚፈልገው ህልም ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ  እኔ ሬስቶራንት ለመክፈት ስፈልግ በቀጥታ ሬስቶራንት አይደለም የጀመርኩት፤ በመጀመርያ  ወደዚያ የሚያደርሱኝን ስራዎች ነው ያከናወንኩት›› ስትል መስከረም የህይወት ተሞክሮዋን  አጋርታለች፡፡
ከሹፍርና፤ ወደ ኤምባሲ ከዚያም
ወደ ግል ድርጅት
ሔኖክ ተሾመ ኢትዮጵያ ውስጥ የባድመ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት የአየር ኃይል አባል ነበር፡፡ ወደ ኳታር ከመጣ በኋላ በቀን አምስት መኪኖችን በማጠብና በሹፍርና ሥራ ላይ ቆይቷል፡፡ በ2013 የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኳታር ውስጥ ሲከፈት ከኤምባሲው ሰራተኞች አንዱ ሆኖ ተቀጥሯል፡፡ በቆንስላ ረዳትነት ተቀጥሮ ዜጎችን በመርዳት፤ በዜጎች ላይ የመብት ጥሰት  ሲያጋጥም እገዛ በማድረግ ሰርቷል፡፡ በዲያስፖራ እንቅስቃሴ በተለይ በህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉንም ይገልፃል። ኤምባሲው በክቡር አምባሳደር ምስጋናው  ይመራ በነበረበት ወቅት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ1.5 ሚሊዮን  ዶላር በላይ ገቢ በተሰባሰበበት እንቅስቃሴ ላይ መሳተፉንም አስታውሷል፡፡ በአጠቃላይ በኤምባሲው ለስምንት ዓመታት  በቆንስላ  ረዳትነት፤  በዲያስፖራ ኦፊሰርነት፤ በዜጎች ጉዳይ በተለያዩ ሃላፊነቶች አገልግሏል፡፡
ከኤምባሲው ሲሰናበት ሔኖክ ቤተሰቡን ይዞ ከዜሮ በመነሳት ማደግ የሚቻልበትን መንገድ ነው ያቀደው፡፡ ይህን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም  ወደ  ሬስቶራንትና ሌሎች ተያያዥ የንግድ መስኮች ገባ፡፡ ከአቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት ባሻገር፤ በትራንስፖርት መስክ የሊሙዚን አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ከፍቷል። ኩባንያው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገራትን ዜጎች በመቅጠር የሚሰራ  ሲሆን መኪኖችን በማሰማራት ዶሃ ውስጥ ኡበርና ካሪም በሚባሉ የታክሲ አገልግሎቶች ውስጥ ይሰራል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የጽዳትና የሆስፒታሊቲ አገልግሎት የሚሰጥም ድርጅት አቋቁሟል፡፡ ሬስቶራንቱን፤ የፅዳትና የመስተንግዶ ስራዎችና፤ የሊሙዚን ትራንስፖርት  አገልግሎትን የሚሰጡ ድርጅቶችን አቢሲኒያ የሚለውን ስያሜ በማስቀድም አንድ ላይ አስተባብሮ እንደሚመራቸው ሔኖክ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ‹‹በአቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት እስከ 16 ሰራተኞች አሉን። በአቢሲኒያ ሊሙዚን ያቀረብናቸውን 12 መኪኖች በሃላፊነት ተረክበው የሚሰሩ 60 የሚሆኑ ሰራተኞች እያስተዳደርን ሲሆን አዳዲስ ሰራተኞችን ለመጨመር የመንጃ ፍቃድ ስልጠና ሌሎች ተግባራትን እያከናወንን ነው። በአቢሲኒያ የንግድና አገልግሎት ድርጅታችን ደግሞ ከ25 በላይ ሰራተኞችን ይዘናል፡፡››
በሌላ በኩል፤ ከአቢሲኒያ ድርጅቶቹ ባሻገር በኤምባሲው ሲሰራበት የቆየውን ልምድ በመጠቀም ኢትዮጵያውያን የስፖንሰር ችግር ሲገጥማቸውና ስራ ሲያስፈልጋቸው ጉዳይ በማስፈፀምና በማማከር እያገዛቸው እንደሚገኝ ሔኖክ ይገልጻል፡፡ ‹‹የኔ ህልም በኳታር ውስጥ አቢሲኒያ  የሚለው ስም ትልቅ ክብር እንዲኖረው ማድረግ ነው፤ ይህንንም ለማሳካት ኢትዮጵያ ውስጥ በመካከለኛው ምስራቅ ሊሰማራ የሚችል የሰው ሃይልን የማደራጅበት ቢሮ ከፍቻለሁ›› ብሏል፡፡
ኳታር ውስጥ ቢዝነስ መስራት
ሔኖክ እንደሚለው፤ በኳታር ውስጥ ቢዝነስ ለመስራት ትልቁ ፈተና የመሥርያ ቦታ ማግኘት ነው፡፡ የቦታ ኪራይ በጣም ውድ እንደሆነ የመብራትና የውሃ ክፍያም ከፍተኛ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በኳታር ህግ መሰረት ማንኛውም የሌላ አገር ሰው በንግድ ስራ ለመሰማራት ከኳታራዊ ጋር መጣመር ይኖርበታል። ስለዚህም ንግዱን ለመስራት ታማኝ የሆነ ኳታራዊ ስፖንሰር ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎችን የሚገጥማቸው ፈተና ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው የሚለው ሔኖክ፤ ንግዱን ለመመስረት ብቻ ሳይሆን ስራው እየሞቀ ሲመጣ አብሮ በመስራት የሚቀጥል ሰው ለማግኘት ጥረት ያስፈልጋል ይላል፡፡ በዶሐ ከተማ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ከሬስቶራንት  ባሻገር፤ በትራንስፖርት ሊሙዚን አገልግሎት፤ በፅዳት ስራዎች፤ በባህላዊ ባልትና፤ በአልባሳትና ሌሎች እቃዎች ንግድ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ለብዙዎቹ ትልቁ ፈተና ለመደብርና ለቢሮ ኪራይ የሚጠየቁት ውድ ክፍያ ነው፡፡ ለንግድ ስራቸው የሚያወጡት ወጭና ገቢያቸው አይመጣጠንም፡፡  በአቢሲኒያ ቢሾፍቱ ሬስቶራንት ከእነ ሔኖክ ጋር በስፖንሰርነት የሚሰራው ኳታራዊ ለሥራ ፈቃዱ የኪራይ ሂሳብ ብቻ  ነው የሚከፍለው። በስምምነታቸው መሠረት፤ የባንክ የሰራተኛ አስተዳደር፤ የኢምግሬሽን ጉዳዮችና የሬስቶራንቱን ወጪና ገቢ የመቆጣጠር ሙሉ ሃላፊነቱ የእነሱ ነው፡፡
በኳታር ብዙ የስራ እድሎች አሉ ግን
ኳታር ውስጥ ብዙ የስራ እድሎች መኖራቸውን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ ከሰው ሃይል ጋር በተያያዘ በተፈለገው መንገድ ለመስራት ግን አገር ቤት የተፈጠሩ እንቅፋቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህግ ከአገር ወጥቶ ለመስራት በቤት ሰራተኝነትና በጉልበት ስራ ላይ ማተኮርን ያስገደደ ይመስላል፡፡ ሔኖክ እንደሚያስረዳው፤ በኳታር ውስጥ ከቤት ሰራተኝነት ባሻገር ለኢትዮጵያውያን የሚሆኑ  ብዙ የስራ እድሎች አሉ፡፡ ለዶክተሮች፤ ለኢንጅነሮች፤ ለፓይለቶችና ሌሎች ሙያተኞች የሚሆኑ የስራ እድሎች አሉ፡፡ ኤሽያኖች ሙያተኞቻቸውን ወደ ኳታር ሲልኩ አገራቱ በተለያዩ መንገዶች የተሳሰሩ በመሆናቸው ብዙ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡ የትምህርት ማስረጃን በማረጋገጥና በመወዳደር ለዜጎች የስራ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኢንጂነር ወደ ኳታር ቢገባ በኢንጂነርነቱ ስራ ሊያገኝ አይችልም፤ በተለያዩ ስራዎች ውስጥ ተሰማርቶ ይቆይና ነው ራሱን በማስተዋወቅ ወደ ንግድ ስራ ውስጥ ሊገባ ወይም ወደ ሙያው ሊመለስ የሚችለው፡፡ በኳታር ኢትዮጵያውያን ከቤትና ከጉልበት ስራዎች በላቁ ሙያዎች ባሉ የሥራ እድሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ የሚያሳስበው ሔኖክ፤ እሱ በሚያስተዳድረው ኩባንያ ይህን ሁኔታ ለማቀላጠፍ ለጀመረው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ከመንግሥት  መጠየቁን ይናገራል፡፡
ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ
ኳታር የዓለም ዋንጫን የማስተናገድ ዕድል በማግኘቷ ልማቷን አቀላጥፋለች፡፡ ግዙፎቹ አውራ ጎዳናዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶቿ ባለፉት 10 ዓመታት የተገነቡ ናቸው፡፡ ሉሴይል የተባለችው ግዙፍ ከተማ የተፈጠረችው በዓለም ዋንጫው ነው፡፡ አሁን ደግሞ ውኪር የሚባለውን ከተማ ፈጥረው እየሰሩበት ነው።  የዓለም ዋንጫው ኳታርን በመላው ዓለም እንድትዋወቅ አድርጓታል፡፡ የዓለም አይኖችና ጆሮዎች ኳታር ላይ ነበሩ፡፡
የዓለም ዋንጫው በተወሰነ ደረጃ የንግድ ስራዎችን ቢያቀዛቅዝም ለብዙዎች ግን የስራ  እድሎችን ፈጥሯል፡፡ በርካቶች በፅዳት፤ በመስተንግዶና በጥበቃ ሥራዎች ላይ የመቀጠር እድል አግኝተዋል፡፡ “ከዓለም ዋንጫው ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚዲያ ባለሙያዎችና እንግዶች ወደ ዶሐ በመምጣታቸው፣ በሬስቶራንታችን እነሱን ስናስተናግድ ቆይተናል፡፡ ዓለም ዋንጫው ከብዙ ወገኖቻችን ጋር እንድንገናኝ ሰበብ ሆኖናል። ከካናዳ፤ ከአሜሪካ፤ ከለንደንና ከሌሎች አውሮፓ ከተሞች የመጡ ኢትዮጵያውያን ጎብኝተውናል፤” የሚለው ሔኖክ፤ “ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የስራ እድሎች የኤስያ አገራት፤ ከአፍሪካ ደግሞ የኬንያ፤ ኡጋንዳ፤ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ ዜጎች  በእጅጉ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን እምብዛም አልተጠቀሙም” ይላል፡፡ “ብዙውን ጊዜ ከአገር ቤት የሚመጡ ሰዎች በህገወጥ መንገድ መስራታቸው የነበሩትን እድሎች አበላሽቷቸዋል፡፡ ወደ ዶሐ ሲመጡ ማን ስፖንሰር እንደሚሆናቸው፤ አሰሪያቸው ማን እንደሆነ፣ ምን እንደሚሰሩ ብዙውን ጊዜ አያውቁም፡፡ በዚህ ሁኔታ የመጡት ቃል የተገባላቸውን ነገር ሲያጡ ከአሰሪዎቻቸው ጠፍተው ሌላ የስራ እድል ፈልገው ይሰማራሉ። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከአሰሪዎቻቸው ይጠፋሉ በሚል ስም እያጠፋ ነው”  ብሏል፡፡
ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያንን በተለያዩ የስራ እድሎች እንዲሰማሩ ከአገር ቤት ለማምጣት እድል ነበረኝ ያለው ሔኖክ፤ ነገር ግን በከፊል ፕሮፌሽናል ደረጃ ከአገር የሚወጡበት አሰራር ባለመዘርጋቱ  ይህን ዕድል መጠቀም አልተቻለም፤  ብሏል ሔኖክ በቁጭት፡፡
የመስከረም የወደፊት ዕቅድ   
ዓለም ዋንጫው ኳታር በቱሪዝሙ መስክ ለዓለም በሯን ክፍት እንደምታደርግ ያስተማረ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህም አገሪቷን የሚጎበኙ ቱሪስቶች እየበዙ ስለሚመጡ የእኛም ሬስቶራንት በዚያ ልክ ደረጃውን አሳድጎ መስራት እንዲቀጥል እፈልጋለሁ፡፡  በሬስቶራንት መስክ የጀመርነው ስራ በአፍሪካ ደረጃ ገዝፎ እንዲቀጥል አስባለሁ፡፡ አሁን ከምንሰራበት ስፍራ በተሻለ ስፋት አገልግሎታችን ለመስጠት ዕቅድ አለኝ፡፡ ኳታርያውያን በቅርባቸው በሚገኙት ሰራተኞቻቸው አማካኝነት ባህላችንን እንጀራችንን እያወቁ መጥተዋል፡፡ ባህልን አገርን ከማስተዋወቅ አንፃር ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ በኤምባሲው በኩል በቂ ድጋፍ የምናገኝ ከሆነ የተለያዩ  ባህላዊ ዝግጅቶችን እያሰናዳን ዶሐ ውስጥ አገራችንን በከፍተኛ  ደረጃ ለማስተዋወቅ እንሻለን፡፡
የሔኖክ የወደፊት ዕቅድ
ኳታር የመላው አለም ህዝብ የሚገኝባት አገር ናት፤ የኔፓል ባንግላዴሽ፣ ህንድ፣ ኬንያ ኡጋንዳ ዜጎች ይኖሩባታል፡፡ በዓለም ዋንጫው የሰው ሃይልን በማቅረብ የኬንያ እና የኡጋንዳ ዜጎች  ተጠቅመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከተሰጠው ኮታ የድርሻቸውን አላገኙም፡፡ ለሆቴል መስተንግዶና ለሌሎች የስራ እድሎች ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ያልተቻለው የመንግስት አሰራር የፈጠረው ቢሮክራሲ ጉዳዮችን በቶሎ ማስፈፀም ስላላስቻለ ነው፡፡ በዓለም  ዋንጫው በከፊል ፕሮፌሽናል በሚባሉት ሙያዎች እንደ ሴኩሪቲ፤ ፅዳትና መስተንግዶ የሚሰሩን ለማስገባት የሚያመች አሰራር አልነበረም፡፡ የሌሎች ምስራቅ አፍሪካ አገራት ዜጎች በኦንላይን ስራ ፈልጎ ደብዳቤዎችን በመፃፃፍ፤ ቃለ ምልልሶችን በማድረግ፤ መረጃዎችን በማድረስ ይወዳደራሉ። በእኛ አገር ያለው አሰራር በደላሎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መንግስት በቀጥታ ከኳታር መንግስት ጋር የሚሰራበት አሰራር መዘርጋት አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በበርካታ የስራ መስኮች ለመሰማራት የሚችሉበት ህግና አሰራር መፈጠሩ የውጭ ምንዛሬን የሚያሳድግ አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በውጭ አገራት ስራ ከማገናኘት አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ከቤት ሰራተኛና ከጉልበት ሙያዎች ባሻገር በፕሮፌሽናል ባለሙያዎች ደረጃ ለመስራት ይቻላል በሚለው አስተሳሰብ መቀየር ይኖርበታል፡፡ የትምህርት ማስረጃዎች ህጋዊ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው እንዲያገለግሉ የትምህርት ሚኒስቴርና ዩኒቨርስቲዎች ከኳታር መንግስት ጋር የሚሰሩበት ህጋዊ መስመር መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ማስረጃዎች ተገቢውን ማረጋገጫ አግኝተው ለስራ እድል ብቁ መወዳደርያ እንዲሆኑ መሰራት ይኖርበታል። ዶክተሮቻችን፤ መሐንዲሶቻችን ወደ ኳታር መጥተው እንዲወዳደሩ የሚያደርግ የስራ ግንኙነት እንዲፈጠር ነው መንቀሳቀስ ያለብን፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከኳታር መንግስት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ማድረጋቸውና የትምህርትና የስራ ልምድ ማስረጃዎች በማረጋገጥ መስራታቸው ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል፡፡ የተማሩ ሃይሎቻችንን ለስራ በተለያዩ የውጭ አገራት ካሰማራን የውጭ ምንዛሬያችንን የሚያሳድግ ነው፡፡ በመንግስት  በኩል ኤምባሲው ውስጥ ከሰራተኛ ጉዳይ ጋር በተገናኘ የሚሰራ አታሼ ያስፈልገዋል፡፡
ኳታር የሥራ እድል ፈጥራልናለች፡፡ በኳታር ከ25ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ በቀጥታ በሙያቸው በተማሩበት መስክ ባይቀጠሩም በኮንስትራክሽን፣ በትራንስፖርቱ፣ በህክምናው፣ በጋራዥና በሌሎች ሙያዎች እየሰሩ ናቸው። በአገሬው ህዝብም የሚከበሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ኳታርም ሆነ ሌላ አገር በስራ ምክንያት ከአገራቸው ሲወጡ ሊያጋጥማቸው ስለሚችል ነገር በቂ እውቀትና ስልጠና የሚያገኙበት ተቋም ያስፈልጋቸዋል። በግልም በመንግስትም  ደረጃ ይህን ተቋም ገንብቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ እኔ በያዝኩት እቅድ በኢትዮጵያ የሰው ሃይል ኤጀንሲ ለመክፈት ነው፡፡ የምከፍተውን ተቋም ካስጀመርኩ በኋላ  በራሴ በኩል ለስራ ከአገር የሚወጡትን ወገኖች  ቋንቋ ባህልና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አሰልጥኜ ለመላክ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከአገሩ ሲወጣ የባንክ ሂሳብ የሚከፍትበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ ከኳታር ሆነው ገንዘባቸውን በአግባቡ ወደ አገር ቤት እንዲልኩ ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን  መብታቸውን አስከብረው ግዴታቸውን ተወጥተው፤ የሚያገኙትን ገቢ ወደ አገር ቤት በአግባቡ ልከው ህይወታቸውን እንዲለውጡ ማስቻል ነው፡፡ከ22ኛው የዓለም ዋንጫ በኋላ የተለያዩ ጉዳዮችን ለማስፈፀም ወደ ኢትዮጲያ የተመለሰው ሔኖክ ተሾመ፤ በአቢሲኒያ ስም ወደ ውጭ አገር አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ የሚሰራበትን ፈቃድ አውጥቷል፡፡ በኳታር ከሚገኝ ኩባንያ ስምምነት ካደረገ በኋላ ሙሉ ስራውን የሚጀምረው ድርጅቱ በህጋዊ መንገድ የቤት ሰራተኞችና ሾፌሮችን በኳታርና በሌሎች የአረብ አገራት የሚወስድ ይሆናል፡፡ ሄኖክ ተሾመ ለአዲስ አድማስ በሰጠው አስተያየት በቀጣይ   በከፊል ፕሮፌሽናል ለሆኑ ባለሙያዎች የስራ እድሎችንም ለመፍጠር በኳታር ተጨማሪ ፈቃዶችን አወጣለሁ ብሏል፡፡
‹‹አገራችን ሰላም ሆና የኳታርና የኢትዮጰያ ግንኙነት አሁን ካለበት ደረጃ የሚሻል ከሆነ ፕሮፌሽናል ለሆኑ ዜጎቻችን ለዶክተሩ፤ ለመሐንዲሱ፤ ለፓይለቱ፤ ለሆቴልና ለቱሪዝም  ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች የሚሆኑ የስራ እድሎች በመካከለኛው ምስራቅ ለመፍጠር እፈልጋለሁ፡፡›› በማለትም ሔኖክ የመጨረሻውም መልዕክት አስተላልፏል፡፡

Read 4439 times